‹‹ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፤ ጥበብንም ያበዛል›› (ምሳ. ፱፥፱)

ኅዳር ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ጥበብ ከእግዚአብሔር አምላክ የሚሰጥ፣ ከሁሉ የበለጠና የላቀ የዕውቀት ሥጦታ እንዲሁም ሰማያዊ ርስትን የሚያወርስ መንፈሳዊ ጸጋ ነው፡፡ በሰዎች አእምሮ ውስጥም ማስተዋልን ያጎናጽፋል፡፡ በዚህም ጸጋ የእውነት መንገድን ማወቅና ጽድቅን መሥራት ይቻላል፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን በምሳሌው እንደተናገረው ‹‹ለጠቢብ ሰው ትምህርትን ስጠው፤ ጥበብንም ያበዛል፤ ጽድቅንም አስተምረው ዕውቀትን ያበዛል፡፡›› (ምሳ. ፱፥፱)

በሕገ ልቡና ምርምር ሰዎች የአምላካቸውን ሕልውና ማወቅ እንደተቻላቸው የቅዱሳን ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እንደተረከብነው የእግዚአብሔርን መኖር ማወቅ መረዳት የተቻላቸው እንደ ቅዱስ አባታችን አብርሃም ያሉ የተመረጡ ሰዎችን ታሪክ ማንበብና ማመን በቂ ነው፡፡ ጻድቁ አባታችን አምላክ በሰማይም ሆነ በምድር የፈጠራቸውን ድንቅ ሥራውን ሁሉ በመመርመሩ ለፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እንዳላቸው ተረድቶ አምላኩን አወቀ፡፡ ከዚህም በኋላ ለእርሱም ተገዝቶ በጸሎትና በጾም እየተጋደለ በጽድቅ ሥራ ኖሯል፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ የብዙዎች አባት እስከመባል ደርሷል፡፡

የጽድቅን ሥራ ለመሥራት የመጀመሪያው ተግባራችን እግዚአብሔር አምላክን ማወቅና በፈሪሃ እግዚአብሔርም መኖር ነው፡፡ ጠቢቡም ‹‹የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው›› ብሎ እንደተናገረው ሕይወታችን ሙሉ እግዚአብሔር አምላካችንን በመፍራት የምንኖር ከሆነ ከኃጢአት እንርቃለን፤ ጽድቅንም አብዝተን እንሠራለን፡፡ ምክንያቱም መልካም ሰዎች በሆንን መጠን የእውነትን ትርጒም ተረድተንና በጽድቁ ጎዳናም መጓዝ ይቻለናል፡፡ (ምሳ. ፩፥፯)

በዘመናት ተነሥተው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነግሠው በጥበብ ሕዝባቸውን መምራት የቻሉ ቅዱሳን እንዳሉም መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ በቀዳሚነትም የሚጠቀሰው ጠቢቡ ሰሎሞን ነው፡፡ በንግሥናው ዘመኑ ዝናው ከዓለም ከጫፍ እስከ ጫፍ የደረሰ ሰው ነበር፤ የነበረው ጥበብ እና የሥራዎቹ ስኬትም እጅግ የላቀ ነበር።

ንጉሥ ሰሎሞን ዙፋን ላይ ከተቀመጠ በኋላ መልካም ተመኝቶ እግዚአብሔር አምላኩን ጥበብን ለመነ፤ ‹‹በሕዝብህ ላይ መፍረድ ይችል ዘንድ፥ መልካሙንና ክፉውንም ይለይ ዘንድ ለባሪያህ አስተዋይ ልቡና ስጠው፤ አለዚያማ በዚህ በታላቅ ሕዝብህ ላይ ይፈርድ ዘንድ ማን ይችላል? እንዲል፤ ‹‹እግዚአብሔርም አለው፦ ፍርድን ትለይ ዘንድ ለራስህ ማስተዋልን ለመንህ እንጂ ለራስህ ብዙ ዘመናትን ባለጠግነትንም የጠላቶችህንም ነፍስ ሳትለምን ይህን ነገር ለምነሃልና እነሆ፥እኔ እንደ ቃል አድርጌልሃለሁ፤ እነሆ፥ ማንም የሚመስልህ ከአንተ በፊት እንደሌለ ከአንተም በኋላ እንዳይነሣ አድርጌ ጥበበኛና አስተዋይ ልቡናን ሰጥቼሃለሁ።›› (፩ኛነገ.፫፥፱-፲፪)

ጠቢቡ ሰሎሞን በዘመነ መንግሥቱ ሕዝቡን በመግዛትም ሆነ ፍርድን በማሳለፍ ረገድ ጥበቡን ከምንም በላይ አሳይቷል። ለዚህም ምሳሌ አንድ ታሪክ እናንሣ፤ ንጉሡ ከነገሠ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ሴቶች ለፍርድ በፊቱ ቀረቡ። በአንድ ቤት ውስጥ ይኖሩ ነበርና እያንዳንዳቸው አንዳንድ ልጅ ነበራቸው፤ አንድ ቀን ሌሊት አንዷ ልጇን ጨቁና ገደለችውና ከሌላዋ ሴት ጎን አስቀመጠች፤ እና የዚያችን ሴት ልጅ ለራሷ ወሰደች፤ ሲነጋም ሴቶቹ መጨቃጨቅ ጀመሩ።ከዚያም ወደ ንጉሡ ለፍርድ ቀረቡ፤ ‹‹አንደኛይቱም ሴት አለች። ጌታዬ ሆይ፥ እኔና ይህች ሴት በአንድ ቤት እንኖራለን እኔም ከእርስዋ ጋር በቤት ሳለሁ ወለድሁ።እኔ ከወለድሁ ከሦስት ቀን በኋላ ይህች ሴት ደግሞ ወለደች እኛ በቤት ውስጥ አብረን ነበርን፥ ከሁለታችንም በቀር ማንም በቤት ውስጥ አልነበረም። እርስዋም በላዩ ስለ ተኛችበት የዚህች ሴት ልጅ በሌሊት ሞተ። እርስዋም በእኩለ ሌሊት ተነሥታ፥ እኔ ባሪያህ ተኝቼ ሳለሁ፥ ልጄን ከአጠገቤ ወሰደች፥ በብብትዋም አደረገችው፥ የሞተውንም ልጅዋን በእኔ ብብት አደረገች። ልጄንም አጠባ ዘንድ በማለዳ ብነሣ፥ እነሆ፥ ሞቶ ነበር ነገር ግን ብርሃን በሆነ ጊዜ ተመለከትሁት፥ እነሆም፥ የወለድሁት ልጄ አልነበረም።ሁለተኛይቱም ሴት። ደኅነኛው የኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው እንጂ አንቺ እንደምትዪው አይደለም አለች። ይህችም። የሞተው የአንቺ ልጅ ነው፥ ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው አለች እንዲሁም በንጉሡ ፊት ይነጋገሩ ነበር። በዚያን ጊዜም ንጉሡ። ይህች ደኅነኛው የእኔ ልጅ ነው፥ የሞተውም የአንቺ ልጅ ነው ትላለች ያችኛይቱም። አይደለም፥ የሞተው የአንቺ ልጅ ነው ደኅነኛውም የእኔ ልጅ ነው ትላለች አለ። ንጉሡም ሰይፍ አምጡልኝ አለ ሰይፍም ይዘው ወደ ንጉሡ ፊት መጡ። ንጉሡም ደኅነኛውን ሕፃን ለሁለት ከፍላችሁ ለአንዲቱ አንዱን ክፍል፥ ለሁለተኛይቱም ሁለተኛውን ክፍል ስጡ አለ። ደኅነኛውም የነበራት ሴት አንጀትዋ ስለ ልጅዋ ናፍቆአልና። ጌታዬ ሆይ፥ ደኀነኛውን ለእርስዋ ስጣት እንጂ አትግደል ብላ ለንጉሡ ተናገረች። ያችኛይቱ ግን፦ ይከፈል እንጂ ለእኔም ለአንቺም አይሁን አለች። ንጉሡም መልሶ፦ ይህችኛይቱ እናቱ ናትና ደኅነኛውን ሕፃን ለእርስዋ ስጡአት እንጂ አትግደሉት አለ። ንጉሡም የፈረደውን ፍርድ እስራኤል ሁሉ ሰሙ ፍርድን ለማድረግ የእግዚአብሔር ጥበብ እንደ ነበረበት አይተዋልና ንጉሡን ፈሩ። (፩ኛ ነገ. ፫፥፲፮-፳፰)

ከዚህም በኋላ ጠቢቡ ሰሎሞን የአባቱን የዳዊትን ምኞት ፈጽሞ በኢየሩሳሌም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ መሥራት ጀመረ። ለዳዊት የተጠቆመው እና አብርሃም ይስሐቅን ለመሥዋዕት ያቀረበበት በሞሪያ ተራራ ላይ የሚሠራበትንም ቦታ መርጦ በሰባት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ በመቶ ሰማንያ አምስት ሺህ ሠራተኞች ቤተ መቅደሱን አሠራ። የቤተ መቅደሱ ግንቦች ከድንጋይ የተሠሩ ነበሩ፤ በውጪው በነጭ እብነ በረድ ተሸፍነው ከውስጥ በኩል በወርቅ ተሸፍነዋል። በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሃይማኖታዊ አገልግሎቶች የሚሆኑ ዕቃዎች በሙሉ ከወርቅ የተሠሩ ነበሩ። ቤተ መቅደሱ ሲዘጋጅ ሰሎሞን ሽማግሌዎችንና ብዙ ሰዎችን ለቅድስና ጠራ። የመለከት ድምጽ እና የመንፈሳዊ ዝማሬ ዝማሬ ታቦተ ሕጉ በውስጡ ተቀመጠ። የእግዚአብሔር ክብር በደመና አምሳል መቅደሱን ሞላው፡፡ (፩ኛነገ.፮፥፩-፲)

ከዚያም ሰሎሞን ወደ ንጉሣዊ ስፍራው ወጣ፤ ተንበርክኮም እጆቹን ከፍ አድርጎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ በዚህ ስፍራ የእስራኤላውያንን ብቻ ሳይሆን የአሕዛብንም ጸሎት እንዲቀበል ጸለየ። ይህን ጸሎት በፈጸመ ጊዜ እሳት ከሰማይ ወርዳ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተዘጋጅቶ የነበረውን መሥዋዕት በላ።

የጠቢቡ ሰሎሞን አገዛዝ ሰላማዊና እግዚአብሔርን የሚያስደስት ነበር። ሰዎች ንጉሡን ለማየትና ጥበቡን ለመስማት ከሩቅ ሀገር ወደ ኢየሩሳሌም ይመጡ ነበር። የሳባ ንግሥት የሰሎሞንን ክብር ሰምታ በእንቆቅልሽ ልትፈትነው መጣችና ጥበቡን ካወቀች በኋላ ‹‹አንተን የወደደ፥ በእስራኤልም ዙፋን ያስቀመጠህ አምላክህ እግዚአብሔር የተባረከ ይሁን! እግዚአብሔር እስራኤልን ለዘለዓለም ወዶታልና ስለዚህ ጽድቅና ፍርድ ታደርግ ዘንድ ንጉሥ አድርጎ አስነሣህ›› ብላ እንደመሰከረች በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፏል፡፡ (፩ኛነገ.፲፥፱)

በሀገራችንም ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት የተነሡ ነገሥታት ከአምላካቸው በተሰጣቸው ጥበብ ሕዝባቸውን በፍቅርና በሰላም እንዲሁም በአንድነት በመምራት በጽድቅ ሥራም ተጠምደው እንደኖሩ እንደ መጽሐፈ ስንክሳር ያሉ ቅዱሳት መጻሕፍት ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም ላይ እነ ንጉሥ ላሊበላ፣ ንጉሥ ፋሲለደስ፣ ቅዱስ ይምርሐነ ክርስቶስና ቅዱስ ነአኩቶ ለአብ እንዲሁም ሌሎች ቅዱሳን ነገሥታት መጥቀስ ተገቢ ነው፡፡ የእነርሱም ሥራ ለብዙዎች የክርስትና ሕይወት ስኬት ሲሆን አማላጅነትና ተራዳኢነታቸውም ደግሞ ድኅነት ሆኗል፡፡ የጽድቅ ሥራቸውም የተደነቀ ነው፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በቅዱሳኑ አማላጅነትና ተራዳኢነት ይማረን፤ አሜን፡፡