በዓለ ደብረ ታቦር

ነሐሴ ፲፩፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

በተከበረች በነሐሴ ፲፫ በታቦር ተራራ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን የገለጠበት ዕለት በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ”በዓለ ደብረ ታቦር‘ ተብሎ ይከበራል፡፡

በዚህችም ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስቱን ደቀ መዛሙርቶቹን ጴጥሮስን፣ ያዕቆብንና ዮሐንስን ይዞ ወደ ታቦር ተራራ ላይ አወጣቸው። መልኩም በፊታቸው ተለወጠ፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ሆነ። ስለ እነርሱም ጌታችን ”የሰው ልጅ በጌትነቱ ሲመጣ እስከሚያዩት ድረስ በዚህ ከቆሙት መካከል ሞትን የማይቀምሱት አሉ‘ አለ።

ሰዎች ሁሉ እርሱ ለሙሴ ጌታውና ከሞት ያስነሣው እንደሆነ ለኤልያስም ፈጣሪው እንደሆነና ካሳረገበትም ያወረደው እርሱ እንደሆነ ያውቁ ዘንድ እነሆ ከጌታ ከኢየሱስ ጋራ እየተነጋገሩ ሙሴና ኤልያስ ወደርሱ መጡ። ስለዚህም ጴጥሮስ ጌታችንን እንዲህ አለው፤ ”አቤቱ በዚህ ትኖር ዘንድ ትወዳለህን? ሦስት ሰቀላዎችንም አንድ ላንተ፣ አንድ ለሙሴ፤አንድ ለኤልያስ እንሠራ ዘንድ።‘

በዚህም ቃል የደካማነትና የትሕትና ምልክት አለበት። ደካማነት የተባለ ጴጥሮስ ጌታችን ከሰማይ የወረደበትን ሥራ ትቶ በተራራ ላይ ይኖር ዘንድና ራሱን የሚሠውርበትን ቤት ይሠራለት ዘንድ የተናገረው ነው። ትሕትና ያልነውም ጴጥሮስ ለራሱና ለባልንጀሮቹ ሐዋርያት ቤት ይሠራ ዘንድ ስለ አላሰበ ነው። ራሱንና ባልንጀሮቹ ሐዋርያትን እንደ ባሮች ነቢያትን ደግሞ እንደ ጌቶች አድርጎ አስቧልና። ስለ ሐዋርያትም የእውቀት ማነስ አታድንቅ፤ በዚያን ጊዜ ፍጹማን አልሆኑምና። እንዲህም በሚልበት ጊዜ ጌታችን በሰው እጅ የተሠራ ማደሪያን የማይሻ መሆኑን ለጴጥሮስ ያሳየው ዘንድ እነሆ ደመና ጋረዳቸው።

የጌታችንን ጌትነቱን የሚገልጽ በሐዋርያትም ልቡና እምነትን የሚያጸና እንዲህ የሚል ቃል ከደመና ውስጥ መጣ። ”ይህ የምወደው በእርሱ ደስ የሚለኝ ልጄ ይህ ነው፤  እርሱንም ስሙት።‘ ሙሴና ኤልያስም ከእርሱ ጋራ ሲነጋገሩ ተሰሙ፤ ስለ እርሱ መምጣት የተናገሩትን ትንቢታቸውንም በቸርነቱ አረጋገጠ። ወደ ተራራ ላይ በመውጣቱም ነቢያትና ሐዋርያት ደስ አላቸው።

ሁለተኛም የአብን ቃል በሰሙ ጊዜ ከእነርሱ ሥውር የነበረ የወልድ ዋሕድን በእውነት ሰው መሆን በዚያን ጊዜ ተረዱ፤ ያን ጊዜ የጌትነቱ ክብር ተገልጦአልና። ሐዋርያትም ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው የሆነ እርሱ ሙሴን ከመቃብር ያስነሣው፤ ኤልያስንም ያሳረገው፣ አውርዶም ያመጣው እርሱ እንደሆነ አወቁ። ከእርሱ በቀር ማንም ማን የሙሴን መቃብር የሚያውቅ የለምና ከዐሳረገው ከእርሱ በቀር ማንም ማን ኤልያስ ያለበትን የሚያውቅ የለምና። በሰማይና በምድር ሥልጣን ካለው ከሁሉ ጌታ በቀር ሙታንን አድኖ ሊያስነሣቸው ማንም አይችልም።

ደብረ ታቦርም የቤተ ክርስቲያን አምሳል ሆነች፤ ከብሉይና ከሐዲስ በውስጧ ሰብስባለችና። የአብንም ቃል በሰሙ ጊዜ በግምባራቸው ፍግም ብለው በምድር ላይ ወደቁ፤ እንደ ሙታንም ሆኑ። ከዓለም አስቀድሞ ከእርሱ ጋራ በህልውና እንዳለ ለልጁ አብ ምስክርን ሆነ፤ ወዲያውኑ ሙሴ ወደ መቃብሩ ኤልያስም ወደ ቦታው ተመለሱ።

ሐዋርያትንም በአነቃቸው ጊዜ ከብቻው ጌታችን በቀር ማንንም አላገኙም። ከባሕርያችን የተዋሐደና ሥጋችንን የለበሰ ፍጹም አምላክ እንደሆነ በዚህ ሐዋርያት አስተማሩ።

እንግዲህ እናስተውል! ሰው ካልሆነ ቅዱስ ገብርኤል እመቤታቸንን ድንግል ማርያምን በአበሠራት ጊዜ ”እግዚአብሔር ከአንቺ ጋራ ነው‘ እንዴት አላት?። አምላክ ካልሆነስ ለመንግሥቱ ፍጻሜ የለውም እንዴት አላት? ሰው ካልሆነ በበረት እንዴት አስተኙት? አምላክስ ካልሆነ መላእክት ከሰማይ ወርደው ለእግዚአብሔር በሰማያት ምስጋና በምድርም ሰላም ለሰውም ግዕዛኑ ሊሰጠው እያሉ እንዴት አመሰገኑ?

ሰው ካልሆነ ዮሐንስ በውኃ እንዴት አጠመቀው? አምላክስ ካልሆነ አልዓዛርን ከመቃብር እንዴት ሊያስነሣው ቻለ? ይህ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው እንድ ልጅ አካላዊ ቃል እግዚአብሔር እርሱ ያለ መለወጥ ያለ መለየት አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው እንደሆነ እናምንበታለን። እርሱም ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋራ ሁል ጊዜ አንድ ህላዌ ነው፤ ዛሬም ዘወትርም ለዘለዓለሙ አሜን።

ምንጭ፡- መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ