ፅንሰታ ለማርያም

ነሐሴ ፮ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ለዓለም ሁሉ የድኅነት መገኛ የሆነች ክብርት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተፀነሰችበት ዕለት ነሐሴ ሰባት የተባረከች እንደመሆና መላው ክርስቲያን በዓሏን ሊያከብር ይገባል፤ የመፀነሷ ነገርም እንዲህ ነው፡፡

አስቀድሞ አምላካችን እግዚአብሔር የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልን በተባረከች በታኅሣሥ ወር ፳፪ ቀን ወደ ከበረና ከፍ ከፍ ወዳለ ጻድቅ ኢያቄም ላከው፡፡ አምላክን የወለደች የእመቤታችን የድንግል ማርያምን ፅንሰቷንና ልደቷን በእርሷም ለዓለሙ ሁሉ ድኅነትና ተድላ ደስታ እንደሚሆንም ነገረው፡፡ ይህ ጻድቅ ሰው ኢያቄምና የከበረች ሚስቱ ሐና ልጅ ሳይወልዱ ሸመገሉ፡፡ የከበረች ሐናም መካን ሁናለችና ስሊዚህም እጅግ ያዝኑ ነበር፡፡ የእስራኤል ልጆች ”ልጅ ያልወለደውን ከእግዚአብሔር በረከትን ያጣ ነው‘ እያሉ ያቃልሉት ነበርና፡፡ እነርሱም ልጅን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ዘወትር ፈጽሞ ይለምኑ ነበር፡፡

ከዚህም በኋላ ወንድ ልጅን ወይም ሴት ልጅን ቢወልዱ ለእግዚአብሔር ቤት አገልጋይ ሊያደርጉ ስለትን ተሳሉ፡፡ የከበረ ኢያቄምም በተራራ ላይ ሳለ ሲጸልይና ሲማልድ እነሆ በላዩ እንቅልፍ እንቅልፍ ብሎት አሸለበ፡፡ ያን ጊዜም ከእግዚአብሔር የተላከ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ተገለጸለት፡፡ እንዲህም አለው፤ ”ሚስትህ ሐና ትፀንሳለች ፤ ዓለሙ ሁሉ ደስ የሚሰኝባትን፣ የብዙዎችም ዓይነ ልቡናቸው በእርሷ የሚበራላቸውንና በእርሷም ድኅነት የሚሆንባትን ሴት ልጅን ትወልድልሃለች፡፡‘ በነቃ ጊዜም ወደ ቤቱ ሂዶ ለሚስቱ ለቅድስት ሐና ነገራት፤ ራእዩም እውነት እንደሆነ አመኑ፡፡

ከዚህም በኋላ በከበረች በነሐሴ ሰባት ቀን ቅድስት ሐና ፀነሰች፤ ለዓለም ሁሉ መመኪያ የሆነች በሁለት ወገን ድንግል የሆነች የአምላክ እናት እመቤታችንን ማርያምንም በግንቦት መባቻ ወለደቻት፡፡

ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን፤ እኛንም በከበሩ ኢያቄምና ሐና ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸው ከእኛ ጋር ይኑር፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

ከመጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ነሐሴ