በዓለ ደብረ ቊስቋም

ኅዳር፤ ፳፻፲፬ ዓ.ም

ደብረ ቊስቋም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የተወደደ ልጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግደል ከሚፈልጉት ሸሽተው መጠጊያ ያገኙበት እንዲሁም ቅዱስ ገብርኤል ንጉሥ ሄሮድስ መሞቱን ለቅዱስ ዮሴፍ በሕልሙ የገለጸበት ስፍራ ነው፡፡ ‹‹የሕፃኑን ነፍስ የሚሹ ሞተዋልና፥ ተነሥተህ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ እስራኤል ሀገር ሂድ›› እንዲል። (ማቴ.፪፥፲፱-፳)

በመጽሐፈ ስንክሳር እንደተጻፈውም ጌታችን ኢየሱስ ዳግመኛም በኋላ ዘመን ሐዋርያትን በደብረ ቁስቋም ሰብስቦ በኅዳር ፮ ቀን ‹‹አስተጋብኦሙ እግዚእነ ለሐዋርያቲሁ ቅዱሳን ውስተ ዝንቱ ደብረ ቊስቋም ወቀደሰ ታቦተ ወቤተ ክርስቲያን ወሠርዐ ቊርባነ ወመጠዎሙ ሥጋሁ ቅዱሰ ወደሞ ክቡረ፤ በዚህ በደብረ ቊስቋም ቅዱሳን ሐዋርያቱን ሰብስቧቸዋል፤ ታቦትንና ቤተ ክርስቲያንንም አክብሮ የቊርባን መሥዋዕትንም ሠርቶ ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን ሰጥቷቸዋል፡፡›› (መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፮)

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከልጇ ጌታችን ኢየሱስ ጋር ከስደት መመለሳቸውን በመዘከር ኅዳር ፮ ቀን ታከብራለች፡፡ ይህም በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈ ሄሮድስ ጌታችንን ለመግደል በፈለገ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ለአረጋዊው ዮሴፍ በሕልሙ ‹‹ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ›› ባለው መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ (ማቴ. ፪፥፲፫-፲፭)

እመቤታችን ቅድስት ማርያም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር ከመሰደዷ አስቀድሞ ነቢዩ ኢሳይያስ ‹‹ወይወርድ እግዚእነ ውስተ ምድረ ግብፅ እንዘ ይጼዐን ዲበ ደመና ቀሊል፤ ጌታችን በፈጣን ደመና (በእመቤታችን ጀርባ) ተጭኖ ወደ ግብፅ ይወርዳል›› ተብሎም በተናገረው መሠረት ትንቢቱ ተፈጽሟል፡፡ (ኢሳ. ፲፱፥፩)

እመቤታችንም ልጇን ይዛ ከስደት ስትመለስ ያረፈችበትን ተራራ ደብረ ቁስቋምን ባረከችው ቀደሰችውም፤ ይህ ተራራ የተቀደሰ ተራራ ስለመሆኑ የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ ቅዱስ ታኦፊሎጎስ በድርሳነ ማርያም እንዲህ አለ፤ ‹‹ይህም ከሀገሮቹ ሁሉ ተራሮች የሚበልጥ (የተለየ) ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በውስጡ ቅዱስ አግዚአብሔር ያድራል፡፡ ይህንን ተራራ የእግዚአብሔር ልጅ ወዶታል፤ አክብሮታልምና፤ ከዓለም ሀገሮች ሁሉ ከተቀደሰች እናቱ ጋር አድሮባታልና፡፡ ከመላእክት ቤት ያድር ዘንድ አልወደደም፤ ቢታንያንም አልመረጠም፡፡ ከተራራው ላይ ባለች ገዳም ቤት ውስጥ አደረ እንጂ፤ ነቢዩ ዳዊት፤ የጽዮንን ተራራ ወደደ፤ በአርያምም መቅደሱን ሠራ እንዳለ፡፡›› ‹‹አንተ ተራራ ሆይ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆንህ ጊዜ በኪሩቤልና በሱራፌል መካከል ፍጹም ደስታ ተደረገ፡፡ የመላእክት ሠራዊት ቅዱስ የሆነ ፈጣሪያቸውንና ጌታቸውን ይታዘዙ (ያገለግሉ) ነበር፡፡ አንተ ተራራ ሆይ ያደረብህ ጌታችን ስለሆነ ከተራሮች ሁሉ ከደብረ ሲናም ይልቅ ከፍ ከፍ አልህ፤ ጌታችን በደብረ ሲና ባረፈ ጊዜ ፍጹም ደስታ፣ ታላቅ ብርሃንም በሆነ ጊዜ መቅረብና መመልከት ከሙሴ በቀር የቻለ የለም፡፡ እርሱም ቢሆን ፊቱን ማየት አልቻለም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እርሱን ዐይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው የለምና፡፡ እኛ ግን አየን፤ ከዚህ ማደሩንም ተረዳን፤ ዳግመኛም ንጽሕት በሆነች በማርያም ዘንድ አየነው፡፡ ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ዘንድ በቤተልሔም ስለ እኛ በተዋሐደው ሥጋ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ያለን እኛን ከቸርነቱና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ መጥቶ አዳነን፤ ከዓለም ሁሉ ይልቅ ጣዖትን በማምለክ ሲበድሉም ወደ ግብፅ ሀገር ወርዶ በእነርሱ ላይ የመለኮትነት ብርሃኑን በማብራት ታላቅ የሆነ ክብሩን ገለጠ››፡፡ (ድርሳነ ማርያም)

ሊቁም በመቀጠል ሙገሳውን እንዲህ ሲል ገልጿል፤ ‹‹አንተ ተራራ ሆይ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሆንህ ጊዜ በኪሩቤልና በሱራፌል መካከል ፍጹም ደስታ ተደረገ፡፡ የመላእክት ሠራዊት ቅዱስ የሆነ ፈጣሪያቸውንና ጌታቸውን ይታዘዙ (ያገለግሉ) ነበር፡፡ አንተ ተራራ ሆይ ያደረብህ ጌታችን ስለሆነ ከተራሮች ሁሉ ከደብረ ሲናም ይልቅ ከፍ ከፍ አልህ፤ ጌታችን በደብረ ሲና ባረፈ ጊዜ ፍጹም ደስታ፣ ታላቅ ብርሃንም በሆነ ጊዜ መቅረብና መመልከት ከሙሴ በቀር የቻለ የለም፡፡ እርሱም ቢሆን ፊቱን ማየት አልቻለም፡፡ ሥጋ ለባሽ ሁሉ እርሱን ዐይቶ በሕይወት መኖር የሚቻለው የለምና፡፡ እኛ ግን አየን፤ ከዚህ ማደሩንም ተረዳን፤ ዳግመኛም ንጽሕት በሆነች በማርያም ዘንድ አየነው፡፡ ቅድስት ከሆነች ከእመቤታችን ማርያም ዘንድ በቤተልሔም ስለ እኛ በተዋሐደው ሥጋ በጨለማና በሞት ጥላ ሥር ያለን እኛን ከቸርነቱና ሰውን ከመውደዱ የተነሣ መጥቶ አዳነን፤ ከዓለም ሁሉ ይልቅ ጣዖትን በማምለክ ሲበድሉም ወደ ግብፅ ሀገር ወርዶ በእነርሱ ላይ የመለኮትነት ብርሃኑን በማብራት ታላቅ የሆነ ክብሩን ገለጠ››፡፡ እመቤታችን ቅድስት ማርያምም ከጌታችን ኢየሱስ ጋር በዚህም ተራራ ስድስት ወራት ዐርፈዋል፡፡ (ድርሳነ ማርያም)

ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን!

ምንጭ፤ ድርሳነ ማርያም መጽሐፍ ትርጉም በመምህር ተስፋ ሚካኤል፤ ፳፻፫ ዓ.ም፣መጽሐፈ ስንክሳር ኅዳር ፮