ቅዱስ ፓትርያርኩ በ፲ኛው በዓለ ሲመታቸው ላይ ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የኒዮርክ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዕ አቡነ ሄኖክ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት

ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያ ኃላፊዎች

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኃላፊዎች

የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች

ክቡራን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎችና በአጠቃላይ በዚህ የበዓለ ሢመት ሥነ በዓል ላይ የተገኛችሁ ምእመናንና ምእመናት በሙሉ

በክብረ ክህነት በፊቱ ቆመን እንድናገለግለው በልዩ ጸጋው የጠራን እግዚአብሔር እንኳን ለ10ኛው ዓመት በዓለ ሢመት በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!!

“ኦ አባ ቅዱስ ዕቀቦሙ በስምከ ለአለ ወሀብከኒ ከመ ይኩኑ አሐደ ብነ ከማነ፤ ቅዱስ አባት ሆ እነዚህ የሰጠኸኝን እንደኛ በእኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው፡፡” (ዮሐ.፲፯፥፲፩)

ይህ ዐረፍተ ነገር ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታወቀውና የመጨረሻ ጸሎቱ በሆነው በምሴተ ሐሙስ ከጸለየው ጸሎት የተወሰደ ጥቅስ ነው፡፡

ጌታችን ሰውነታችንን ሰውነት አድርጎ በዚህ ዓለም እንዲገለጥ ምክንያት የሆነው በዚህ ዐረፍተ ነገር የተቀመጠው ደ መሠረተ ሐሳብ ነው፤ ይኸውም “የተለያዩትን አንድ ማድረግ” የሚለው ነገር ነው። ለዚህም አንድነት እውን መሆን እንደ ዐቢይ መመዘኛ አድርጎ ያቀረበው መለኪያ “እንደ እኛ” የሚለው ኀይለ ቃል ነው። ጌታችን ‘እኛ አንድ እንደሆንን እነሱም እንደ እኛ በእኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው’ ሲል የአባቱን÷ የቅዱስ መንፈሱንና የራሱን አንድነት ማመልከቱ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ከዚህ አንጻር የእሱ ተከታዮች ሊከተሉት የሚገባ አንድነት የእግዚአብሔር አብን የእግዚአብሔር ወልድንና የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን አንድነት የመሰለ አንድነት ነው። የሥሉስ ቅዱስ አንድነት ነቅዕ የሌለው ፍጹምና የተለየ ዘላለማዊ አንድነት እንደሆነ ሁሉ፥ የክርስቲያኖች አንድነትም በዚያው ልክ ነቅዕ የሌለው ፍጹም አንድነት እንዲሆን ጌታችን ጸልዮአል፤ ለአንድነታችን አስተማማኝ እ ጥበቃ እንዲደረግለትም የኩነት አባቱ ለሆነው እ ለእግዚአብሔር አብ ጸሎት አቅርቦአል። ከዚህ የጌታችን ጸሎት እንደምንገነዘበው በእግዚአብሔርና በሰዎች፣  በሰዎችና በመላእክት በሰዎችና በሰዎች መካከል ያለውና የሰፋ መለያየት መኖሩን ነው፡፡

ጌታችን የማይፈልገውና ሊያስወግደውም የፈለገው ይህን መለያየት ነው፤ መቼም ቢሆን ንጹሐ ባሕርይ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ ይቅርና ጤናማ አእምሮ ያለው ፍጡርም መለያየትን ይመርጣል ወይም ይደግፋል ተብሎ አይታሰብም፤ እግዚአብሔር ደግሞ ከማንም በላይ መለያየትን ይጠላል። እንዲህ ባይሆን ኖሮስ ለምእመናን አንድነት ሲል ሰው ሆኖ ደሙን ባላፈሰሰ ነበር፤ የተለያዩትን ለማስታረቅ ሲል ግን እስከ መሰቀል ደረሰ፤ በመሰቀሉም ሁሉን አስታርቆ የተለያዩትን አንድ አደረገ፤ ከዚህ አኳያ በኅብረትና በአንድነት መኖር ለፍጡራን የውዴታ ሳይሆን የግዴታ ሆኖ እንዲቀጥል የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡

በመሆኑም መለያየት ለጊዜያዊ ፍላጎት ተብሎ ይሞከር እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ሆኖ አያውቅም፤ ምክንያቱም መለያየት የእግዚአብሔር ፈቃድ ካለመሆኑም ባሻገር ፍጡራን ከመተባበርና አንድ ሆኖ ከመኖር የተሻለ አማራጭ የላቸውምና ነው፡፡

የዓለም ማኅበረሰብም ይህን የእግዚአብሔር ጥበብና ፈቃድ አውቆም ይሁን ሳያውቅ በኅብረት መኖርን አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ አምኖ በመቀበል ለተግባራዊነቱ ደፋ ቀና ሲል መታየቱ ይህንን ሐቅ ያረጋግጣል። የዓለም ማኅበረሰብ በዓለም አቀፍና በአህጉር ደረጃ፡ ከዚያም በየቀጠናው የብረት ተቅዋማትንና ድርጅቶችን እየመሠረተ ለጋራ ጥቅም በጋራ እየሠራ ይገኛል:: የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፥ የአፍሪካ በኅብረትም፥ኢጋድ እና ሌሎች የኅብረት ተቅዋማት የዚህ ማሳያዎች ናቸው፤ ሃይማኖታውያንም በተመሳሳይ ከዓለም አቀፍ ጀምሮ እስከ ሀገር ድረስ ያሉ የተለያዩ የሃይማኖት ተቋማትን በጋራ ለጋራ በማቋቋም የጋራ ችግራቸውን በጋራ ለመፍታት እየሠሩ ናቸው፡ ታዲያ በብዙ ምክንያት ተለያይተው የነበሩ አካላት በኅብረትና በአንድነት ሆኖ መሥራት የሚያስገኘውን ጥቅም በሚገባ ተረድተው ሲሰባሰቡ፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለመለያየት ሙከራ ሲያደርጉ የሚታዩት ለምንድን ነው?

እርግጥ ነው አንዳንድ ጊዜ ሰዎች መለያየት ጐጂ መሆኑን እያወቁም መለያየትን እንደ አማራጭ ሊያዩ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ከመልካም አስተዳደር እጦት የተነሣ በሚደርስ ጥቃትና ጫና ሊሆን ይችላል ተብሎ ይገመታል፤ ሆኖም የዚህ መድኀኒቱ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እኩልነትን ማረጋገጥ፡ ፍትሕንና ርትዕን ማንገሥ ልማትንና ዕድገትን ማቀላጠፍ፥ ዜጎች በሀገራቸው የተሟላ ዋስትና ባለው ህላዌ እንዲኖሩ ማስቻል እንጂ መለያየት ምንጊዜም ቢሆን መፍትሔ ሊሆን አይችልምና ሰከን ብሎ ነገሮችን ማየት ተገቢ ነው እንላለን፡፡

መለያየት አንዱን ወገን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በእኩል ይጐዳል፤ በቤተ ክርስቲያን የሚፈጠር መለያየትም ከሌላው ሁሉ በባሰ ሁኔታ የማኅበረሰብን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ሕይወት በእጅጉ ይጐዳል። በውጤቱም ደካማ ሀገርንና ማኅበረሰብን ይፈጥራል። በዓለም ታሪክ በግልጽ ተጽፎ የምናገኘው ሀቅ ይህ ነው፤ “እርስ በርስዋ የምትለያይ መንግሥት ትጠፋለች፤ እርስ በርሱ የሚለያይ ቤትም ይፈርሳል” የሚለው የጌታችን አስተምህሮም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡

በሀገራችን እየታየ የከረመው ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ትርምስም ለዚህ አደጋ ያልተጋለጠ ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ እርግጥ ነው እጅግ የሚያስቆጡና የሚያበሳጩ ነገሮች በዚህች ሀገር መፈጸማቸውን በትክክል አይተናል፤ ይህ ፈጽሞ መሆን ያልነበረበት ነው፤ ከሆነ በኋላ ግን በንስሓ ከማስተካከል በቀር ሌላ አማራጭ አይኖርምና በተፈጠረው ስሕተት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ዕንባቸውን በአግባቡ ማበስ ብንችል፣ የተዛባውንም ሁሉ ወደነበረበት ብንመልስ፤ ትክክለኛ ፍትሕንም ብንሰጥ፤ የጠፋውና የወደመውንም እንደነበረው አድርገን ብንተካ ንስሓው በእግዚአብሔርም ሆነ በሰው ተቀባይነት ይኖረዋል፤ ምክንያቱም ለአብሮነትና ለአንድነት ፈዋሽ መድኍኒቱ ይህና ይህ ብቻ ነውና።

ከቅርብ ቀናት በፊት በቤተ ክርስቲያን አንድነት ላይ አጥልቶ የነበረው አደገኛ አዝማሚያ በሰላማዊ መንገድ ለማረም ጥቅም ላይ የዋለው የዕርቅና የሰላም ጥበብ በሁሉም ሀገራዊ ችግሮች ሊደገም ይገባዋል፡፡ ትልቁ የችግር መፍትሔ ትዕግሥት ውይይትና መቻቻል እንጂ ግጭት አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ያጋጠማትን ችግር በቀላሉ ለመፍታት የወሰደችው እርምጃ በንስሓ፡ በሰላምና በውይይት መፍታት የሚያስገኘውን መንፈሳዊ ጥቅም በመረዳት እንጂ የተፈጸመው ሕገ ውጥ ድርጊት ቀላል ስለሆነ አይደለም።

ለችግሩ መከሠት እንደ ምክንያት ሆነው ይጠቀሱ ከነበሩ መካከል ቋንቋ ነክ ነገሮች እንዳሉበት ሰምተናል፤ ነገር ግን በቋንቋ መማርና ማስተማር፡ ማምለክና መተዳደር የመለያየት ምክንያት ሊሆን አይገባውም ነበር፤ ምክንያቱም በቋንቋ የመገልገል ጥያቄ በቅዱስ መጽሐፍና በሕገ ቤተ ክርስቲያን በግልጽ ተመልሷልና ነው፡፡

ከዚህ የተለየ ሌላ ችግር ካለ ጥያቄው በግልጽ እስከቀረበ ድረስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ጠብቀንና ሕገ ቤተ ክርስቲያንንና ቀኖና አበውን መሠረት አድርገን በጋራ የማንፈታው ችግር አልነበረም፤ የተዛቡትን ነገሮች በሕግና በሥርዐት ለማስተካከል ከሁሉም በፊት የሕግ የበላይነት ተከብሮ ነገሮች ወደነበሩበት እንዲመለሱ ማድረግ ግድ ነበር። ሕገ ወጥ ድርጊት ሲፈጠር እንዲህ ያለውን መርሕ የማንከተልና የተፈጠረውን ችግር በንስሓና በይቅርታ የማናስተካክል ከሆነ በእግዚአብሔርም በሰውም በታሪክም ከተጠያቂነት አናመልጥም።

በዚህ ሥልጣነ ክህነት በሐዋርያት እግር ተተክተን የምንገኘው ሁላችንም ሊቃነ ጳጳሳት በጎቹን ለመበታተንና አለያይተን ለማፋጀት ሳይሆን ለማሰባሰብና አንድ ለማድረግ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም፤ ይህንን የማናስከብር ከሆነ በዓለ ሢመትን ማክበር፡ ሥልጣነ ክህነትም አለኝ ማለት ምን ፋይዳ አለው ስለዚህ አሁንም ሰከን ብለን እናስብና ወደ ልባችን እንመለስ፡፡

የተከሠተው ችግር ለጊዜው መልክ ቢይዝም ቀጣይ ሥራ እንዳለን ግን ከሁኔታው አይተናል፣ ጉዳዩን በጥልቀት አይተን ዘላቂ መፍትሔን ማበጀት አሁንም ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ሊሠሩ የሚገባቸው ብዙ ሥዎች አሉ፤ የተዘነጉና መስመራቸውን የለቀቁም አይታጡም፣ ሕዝቡና የሚመለከታቸው አካላትም አንድ ሁለት ሦስት ብለው ሲነግሩን እየሰማን ነው፤ ይህ በምንም ተአምር ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፤ ማስተካከልም አለብን።

የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ህልውና ከሚያስቀጥለው ሐዋርያዊ ተልእኮ ባሻገር፣ የቤተ ክርስቲያንን የሥራ አፈጻጸም ከአባካኝነት ከአድልዎ ከዘረኝነትና ከፖለቲከኝነት ለማጽዳት በቁርጠኝነት መሥራት አለብን፡፡ እስከ መቼ በዚህ ስንታማ እንኖራለን፤ ከእንግዲህ ወዲህ በቃ፤ ማስተካከል አለብን ማስተካከል አለብን ማስተካከል አለብን!

ከዚህ ይሁን በኋላ ከላይ ጀምሮ እስከታች ባለው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር የምንገኘው ውሉደ ክህነት ለዚህ ቅዱስ ዓላማ አንድ ሆነን በጽናት መቆምና መሥራት አለብን) ድጋፍ ሰጪ አካላትም በዚህ ጉዳይ ከጎናችን ሆነው እንዲያግዙን መፍቀድ አለብን፤ ይህንን ምኞታችንን እንዲያሳካልንም ወደ እግዚአብሔር ከልብ እንጸልይ፡፡

መልካም በዓለ ሢመት ያድርግልን፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤

አባ ማትያስ ቀዳማዊ

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

የካቲት ፳፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ