ቃል ኪዳን

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

የካቲት ፲፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለከበረው ጤንነታችሁ እንደምን አላችሁ? ነቢየ እግዚአብሔር ንጉሥ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ ‹‹…እናንት ልጆች የአባትን ተግሣጽ ስሙ፤ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ›› (መዝ.፬፥፩) በማለት እንደተናገረው የአባቶቻችሁን ተግሣጽ (ምክርና ቁጣ) ሰምታችሁ፣ በእግዚአብሔር ጥበቃ ከትላንት ዛሬ የደረሳችሁ ልጆች! ለዚህ ያደረሰንን እግዚአብሔር ይመስገን አላችሁ? መልካም!

በዓላት እንዴት አለፉ? ትምህርተስ እንዴት ነው? መቼም የመንፈቀ ዓመት ፈተና የተፈተናችሁ አላችሁ! እንዲሁም በፈተና ላይም የምትገኙም አላችሁና በርቱ! ብልህና አስተዋይ መሆን አለባችሁ!

ልጆች! የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ታሪክ ቅዱስ ሉቃስ በጻፈልን ወንጌል ላይ ስናነብ እንዲህ የሚል ቃል ተጽፏል፤ ‹‹…ኢየሱስም ደግሞ በጥበብና በቁመት በሞገስም በእግዚአብሔርና በሰው ፊት አደገ…›› (ሉቃ.፪፥፶፪) እናም ልጆች በጥበብና በሞገስ ልናድግ ይገባል፤ ስለሁሉም ነገር በርቱ!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ የምንነግራችሁ ታሪክ ስለ እመቤታችን ቃል ኪዳን ነው፤ ቃል ኪዳን ማለት ‹‹ውል ወይም ስምምነት›› ማለት ነው፤ እግዚአብሔር ከአባቶቻችን ጋር በተለያየ ጊዜ ቃል ኪዳንን ገብቷል፤ እንደ ትእዛዙ ለሚኖሩ የሚፈልጉትን ሊያደርግላቸው ቃል ኪዳንን ሰጥቷቸዋል፤ በነቢዩ ሕዝቅኤል ‹‹የሰላምም ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር አደርጋለሁ፤ ዘለዓለም ቃል ኪዳን ይሆንላቸዋል፤ እኔም እባርካቸዋለሁ፤ አበዛቸውማለሁ፤ መቅደሴንም ለዘለዓለም በመካከላቸው አኖራለሁ…›› (ሕዝ.፴፯፥፳፮) በማለት ነግሮናል፡፡

ውድ እግዚአብሔር ልጆች! የእመቤታችንን በዓላት ከምናከብራቸው አንዱ ኪዳነ ምሕረት      (የምሕረት ቃል ኪዳን) የሚባለውና ወር በገባ በ ፲፮ (ዐሥራ ስድስት) የምናዘክረው አንዱ ነው፤ ይህ በዓል ጌታችን ኢየሱስ ለእመቤታችን ስሟን የጠራ (የተማጸነ) ዝክሯን ለዘከረ (ለነዳያን በስሟ ለመገበ)፣ በአማላጅነቷ ለተማጸነ፣ ይቅርታን እንደሚያገኝ እመቤታችን በሥጋም በነፍስም ከሚገጥመው መከራ እንደምትታደገው የተገባላት ቃል ኪዳን ነው፡፡ ይህም ዕለት የካቲት ፲፮ ቀን ስለሆነ ዓመታዊ ክብረ በዓሏ በመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ይከበራል፡፡

ልጆች! ለግንዛቤ ያህል ስለቃል ኪዳን ይህን ካልን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት እመቤታችን በቃል ኪዳኗ ስላዳነችው አንድ ሰው ታሪክ በአጭሩ እንመልከት፤

እመቤታችንን የሚወድ ለሰዎች መልካም የሚያደርግ ስምዖን (በላኤ ሰብ) የተባለ መልካም ደግ ሰው ነበር፡፡ ካለው ነገር ሁሉ ለሌላቸው ሰዎች ያካፍላል፤ በእመቤታችን ስም ዝክር እያዘጋጀ ለድሆች ይመግባል፤ እንዲህ ያለ መልካም ሥራ እየሠራ ሲኖር በዚህ መልካም ሥራው ሰይጣን ቀና፤ ከዚያም ይፈትነው ጀመር፤ ልጆች! መልካም ሥራ ልንሠራ ስንነሣ ብዙ እንቅፋች ይገጥሙናል፤ በዚህ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፤ ፈተናውን ታግሠን በመልካምነታችን መቀጠል ይገባናል፤ እናም ይገርማችኋል! ሰይጣን ይህንን መልካምና ደግ ሰው ፈተነው፤ አሳሳተውም፤

ከዚያም ለሰዎች መልካም ያደርግ የነበረውን ሰው ጨካኝና ሰዎችን የሚጎዳ ሆነ፤ ብዙ ዘመን ሰው እያሳዘነ፣ ክፉ ሥራ እየሠራ ኖረ፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ ክብርን ቅድስናን የሚያሰጠውን ለሰዎች ማዘን፣ የተራበ ማብላት፣ ማጠጣት፣ ደካሞችን መደገፍ፣ መጾም፣ መጸለይ ፣ በእመቤታችን ስም መዘከር እነዚህን ሁሉ በጎ ምግባር ማድረግ ትቶ የሰዎችን ንብረት እየዘረፈ መኖርን ለመደው፤ ከእርሱም የእግዚአብሔር ረድኤት ተለየው፤ በጣም ጨካኝም ሆነ፡፡

ልጆች! መልካም ከሠራን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፤ ጥበብን፣ ሞገስን፣ ማስተዋልን እናገኛለን፤ የምንማረው ይገለጥልናል፤ የምንሠራው ይባረክልናል፤ ያሰብንብት እንደርሳለን፤ ዕቅዳችን ይሳካል፤ ይገርማችኋል! ይህ መልካም የነበረው ስምዖን (በላኤ ሰብ) በክፉ ሥራ ተጠምዶ እየኖረ ሳለ ለሰው ማዘን ተወ፤ ይሰጥ የነበረው ቀማኛ ሆነ፤ ተስፋ ቆርጦ መከራ ደረሰበት፤ ከሰው ተለይቶ ጫካ ለጫካ እየዞረ እንደተጨነቀ ኖረ፡፡

ታዲያ አንድ ቀን ምን ሆነ መሰላችሁ? በመንገድ ሲሄድ አንድ በጣም የተቸገረና የሚበላው የሚጠጣው አጥቶ ከመራቡና ከመጠማቱ የተነሣ ደክሞት የተኛ ሰው አየ፤ ይህ ችግረኛ ሰው ‹‹ስለ እግዝእትነ ማርያም፤ ስለ ቤዛዊት ዓለም ራበኝ፤ አብሉኝ! ጠማኝ አጠጡኝ!›› እያለ ይለምን ነበር፡፡ ስምዖን እግዝእትነ ማርያም የሚለውን ስም ሲሰማ ቆም አለ፤ ‹‹ይህን ስም ድሮ አውቀዋለው›› ብሎም ስለእግዝእትነ ማርያም ሰውየው ላይ ጠብታ ውኃ አፉ ላይ ጠብ አደረገለትና መንገዱን ቀጠለ፡፡

ከዚያም ስምዖን የተባለው ሽፍታ (በላኤ ሰብ) ድንገት ሞተና ነፍሱን መላእክተ ጽልመት የተባሉ (የጨለማ መላእክት) ይዘው ወደ ሲኦል ሊወስዷት ሲሉ እመቤታችን ‹‹ይህቺ ነፍስ የእኔ ናት፤ ወደ ገነት ነው የምትሄደው›› አለች፤ ያቺን ነፍስ ጌታችን ጋር ወሰዷት፤ ከዚያም እመቤታችን ለልጇ ለመድኃኔ ዓለም ‹‹በስምሽ የተራበ ያበላ፣ የተጠማ ያጠጣውን እምርልሻለው ብለህ ቃል ኪዳን ገብተህልኛል፤ ይህች ነፍስ በደለኛ ከመሆኗ በፊት በስሜ ትመጸውት ነበር፤ ዝክሬን ትዘክር ነበር፤ ትጾምና ትጸልይ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን አታሏት በኃጢአት ትኖር ነበር፤ ምንም እንኳ በኃጢአት የነበረች ቢሆንም በስተመጨረሻ በእኔ ስም ለተጠማ ሰው ውኃ አጠጥታለች፤ ስለዚህ ወደ ሲዖል ልትገባ አይገባትም፤ በእኔ ቃል ኪዳን ገነት መግባት አለባት›› ብላ አማለደቻት፤ ጌታችንም በገባላት ቃል ኪዳን መሠረት ያቺን ነፍስ ይቅር አላት፡፡

አያችሁ የእግዚአብሔር ልጆች! መልካም ሥራን መሥራት ጥሩ ነው፤ በችግር ጊዜ ድጋፍ ይሆነናል፤ ፈጽሞ ጠፍተን እንዳንቀር ለንስሓ ያበቃናል፤ እናም መልካም እንሥራ! በእመቤታችን አማላጅነት፣ ቃል ኪዳን እንመን! በስሟ ለተራቡ እናብላ፤ ለተጠሙ እናጠጣ፣ ለተቸገሩ እንርዳ፤ በውዳሴ ማርያም ጸሎት ዘወትር ‹‹ቅድስት ሆይ ለምኚልን›› እንበላት!

ልጆች! በቀጣይም ስለ እመቤታችን ታሪክ እንማራለን! በረከት ረድኤቷ ከእኛ ጋራ ይሁን!  ቸር ይግጠመን፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!