ሶርያዊው ቅዱስ ኤፍሬም (ክፍል ሦስት)

ዲ/ን ዮሐንስ ልሳነወርቅ

ግንቦት 4፣ 2003ዓ.ም

ከክፍል ሁለት የቀጠለ

5.የሥጋ(ሰውነት) ክብር (The value of the Body)

ቅዱስ ኤፍሬም የሥጋን ክብር ለመንቀፍ  ከሚሹ ከተወሰኑ የቀድሞ የክርስትና ልማዶች መገለጫ ከሆኑት ከፕላቶናዊ ወይም ከምንታዌ ዝንባሌዎች  ፣  በእጅጉ የራቀ ነው። ለቀና አመለካከቱ መነሻው ነጥብ ሥጋ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት መካከል ስለሆነ ሊጠላ አይገባዉም የሚል እውነታ ነው፤ በየትኛዉም መንገድ  ክፉ ተደርጎ ከሚታሰበው አስተሳሰብ  የራቀ ይሁን። ግና በተጨማሪ ቅዱስ ኤፍሬም ሦስት ጠቃሚ ግንዛቤዎች አሉት።

የመጀመሪያው የራሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥክርነት ነው። 1ቆሮ.619 ላይ ያለውን በመተርጎምሰውነታችሁ ከእናንተ ጋር የሚኖረው የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን?” ቅዱስ ኤፍሬም እግዚአብሔር ራሱ ሰውነትን ለቅድስት ሥላሴ ማደሪያ በማድረግ የሰጠውን ክብር ይጠቁማል።(የቅ/ኤፍሬም አንድምታ በቅ/ጳውሎስ መልእክታት ላይ ገጽ 62) በኋላም 2ቆሮ.5 ያለውን ሲተረጉም እንዲህ ይላልሰውነታችን ለእግዚአብሔር መንፈስ ማደሪያነት የተገባ እንደሆነ ሁሉ በመጨረሻም ለዘለአለማዊ ክብር የተገባ አድርጎታል።”(የቅ/ኤፍሬም አንድምታ በቅ/ጳውሎስ መልእክታት ላይ ገጽ 96) የሰው ሰውነት በጽዮን ተራራ የነበረውን ቤተ መቅደስ በመተካት አዲሱ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እንደሆነ ቅዱስ ኤፍሬም በማንኛዉም ቦታ ይናገራል። (Heresies 42:4)

 

ሁለተኛም እግዚአብሔር ሥጋን የመዋሐዱ እውነታ ስለ ሥጋ ርኩሰት ወይም ለሥጋ አይገባም የምንለው ምንም ነገር እንደሌለ ያመለክታል።(Nativity 9:2) በመጨረሻም ቅዱስ ቁርባን ለቅዱስ ኤፍሬም ስለ ሥጋ ክብር ተመሳሳይ መረጃን ይሰጠዋል። በሚከተለው ጽሑፍ በቅዱስ ቊርባን እያመኑ ነገር ግን  ሰውነትን ርኩስ አድርገው የሚቆጥሩት የክርስቲያን ቡድንን ይሞግታል።

ጌታ ሥጋን እንደ ርኩስ፣ የተጠላና ስሑት

አድርጎ ወቅሶ ቢሆን ኖሮ

ስለዚህ የድሳነት ሕብስቱ ጽዋውም ለእነዚህ መናፍቃን

የተጠላና ርኩስ መሆን አለበት፤

ራሱን በሕብስቱ ውስጥ የሰወረ ሆኖ እያለ

ያ ሕብስት ከዚያ ደካማ ሰውነት ጋር የተዛመደ መሆኑን እያየ

ክርስቶስ ሰውነትን እንዴት ሊንቅ ይችላል።

እንዲሁም እርሱ በማይናገር ሕብስት ተደስቶ ከነበረ

በሚናገርና አመክንዮን ገንዘብ ባደረገ በሰውነትማ

ምን ያህል እጅግ ይደሰት ይሆን!(Heresies 47:2)

እግዚአብሔር የተቀደሰውን ምሥጢር ሥጋዉንና ደሙን በሰው ሰውነት እንዲመገቡት በመፍቀዱ በትክክል ተመሳሳይ ነገር ተጠቁሟል።

ሰውነት ከክፉ ነገር የተገኘ ቢሆን ኖሮ

እግዚአብሔር  ምሥጢራቱን  በሰውነት ላይ ባላሳደረ ነበር።(Heresies 43:3)

ስለዚህም በቅዱስ ኤፍሬም ዓይን ሥጋና ነፍስ እኩል አስፈላጊነት አላቸው፤ የሚጫወቱት የተለያየ ሚና አላቸው።

ሥጋ ላንተ ምሥጋናን ያቀርባል

ምክንያቱም ላንተ መኖሪያ ይሆን ዘንድ ፈጥረኸዋልና፤

ነፍስ አንተን ታመልካለች

ምክንያቱም በመምጣትህ ለሙሽሪትነት አጭተሃታልና። (Heresies 17:5)

ሰውነት የሰርግ ቤትን ሲሆን ሙሽሪት ነፍስ ግን ሰማያዊ ሙሽራን ትገናኛለች።

6.በመንፈሳዊ ትምህርት ጥያቄን ለመጠየቅ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች (The prerequisities for Theological Enquiry)

መንፈሳዊ ትምህርት እንደሌሎች ማናቸውም የህሊና ጥያቄዎች ጥያቄ በሚያቀርበው ሰው ባለው የህሊና ዝንባሌ መሠረት ሦስት የተለያዩ  መልኮች ሊኖረው ይችላል።

በመጀመሪያ ደረጃ ህሊና የጥያቄውን አካል ለመጫንና ለመቆጣጠር ሊፈልግ ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ዝንባሌ ከፍራንሲስ ባኮን ዘመን ጀምሮ በብዛት ለሳይንሳዊና ሌላ ጥያቄ መገለጫ ሆኗል። በትክክልም ይሁን በስህተት ቅዱስ ኤፍሬም ይኽ በዘመኑ ለነበሩ ብዙ የኑፋቄ አሳቢዎች እንደ ዋና ዝንባሌ እንደሆነ አስተውሏል፤በተለይ በመንፈሳዊ ትምህርት መስክ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የህሊና ኩራት ለእርሱ ተቀባይነት የሌለው ነው።

ለሁለተኛው አቀራረብ በአጀማመሩ እጅግ ተቀባይነት ያለው ይመስላል፤በአሁኑ ዘመን የመንፈሳዊ ትምህርት ጥያቄ መለያ የሆነ መልክ አለው። እዚህ ላይ ህሊና በተቻለ መጠን ከተጽእኖ ነጻ በሆነ መልኩና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ የጥያቄውን አካል ለማጥናት ይዘጋጃል። በብዙ አቅጣጫዎች ፍሬያማ የሆነ አቀራረብ ነው፤እንዲሁም ይኽ አቀራረብ ቅዱስ ኤፍሬም የሞከረው መሆኑን ያመለክታል።ግና …

 

ወደ ትምህርትህ መልሰኝ ከኋላ ልቆም ፈልጌ ነበር

ግና እጅግ ደሀ ወደ መሆን እንደመጣሁ አየሁ

ነፍስ ካንተ ጋር ከመነጋገር በቀር

ሌላ ምንም ጥቅም አታገኝምና። (Faith 32:1)

የቅዱስ ኤፍሬም የሆነው ሦስተኛው አቀራረብ ታማኝነት ነው፤ከሁሉም በላይ ለፍቅርና ለአድናቆት የሚደረግ ታማኝነት። ነገር ግን ሁለተኛው አቀራረብ ከህሊና ወደ ተጠያቂው አካል የሚደረግ የአንድ አቅጣጫ እንቅስቃሴ ነው ፤ይኽ ሦስተኛው አቀራረብ በሁለት አቅጣጫ የሆነና ቀጣይነት ያለው ሱታፌ ነው።

ስለ ፈጣሪ እውነተኛነት የሰው እውቀትሊያድግ የሚችለው በእንዲህ ዓይነት የፍቅር መስትጋብር ብቻ ነው።

 

በዚሁ መዝሙር ላይ ቅዱስ ኤፍሬም እንዲህ በማለት ይቀጥላል።

አንተን በማሰብ በተመሰጥኩ ጊዜ

ካንተ ፍጹም ዋጋን አገኛለሁ

ስላንተ ባሰብኩበት በየትኛዉም አቅጣጫ

ካንተ ምንጭ ይፈስሳል

እኔ ምንጩን ልይዝበት የምችልበት ምንም መንገድ የለም

ጌታ  ያንተ ምንጭ ስላንተበማሰብ ከማይጠማ ሰው የተሰወረ ነው

አንተን ለማይቀበል ሰው ያንተ ዋጋ ባዶ ይመስለዋል

ፍቅር ያንተ ሰማያዊ ግምጃ ቤት ባለቤት ነው። (Faith 32:2-3)

ስለዚህ እግዚአብሔርንና ስለእኛ የተፈጠረውን ዓለም የምንረዳበት መንገድ በእኛ መሠረታዊ ዝንባሌና አቀራረብ የተደገፈ ነው፤ከእኛ ከራሳችን እነደተለዩ የጥያቄ አካላት የምንረዳቸው እንደሆነ (እነርሱን ለመጫን መሞከር እንችላለን ወይም በአማካይ ከእኛ ጋር እንዳሉ መረዳትእንችላለን) ወይም ራሳችንን ሊቀየር በማይችል መልኩ በጥያቄያችን አካል ላይ እንደተሳተፍን ማየታችን እንዲሁም በምሥጢሩ ለመሳተፍ ፈቃደኞች መሆናችን ይደገፋል። ቅዱስ ኤፍሬም ይኽ የመጨረሻው መንገድ ብቸኛው በእውነት ተቀባይነት ያለው መንገድ ብቻ ሳይሆን የትኛውም የእግዚአብሔር እውቀት ሊሻበት የሚችል ብቸኛው መንገድ እንደሆነ አይጠራጠርም።

ከዚህ ከመነሻው የታማኝነትና ሱታፌ ዝንባሌ ጋር እኩል ጠቀሜታ ያለው የመደነቅና የመገረም ስሜት ነው።እንዲህ ዓይነቱ የመደነቅ ሰሜት በቅዱስ ኤፍሬም በየትኛዉም ጽሑፎች ላይ የሚገኝ ነው።እንዲህ በማለት ይናገራል፤”በሕይወት በሚያጋጥሙ ቀላል ነገሮች አስተሳሰባችን አድናቂ እንዲሆን ያደረገ እርሱ(እግዚአብሔር) ምስጉን ነው።”(Faith 43) ግና ከሁሉም በላይ ተደናቂ የሆነው  ሰውን በመውደድ በእግዚአብሔር ከፍተኛ መገለጥ እርሱ ራሱ ከሥጋ ጋር በተዋሐደ ጊዜ  ነው።(Fast 3:6, Heresies 35:7) የእግዚአብሔር ወደ ትቢያ መውረድ (መምጣት)  የሚያስደንቅ ነው።(Faith 46:11)

መደነቅ ወደ ፍቅርና ወደ ምሥጋና ያደርሳል፤እንዲሁም በፍቅራችን መጠን በማመሥገን በኩል መለኪያ የሌለውን ሕይወት እናገኛለን።(Nisibis 50:5) እንዲያዉም ባለማመስገን መኖር ሙት ሆኖ እነደ መኖር ነው።

 

በምኖርበት ጊዜ ምሥጋናን አቀርባለሁ

እኔ ህልውና እንደሌለኝም አይደለም

በሕይወት ዘመኔ ምሥጋናን አቀርባለሁ

በሕያዋን መካከል እንደሞተ ሰውም አልሆንም

ሥራ ፈትቶ የሚቆም ሰው ሁለት ጊዜ የሞተ ነው

ፍሬ ማስገኘት የተሳናት ምድርም የሚያዘጋጃትን ትከዳዋለች። (Nisibis 50:1)

እንዲሁም ያለ ፍቅር እውነት ሊደረስበት አይችልም።

እውነትና ፍቅር ሊለያዩ የማይችሉ ክንፎች ናቸው

እውነት ያለ ፍቅር መብረር እንደማይችል ሁሉ

እንዲሁም ፍቅር ያለ እውነት ወደ ላይ ሊወነጨፍ አይችልም

የስምምነት ቀንበራቸው አንድ ነው።(Faith 20:12)

የዚህ ግጥም ክፍል ሦስተኛ ስንኝ ለቅዱስ ኤፍሬም ተጨማሪ ጥቅም ወዳለው ጉዳይ ያመጣናል፤ለማንኛዉም ዓይነት መንፈሳዊ ጥያቄ መነሻው ነጥብ በሰው ህሊና የትኞቹ የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍሎች ሊመረመሩ እንደሚችሉና የትኞቹ የመንፈሳዊ ትምህርት ክፍሎች ሊመረመሩ እንደማይችሉ ማወቅ ነው፤በሌላ አነጋገር አንድ ሰው በፈጣሪና በፍጡር መካከል ያለውን የነገረ ህላዌን ልዩነት የት ላይ ማስቀመጥ እነዳለበት በሚገባ ማወቅ አለበት ።ይኽም ማለት አንድ ሰው ከኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊ ትምህርት አቋቋም ካልተነሳ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስህተትን ይሠራል፤ስህተት የሆኑ የመነሻ ግንዛቤዎችም ወደ ተጨማሪ ስህተት ብቻ ይመራሉ። ይኽም ቀድመን እንዳየነው ከተለያዩ የአርዮሳዊ አቋቋም ጋር ቅዱስ ኤፍሬም መሠረታዊ ቅራኔ ውስጥ የሚገባበት ጉዳይ ነው። በተመሳሳይ ቅዱሳት መጻሕፍት በአግባቡ ሊተረጎሙ የሚችሉት በኦርቶዶክሳዊ እምነት ብርሃን ብቻ ነው።

ሁሉን ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚከፍቱ የዶግማ ቁልፎች

በእኔ ዓይን ፊት የሥነፍጥረትን መጽሐፍ ፣

የታቦቱን ግምጃ ቤት፣የህጉን ዘውድ ከፍተዋል

ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ በራቀ በትረካው  ፈጣሪን የተረዳና

ሥራዎቹንንም ያስተላለፈ ቅዱስ መጽሐፍ ነው።

ሁሉንም የእርሱ የእጅ ሥራዎችን በማስተዋል

መጽሐፍ ቅዱስ የሥራዎቹን አካላት ገልጿል ። (Paradise 6:1)

ይቆየን…