ስብከተ ወንጌል

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

ታኅሣሥ ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት 

ስብከት

ስብከት “ሰበከ፤ አስተማረ” ከሚለው የግእዝ ግሥ የመጣ ሲሆን፣ በጌታ የታዘዘ፣ የእግዚአብሔርን ቃል መናገር፣ ወንጌልን ለዓለም መስበክ፣ ያላመኑትን ለማሳመን መናገር፣ የክርስቶስ ምስክር መሆን ማለት ነው። (መጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ ፸፬)

ቅዱስ ዳዊት “ኢትዝክር ለነ አበሳነ ዘትካት ፍጡነ ይርከበነ ሣህልከ እግዚኦ እስመ ተመንደብነ ፈድፋደ፤ የቀደመውን በደላችንን አታስብብን፥ ምሕረትህ በቶሎ ታግኘን፥ እጅግ ተቸግረናልና”  እንዳለ  የቀደመ በደላችንን ሳያስብብን ጭንቀታችንን ችግራችንን ይቅር ብሎ ወደ እዚህ ምድር መጥቶ የምሥራች፣ ብርሃን፣ መንገድ፣ መስታወት፣ የሕይወት ዛፍ የሆነችውን ወንጌልን ሰበከን፤ አስተማረን። (መዝ.፸፰፥፰) ሐዋርያትንም “ሑሩ ውሰተ ኩሉ ዓለም ወስብኩ ወንጌለ ለኩሉ ፍጥረት፤ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ” በማለት በይሁዳ፣ በኢየሩሳሌም፣ በሰማርያና እስከ ዓለም ዳርቻ እንዲያስተምሩ ላካቸው። (ማር.፲፮፥፲፭)

ወንጌል

ወንጌል ምንድን ነው? የሚለውን አንድ ሐሳብ ጠቁመን እንለፍ፤ ወንጌል ምእመናን ወደ እግዚአብሔር የሚሔዱባት ብርሃን፥ መንገድ፥ ስንቅ፥ መመርያ ናት፤ የሶርያ አባቶች ወንጌልን በመስታወት ይመስሏታል። “ለፓፕሊየስ በተላከ ደብዳቤ እንዲህ ይላል “ወዳጄ ፓፕሊየስ ሆይ! እንደ ንጹሕ መስታወት የሆነውን የጌታችንን ቅዱስ ወንጌል በእጅህ መያዝን ስላልተውክ መልካምን አደረግህ። በእርሱ መስታወትነት ማን ምን መምሰል እንዳለበት ይረዳበታል።

እያንዳንዱን የሰውነታችንን ገጽታ በዚህ መስታወት ውስጥ እናየዋለን። መልከ ጥፉዎች በመጻሕፍት መስታወትነት ራሳቸውን ተመልክተው ስለመልከ ጥፉነታቸው ራሳቸውን ይገሥጻሉ። ስለዚህም ራሳቸውን ከጉድፍ ያጸዳሉ፤ አስቀያሚ ሆነው እንዲታዩ ያበቃቸውን ቆሻሻ ከፊታቸው ላይ ያስወግዳሉ። ቆነጃጅቶችም ውበታቸውን ጠብቀው እንዲዘልቁና ቆሻሻም እንዳይነካቸው ይህ መስታወት ያተጋቸዋል። ይህ መስታወት በክርስቶስና በሐዋርያት የተሰበከው ወንጌል ነው። ይህ መስታወት ልክ እንደ ተፈጥሮአዊው መስታወት የራስን መልክ መልሶ የሚያሳይ መስታወት ነው። ዐይኖቻቸው ንጹሐን የሆኑላቸው ወገኖች በዚህ መስታወት ውስጥ መንግሥተ ሰማያትን በውስጧ ተስላ ያገኟታል። በገነት ስላለው ደስታና ተድላ ያስተውላሉ።” (እነኋት ክርስትና በመምህር ሽመልስ መርጊያ ገጽ ፻፲፱-፻፳)

ጌታችን ሐዋርያትን መስታወት የሆነችውን ወንጌል ይሰብኩ ዘንድ ሲልካቸው የሐዋርያት የስብከታቸው ዓላማ ኢየሱስ ክርስቶስን በዓለም መግለጥ፣ ምስክር መሆን፣ አዳኝነቱን መናገር ነበር፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “ንሕነሰ ንሰብክ ክርስቶስሃ ዘተሰቅለ፤ እኛስ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን” በማለት አስተምሮናል። (፩ቆሮ.፩፥፳፫) ሐዋርያት ስብከታቸውን የጀመሩትም መንግሥተ ሰማያት በልጅነት በጥምቀትና ንስሓ በመግባት እንደምትገኝ በማስተማር ነበር።

በሐዋርያት እግር የተተኩት ሐዋርያነ አበውም ወንጌልን በመስበክ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ እግዚአብሔር እንደሆነ በመመስከር፣ መድኃኒት ክርስቶስን በመስበክ፣ አንገታቸውን ለሰይፍ ደረታቸውን ለጦር እየሰጡ ምስክርነታቸውን ፈጽመዋል። የሐዋርያነ አበውን ፈለግ ተከትለው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ነገረ መለኮትን አምልተው አስፍተው አመሥጥረው አስተማሩን እያስተማሩንም ነው። ቅዱስ ያሬድም በአበው በረከት የተባረከ ነውና እንዲህ አለ “ወልዶ መድኅነ ንሰብክ ዘእምቅድመ ዓለም ሀሎ አክሊለ ሰማዕት ሠያሜ ካህናት ወተስፋ መነኮሳት ወልዶ መድኅነ ንሰብክ፤ ዓለም ሳይፈጠር ከዓለም በፊት የነበረ የሰማዕታት አክሊላቸው የካህናት ሹመታቸው የመነኮሳት ተስፋቸው መድኃኒት ወልድን እንሰብካለን” በማለት የካህን ሥራው ክርስቶስን መስበክ እንደሆነ ተናገረን። (ድጓ ዘዮሐንስ)

የስብከተ ወንጌል ጥቅም

በዚህ ጉዳይ ሦስት ነገሮችን እንመልከት፡-

፩. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመግለጥ፦ በዮሐንስ ወንጌል ም.፮ ቁጥር ፴ ጀምሮ ስናነብ አይሁድ እንዴት የሰው ሥጋ እንበላለን ብለው ይከተሉት የነበሩት በሙሉ ወደ ኋላ ሲመለሱ ሐዋርያትን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ ደግሞ ልትሔዱ ትወዳላችሁን?” ሲላቸው ቅዱስ ጴጥሮስ “ጌታ ሆይ ወደ ማን እንሔዳለን? አንተ የዘለዓለም የሕይወት ቃል አለህ። እኛስ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ አምነናል፤ አውቀናልም” በማለት የዘለዓለም ሕይወት የሆነውን አምላክ መከተል እንዲገባ ይነግረናል።

ቅዱስ ያሬድ በጾመ ድጓው ላይ እንዲህ የሚል ቃል ያስቀምጣል፤ “ወሪድየ ብሔረ ሮሜ ርኢይክዋ አእመርክዋ ወአፍቀርክዋ ለቤተ ክርስቲያን፤ ወደ ሮሜ ሀገር ወረድኩኝ ቤተ ከርስቲያንን አየኋት አወኳት፤ ወደድኳትም” በማለት ዕውቀት በማየትና በመውደድ እንደሆነ ይናገራል። ክርስቶስ ሃይማኖታችን ሕይወታችን ነው። ክርስቶስን ማወቅ ማለትም ሃይማኖትን ማወቅ ማለት ነው፤ “ኢየሱስ ክርስቶስ ሃይማኖትየ ወንጌል” እንዲል (መልክአ ኢየሱስ) ስለዚህም የስብከት ዋናው ዓለማ ሃይማኖትን መስበክ ማሳወቅ በሃይማኖት እግዚአብሔርን በጸጋ ተዋሕዶ ወደ እግዚአብሔር የሚደረገውን ጉዞ ማሳየት ነው፡፡

ቅዱስ አባ ጊዮርጊስ እንዲህ ይላል፤ “በሥላሴ ገመድ ታሠርን። በማይለያይ ሰንሰለቱም ታተምን። ከልቡናዎቻችን በማይነቀሉ የፍቅሩ ችንካሮች ተቸነከርን። ያዝነው አንለቀውም፤ እርሱም አቀፈን አልተወንም። ወደ እርሱም በሃይማኖት አቀረበን ከእርሱም ወደ ቀኝ ወደ ግራ አንሸሽም። እንደ ቀለበት በልባችን እንደ ማኅተም በክንዳችን አኖርነው። እንደ ዕንቁ በልባችን ሣጥን አስቀመጥነው፤ እንደ ወርቅ መሐለቅ በኅሊናችን መዝገብ አኖርነው። እንደ ሐር ግምጃ ተጎናጸፍነው፤ እንደ ነገሥታት ወታደሮች ሰይፍ ታጠቅነው፤ ለጦር ዕቃ እንደተዘጋጀ የድል ጋሻ ተደገፍነው። ተከዜና ግዮን በኢሎል ወር እንደሚመሉ ፍቅሩ በልባችን መልቷልና” በማለት ስብከት ፍቅሩ በልባችን መልቶ እግዚአብሔርን እንድናውቅ የሚያደርገን መሆኑን አስረዳን። (መጽሐፈ ምሥጢር ምዕራፍ ፫ ቁጥር ፳)

፪ ክርስቶስን እንድንመስል የሚያደርገን ነው፦ “ቅዱስ ጳውሎስ “ተመሰሉ ኪያየ በከመ አነ እትሜሰሎ ለክርስቶስ፤ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” በማለት (፩ቆሮ.፲፩፥፩) ክርስቶስን እንድንመስለው ይነግረናል። ክርስቶስ ማለት መለኮት ከሥጋ ጋር ተዋሕዶ የሥጋ ገንዘብ ለመለኮት የመለኮት ገንዘብ ለሥጋ ከሆነ በኋላ የሚጠራበት ስም እንደሆነ ሁሉ ክርስቲያን ማለትም በፀጋ እግዚአብሔርን ተዋሕደን የምንጠራበት ስም ነው። ይህ ማለት እግዚአብሔር የሌለበት ቦታ አለ ማለት ሳይሆን በረድኤት አድሮብን የሚኖርብን ስለሆነ ነው እንጅ።

ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን የመሰለው በምንድን ነው፡ የሚለውን እንመልከት፦ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖር ነው። የሚኖረውም ለክርስቶስ ነው “እመኒ ሐየውነ  ለእግዚአብሔር ነሐዩ ወእመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንመውት እመኒ ሐየውነ ወእመኒ ሞትነ ለእግዚአብሔር ንሕነ” እንዲል፤ (ሮሜ ፲፬፥፰) ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቶስን በመከራው መሰለው ስለ ክርስቶስ መከራ በመቀበሉ ደስ ይሰኝም ነበር፡፡ በግብረ ሐዋርያት “በመንፈቀ ሌሊት ጳውሎስና ሲላስ እግዚአብሔርን በወኅኒ ቤት ያመሰግኑ ነበር” እንዲል፤ (ሐዋ.፲፮፥፳፭) በቆሮንቶስ መልእክቱ የደረሰበትን መከራ እንዲህ ይገልጻል፤ “እንደ እብድ ሰው እላለሁ እኔ እበልጣለሁ፤ በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሠር አትርፌ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ፤ ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በደንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ፤ ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ” በማለት ስለ ክርስቶስ፣ ስለ ወንጌል፣ ስለ ቤተ ክርስቲያን ምን ያህል መከራ እንደ ተቀበለ ይነግረናል።

ስብከትም በትሕትና፥ በትግዕሥት፥ በመከራ በፍጹም ክርስቶስን መምሰል እንዳለብን የምንማርበት ነው። ምግባራችን የቀና ሃይማኖታችን የጸና ካልሆነ ክርስቶስን መምሰል አንችልምና። ቅዱስ ያእቆብ በመልእክቱ “ሃይማኖት ዘእንበለ ምግባር ምውት ይእቲ” እንዳለ በምግባር በትሩፋት አምላካችንን እንድንመስል ስብከት ያስፈልጋል።

፫  በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ። (ኢሳ.፶፮፥፭) እንደተባለ እግዚአብሔር ያከበራቸው የመረጣቸው እነርሱም መርጠውት ከዘመድ ባዳ ከሀገር ምድረ በዳ ብለው ዳዋ ጥሰው ጤዛ ልሰው ደንጋይ ተንተርሰው ግርማ አራዊቱ ፀብአ አጋንንቱ ሳያስፈራቸው ስሙን ብቻ ይዘው የወጡትን እናመሰግናቸው እናከብራቸው በረከታቸው ታድርብን ዘንድ የምንማርበት ነው።

በሕጉና በትእዛዙ ፀንተው በጾም በጸሎት ተወስነው ዓለምን ድል ያደረጉትም በተጋድሎ ላይ ያሉትም ሕያው ወንጌል ማለትም የሚንቀሳቀስ ወንጌል ማለት ናቸውና። ወንጌልን የምንረዳባቸው የምናውቅባቸው እግዚአብሔርን የምናይባቸው መነጸር ማለት ናቸው።

በወንጌል ላይ የተጻፈውን የሚተረጉሙ፣ አይቻልም የምንለውን ችለው፣ በተግባር የሚገልጡ ናቸው፡፡ ጌታችን በወንጌሉ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል” በማለት ተናግሯል፡፡ (ዮሐ.፲፬፥፲፪)   እርሱ እንደ ተሰደደ የሚሰደዱ፣ እንደ ተራበ የሚራቡ፣ እንደ አስተማረ የሚያስተምሩ፣ እንደ ተገረፈ እንደ ተሰቀለ የሚገረፉ የሚሰቀሉ፣ ሙት እንደ አስነሳ ሙት የሚያስነሱ፣  ድውይ እንደፈወሰ ድውይ የሚፈውሱ፣ ለምጻም እንዳነጻ ለምጽ የሚያነጹ፣ የሰማይ አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ ፍጹማን ሁኑ እንዲል በቅድስና በንጽሕና የሚኖሩትን እናውቃቸው፥ አሠረ ፍኖታቸውን፥ እንከተል ዘንድ ስብከት ይጠቅመናል።

ወንጌልን በተግባር እንዴት እንደሚተረጉሙት አንድ ቅዱስ አባት አንስተን እንመልከት፦ ጌታችን መድኃኒታችን በወንጌሉ “እመኒ እግርከ ዘየማን ታስሕተከ ምትራ ወግድፋ እምላዕሌከ፤ ቆኝ እግርህ ምክንያተ ስሕተት ብትሆንብህ ቆርጠህ ጣላት” በሚለው ቃል እንመልከት ከዕለታት አንድ ቀን ዘማዎች ተሰብስበው ሲጫወቱ የአባ መርትያኖስ ባት ከመንደር አጠገብ ነው። (ማቴ.፭፥፴) ወጥቶ ሲገባ አይተው እንዲህ ያለ ኃያል ጽኑዕ መነኩሴ የለም አሉ፤  አንዲቱ ጊዜ ቦታ ባያጋጥመው ነው እንጅ፤ ለሰው ምን ኃይል ጽንዕ አለው፤ አሁን እኔ ሒጄ ባስተውስ ምን ትላላችሁ አለች። አታስችውም አሏት ይህን ብላ ቀን የሔድኩ እንደሆነ መልሶ ይሰደኛል ብላ፤ ሲመሽ ልብሷን ሰውራ ይዛ ሒዳ እጇን ጸፋች።

አባ መርትያኖስ ምንድር ነሽ አላት። ከርቁ ሀገር የመጣሁ የእግዚአብሔር መንገደኛ ነኝ፤ አውሬ ይጣላኛል ወንበዴ ይቀጠቅጠኛል ብዬ አለችው፤ ባስገባት ፆር ይነሳብኛል ብከለክላት እንግዳ ብሆን አልተቀበልከኝም ብሎ እግዚአብሔር ይፈርድብኛል፤ አስገብቻት ፆሬን እታገሳለሁ ብሎ አስገባት። እሳቱን አንድዶላት እልፍ ብሎ ተግባሩን ያዘ፤ ወዲያው የምትለብሰውን ትለብስ፤ የምታጤሰውን ታጤስ፤ የምትቀባውን ትቀባ ጀመረች። የሽቶ መዓዛ ቢሸተው ፆር ተነሳበት፤ ከዚህ ያደረሽኝ አንች እግሬ አይደለሽም ብሎ ከእሳቱ ማገደው፤ የእግሩ መዓዛ የሽቱን መዓዛ እስኪ ለውጠው ድረስ፤ ዘማዊቷም አባቴ ከዚህ ያደረስሁህ እኔ አይደለሁም አመንኩሰኝ አለችው፤ አመንኩሷት በዓቱን ለቆላት ሂዷል።

አንድም ሳታፍር ሳትፈራና እንተኛ አለችው፤ እንተኛስ ካልሽ ነይ ከእሳቱ እንተኛ አላት፤ እሱማ ይፈጀን የለም አለችው። ምድራዊ እሳት የፈጀን ሰማያዊ እሳት እንደምን አይፈጀን አላት። አባቴ ደግሞ በሰማይ እሳት አለ አለችው፣ አዎን አላት አመንኩሰኝ አለችው አመንኩሷት በዓቱ ለቆላት ሂዷል። እንግዲህ አባ መርትያኖስ ወንጌልን እንዴት እንደኖረው አስቡ ስለቅዱሳን መማር ማወቅ ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ነው ሲባልም እግዚአብሔር ሥራውን የሚሠራው በቅዱሳን ላይ አድሮ ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት “መንክር እግዚአብሔር በላዕለ ቅዱሳኒሁ” እግዚአብሔር በቅዱሳን ላይ ድንቅ ነው” በማለት ተናግሯል። (መዝ.፷፰፥፴፭)

በነቢዩ በኢሳይያስ ላይ አድሮ “ወደ አባታችሁ ወደ አብርሃም ወደ ወለደቻችሁ ወደ ሣራ ተመልከቱ” እንዳለን (፶፩፥፪) እንግዲያውስ ቅዱሳን እግዚአብሔርን የምናይባቸው መነጸር ናቸውና ዘወትር ዓይነ ልቡናችንን ወደ ቅዱሳን እናድርግ።