ሰብእ

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል
ሐምሌ ፲፫ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ለሰው ሰውነቱ
ከአፈር መስማማቱ
የሸክላ ብርታቱ
እሳት ነው ጉልበቱ
ውኃ ደም ግባቱ
ነበር መድኃኒቱ!

ታዲያ! …ምን ያደርጋል
ከነፋስ ተዋሕዶ ዕድሜውን በመጠቅለል
… ይሮጣል ለሞቱ።
ሰው ለሰውነቱ
ከእሳት ነው ሥሪቱ

ያገኘውን ሁሉ ለብልቦ እየበላ
በደሉ በዛና በምድር ሁሉ ሞላ
ምድርን ሊያጠፋት እግዚአብሔር ተቈጥቶ
ከእልፍ አእላፋት ሕዝብ ኖኅን ተመልክቶ
፻፳ ዓመታት ከቊጣው ዘገየ ለአንድ ኖኅ ራርቶ

ሰው በሰውነቱ ለ፻፳ ዓመታት እሳት በርትቶበት
…በኃጢአት ሲባላ …ኃጢአት ኖሮበት
ኖኅ ግን በጽናቱ መርከቡን ይሠራል
ውኃ ለጥፋቱ ከእሳት ይበረታል
የታላቁን ቀላይ ምንጮች ያፈነዳል
ምድርን ከኃጢአት ከርኩሰት ያጸዳል
ኖኅና መርከቡን ከምድር ለይቶ ከፍ ከፍ ያደርጋል።

ኖኅ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል ኪዳን ገባና
ሰማይ ተጋረደ በቀስተ ደመና
ዘመን በዘመን ላይ አድሮ እየዘመነ
በዘመነው ትውልድ የኖኅ ቃል ኪዳኑ ቀለም ብቻ ሆነ

በአባቱ ተጋድሎ ልጁ እያፈረ
ማንነቱን ገ’ሎ ታሪኩን ቀበረ
ከሐሰት ተጋብቶ ከተኩላ ጋር ዋለ
የወርቅ ቀለሙን ብራናውን ፍቆ ተረት ተረት አለ!

ከባሕር ዳር ሆነው ጸንቶ ማዕበሉ
ቀስተ ደመናውን አሻግረው እያዩ የላም በረት አሉ!
ከምዕራቡ ዓለም ለሚነፍሰው ነፋስ ለቁሩ ለብርዱ
ከኖኅ መርከብ ፍልጥ እየፈለጡ ለተረት ማድመቂያ እሳት አነደዱ

እሳት!… እሳት!… ይነዳል እሳቱ
ጊዜ እየቈጠረ ይገፋል ሌሊቱ
የጠቆረው ሰማይ ደመና እያዘለ
መብረቅ ነጎድጓዱ ባሕሩን ከፈለ

እያስገመገመ ዝናቡ ወረደ
ማዕበሉ አይሎ አሸዋው ተናደ
ባላሰብናት ሰዓት ድንገት ተገለጠች
መከራ በእኛ ላይ ውቅያኖስ ሆነች
ያቺ የኖኅ መርከብ ከፍ ከፍ እያለች
አራራት ላይ ቆመች

ዶሮው ካልተሰማ በንጋት ጩኸቱ
ድሮም ለእሳቱ ውኃ ነው ቅጣቱ
የዶሮውን ጩኸት በሌሊት የሰሙ
በጴጥሮስ ንስሓ ዳግም እየቆሙ

ሳይወጡ ሳይወርዱ በመርከቧ ጸኑ
ሥሉስ ቅዱስ ብለው እያመሰገኑ
ወልድ ዋሕድ ብለው…በእውነት የታመኑ
የመርከቧን ምሥጢር እያመሠጠሩ
በማርያም መቀነት በቀስተ ደመናው ለምሕረት ተጠሩ

የአባቶችን ድንበር ተግተው የጠበቁ
ቀድመው የተጠሩ ደግሞም የከበሩ ከብረው የጸደቁ
በዱር በበረኃ በዋሻ ያደሩ
በገድል በትሩፋት ለወንጌል የኖሩ

ምእመናንና ካህናት ሃሌ ሉያ እያሉ እያሸበሸቡ
በዚያች በኖኅ መርከብ ደብረ አሮን ገቡ።

መንክራዊው አሮን ከዐለት የወቀራት
ባለ አምስት ክፍሎች ዐሥራ ዐራት ዐምድ ያላት
በሁለት በሮቿ በሰባት መስኮቶች አስጊጦ ያነጻት ናት!

የኖኅ ቃል ኪዳኑ ዛሬም የጸናባት
ነጎድጓድ መብረቁ ከቶ የማይነጥብባት
የክርስቶስ ሥጋው እና ደሙ የሚፈተትባት
መንክራዊው አሮን ከዐለት የወቀራት
ቤተ ክርስቲያን የገነት በር ናት!!!