mk 20th year

ሰበር ዜና፡ የእግር ጉዞው መርሐ ግብር ተቀየረ፡፡

ግንቦት 24 ቀን 2004 ዓ.ም.

እንዳለ ደምስስ

  • መርሐ ግብሩ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ ይካሔዳል፡፡

mk 20th yearግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም ከማኅበረ ቅዱሳን 20ኛ ዓመት የምሥረታ ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ ሊካሔድ የነበረው የእግር ጉዞ መርሐ ግብር ጠቅላይ ቤተ ክህነት መጻፍ ያለበትን ደብደቤ ባለመጻፉ በታቀደለት  መሠረት ሊከናወን አልቻለም፡፡ መርሐ ግብሩ እሑድ ጠዋት ከ 3፡00 ጀምሮ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ በድምቀት ይከበራል፡፡

 

መርሐ ግብሩ አዲሱ ገበያ አካባቢ በሚገኘው መንበረ ክቡር ቅዱስ ሚካኤልና አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም ለማካሄድ እንደ ታቀደ አስታውሰን ለምን እንደተቀየረ ላቀረብንላቸው ጥያቄ የማኅበሩ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን ሙሉጌታ ኃ/ማርያም ሲመልሱ “ለሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ በጻፍነው ደብዳቤ ሚያዝያ 27 ቀን 2004 ዓ.ም የእግር ጉዞ እንደምናካሂድ ያሳወቅን ሲሆን ነገር ግን ምእመናን ቀኑ እንዲራዘምላችው በመጠየቃቸው ጉዞው ወደ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም እንዲቀየር ጠይቀናል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለ የርክበ ካህናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረሰ፡፡ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ማኅበረ ቅዱሳንም ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሆን ተወሰነ፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ በወሰነው ውሳኔ መሰረት ተጠሪነታችን ለጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆኑ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጽ/ቤት ጉዞውን ለማካሔድ እንድንችል እንዲጻፍልን ጠይቀናል ብለዋል፡፡

 

የጉዞው አስተባባሪ ዲ/ን ዋሲሁን በላይ አያይዘው እንዳስረዱት ከሆነ በብፁዕ  የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ፊርማ የወጣው የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መዝገብ ቤት ገብቶ ወደሚመለከታቸው ክፍሎች እንዳይደርስ ´የመዝገብ ቤት ሰራተኞች ደብዳቤው እንዳይወጣ ከበላይ ታዘናል በሚል ደብዳቤው አልወጣም፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስን ውሳኔ የያዘው ደብዳቤ የጠቅላይ ቤተክህነት የአስተዳደር ሃላፊዎችም አልደረሰንም በሚል እስካሁን ሊጓተት ችሏል፡፡በዚህም ምክንያት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደብዳቤ ለመጻፍ አልቻልንም፡፡”

 

‹‹ነገር ግን መርሐ ግብሩ በጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ውስጥ እንዲካሔድ ስለተፈቀደ እሑድ ግንቦት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ከጧቱ 3፡00 ስዓት መርሐ ግብሮቹ እንደተጠበቁ ይከናወናሉ፡፡ ይህንን የጉዞ መርሐ ግብር በታቀደለት መሰረት ማካሔድ ባለመቻላችን ምእመናንን ይቅርታ እየጠየቅን የጉዞውን ቦታ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነት አዛውረናል፡፡እሁድ ከጧቱ 3፡00 ስዓት ጀምሮ በሚካሔደው መርሐ ግብር በጠቅላይ ቤተክህነት ግቢ ውስጥ በመገኘት የበረከቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ዋና ጸሐፊው አስታውቀዋል፡፡››