ወላጆች እንደሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም ዮሐ.14፥18

ግንቦት 24/2004 ዓ.ም.

በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ

ይህንን የተስፋ ቃል ለቅዱሳን ሐዋርያት የተናገረው ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት ደቀ መዝሙርነት የተጠሩት በልዩ ልዩ ሙያ ተሰማርተው ሳለ ነው፡፡ በየሙያቸው ሥራ እየሠሩ ከሚተዳደሩበት ሥፍራ ሁሉ ደርሶ ፈጣሪያችን በቸርነቱ ለከበረው የወንጌል አገልግሎት ጠራቸው፡፡ “ወእንዘ ያንሶሱ መንገለ ባሕረ ገሊላ፤ ርእየ ክልኤተ አኅወ፥ ስምዖንሃ ዘተሰመየ ጴጥሮስ ወእንድርያስሃ አኅዋሁ እንዘ ይወድዩ መርበብቶሙ ውስተ ባሕረ፤ እስመ መሠግራነ እሙንቱ፡፡ ወይቤሎሙ እግዚእ ኢየሱስ ንዑ ትልዉኒ፤ ወእሬስየክሙ ትኩኑ መሠግራነ ሰብእ፡፡…. በገሊላ ባሕር ዳር ማዶ ሲመላለስ ሁለት ወንድማሞችን አገኘ፡፡ ጴጥሮስ የተባለውን ስምዖንና ወንድሙን እንድርያስን መረባቸውን ወደ ባሕር ሲጥሉ አየ፣ ዓሣ አጥማጆች ነበሩና፡፡ ጌታችንም “ለጊዜው በእግር ተከተሉኝ ፍጻሜው በግብር ምሰሉኝ፡፡ እኔም ሰውን እንደ ዓሣ ወንጌልን እንደ መረብ፣ ይህን ዓለም እንደ ባሕር አድርጋችሁ እንድታስተምሩ አደርጋችኋለሁ” አላቸው፡፡ ያን ጊዜ መርከባቸውንና መረባቸውን ትተው ተከተሉት” የተቀሩትም ሁሉ እንዲህ ባለ ጥሪ ጠራቸው /ማቴ.4፥18-22፣9፣ ዮሐ.1፥46፤ 44፥51/

ቅዱሳን ሐዋርያትም ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ጌታችን በዋለበት ውለው ባደረበት እያደሩ የቃሉን ትምህርት ሰምተው የእጁን ተአምራት አይተው ከእርሱ ጋር ሆኑ፡፡ በኋላም የተጠሩለትን አገልግሎት በመፈጸም ክብርን አግኝተውበታል /ማቴ.13፥42፣ ሕዝ.47፥10/፡፡

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያላቸውን ሁሉ ትተው ጥለው የተከተሉትን ሐዋርያትን “ወላጆች እንደ ሌላቸው ልጆች አልተዋችሁም” አላቸው፡፡ አጽናኝ ጰራቅሊጦስ ይሰጣችኋል፡፡

“እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ፤ እናንተ ግን ከአርያም ኀይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” ብሏቸዋል፡፡ /ሉቃ.24፥49፣ ዮሐ.15፥26፣ 16፥7 ሐዋ.1፥4/ በዚሁ መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት ከእመቤታችን ጋር ሆነው በኢየሩሳሌም በአንድነት በጸሎት እየተጉ ሳለ አምላካችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል በእያንዳንዳቸው አድሮባቸዋል፡፡

እነሱም መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው ከብልየት ታደሱ፥ በአእምሮ ጎለመሱ፥ሕጹጻን የነበሩ ፍጹማን፥ ፍሩሃን የነበሩት ጥቡዓን ሆኑ ባንድ ልሳን ይናገሩ የነበሩ ሰባ አንድ ልሳን ተገለጸላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ኢየሩሳሌምን ባንድነት ዓመት በኅብረት አስተማሩ፡፡ “ወነበሩ ዓመተ ፍጽምተ በኢየሩሳሌም” እንዲል፡፡ ዓለምን 12 አድርገው ተካፍለው በእየ ሀገረ ስብከታቸው ሄደው አምልኮተ እግዚአብሔርን አስተማሩ፡፡ አሕዛብን ከአምልኮተ ጣዖት ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከገቢረ ኀጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ መለሱ፡፡

በዓለ ሃምሳ በኦሪት የነበረው ገጽታ

እስራኤል ከሀገራቸው ወጥተው በልደት ለ430 ዓመታት መከራና ስቃይ ሲደርስባቸው ኖረው በሙሴ መሪነት በፋሲካው በግ ከሞተ በኲር ድነው ምድረ ርስትን እንዲወርሱ ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት በየዓመቱ መጀመሪያ ወር /ሚያዚያ 14 ቀን/ የፋሲካን በዓል ያከብራሉ /ዘጸ.12፥1-13/ ይህን በዓል ካከበሩ ሰባት ሱባኤ ቆጥረው በማግስቱ /በሃምሳኛው ቀን/ ደግሞ የእሸት በዓል /በዓለ ሠዊትን/ ያከብራሉ፡፡ ይህም በኦሪቱ እንደተገለጸው የስንዴ በኲራት አጨዳ መታሰቢያ፣ የምስጋና ጊዜ ነው፤ /ዘጸ.23፥16፣ ዘሌዋ.23፥15-18፣ ዘኁ.28፥26/

በዓለ ሠዊት በበዓለ ሃምሳ

ጌታችን እርሱ ባወቀ ይህንኑ በዓል በበዓለ ሃምሳ /በበዓለ ጰራቅሊጦስ/ እንዲተካ አድርጎታል፡፡ ከዘመነ ሐዋርያት ወዲህ በበዓለ ሠዊት በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል፡፡ ጰራቅሊጦስ የመንፈስ ቅዱስ ልዩ የሆነው አካሉ መጠሪያ ስም ነው፡፡ ጰራቅሊጦስ የግሪክ ቃል ሲሆን ትርጉሙ በችግር ጊዜ ተራዳኢ፣ በሃዘን ጊዜ አጽናኝ፣ መዘንጋት ላለበት ልብ አስታዋሽ፣ በአላውያን ፊት ተከራካሪ ጠበቃ ማለት ነው፡፡ /ዮሐ.14፥16-26፣ 15፥26፣ 16፥7/ ዘመነ ጰራቅሊጦስ የሚባለው ጊዜ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተነሣ ከሃምሳኛው ቀን ጀምሮ ቀጥሎ እስከ አለው እሑድ ድረስ ያለው 8 ቀን ነው፡

“ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ” የሐዋ.ሥራ.2፥2

በዓለ ሃምሳ በተባለው በዓል መንፈስ ቅዱስ እንዲህ ባለ ድምጽና ግርማ ተገለጠ፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን ሞትን ድል አድርጎ በተነሣ በሃምሳኛው ቀን ሐዋርያት በዝግ ቤት ውስጥ ተሰብስበው ሳሉ መንፈስ ቅዲስ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደ ተገለጠላቸው ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡፡

“በዓለ ሃምሳ የተባለው ቀን በደረሰ ጊዜ፥ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው አብረው ሳሉ፥ ድንገት እንደሚነጥቅ ዓውሎ ነፋስ ከሰማይ ድምጽ መጣ፥ ተቀምጠው የነበሩበትንም ቤት ሁሉ ሞላው እንደ እሳትም የተከፋፈሉ ልሳኖች ታዪአቸው፤ በያንዳንዳቸውም ላይ ተቀመጡባቸው፡፡ በሁሉም መንፈስ ቅዱስ አደረባቸው፣…” /የሐ.ሥራ.2፥1-4/

መንፈስ ቅዱስ ስለምን በንፋስና በእሳት አምሳል ተገለጠ?

ሀ/ መንፈስ ቅዱስ በንፋስ /በዓውሎ ነፋስ/ ድምጽ መጣ ብሎ የተናገረበት ምክንያት?

–    ነፋስ ረቂቅ ነው መንፈስ ቅዱስም የማይመረመር የማይዳሰስ ረቂቅ ነውና፤

–    ነፋስ ኀያል ነው መንፈስ ቅዱስም ኀያል ነውና፤

–    ነፋስ ፍሬውን ከገለባው ይለያል፤ መንፈስ ቅዲስም ጻድቃንን ከኀጥአን ይለያልና፤

–    ነፋስ በምላት ሳለ አይታወቅም ባሕር ሲገሥጽ ዛፍ ሲያናውጥ ይታወቃል እንጂ፡፡ መንፈስ መንፈስ ቅዱስም በምላት ሳለ አይታወቅም ቋንቋ ሲያናግር፤ ምሥጢር ሲያስተረጉም ይታወቃልና፡፡

–    ነፋስ መንቅሂ ነው፤ መንፈስ ቅዱስም ሰማእታትን ወደደም ጻድቃንን ወደ ገዳም ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን አነቃቅቶ የሚመራቸው እርሱ ነውና በነፋስ መስሎ ተናገረለት፡፡

ለ/ እንደ እሳት የተከፋፈሉ ልሳኖች /በእሳት አንጻር የተገለጠውም/ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አባቶቻችን መምህራን የመንፈስ ቅዱስን በእሳት የመመሰል ትርጉም እንዲህ ገልጠው ያስተምሩናል፡፡

እሳት ምሉዕ ነው መንፈስ ቅዱስም ምሉዕ ነውና፤ እሳት በምልዓት ሳለ ቡላድ ካልመቱ አይገልጽም፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቋንቋ ሲያናግር ምሥጢር ሲያስተረጉም እንጂ አድሮ ሳለ አይታወቅምና እሳት ከቡላዱ ሲወጣ በመጠን ነው፤ ኋላ በእንጨት እያቀጣጠሉ ያሰፉታል፤ መንፈስ ቅዱስም በጥምቀት ሲሰጥ በመጠን ነው፡፡ ኋላ በሥራ ያሰፉታልና፤ እሳት ጣዕመ መዓዛን ያመጣል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ጣዕመ ጸጋን ያመጣልና፡፡ እሳት በመጠን ቢሞቁት ሕይወት ይሆናል፡፡ ከመጠን አልፎ የሞቁት እንደሆነ ግን ያቃጥላል፡፡ መንፈስ ቅዱስም በሚገባ በተጻፈው የመረመሩት እንደሆነ ሕይወት ይሆናል፤ በማይገባ ከተጻፈው ወጥቶ የመረመሩት እንደሆነ ግን ይቀስፋልና፤ “እሳት በላኢ ለዓማጽያን ለእለ ይክሕዱ ስሞ ወእሳት ማሕየዊ ለርቱዓነ ልብ ለእለ ይገብሩ ፈቃዶ” እንዲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም፡፡

እሳት ያቀረቡለትን ሁሉ ያቀጥላል፤ መንፈስ ቅዱስም ሕዝብ አሕዛብ የጸለዩትን ጸሎት ያቀረቡትን መሥዋዕት ይቀበላልና፡፡ እሳት ውኃ ገደል ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ መንፈስ ቅዱስም ቸርነቱ ካልከለከለው ሁሉን ላጥፋ ቢል ይቻለዋል፡፡ እሳት ዱር ይገልጻል መንፈስ ቅዱስም ምሥጢርን ይገልጻልና፡፡ እሳት የበላው መሬት ለእህል ለተክል ይመቻል፤ መንፈስ ቅዱስም ያደረበት ሰውነት ለገድል ለትሩፋት ያመቻል፡፡ እሳት ካንዱ ፋና አምሳ፣ ስልሳ፣ ፋና ቢያበሩለት ተከፍሎ የለበትም፤ መንፈስ ቅዱስም ተከፍሎ ሳይኖርበት እስከ ምጽአት ድረስ ሲሰጥ ይኖራልና፡፡

ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን መቀበል ያስፈለጋቸው ለምንድር ነው?

ሐዋርያት “ወረደ፣ ተወለደ፣ ተሰቀለ፣ ሞተ ተነሣ አረገ” ብለው ለማስተማር ለማሳመን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋው ባይታደላቸው ኖሮ በራሳቸው ብቻቸውን በደከሙ፣ ደክመውም በቀሩ ነበር፡፡ ሰው ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር መንፈሳዊውን ተግባር ቀርቶ ምንም ዓይነት ሥራ መሥራት አይቻለውም፡፡ መንፈሳዊው ሥራ ደግሞ በሰይጣን ዲያብሎስና በሠራዊቱ /ርኲሳን መናፍስት/ ልዩ ልዩ ፈተናና መሰናክል ያጋጥመዋል፡፡ ስለሆነም በመንፈስ ርኲስ የሚመጣውን ፈተና ለመቋቋም ምንጊዜም ቢሆን ከእግዚአብሔር ጋር መኖር ያሻል፡፡

ሐዋርያት ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ከመቀበላቸው በፊትና በኋላ

ቅዱሳን ሐዋርያት የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ከመሳተፋቸው በፊት ምንም እንኳን ከጌታችን ባለመለየት ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ቢቆዩ ነገር ግን በልብ የሚያምኑትን በአንደበታቸው ገልጸው ለመመስከር ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ የችግሩም መንስኤ “የምናምነውን ብንመሰክር እንገረፋለን፣ እንሰቀላለን” የሚል ፍርሃት ነበር፡፡ ሊቀ ሐዋርያት ቅዱስ ጴጥሮስ በዕለተ አርብ ጌታችን በቀያፋ ግቢ ውስጥ መከራን ሲቀበል ተከትሎት ወደዚያው አምርቶ ነበር፡፡ ሆኖም በተለያዩ ሰዎች ለሦስት ጊዜያት “ከገሊላው ኢየሱስ ጋር አይደለህምን?” ተብሎ ቢጠየቅ፤ የሰጠው ምላሽ “ሰውየውን /ጌታችንን ነው/ አላውቀውም” የሚል ነበር /ማቴ.26፥69-72/ በኋላ ግን /ማለትም መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ካሳደረበት በኋላ/ በሸንጎ ሹማምንት “በዚህ ስም እንዳታስተምሩ አጥብቀን አላዘዝናችሁምን? እነሆም፣ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞልታችኋል፤ የዚያንም ሰው /የጌታችንን ነው/ ደም በእኛ ታመጡብን ዘንድ ታስባላችሁ ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ጴጥሮስና ዮሐንስም መልሰው አሉ፡፡ ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል፡፡…. ሐዋርያትንም ወደ እነርሱ ጠርተው ገረፏቸው፣ በኢየሱስም ስም እንዳይናገሩ አዝዘው ፈቱአቸው፡፡ እነርሱም ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጡ” /የሐዋ.ሥራ.5፥28-41/

ከዚህ በላይ የትምህርታቸው ቃል በሰማዕያን ልቡና ገብቶ ካለማመን ወደ ሃይማኖት፣ ከአምልኮተ ባዕድ ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር የሚመልስ ሆኗል፡፡ ልዩ ልዩ ገቢረ ተአምራት ያደርጉም ጀመር አንድ ቋንቋ ብቻ ያውቁ የነበሩት ሐዋርያት ሰባ አንድ ቋንቋ ተጨምሮላቸው የጌታችንን ወንጌል በመላው ዓለም ተዘዋውረው አስተምረዋል፡፡

በዓለ ሃምሳ ለቤተክርስቲያን

ይህ በዓል የቤተ ክርስቲያን የልደት በዓል ተብሎ ይጠራል፡፡ ይህም ስያሜ ያለ ምክንያት የተሰየመ /የተሰጠ/ አይደለም፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያት ጀምሮ በየዘመኑ የተነሡ ሊቃውንት ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፍት እንደሚገልጹት በዚህች ቀን ቁጥራቸው ከሦስት ሺህ ያላነሱ አይሁድ ወደ ክርስትና የመጡበት፤ወንጌል ከመካከለኛው ምስራቅ አልፋ በመላው ዓለም የተነገረችበት የተስፋፋችበት ቀን ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ “የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ” በተባለ መጽሐፋቸው ይህንን ሁኔታ እንዲህ ገልጸውታል፡-

“…. ጌታ ባረገ በአስረኛው ቀን ጧት መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት ተሰጠ፡፡ ጌታ የነገራቸው የተስፋ ቃል ሁሉ ተፈጸመ፡፡ ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ተቀብለው የሞቱና የትንሣኤው ምስክሮች ሆኑ፣ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በእነርሱ ላይ ሲያድር ለቤተ ክርስቲያን ጉዞ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ፡፡ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው “መንፈስ ቅዱስ ባይወርድላት ኑሮ የቤተ ክርስቲያን ሕልውና ኮስምኖ ቀጭጮ ይቀር ነበር፤ ስለዚህም በሚገባ አነጋገር ይህች ዕለት የቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ትባላለች” ይላል፡፡ ብዙ ሊቃውንት ይህችን ዕለት የበዓላት ሁሉ እመቤት ይሏታል፡፡….”

በመላው ዓለም የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ይህንኑ በዓል በጸሎትና በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት አክብረውት ይውላሉ፡፡

በዚህ ዕለት የሚቀደሰው ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ፥ ምንባባቱ ደግሞ፡-

ኤፌ.4፥1-17

/ቁጥር7/ እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን፥

1ኛ ዮሐ.2፥1-18

/ቁጥር.17/ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል

የሐዋ.ሥራ.1፥1-18

/ቁጥር 4/ በሁሉም ይናገሩ ዘንድ እንደሰጣቸው በሌላ ልሳኖች ይናገሩ ጀመር

የሚለው ሲሆን ምስባኩ “ወወሀብከ – ጸጋከ ለእጓለ እመሕያው” የሚለው ነው፥ /መዝ.67፥18/

በዚህ ዕለት ጌታችን ለቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ ስለ መንፈስ ቅዱስ ጸጋ የሰጣቸው ተስፋም በወንጌል ንባብ ጊዜ ይሰማል፡፡ ይኸውም፡- “ወኢየኅድገክሙ እጓለማውታ ትኲኑ” የሚለው ነው፡፡

ኢየሩሳሌም -ቤተ ክርስቲያን

ቅዱሳን ሐዋርያት ፈጣሪያችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዘዛቸው ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የተቀበሉ በኢየሩሳሌም ከተማ ጸንተው /ቆይተው/ ነው፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ ቢናወጹ ይህን ጸጋ ለመሳተፍ ባልታደሉ ነበር፡፡ ያለ ረድኤተ እግዚአብሔር /ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ/ ደግሞ ምንም ምን ተግባር ማከናወን ባልተቻላቸው ነበር፡፡ በዚህ የተነሣ ከኢየሩሳሌም ሳይወጡ እመቤታችንን ይዘው ሲጸልዩ መንፈስ ቅዱስን ተቀብለዋል፡፡ ይህም በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች የሚያስተምረን ነገር፡- በሃይማኖት በምግባር ጸንቶ የሚኖር ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ይጎበኘዋል፡፡ በጸጋ ላይ ጸጋ ይጨምርለታል፡፡ ኋላም ለመንግሥተ ሰማይ ያበቃዋል፡፡

ይህንን ጸጋ ለማግኘት ፈጣሪያችን ኢየሩሳሌም ከተባለች ለሰማያዊቷ ኢየሩሳሌም አምሳያ ከሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንዳንናወጽ እንዳንወጣ አዞናል፡፡ ኢየሩሳሌም ማለት የሰላም ሀገር /ሀገረ ሰላም/ ማለት እንደሆነ፤ ቤተ ክርስቲያን /ቤተ ክርስቶስ/ ማለት ደግሞ የሰላም ቤት ማለት ነው፡፡ የሰላም አለቃ፣ የሰላም ባለቤት የክርስቶስ ቤት ናትና፡፡ /ኢሳ.9፥6/

እንግዲህ አባ ሕርያቆስ ባስተላለፈልን ቡራኬ መሠረት “ኦ አንትሙ ሕዝበ ክርስቲያን፥ በከመ ተጋባእክሙ በዛቲ ዕለት፣ ከማሁ ያስተጋብእክሙ በደብረ ጽዮን ቅድስት፣ ወበ ኢየሩሳሌም አግዓዚት እንተ በሰማያት፡- እናንተ የክርስቲያን ወገኖች በዚህች ቀን እንደተሰበሰባችሁ ክብርት በምትሆን በደብረ ጽዮን ይሰብስባችሁ፡፡ በልዕልና ባለች በኢየሩሳሌም ሰማያዊት ይሰብስባችሁ፡፡”  እንዳለን እስከ መጨረሻ ሕይወታችን ቅድስት ንጽሕት ርትእት በሆነች ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖታችን ፈጣሪያችን ልዑል እግዚአብሔር ያጽናን፡፡ በዓሉን የበረከት የረድኤት ያድርግልን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር