ሦስቱ ነገሥታት

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ፳፻፲፬ .

ኢየሩሳሌም ከተማ ከወትሮው በተለየ መልኩ የፍርሃት ድባብ ተንጸባርቆባታል፤ በንጉሥ ሄሮድስ ቤተ መንግሥት ዙሪያ በሠራዊቱና በቤተ መንግሥቱ የቅርብ ሰዎች የሰሞኑ ወሬ የሦስቱ ነገሥታት ጉዳይ ነው፡፡ ከሩቅ ምሥራቅ ሠራዊቶቻቸውን አስከትለው የመጡት  ማንቱሲማር፣ በዲዳስፋ፣ እና ሜልኩ የተባሉ ነገሥታት በእስራኤል ምድር መምጣታቸው ብቻ ሳይሆን ተወልዷል ለተባለው ንጉሥ እጅ መንሻ ለመስጠት እንደመጡ መናገራቸው ንጉሥ ሄሮድስን ቅር አሰኝቶታል፤ ፍርሃት በልቡ እንዲነግሥም አድርጎታል፡፡ (ማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ፪፥፫)

ንጉሥ ሄሮድስ ይህንን ዜና ከሰማ በኋላ ለዓይኖቹ ሽፋሽፍት በቂ እንቅልፍን፣ ለጀርባው በቂ ዕረፍትን ከሰጠ ቀናቶች ተቆጥረዋል፡፡ ነገሥታቱ ከሩቅ ምሥራቅ ኮከብ እየመራቸው ከንጉሥ ሄሮድስ ቤተ መንግሥት ከገቡ ጊዜ አንሥቶ የተወለደውን ንጉሥ አግኝተው ከአባቶቻቸው በአደራ የተረከቡትን ሥጦታ ለመስጠት ንጉሡንም ለማየት እጅግ ጓጉተዋል፡፡ ከማረፊያ ቤት እንዲቀመጡ ከተደረገ በኋላ ንጉሥ ሄሮድስ መምህራራን አስጠርቶ በእስራኤል ሀገር ይወለዳል ስለተባለው ንጉሥ የተነገሩ ትንቢቶች ካሉና የትውልድ ቦታውን እንዲነግሩት ጠየቃቸው፤ ሊቃውንቱ፣ ከአስፈሪውና ከጨካኙ ንጉሥ ሄሮድስ ዘንድ ቀርበው የተጠየቁትን ጥያቄ ለመመለስ በመጻሕፍት የተጻፉትን ማስታወስ ጀመሩ፤ ከዚያም ስለሚወለደው ንጉሥ በነቢዩ ሚክያስ ‹‹አንቺ ቤተ ልሔም የይሁዳ ምድር ከይሁዳ ምድር፣ ከይሁዳ ገዢዎች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ  መስፍን ከአንቺ ይወጣልና ተብሎ በነቢይ እንዲህ ተጽፎአልና በይሁዳ ቤተ ልሔም ነው›› አሉት፡፡  (ማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ ፪፥፮)

ንጉሥ ሄሮድስ ሦስቱን ነገሥታት ከእንግዳ ማረፊያ ቤት አስጠርቶ ‹‹… ይወለዳል የተባለው ንጉሥ በቤተ ልሔም ነው፤ ስለዚህ ወደዚያ ሂድ! ነገር ግን ካገኛችሁት ለእኔም ንገሩኝ፤ እኔም እሰግድለታለው›› አለ… (ማቴ.፪፥፯-፰) ሦስቱ ነገሥታት አመስግነው በተነገራቸው መሠረት ጉዞ ወደ ቤተ ልሔም አደረጉ…፤ በጉዟቸው ወቅት ከሀገራቸው ሲመጡ በሰማይ እያበራ ይመራቸው የነበረው የሚያበራ ኮከብ ዳግመኛ ታያቸው፤ ከዚያም አቅጣጫውን እየመራ ወደ ቤተ ልሔም ወሰዳቸው …. ፤ ቤተ ልሔም ከተማ ትሕትና በአካል ገዝፎ የታየባት ድንቅ ሥፍራ ናት፡፡ ከኢየሩሳሌም ከተማ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቃ በስተደቡብ የምትገኝ ከተማ ናት፤ ቤተ ልሔም የቀድሞ ስሟ ኤፍራታ ይባላል፤ ጸዋሪተ ፍሬ (ፍሬን የያዘች) ማለት ሲሆን ቤተ ልሔም ማለት ደግሞ የእንጀራ ቤት ማለት ነው፤ እውነትም የእንጀራ ቤት ‹‹.. የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም…›› በማለት እንደተናገረው፤ ያውም በልተው የማይራቡት የሕይወት እንጀራ መድኅነ ዓለም ክርስቶስ የተወለደባት ቅዱስ ሥፍራ፡፡ በቤተ ልሔም ንጉሥ ዳዊት ተወልዶባታል፤ ያዕቆብ ሚስቱ ራሔልን ባረፈች ጊዜ የቀበራት በዚሁ ሥፍራ ነው፡፡ (ዮሐ.፮፥፴፭)

ከተማዋ መግቢያ ሲደርሱ ከተማዋ በብርሃን ተሞልታለች፡፡ ልብን በሐሤት የሚሞላ ልዩ ድባብ ይንጸባረቅበታል፤ ኮከቡ የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ከተወለደበት በኤፍራታ ዋሻ ከእንስሳቱ ማደሪያ አመለከታቸውና ተሠወረ፤ ሦስቱ ዕድለኞች ነገሥታት በጽናት ተጉዘው የተወለደውን ንጉሥ በማግኘታቸው እጅግ ተደሰቱ፤ ሕፃኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእናቱ ከእመቤታችን ከንጽሕተ ንጹሓን ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር አገኙት፤ ወላዲተ አምላክ ድንግል ማርያም ፍጥረታቱን በቸርነቱ የሚመግብን ፈጣሪያችንን ታቅፋው አገኙ፤ እንደገቡም ለነገሥታት ንጉሥ ለክርስቶስ ሰገዱለት፤ ከዚያም ይዘው የመጡትን እጅ መንሻ ወርቅ፣ ዕጣን፣ ከርቤ ሌሎችንም ሥጦታዎች ሰጡት፤ የልባቸው መሻት በመፈጸሙ በጣም ተደሰቱ፤ የእግዚአብሔርም መልአክ በሌሊተ ተገልጾ በመጡበት ሳይሆን በሌላ መንገድ እንዲመለሱ ነገራቸው፤ ሦስቱ ነገሥታት ሲመጡ ረጅም ጊዜ የፈጀባቸውን መንገድ በአጭር ቀን ተመለሱ፤ ሲመጡ ‹‹የተወለደው ንጉሥ የታለ›› እያሉ ነበር፤ ሲመለሱ ‹‹አገኘነው›› እያሉ ተመለሱ፤ ሲመጡ ምድራዊ ንጉሥ መስሏቸው ነበር፤ የሰማይና የምድር ፈጣሪ ነገሥታትን የሚሾም ንጉሥ እንደሆነ አምነው ተመለሱ፡፡

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!