‹‹ሚስቶች ሆይ፥ በጌታ እንደሚገባ ለባሎቻችሁ ተገዙ›› (ኤፌ.፭፥፳፪)

ጥር ፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በትዳር ሕይወት ውስጥ ባልና ሚስት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እና የቤተ ክርስቲያን ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ በክርስቲያን ቤተሰብ ባል ራስ፤ ሚስትም ደግሞ ዘውድ ናት። ‹‹ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።›› እንዲል፤ (፩ኛቆሮ.፲፩፥፫)

በክርስቲያናዊ ትዳር እኩልነትና ሥርዓት አለ። ባል የሚስቱ ራስ ሆኖ እግዚአብሔርን ማገልገል አለበት፤ ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ እና ሚስት ለባሏ እንደ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም ለጌታችን ክርስቶስ እንድትገዛ ያዛል። ነገር ግን ሚስት በትዳር ውስጥ ተጨቁና መኖር አለባት ማለት እንዳልሆነ ልንረዳ ይገባል፡፡

ታዲያ ‹‹ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል፣ እርሱም ገዥሽ ይሆናል›› ለምን ተባለ? ብለን ልንጠይቅ እንችላለን። (ዘፍ. ፫፥፲፮) ነገር ግን ይህ የእግዚአብሔር ቃል ሔዋን ሕግን ከመተላለፏ የተነሣ የተነገረ ነው፤ እግዚአብሔር ሰው አድርጎ የፈጠራቸውን አዳምን እና ሔዋንን ለማበላለጥ የተናገረው ግን አይደለም። አምላካችን ሔዋንን ‹‹ፈቃድሽ ወደ ባልሽ ይሆናል›› ያላት የእባብን ምክር ሰምታ በራስዋ ፈቃድ ብቻ የታዘዘቸውን በማፍረሷ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ግን ከአዳም (ከባልዋ) ጋር ስትኖር ለእርሱ በመታዘዝ መኖር እንዳለባት የሚገልጽ ነው። ለአዳምም ‹‹እርሱም ገዥሽ ይሆናል›› ተብሎ የታዘዘው የሔዋንን ምክር ሰምቶ አትብላ የተባለውን እንደበላ ሳይሆን ሐሳቧንና ምክሯን የሚሞግትና ያለ እርሱ በትዳር ውስጥ ብቻዋን እንደማትወስን ሲገልጽ ነው። ‹‹ይገዛሻል›› የተባለውም በፍቅር በትዳር አንዱ ለአንዱ እንደሚገዛውና እንደሚረዳዱ ‹‹በፍቅሩ ይገዛሻል›› የሚል እንጂ እንደ ምድር ነገሥታት ምርኮ በባርነት መግዛትን አያመለክትም። እግዚአብሔር አምላክ ሁለቱም እኩል ሕግን አፍርሰው የበደሉትን አንዱን ገዥ ሌላውን ተገዥ (አንዱን የበላይ ሌላውን የበታች) አላደረገም።

ከዚህ ላይ ማስተዋል የሚሻው ሌላው ነገር እግዚአብሔር አምላክ ለይቶ ‹‹ባልሽ›› አለ እንጂ ‹‹ወንድ›› አላለም። እንዲህም ማለቱ በትዳር ውስጥ ያለውን ለይቶ ለማሳየት ነው። እንዲሁም ‹‹ፈቃድሽ›› የተባለው ሔዋን አምላክ ለመሆን የፈለገችውና ሕግን ለመተላለፍ ያበቃት መሻት/ፍላጎት ነው። ይህም ፈቃድ ዳግማዊ አዳም ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ፍጹም አምላክ በመሆኑ ተፈጽሟል። ይህም እግዚአብሔር ‹‹እነሆ አዳም መልካሙንና ክፉውን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ›› በማለቱ ይታወቃል፡፡ (ዘፍ. ፫፥፳፩)። ያ አምላክ የመሆን ፈቃድ በእርሱ ተፈጸመ። ‹‹እርሱም ገዥሽ ይሆናል›› የተባለውም በመስቀል ተሰቅሎ በፍቅሩና በደሙ የገዛን መሆኑን የሚያመለክት ነው። ስለዚህ ይህ ቃል ለጊዜው ለአዳምና ለሔዋን ይነገር እንጂ ፍጻሜው በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ ሞትን ድል አድርጎ በመነሣቱ በደሙ የተገዛን መሆናችንን የሚያሳይ ነው።

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን በፍቅር ሞቷል እና ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ትገዛለች፤ በተመሳሳይ ፍቅር ምክንያት ‹‹ሚስቶች ሆይ፤ ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁም ተገዙ፤ ክርስቶስ አካሉ ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ራስዋ እንደሆነ ሁሉ፣ አዳኝዋም እንደ ሆነ ወንድ ለሴት ራስዋ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ እንደምትገዛ፣ ሚስቶችም ለባሎቻቸው በሁሉ ይገዙ። ባሎች ሆይ፥ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳትና ራሱንም ስለ እርስዋ አሳልፎ እንደ ሰጠ እናንተም ሚስቶቻችሁን ውደዱ!›› በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ አስተምሮናል፡፡ (ኤፌ.፭፥፳፪-፳፭) በዚህም ትዳር የአንድን ሰው ፍላጎት ለሟሟላት ብቻ ወይም በምድራዊ ሕይወት ተድላ ደስታን ለማግኘት እንደማይመሠረት ልናስተውል ይገባል፤ ለመንግሥተ ሰማያት መዘጋጀትም ነው እንጂ፤

ሆኖም ግን በአሁኑ ጊዜ ባልና ሚስት የሚጋቡት በራሳቸው የግል ሕይወት ውስጥ የሚፈልጓቸውን አንዳንድ ፍላጎቶች ለሟሟላት ነው። ትዳር የሚመሠርቱት ጊዜያዊ ደስታን፣ እና የግል እርካታን ለማግኘት ነው። እነዚህን ነገሮች ካላገኙ እንደተታለሉ ይሰማቸዋል፤ ወይም የትዳር ጓደኛቸውን ይወቅሳሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ በትዳራቸው መካከል ፍቅርም ሆነ መከባበር አይኖርም፤ ሚስቶችም ባሎቻቸውን ከማክበርና ከመታዘዝ ይልቅ መናቅ ይጀምራሉ፤ ከመውደድ ይልቅ ለጊዜያዊ ደስታ ብቻ በማስመሰል ይኖራሉ፡፡ በሌሎች ሰዎች ዘንድ ለሐሜት እንዳይዳረጉ ወይም በሐሰተኝነት እንዲደነቁ ብቻ በትዳራቸው ደስተኞች እንደሆኑና ባሎቻቸውን አክብረው ወይም ተገዝተው እንደሚኖሩ ያስመስላሉ፡፡ ይህ ግን የኋላ ኋላ ቂምና ጥላቻ ከማጫሩም በላይ በመከባበርና በመተሳሰብ ላይ ያልተመሠረተ ትዳር በመሆኑ ይፈርሳል፡፡

ከዚህም ባሻገር ሚስት ባሏን በመታዘዝ ትዳሯን የማታከብር ከሆነ፤ ባልም በእርሷ እየተከፋና እያዘነባት ወይም እርሱም በእኩይ ተግባሯ በመጎዳትና በማዘን በተመሳሳይ መልኩ በደል የሚፈጽም ከሆነ ሁለቱም እግዚአብሔርን በሚያስከፋ ሥራና በይስሙላ ትዳር ውስጥ በኃጢአት እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም የትዳርን ትርጒም ከማሳጣቱ በላይ ለዘለዓለማዊ ቅጣት ይዳርጋልና ባልና ሚስቶች በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመከባበር ሊኖሩ ይገባል፤ ትዳር የተቀደሰ ነውና አናርክሰው!