ምሬሃለሁ በለኝ!

 

በመዝሙርና ኪነ ጥበባት ክፍል

ነሐሴ ፳ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ባስፈሪው ነጎድጓድ ምድር ስትታረስ

ዋይታ ጩኸቱ በርክቶ መልካም ያልሠራ ሲያለቅስ

ጻድቃን በቀኝህ ሲቆሙ የጽድቁን መንግሥት ለመውረስ

እኔ እማልድሃለሁ በቅዱስ ጊዮርጊስ

አምላኩን ባሰበው በጉብዝናው ወራት

ዘንዶውን በጣለው በልዳው ሰማዕት

በሰባው ነገሥታት በጨካኞች ሴራ

ገድሉን በፈጸመው ደሙን እያዘራ

በመንኮራኩር ተፈጭቶ በተዘራው ዐፅሙ በይድራስ ተራራ

በቤሩታዊት ረዳት በ‘ርሱ እማልድሃለሁ

በቅዱስ ጊዮርጊስ በለኝ ምሬሃለሁ

እስካሁንም ያልሆነ ከቶ የማያዳግም

በረድ እና ድንጋይ እሳት ዲኑ ሲዘንም

ከዋክብት ከሰማይ ሲወድቁ

ፍጥረታት በፊትህ ያኔ ሲጨነቁ

እኔ እማልድሃለሁ በአቡነ ተክለ ሃይማኖት

ገና በሦስት ቀን በጀመረው ስብሐት

በወንጌሉ መረብ ሕዝብህን ባጠመደው

ጣዖትን አጥፍቶ ከሞት አፍ ባስጣለው

ጦርን አስተክሎ በአንድ እግሩ በቆመው

በጻድቁ አባቴ በተክለ ሃይማኖት

ምሬሃለሁ በለኝ ጌታዬ በዚያች ዕለት

በመላእክቱ …ሲነፋ መለከቱ

ነጋሪት ሲጎሰም ፍጥረት ሲቆም ፊቱ

ኃጥአን ከጻድቃን በመንሽህ ሲለዩ

ምድርም አደራዋን ስትመልስ ተከፍቶ ሰማዩ

ጫጉላውን ትቶ ስለተሰደደ

ከዓለም ተድላ ይልቅ አንተን በወደደ

ከአባቱ በራፍ በስምህ ተጥሎ

ገድሉን በፈጸመው ከውሻ ጋር ታግሎ

ምሬሃለሁ በለኝ

በገብረ ክርስቶስ በጻድቁ መናኝ

ምድር ስትጨልም በጭንቅ መከራ ገደሎች ሲናዱ

የበረድ ድንጋዮች ከሰማይ ሲውርዱ

ውበት ሐሰት ነው ደም ግባትም ከንቱ

ፈጣሪን ማሰብ ነው የሰው ልጅ ውበቱ

ብላ በጸናችው በቅድስት አርሴማ በሰማዕቷ

ምሬሃለሁ በለኝ ጌታዬ ያን ‘ለታ

ተራራው ተገምሶ አለት ሲፍረከረክ

መልካምን ያልሠራ ጉልበት ሲብረከረክ

የበደሉን ጦማር ከፊትህ ዘርግቶ

ራሱ ሲተርክ አንደበት ተከፍቶ

ትዳሯን ንብረቷን አልፈልግም ብላ

መኖር ለመረጠች በስምህ ተጥላ

ደግሞም እማልድሃለሁ በክርስቶስ ሰምራ

ታረቅልኝ ባለች ከዲያብሎስ ጋራ

ምሬሃለሁ በለኝ እናቴን ስጠራ

ሰማዩ ሲጠቁር ሲሆን ንውጽውጽታ

ማዕበሉ ሲያይል ንፋሱ ሲማታ

ምሬሃለሁ በለኝ ጌታዬ ያን ‘ለታ

በቀን በሌሊት ለዓይን ጥቅሻ ሳያርፉ

ለምስጋና በትጋት ዘወትር በሚሰለፉ

ስለ መላእክቱ ተማጽኜሃለሁ

በለኝ ምሬሃለሁ

ስለ ስምህ ሲሉ…

እንደ ትቢያ በተጣሉ

በሰይፍ በተቀሉ

ደማቸውን ስላፈሰሱ

መከራውን ሁሉ በጥብዓት ስለታገሡ

በጻድቃን በሰማዕታቱ

ፊትህ በሚቆሙት ምንም ሳይታክቱ

በምልጃ ጸሎታቸው ብዬ እማልድሃለሁ

ስለ አቡነ ሐራ ድንግል በለኝ ምሬሃለሁ

መብራቴም አልበራ ባዶ ነው መቅረዜ

መና አድርጎኛል በዓለም መፍዘዜ

ዘይታቸው ሳይነጥፍ መብራቱን አብርተው ከጠበቁህ ጋራ

ነፍሴን አሰልፋት ከምርጦችህ ተራ

ስለመረጥካቸው ምሬሃለሁ በለኝ

ዳግም ስትመጣ በቀኝህ አቁመኝ!