መክሊት

በምድራዊ ሕይወታችን ሰዎች የራሳችን መክሊት አለን፤ ይህም የእግዚአብሔር መልካም ስጦታ ነው፡፡ ስጦታዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ናቸውና ፈጣሪያችን ከጊዜ (ዕድሜያችን) ጋር ለእያንዳንዳችን ተሰጥኦ አድሎናል፡፡ ለአንዱ ጥበብ ለሌላው ዕውቀት ይሰጣል፤ አንዱን የዋህ ሌላውን ደግሞ ትሑት ያደርጋል፤  አስተዋይነትን ወይንም ብልሀትንም ያድላለል፤ እንዲሁም አንዱን ባለጠጋ ሲያደርገው ገንዘብ የሌለውን ደግሞ ባለሞያ ያደርገዋል፤ አንዱን የሥዕል ተሰጥኦ ሲያድለው ሌላውን ደግሞ ድምጸ መረዋ ያደርገዋል፤ የእግዚአብሔር ሥራ ድንቅ ነውና፡፡ በመክሊታችን ሠርተን ማትረፍ ግን ከእኛ ይጠበቃል፡፡

ጥበበኛ እንደ ጠቢቡ ሰለሞን፣ መዝሙረኛ እንደ ነቢዩ ዳዊት እንዳልተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ ምስክር ነው፤ እነርሱም በነገሡበት ዘመን ፈጣሪያቸው ባደላቸው ተሰጥኦ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቅ ሕዝቡን በሚገባ የመሩ ነበሩ፡፡

በዘመናት የተነሡ ጻድቃንና ሰማዕታትም እግዚአብሔር አምላክን ያገለገሉት በተሰጣቸው መክሊት ሠርተው እና ነግደው በማትረፋቸው ነው፡፡ በዘመነ ሥጋዌ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ለደቀ መዝሙርቱ በምሳሌ ሲያስተማራቸው እንዲህ አላቸው፤ ‹‹መንገድ እንደሚሄድ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት፥ ለአንዱ ሁለት፥ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውና ሄደ፡፡ ያ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፡፡ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታውን ወርቅ ቀበረ፡፡

ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቈጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም፡- መልካም፥ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሀለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ፡- አቤቱ፥ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፍሁ አለ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው መጣና እንዲህ አለ፡- አቤቱ፥ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፥ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እንሆ፥ መክሊትህ፡፡ ጌታውም መልሶ አለው፡- አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ፥ እኔ  ካልዘራሁበት የማጭድ፥ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡ ከዚያ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፤ ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን፥ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት፡፡›› (ማቴ.፳፭፥፲፬-፴)

ከዚህ ታሪክ እንደምንረዳው ለአገልጋዮቹ ጌታ መክሊቱን ሠርተው እንዲያተርፉበት ከሰጣቸው ከረጅም ጊዜ በኋላ ወደ እነርሱ የተመለሰው በጊዜያቸው ተጠቅመው እና በመክሊታቸው ሠርተው እንዲያተርፉ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ መክሊት ወይንም ገንዘብ ብሎ እንደምሳሌ የተጠቀመበት ለፍጥረቱ ሁሉ እንደችሎታው የሰጠውን ስጦታ የተባለው ተሰጥኦ ሲሆን በዚያም የፈጠራቸውን አምላክ እንዲያገለግሉበት ነው፡፡ ባለ አምስቱ እና ባለ ሁለቱ አገልጋይ ለጌታቸው በመታዘዝ በተሰጣቸው መክሊት ሠርተው ቢያተርፉም ባለ አንዱ መክሊት አገልጋይ ግን የተሰጠውን መክሊት በመናቅ መክሊቱን መልሶ ለመስጠት ሞክሯል፤ ጌታውንም እስከ መወንጀል ጭምር ደርሷል፡፡ ይህም መክሊቱ እንዲወሰድበትና መጨረሻው በጨለማ  እንዲኖር ተፈርዶበታል፡፡

ባለ ሁለቱ እና ባለ አምስቱ መክሊት አገልጋዮች በተሰጣቸው ተሰጥኦ እግዚአብሔር አምላካቸውን በመታዘዝ አገልግለው እስከ ሕይወት ፍጻሜያቸው በጎ ምግባርን ሠርተው በጽድቅ ተጉዘው መንግሥተ ሰማይትን የወረሱ ሰዎች ምሳሌ ነው፡፡ ባለ አንድ መክሊቱ አገልጋይ ግን የፈጣሪውን ህልውና  ያልተረዳ፣ የተሰጠውን መክሊትም መጠቀም ያልቻለና ጊዜውንም አብክኖ ወደ ዘለዓለማዊ ጨለማ የተጣለ ወይንም የሚጣል ኃጢአተኛ ሰውን ይወክላል፡፡

በመጀረመሪያ እግዚአብሔር አምላክ በአምሳሉ ለፈጠረው ሰው የጊዜን ስጦታ የሰጠው ዘወትር ፈጣሪውን በመፍራት እንዲኖር፣ እንዲጸልይ እና እንዲጾም ነው፡፡ በመንፈሳዊ ትጋትም ፈጣሪውን ያገለግለው ዘንድ ዕድሜን ሰጥቶታል፡፡ ሰዎች በሕይወት ዘመናችን በጎ ምግባር እንድንሠራ የተለያየ ዕድሜ ሰጥቶናል፡፡ ስለዚህም በእግዚአብሔር ሕግ ኖረን ዘለዓለማዊ ርስትን እንድንወርስ በምድራዊ ሕይወታችን ልንተጋ ይገባል፡፡ የጊዜን ዋጋ ልንረዳ የምንችለው ዕለታቱን፤ ወራቱን እንዲሁም ዓመታቱን ተጠቅመን በጎ ምግባራትን ስንፈጽም ነው፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን ለመባል በሕይወታችን የሚገጥመን ችግር፣ መከራ እና ሥቃይ በመቋቋም እስከመጨረሻው በትጋት መኖር አለብን፡፡

በሕይወት ዘመናችን ዕውቀት ወይንም ሀብት ልናካብት እንችላለን፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወይንም በዓለማዊ ትምህርት ያካበትነውን ዕውቀት ልንተገብረው የሚገባው ግን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለመኖር ወይንም ለማጠንከር መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ወደ አዘቅት ይከተናል፤ ይህም በዘመናት በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የተንጸባረቀ ክስተት ነው፡፡

ዓለማችን በዚህ ወቅት የተለያዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ሰዎች ታስተናግዳለች፤ የሕክምና ጠቢባን፣ ባለጠጎች፣ መዘምራን፣ ደራስያን፣ ሠዓልያን፣ እንዲሁም በተለያዩ ሞያ ውስጥ ያሉ ሰዎችም ይኖሩባታል፡፡ ነገር ግን ሁሉም ተሰትኦቸውን ለእግዚአብሔር ውለታውን ለመክፈል ያውሉታል ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ዕውቀታቸውን ሆነ ሀብታቸውን እንዲሁም ብቃታቸውን ለዓለማዊ ጥቅማቸው የሚያውሉ ሰዎች ፈጣሪያቸውን ከሚያገለግሉት እጥፍ በርክተዋልና፡፡ ይህም ዓለም በሰይጣናዊ አመለካከት የተገዙ ሰዎች የበዙባት እንደሆነች አመላካች ነው፤ ለዚህም ምስክር በምድር የተስፋፋው የቅርብ ጊዜው መድኃኒት የለሹ የኮሮና በሽታ የእግዚአብሔር መቅሠፍት ነው፤ እስካሁንም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡

በመሆኑም እኛ ሰዎች ስንባል ምን ጊዜም ቢሆን የመፈጠራችን ምክንያት እግዚአብሔር አምላካችንን ለማገልገል መሆኑን አውቀንና አምነን እርሱ በሰጠን መክሊት ልናገለግለው ይገባል፡፡ ይህም በማንኛውም የአገልግሎት መደብ ወይንም የሥራ ዘርፍ ያሉትን ሰዎች በሙሉ ያካትታል፡፡ አለበለዚያ ግን እንደ ባለ አንድ መክሊቱ አገልጋይ ተሰጥኦአችንን ሳናውቅ ወይንም አሳንሶ በመናቅ ፈጣሪን አሳዝነን ወደ ዘለዓለም ጨለማ እንጣላለንና መክሊታችንን እንወቅ!

እግዚአብሔር አምላክ በመክሊታችን ሠርተን እንድናተረፍ ይርዳን፤ አሜን፡፡