መካነ ጉባኤያት ወላዴ ሊቃዉንት ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ዕድሳት ሊደረግለት ነዉ፡፡

ታኅሣሥ 27/2004 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ
  • ለዕድሳቱ 1.5 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል፡፡

frontመካነ ጉባኤያት የሆነዉን ታሪካዊዉንና ጥንታዊዉን ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ለማደስ የገቢ ማሰባሰቢያ ጉባኤ ተካሔደ፡፡ታኅሣሥ 22 ቀን 2004 ዓ.ም . በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሁለገብ አዳራሽ በተካሄደዉ በዚህ ጉባኤ የአራቱ ጉባኤያት የትርጓሜ መምህር የሆኑት ሊቀ ሊቃዉንት ዕዝራ ሐዲስና የደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ አስተዳዳሪና የድጓ መምህር የሆኑት መልአከ ሃይማኖት ሲሳይ አሰፋ ጉባኤያቸዉን ትተዉ የተገኙበት ሲሆን፣ ከአዲስ አበባም በአሁኑ ጊዜ የሊቃዉንት ጉባኤ ሰብሳቢ የሆኑት መልአከ ሰላም ዐምደ ብርሃን እና  መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ ሊቀ ስዩማን ራደ አስረስና ሌሎች የሊቃዉንት ጉባኤ አባላት እንዲሁ ም በሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳዉሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት የሐዲስ ኪዳን ትርጓሜ መምህር የሆኑትን መጋቤ ሐዲስ ስቡሕ አዳምጤን ጨምሮ በቦታዉ የተማሩና የጉባኤ ቤቱን ታሪክ የሚያዉቁ በርካታ ሊቃዉንት በጉባኤዉ ላይ ተገኝተዋል፡፡

 

 

በጉባኤዉ ላይ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝና ሊቀ ሊቃዉን ዕዝራ ሐዲስ ትምህርተ ወንጌል ሰጥተዋል፡፡የቦታዉ የድጓ መምህርና የቤተ ክርስቲያኑ አgubae z mekane Eyesus 047ስተዳዳሪ መልአከ ሃይማኖት ሲሳይ አሰፋ አጂግ በሚመስጠዉ ድምጻቸዉ ያሬዳዊ ወረቦችን ሲያንቆረቆሩ ሊቃዉንቱን ሁሉ አስደምመዋል፡፡

የቀዳሜ ዜማ ሊቃዉንት ማኅበር አባላት የሆኑት ሊቃዉንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያም ገዳም ሰንበት ትምህርት ቤትgubae z mekane Eyesus 118 መዘምራን ልምላሜ ነፍስ የሚያስገኙ ወረቦችን አቅርበዋል፡፡ የደብረ ኃይል ቅዱስ ራጉኤል ጎልማሶች ጉባኤ መዘምራንና ዲያቆን ምንዳዬ ብርሃኑም ሕዝቡን ያሳተፉ ጥዑም ዝማሬዎችን አሰምተዋል፡፡ ጉባኤዉ ከላይ ከተገለጹት መርሐ ግብራት በተጨማሪ የቦታዉን መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ቤተ ክርስቲያኑን፣ አብያተ ጉባኤያቱንና የክብረ በዓል ሥርዓቱን የሚያሳይ 10 ደቂቃ ቪዲዮ ከቀረበ በኋላ  በሊቀ ስዩማን ራደ አስረስና በመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን ከቦታዉ ተምረዉ ለታላቅ መዓርግ ስለበቁት ሊቃዉንትና ስለ ጉባኤቤቱና ስለ ቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ሰፊ ገለጻ ቀርቧል፡፡

 

በዐጼ አድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት የተተከለዉ ጥንታዊዉና ታሪካዊዉ ደብረ ሃማኖት መካነ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን በሦስት ታላላቅ ጉባኤያቱ የታወቀ ነበር፡፡በቅዱሳት መጻሕፍት ትርጓሜ ቤተ ጉባኤ፣ በቅኔ ቤተ ጉባኤ እና በድጓ ቤተ ጉባኤ፡፡በሦስቱም አብያተ ጉባኤያት ታላላቅ ሊቃዉንትን ለሀገሪቱም ሆነ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲያበረክት የቆየዉ ይህ ታሪካዊ ቦታ እስከ 1950ዎቹ ሦስቱም ጉባኤያት የነበሩት ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ግን የቅኔ ጉባኤ ቤቱ ታጥፎ የትርጓሜ መጻሕፍቱና የድጓ ጉባኤዎቹ ግን አሁንም ሳይታጎሉ የሚሰጥበት ቦታ ነዉ፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ በንግሥተ ንግሥታት ዘዉዲቱ ዘመን በጥሩ ሁኔታ በዘመናዊ መንገድ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ወዲያዉኑ ጠላት (ጣልያን) ወደ ሀገራችን በመግባቱ ምክንያት ቤተ ክርስቲያኑ ተቃጥሎ ነበር፡፡ በጊዜዉ በአካባቢዉ ከነበሩት ስዉራን አበዉ አንዱ በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ተገልጠዉ በ 7 እሳት ይወgubae z mekane Eyesus 018ርዳል እያሉ ትንቢት ሲናገሩ የሰሙት አበዉ ታቦታቱን መጻሓፍቱንና ንዋያተ ቅድሳቱን በሙሉ ይዘዉ በአቅራቢያዉ ወደምትገኘዉ ዋሻ ማርያም የምትባል የዋሻ ዉስጥ ቤተ ክርስቲያን አስገቡት፡፡ እንደ ተነገረዉም በተጠቀሰዉ ቀን ጣሊያን አካባቢዉንና ቤተ ክርስቲያኑን ሲያቃጥል የተጠቀሱት ንብረቶች በሙሉ ከዉድመት ዳኑ፡፡ ጣልያን ድል ተነሥቶ ከሀገር እስኪወጣ ድረስም ለሦስተ ዐመታት ያህል በዚያ ዋሻ ዉስጥ ተቀምጦ ሊቃዉንቱና ማኅበሩም በየዐመቱ የልደትን በዓል በዚያ ዋሻ ዉስጥ በሐዘን ሲያከብሩ አሳልፈዋል፡፡ እንደ ሊቀ ስዩማን ራደ አስረስ ገለጻ የመልክአ ኢየሱስ ነግሦች ከሆኑት (ከሚወረቡት) የመጨረሻ የሆነዉ ከምዕራጉ ‹‹ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀ ካህናቲነ፣ አስተጋብአነ ኀበ ትረፍቅ መካነ፤ እስመ ዝርዋን አግብርቲከ ንህነ›› በለቅሶና በሐዘን ይወረብ ነበርና ሐዘኑና ሱባኤዉ ጠላት ጣሊያንን ለመመለስ ጠቅሟል፡፡ ጣሊያን ከሀገራችን ከወጣ በኋላ በመቃረቢያ ታቦቱ ገብቶ መምህራኑም ጉባኤያቸዉን ተክለዉ ጥቂት ዐመታት እንደቆየ በቦታዉ ላይ የትርጓሜ መምህር በነበሩትና ከጠላት መመለስ በኋላ ከመጀመሪያዎቹ ጳጳሳት አንዱ በነበሩት የጥንቱ አቡነ ሚካኤል ( የቅዳሴ ትርጓሜን አዘጋጅተዉ ያሳተሙት) አሳሳቢነትና አስተባባሪነትም ጭምር በንጉሡ በዐፄ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድ እንደገና አሁን በሚታየዉ መልኩ ተሠርቶ በእግዚአብሔር ቸርነት ተጠናቀቀ፡፡

ይህ አሁን ያለዉ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ግንባታዉ ከተጀመረ ከአንድ ዐመት በኋላ ራሳቸዉ ንጉሠ ነገሥቱ እቦታዉ ድረስ ሄደዉ ግንባታዉንም በቦታዉ ተቀምጠዉ በማሰራት ላይ የነበሩትን ብጹዕ አቡነ ሚካኤልንም አይተዉ ተመልሰዋል፡፡በጊዜዉ በቦታዉ ላይ ቅኔዉንና ትርጓሜ መጻሕፍቱን አንድ ላይ አድርገዉ ያስተምሩ የነበሩት እጅግ ስመ ጥር የነበሩት የኔታ  ገብረ ጊዮርጊስ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት በድጓ ቤት ያሉትን ሳይጨምር ከ450 በላይ የቅኔና የትርጓሜ መጻሕፍት ተማሪዎች የነበሩበት ጊዜ ነበር፡፡

ይህ አሁን ያለዉ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሞ በሚመረቅበት ጊዜ ደግሞ ንጉሠ ነገሥቱ ተጠብቀዉ ባይገኙም የጎንደሩ ገዥ ደጃዝማች ክፍሌ ዳዲ እና   የዚያን ጊዜዉ ጳጳስ የኋላዉ ፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስና ታላቁ አቡነ ዮሐንስ ከሌሎች የጊዜዉ የመንግሥት ባለ ሥልጣናትና ሊቃዉንተ ቤተ ክርስቲያን ጋር ተገኝተዉ እንደነበርም ተገልጾአል፡፡

Beataደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ የሃይማኖት አባቶችን ለሀገሪቱ ከማበርከቱም በላይ በኢትዮጵያ ካቶሊኮች ገብተዉ ከወጡበት የጥንቱ ጊዜ በኋላ መልኩን ቀይሮ የቤተ ክርስቲያን ሊቃዉንትን ሲያበጣብጥ የቆየዉ የቅባትና የጸጋ ሰርጎ ገብ ፈጽሞ ካልረገጣቸዉ የሰሜን ኢትዮጵያ የትርጓሜ ትምህርት ቤቶች አንዱ መሆኑ በሊቃዉንቱ በተደጋጋሚ ተመስክሮለታል፡፡የደብሩ አስተዳዳሪና የድጓ መምህር መልአከ ሃይማኖት ሲሳይ አሰፋ በታሪክ የሚታወሱትን ሊቃዉንት ሲያወሱ የታች ቤት ትርጓሜ መሥራች የሚባሉት መምህር ኤስድሮስ የዚህ ቦታ መምህር እንደ ነበሩና ጣና ገብተዉ መጻሕፍትን መርምረዉ የታች ቤቱን ትርጓሜ ጎንደር ልደታ ላይ ከማስተማራቸዉ በፊት መካነ ኢየሱስ ላይ ተምረዉ ከዚያም ወንበሩን ተረክበዉ ማስተማራቸዉንና በኋላም መጥተዉ በቦታዉ ጥቂት ጊዜያትን ከቆዩ በኋላ እዚያዉ አርፈዉ መቀበራቸዉን አስረድተዋል፡፡ የቦታዉን ታላቅነት አስመልክቶ በሊቃዉንቱ ዘንድ ብዙ የሚነገርለት መሆኑን ያወሱት መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንም በታላቁ ሊቅ የኔታ ገብረ ጊዮርጊስ ከተቀኙት መወድስ ዉስጥ ፤

‹‹… ቤተ ጽድቅሂ ቤተ ሥላሴ መካነ ኢየሱስ ዉእቱ፣
እስመ ኢያንቀለቅል ለዓለም ሃይማኖት መሠረቱ፣
ባሕቱ ድልዉ መልዕልተ ሰማያት ሰባቱ፣
መካነ ኢየሱስ መንበረ አብ ዘይጸዉርዎ አርባዕቱ፡፡…››

የሚለዉን ዘርዕ በማሰማት በምሥጢር ‹ ልክ እንደ አርባእቱ እንስሳ ኪሩቤል አራቱ ጉባኤያተ መጻሕፍትን በመዘርጋትና የማይናወጽ የሃይማኖት መሠረት በመሆን ኑፋቄንም ባለማስደረስ  መካነ ኢየሱስ በእዉነት የሥላሴ ቤት የእግዚአብሔር መንበሩ ነዉ › ተብሎ ይነገርለት እንደነበር አስረድተዋል፡፡ መልአከ ሰላም ዐምደ ብርሃንም የኔታ ገብረ ጊዮርጊስን ከመካነ ኢየሱስ ወደ አክሱም እንዲሄዱ ለአክሱሞች ከፍተኛ ዋስትና የሰጠዉ ይሄዉ በሃይማኖት ነቅዕ ጥርጣሬ የሌለዉ ጉባዔ የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቦታዉ ለቅርቧ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም ያበረከታቸዉ ሊቃዉንት እጅግ ብዙዎች ናቸዉ፡፡እንደ ሊቀ ስዩማን ራደ አስረስ ገላጻ በ1921 ዓ ም ግብጽ ወርደዉ ከተሾሙት ከዐራቱ አንዱ የሆኑት ጎሬ ላይ በጣልያን እንደ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት የተቀበሉት ብጹዕ አቡነ ሚካኤል በዚህ ቦታ በትምህርት ካለፉት ዉስጥ አንዱ ናቸዉ፡፡ በኋላም በጣልያን ሁለቱ አበዉ ማረፋቸዉን በማየት የኢትዮያ ሊቃዉንት ከሾሟቸዉ ዉስጥ አቡነ ዮሐንስ የተባሉት ሐዲስ ተክሌ የተማሩት ደብረ ሃይማኖት መካነ ኢየሱስ ነበር፡፡ ከጣልያን መመለስ በኋላም በ1941 ከተሾሙት ከቀዳሚዎቹ ሊቃነ ጳጳሳት አንዱ ከሆኑት ከብጹዕ አቡነ ሚካኤል ጀምሮ እነ አቡነ በርተሎሜዎስ፣ አቡነ ኤልያስ (አሁን ስዊድን ያሉት) የኋላዉ አቡነ ኤልያስ (የቀለም ቀንዱ ሊቀ ጉባኤ አስበ)፣ ተጠቃሾች ሲሆኑ ከሊቃዉንቱም እነ ርዕሰ ደብር ጥዑመ ልሣን፣ መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ ሊቀ ሥዩማን ራደ አስረስ፣ መልአከ ሰላም መርዓዊ ተበጀ፣ … ተቆጥረዉ የማያልቁ የብሉይ፣ የሐዲስ፣የመጻሕፍተ ሊቃዉንት፣ የመጻሕፍተ መነኮሳት፣ የቅኔና የዜማ ሊቃዉንትን አፍርቷል፡፡

ቤተ ክርስቲያኑ ባለፉት ሃምሳ ዐመታት ዉስጥም በቦታዉ ብሉይና ሐዲስን በማስተማር፣ የተጣሉትን ከማስታረቅ ጋር በብሕትዉና በመኖር የgubae z mekane Eyesus 130ሚታወቁት መጋቤ ሐዲስ ኃይለ ሚካኤል ብዙ ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ያገለገሉበት ሲሆን እርሳቸዉ በዕርጅና ማስተማሩን ሲያቆሙ በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ሐዲሳቱን ከእርሳቸዉ ብሉያቱን ደግሞ ጎንደር ዐቢየ እግዚእ ከየኔታ ፀሐይ የተማሩት የኔታ ሐረገወይን ተተክተዉ በማስተማር ላይ ይገኛሉ፡፡ የደብሩ አስተዳዳሪ የሆኑት መልአከ ሃይማኖት ሲሳይ አሰፋም በቦታዉ ላይ ድጓዉን በማስተማርና ብዙ መምህራንና ደቀ መዛሙርትን በማፍራት ከሃያ አምስት ዐመት በላይ ኖረዉበታል፡፡

ቦታዉ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችን የያዘ ከመሆኑም በላይ ከጥንት ጀምሮ እጅግ ብዙ ሕመምተኞች (ብዙ የእስልምና ተከታዮችን ጨምሮ) የሚፈወሱባት የኪዳነ ምሕረት ጸበል ይገኝበታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ቆርቆሮዉ አርጅቶ በማፍሰስ ላይ ከመሆኑም በላይ ሌሎቹንም ጨምሮ ከ 1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ የሚጠይቅ እድሳት እንደሚያስፈልገዉ በባለሞያዎች የተጠናዉ ጥናት ያመለክታል፡፡ እንደ ባለሞያዎቹ ገለጻ 750 ቆርቆሮና ለጣራ ሥራዉ የሚሆኑ የተለያዩ ጣዉላዎች፣በጣዉላ የሚሰራ ኮርኒስ፣ የኤሌክትሪክ፣የፍሳሽ፤ 24 ቆመ ብእሲዎች ወይም አምዶች (Columns)፣ የግቢዉን በርና ሌሎቹንም ያካትታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ የሚገኘዉ ገጠር ዉስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሌሎቻችንን በተለይም በቦታዉ ላይ በመማርና ከተማሩት አገልግሎት በማግኘት ላይ ያሉትን እንዲሁም ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ድረስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኘዉን ታሪካዊዉን ቦታ በመርዳት እንደ ቀድሞዉ ሁሉ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያለዉን አስተዋጥኦ ማሳደግ እንደሚጠበቅ በዕለቱ ከነበሩት በመልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁንና በሊቃዉንት ጉባኤ ሰብሳቢዉ መልአከ ሰላም ዐምደ ብርሃን በአጽንዖት ተገልጾአል፡፡

በመርሐ ግብሩ ተሳታፊዎች ጥያቄ መሠረት ሥራዉን ለመርዳት ለሚፈልጉ በስልክ ቁጥሮች
0911 68 93 22
0911 10 95 84
0911 13 73 50

በመደወልና በማነጋገር በዐይነትም ሆነ በገንዘብ መርዳትና ለለገሱት እርዳታም ሕጋዊ ደረሰኝና በዐይነትም ከሆነ የተላከዉ ዕቃ መድረሱን ማረጋገጫ ባለ ማኅተም ደብዳቤ መቀብል እንደሚገባ ተገልጾ ጉባኤዉ በጸሎት ተጠናቅቋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ እስከ 12፡ 30 ድረስ በቆየዉ በዚህ ረጂም ጉባኤ ተሳታፊዎቹ በትዕግስት ጸንተዉ የሊቃዉንቱን ትምህርቶችና ገለጻዎች እነዲሁም ወረቦችና ዝማሬዎች ሲኮመኩሙ እንዲዉሉ ያስቻለዉ ጉባኤዉ የገቢ ማሰባሰቢያ ሳይሆን የትምህርትና የዝማሬ ብቻ መስሎ በመዘጋጀቱ እያመሰገንን ሌሎቹም አራአያዉን ሊከተሉት የሚገባ መሆኑን ሳንጠቁም አናልፍም፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!