ሐዋርያው ይሁዳ

ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

በስመ ይሁዳ የሚጠሩ በርካታ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ ተጠቃሾች ቢኖሩም በሰኔ ፳፭ ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የምታከብረው ሐዋርያው ይሁዳ ከሰባ ሁለቱ አርድእት አንዱ የሆነው የፀራቢው የዮሴፍ ልጅ እንዲሁም ያዕቆብ ለተባለው ሐዋርያ ወንድም ነው፡፡ አስቀድሞም ስሙ ታዴዎስ ይባል ነበር፡፡ ይህም ሐዋርያ ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ያመነና በብዙ ሀገሮች የሰበከ ነው፤ ከእነርሱም መካከል በአንዲት ዴሰት ገብቶ በማስተማር በዚያ የነበሩትን ሰዎች በጌታችን ስም አሳምኖ ቤተ ክርስቲያን እንደሠራላቸውና በቀናች ሃይማኖትም እንዳጸናቸው በመጽሐፈ ስንክንሳር ተጠቅሷል፡፡

በ፷፭ ዓ.ም አካባቢም በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች በግኖስቲክ ትምህርት ሳቢያ ግራ መጋባታቸውን በሰማ ጊዜ ሐዋርያው መልእክትን ጽፎ ልኮላቸዋል፤ የሊቀ ነቢያት ሙሴን ገድል የሚያትተውን የዜና ሙሴን በማካተቱ ሐዋርያት ለአዋልድ መጽሐፍት የሚሰጡትን ክብሩ በጻፈው መልእክቱ ገልጧል፤ ከሐዋርያት መልእክተኞች ሰባተኛ የሆነች ምሥጢርን የተመላች ናት፤ በእርሷም ብዙዎች አረማውያንን ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ወደ ማመን መልሷቸዋል፡፡ በመልእክቱም መጽሐፈ ሄኖክንም በመጥቀስ የመጽሐፍ ቅዱስ ቁጥር ከ፷፮ በላይ መሆኑን ያስረዳው ይህ ሐዋርያ ነው፡፡

የሐዋርያው ይሁዳ መልእክትም እንዲህ የሚል ነው፤ ‹‹የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ የያዕቆብም ወንድም የሆነ ይሁዳ፥ በእግዚአብሔር አብ ለሚወደው ለኢየሱስ ክርስቶስም ተጠብቀው ለተጠሩ  ምሕረትና ሰላም ፍቅርም ይብዛላችሁ። ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ።

ከብዙ ጊዜ በፊት ለዚህ ፍርድ የተጻፉ አንዳንዶች ሰዎች ሾልከው ገብተዋልና፤ ኃጢአተኞች ሆነው የአምላካችንን ጸጋ በሴሰኝነት ይለውጣሉ፤ ንጉሣችንንና ጌታችንንም ኢየሱስ ክርስቶስን ይክዳሉ።  ዳሩ ግን ሁሉን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ምንም የተማራችሁ ብትሆኑ ጌታ ከግብፅ አገር ሕዝቡን አድኖ የማያምኑትን በኋላ እንዳጠፋቸው ላሳስባችሁ እወዳለሁ። መኖሪያቸውንም የተውትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘለዓለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል።  እንዲሁም እንደ እነርሱ ዝሙትን ያደረጉና ሌላን ሥጋ የተከተሉ ሰዶምና ገሞራ በዙሪያቸውም የነበሩ ከተማዎች በዘለዓለም እሳት እየተቀጡ ምሳሌ ሆነዋል። እንዲሁም እነዚህ ሰዎች ደግሞ እያለሙ ሥጋቸውን ያረክሳሉ፤ ጌትነትንም ይጥላሉ፤ ሥልጣን ያላቸውንም ይሳደባሉ።

የመላእክት አለቃ ሚካኤል ግን ከዲያብሎስ ጋር በተከራከረ ጊዜ ስለ ሙሴ ሥጋ ሲነጋገር ጌታ ይገሥጽህ አለው እንጂ የስድብን ፍርድ ሊናገረው አልደፈረም፤ እነዚህ ግን የማያውቁትን ሁሉ ይሳደባሉ፤ አእምሮም እንደሌላቸው እንስሶች በፍጥረታቸው በሚያውቁት ሁሉ በእርሱ ይጠፋሉ። ወዮላቸው፥ በቃየል መንገድ ሄደዋልና ስለ ደመወዝም ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፤ በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል። እነዚህ ከእናንተ ጋር ሲጋበዙ በፍቅር ግብዣችሁ እንደ እድፍ ናቸው፤ እንደ እረኞች ያለ ፍርሃት ራሳቸውን ይጠብቃሉ፤ በነፋስ የተወሰዱ ውኃ የሌለባቸው ደመናዎች፣ ፍሬ የማያፈሩ ሁለት ጊዜ የሞቱ ከነሥራቸው የተነቀሉ በበጋ የደረቁ ዛፎች፣  የገዛ ነውራቸውን አረፋ እየደፈቁ ጨካኝ የባሕር ማዕበል፣ ድቅድቅ ጨለማ ለዘለዓለም የተጠበቀላቸው የሚንከራተቱ ከዋክብት ናቸው። እነዚህ እንደ ምኞታቸው እየሄዱ የሚያንጎራጉሩና ስለ ዕድላቸው የሚያጕረመርሙ ናቸው፤ እንዲረባቸውም ለሰው ፊት እያደሉ አፋቸው ከመጠን ይልቅ ታላቅ ቃል ይናገራል።

እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት ቀድሞ የተነገረውን ቃል አስቡ፤  እነርሱ በመጨረሻው ዘመን በኃጢአተኝነት እንደ ገዛ ምኞታቸው እየሄዱ ዘባቾች ይሆናሉ ብለዋችኋልና። እነዚህ የሚያለያዩ ሥጋውያንም የሆኑ መንፈስም የሌላቸው ሰዎች ናቸው። እናንተ ግን ወዳጆች ሆይ፥ ከሁሉ ይልቅ በተቀደሰ ሃይማኖታችሁ ራሳችሁን ለማነጽ እየተጋችሁ፣ በመንፈስ ቅዱስም እየጸለያችሁ፣ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ።  አንዳንዶች ተከራካሪዎችንም ውቀሱ፤ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ፤  አንዳንዶችንም በሥጋ የረከሰውን ልብስ እንኳ እየጠላችሁ በፍርሃት ማሩ።  ሳትሰናከሉም እንዲጠብቃችሁ በክብሩም ፊት በደስታ ነውር የሌላችሁ አድርጎ እንዲያቆማችሁ ለሚችለው ብቸኛ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።››

ከዚህም በኋላ ሐዋርያው ይሁዳ ሮሃ ሀገር ሄዶም ንጉሡ አውጋንዮስን ከደዌው በመፈወስ የክርስትና ጥምቀትንም አጥምቆታል፤ ሐራፒ በተባለ ሀገርም ሄዶ በውስጣ ሰብኳል፤ ብዙዎቹንም ካጠመቀ በኋላ ቤተ ክርስቲያንም ሠርቶላቸዋል፡፡

በዚህም ጊዜ የሀገሩ ገዥ ይዞ ጽኑዕ ሥቃይ አሠቃየው፤ ችንካር ያለው ጫማ በእግሮቹ ውስጥ አድርጎ አንድ ምዕራፍ ያህል አስሮጠው፤ ከዚህም በኋላ ሰቅሎ በፍላፃ ነደፈው፤ ክብር ይግባውና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እጅ ነፍሱን ሰጠ፡፡

እግዚአብሔር አምላክ በሐዋርያው ቅዱስ ይሁዳ ጸሎት ይማረን፤ አሜን!

ምንጭ፡- ፹፩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፳፭፣  የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቁጥር ፩