ነቢዩ ኢያሱ ወልደ ነዌ

ሰኔ ፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

የነዌ ልጅ ኢያሱ የታላቁ ነቢይና መስፍን የነቢያት አለቃ የሙሴ ደቀ መዝሙር የነበረ በኋላም እግዚአብሔር የመረጠው ነቢይ ነው፡፡ የስሙ ትርጓሜም ‹‹እግዚአብሔር አዳኝ›› ማለት ነው፤ ‹‹የእግዚአብሔር ባሪያ ሙሴ ከሞተ በኋላ እግዚአብሔር የሙሴን አገልጋይ የነዌን ልጅ ኢያሱን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ባሪያዬ ሙሴ ሞቶአል፤ አሁንም አንተና ይህ ሕዝብ ሁሉ ተነሥታችሁ ለእስራኤል ልጆች ወደምሰጣቸው ምድር ይህን ዮርዳኖስ ተሻገሩ። ለሙሴ እንደ ነገርሁት የእግራችሁ ጫማ የሚረግጠውን ቦታ ሁሉ ለእናንተ ሰጥቼአለሁ። ከምድረ በዳው ከዚህም ከሊባኖስ ጀምሮ እስከ ታላቁ ወንዝ እስከ ኤፍራጥስ ድረስ የኬጥያውያን ምድር ሁሉ እስከ ፀሐይ መግቢያ እስከ ታላቁ ባሕር ድረስ ዳርቻችሁ ይሆናል። በሕይወትህ ዕድሜ ሁሉ ማንም አይቋቋምህም፤ ከሙሴ ጋር እንደ ሆንሁ እንዲሁ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ አልጥልህም፥ አልተውህም። ለአባቶቻቸው እሰጣችኋለሁ ብዬ የማልሁላቸውን ምድር ለዚህ ሕዝብ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ። ነገር ግን ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል። የዚህ ሕግ መጽሐፍ ከአፍህ አይለይ፥ ነገር ግን የተጻፈበትን ሁሉ ትጠብቅና ታደርግ ዘንድ በቀንም በሌሊትም አስበው፤ የዚያን ጊዜም መንገድህ ይቀናልሃል ይከናወንልሃልም። በምትሄድበት ሁሉ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነውና ጽና፥ አይዞህ፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ ብዬ አላዘዝሁህምን?›› (ኢያ.፩፥፩-፱)

በዚህም ጊዜ የነቢዩ ኢያሱ ልብ ጸና፤ የእግዚአብሔርንም ትእዛዝ እየተቀበለ ሕዝበ እስራኤልን መምራት ጀመረ፤ የዮርዳኖስንም ወንዝ አሻገራቸው፤ ካህናቱም ታቦተ ሕጉን ተሸክመው በወንዙ መካከል አልፈው እስኪሻገሩ ድረስ እግዚአብሔር ውኃውን እንድ ግድግዳ አቁሞት ነበር፡፡ በከነዓን ምድርም ከበቧት፡፡ ነቢዩም ኢያሱም ሕዝበ እስራኤልን ለጦርነት ይዘጋጁ ዘንድ አዘዛቸው፤ እርሱም ለጦርነቱ እንዲያመች ሁለት ሰላዮችን ወደ ኢያሪኮ ላከ፤ ሰላዮቹም ወደ ኢያሪኮ ከተማ በመግባት ረዓብ በተባለች ሴተኛ አዳሪ ቤተ ውስጥ በመደበቅ ከቆዩ በኋላ ጠላት ሳያያቸው ወደ እስራኤል ተመልሰው ሄዱ፤ በዚህም ኢያሪኮን መያዝ ቻለ፤ ይህ ነቢይ በግንብ የተከበበችው ኢያሪኮን ሰባት ቀን ዞሯታል፡፡ ቅጽሮቿንም አፍርሶ አሕዝብኑና ንጉሣቸውን በሙሉ አጠፋቸው፤ የእስራኤል ልጆችም በአሕዛብ ዘንድ የተፈሩ ሆኑ፡፡ ታቦተ ሕጉም ከእርሱ ጋር ነበረች፤ ስለዚህም በተንኰል የተነሡበትን ሁሉም በእግዚአብሔር ኃይል አጠፋቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ለእስራኤል ልጆች ሁሉ ርስትን አካፈላቸው፤ ለሌዊ ነገድ ልጆችም ፵፰ ከተሞችን ሰጣቸው፡፡

ነቢዩ ኢያሱም ዕድሜው መቶ ሃያ በሆነው ጊዜ ሕዝቡን ሰብስቦ የኦሪትን ሕግ እንዲጠብቁና አምልኮተ እግዚአብሔርም እንዲጸኑ ትእዛዞቹንም እንዳይተላለፉ አዘዛቸው፡፡ እንዲህም አላቸው፤ ‹‹የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። አባቶቻችሁ፥ የአብርሃምና የናኮር አባት ታራ፥ አስቀድመው በወንዝ ማዶ ተቀመጡ፤ ሌሎችንም አማልክት አመለኩ።አባታችሁንም አብርሃምን ከወንዝ ማዶ ወስጄ በከነዓን ምድር ሁሉ መራሁት፤ ዘሩንም አበዛሁ፥ ይስሐቅንም ሰጠሁት።ለይስሐቅም ያዕቆብንና ዔሳውን ሰጠሁት፤ ለዔሳውም የሴይርን ተራራ ርስት አድርጌ ሰጠሁት፤ ያዕቆብም ልጆቹም ወደ ግብፅ ወረዱ።ሙሴንና አሮንንም ላክሁ፥ በመካከላቸውም እንዳደረግሁ ግብፅን ቀሠፍሁ፤ ከዚያም በኋላ አወጣኋቸው።አባቶቻችሁንም ከግብፅ አወጣኋቸው፥ ወደ ባሕሩም ደረሳችሁ፤ ግብፃውያንም አባቶቻችሁን በሰረገሎችና በፈረሰኞች እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ አባረሩአቸው።ወደ እግዚአብሔርም በጮኹ ጊዜ በእናንተና በግብፃውያን መካከል ጨለማ አደረገ፥ ባሕሩንም መለሰባቸው፥ አሰጠማቸውም፤ ዓይኖቻችሁም በግብፅ ያደረግሁትን አዩ፤ በምድረ በዳም ብዙ ጊዜ ተቀመጣችሁ።እኔም በዮርዳኖስ ማዶ ወደ ተቀመጡበት ወደ አሞራውያን ምድር አመጣኋችሁ፤ ከእናንተም ጋር ተዋጉ፥ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋችሁ፥ ምድራቸውንም ወረሳችሁ፤ ከፊታችሁም አጠፋኋቸው።የሞዓብም ንጉሥ የሴፎር ልጅ ባላቅ ተነሥቶ ከእስራኤል ጋር ተዋጋ፤ እንዲረግማችሁም የቢዖርን ልጅ በለዓምን ልኮ አስጠራው። እኔ ግን በለዓምን መስማት አልወደድሁም፤ እርሱም ፈጽሞ ባረካችሁ፥ እኔም ከእጁ አዳንኋችሁ። ዮርዳኖስንም ተሻገራችሁ፥ ወደ ኢያሪኮም መጣችሁ፤ የኢያሪኮም ሰዎች፥ አሞራዊው፥ ፌርዛዊው፥ ከነዓናዊው፥ ኬጢያዊው፥ ጌርጌሳዊው፥ ኤዊያዊው፥ ኢያቡሳዊው ተዋጉአችሁ፤ አሳልፌም በእጃችሁ ሰጠኋቸው።በፊታችሁም ተርብ ሰደድሁ፥ በሰይፍህም በቀሥትህም ሳይሆን ሁለቱን የአሞራውያንን ነገሥታት ከፊታችሁ አሳደዳቸው። ያልደከማችሁበትንም ምድር፥ ያልሠራችኋቸውንም ከተሞች ሰጠኋችሁ፥ ተቀመጣችሁባቸውም፤ ካልተከላችኋቸውም ከወይንና ከወይራ በላችሁ። አሁንም እግዚአብሔርን ፍሩ፥ በፍጹምም በእውነተኛም ልብ አምልኩት፤ አባቶቻችሁም በወንዝ ማዶ በግብፅም ውስጥ ያመለኩአቸውን አማልክት ከእናንተ አርቁ፥ እግዚአብሔርንም አምልኩ።እግዚአብሔርንም ማምለክ ክፉ መስሎ ቢታያችሁ፥ አባቶቻችሁ በወንዝ ማዶ ሳሉ ያመለኩአቸውን አማልክት ወይም በምድራቸው ያላችሁባቸውን የአሞራውያንን አማልክት ታመልኩ እንደ ሆነ፥ የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ። እኔና ቤቴ ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን።››

ሕዝቡም መልሰው እንዲህ አሉ። ‹‹እግዚአብሔርን ትተን ሌሎች አማልክትን ማምለክ ከእኛ ይራቅ፤ እኛንና አባቶቻችንን ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣን፥ በዓይናችንም ፊት እነዚያን ታላላቅ ተአምራት ያደረገ፥ በሄድንባትም መንገድ ሁሉ ባለፍንባቸውም አሕዛብ ሁሉ መካከል የጠበቀን፥ እርሱ አምላካችን እግዚአብሔር ነውና። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ፥ በምድሪቱም የተቀመጡትን አሞራውያን ከፊታችን አሳደደ፤ ስለዚህ እርሱ አምላካችን ነውና እግዚአብሔርን እናመልካለን።››

ነቢዩም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹እርሱ ቅዱስ አምላክ ነውና፥ እርሱም ቀናተኛ አምላክ ነውና እግዚአብሔርን ማምለክ አትችሉም፤ መተላለፋችሁንና ኃጢአታችሁን ይቅር አይልም።እግዚአብሔርን ትታችሁ እንግዶችን አማልክት ብታመልኩ፥ መልካም ካደረገላችሁ በኋላ ተመልሶ ክፉ ነገር ያደርግባችኋል፥ ያጠፋችሁማል።››

የእስራኤልም ሕዝብ በአንድነት ነቢዩ ኢያሱን ‹‹እንዲህ አይሁን፤ ነገር ግን እግዚአብሔርን እናመልካለን›› አሉት። ኢያሱም ሕዝቡን  ‹‹እንድታመልኩት እናንተ እግዚአብሔርን እንደ መረጣችሁ፤ በራሳችሁ ላይ ምሥክሮች ናችሁ›› አላቸው፤ እነርሱም ‹‹ምስክሮች ነን›› አሉ። እርሱም ‹‹አሁን እንግዲህ በመካከላችሁ ያሉትን እንግዶች አማልክት አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እስራኤል አምላክ ወደ እግዚአብሔር አዘንብሉ›› አላቸው። ሕዝቡም ኢያሱን ‹‹አምላካችንን እግዚአብሔርን እናመልካለን፥ ድምፁንም እንሰማለን›› አሉት። በዚያም ቀን ኢያሱ ከሕዝቡ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፥ በሴኬምም ሥርዓትና ፍርድ አደረገላቸው።

ነቢዩ ኢያሱም ይህን ቃል ሁሉ በእግዚአብሔር ሕግ መጽሐፍ ጻፈ፤ ታላቁንም ድንጋይ ወስዶ በእግዚአብሔር መቅደስ አጠገብ ከነበረችው ከአድባሩ ዛፍ በታች አቆመው። ኢያሱም ለሕዝቡ ‹‹እነሆ፥ የተናገረንን የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉ ሰምቶአልና ይህ ድንጋይ ይመሰክርብናል፤ እንግዲህ አምላካችሁን እንዳትክዱ ይህ ምስክር ይሆንባችኋል›› አላቸው። ኢያሱም ሕዝቡን በእያንዳንዱ ወደ ርስቱ ሰደደ።

ከዚህም በኋላ የእግዚአብሔር ባሪያ የነዌ ልጅ ኢያሱ ዕድሜው መቶ ዐሥር ዓመት ሲሆነው በሰኔ ፳፭ በሰላም ዐረፈ፤ በተራራማውም በኤፍሬም ሀገር በገዓስ ተራራ በሰሜን ባለችው በርስቱ ዳርቻ በተምናሴራ ከኤሞር ልጆች በመቶ በጎች በገዛው ናብሎስ በሚባል ቦታ ተቀበረ፡፡ (ኢያ.፳፬፥፪-፴)

እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ኢያሱ ጸሎት ይማረን፤ አሜን!

ምንጭ፡- ፹፩ መጽሐፍ ቅዱስ፣ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ፣  የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቁጥር ፩