ሆሣዕና በአርያም

በመዝሙርና ሥነ ጥበባት ክፍል

ሚያዚያ ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ሆሣዕና በአርያም . . . ሆሣዕና በአርያም

ለዳዊት ልጅ መድኃኔ ዓለም

በጌታ ስም የሚመጣ

ከምርኮ ሀገር ከባርነት የሚያወጣ

ብሩክ ቅዱስ የአበው ተስፋ

የመርገም ጨርቅ ባንተ ጠፋ

የነቢያት ትንቢት የጽድቃቸው ዜና

የሕይወት እንጀራ የእስራኤል መና

ቃል ከሥጋ ጋራ በተዋሕዶ ጸና

በኪሩቤል ግርማ የሚቀመጥ አልፋና ኦሜጋ

በቀስተ ደመና ላይ ዙፋኑን የዘረጋ

በእሳት መድረክ ላይ የሚመላለስ

በሱራፌል . . . የሚቀደስ  . . . የሚወደስ

ሰባት መቅረዝ በፊትህ የሚበራ

መንጦላዕትህ ብርሃን ማደሪያህ የሚያስፈራ

በልዩ ልዩ ቅኔ በመለከት ድምፅ

በመብረቅና በነጐድጓድ የምትገሥፅ

የልብስህ ዘርፍ ቤተመቅደሱን የሞላ

የኃያላን ኃያል ባለብዙ ሺህ ሠረገላ

በሰማያት የተከለልክ የተጋረድክ በደመና

በምድር ላይ ተመላለስክ ታየህ በጎዳና

አላዋቂ . . . በማስተዋሉ ተደገፈ . . . በጥበቡ አመነ

የዚህ ዓለም እውቀት ግን . . . ከንቱ ሆነ

በማኅበር በጉባኤ መካከል ተገለጠ

የዋህ ሆኖ የጽዮን ልጅ በአህያ ላይ ተቀመጠ

ከሕፃናት ከሚጠቡ አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ

ከንፈሮቻችንን ለምስጋና አንደበታችንን ለዝማሬ ከፈትህ

እኛም ልጆችህ ይዘን ዝንጣፊ ዘንባባ

በሐሴት ተመልተን አሸብርቀን እንደ አበባ

የሰላም ንጉሥ መድኃኔዓለም

ስለ ስምህ ተቀኝተናል ሆሣዕና በአርያም፡፡

በማደሪያህ በጸባኦት ባይቻለን አንተን ማየት

ልትባርከን በበረከት ልትፈውሰን በምሕረት

የአዳም ልጅ የእግዚአብሔር ልጅ ልትጨበጥ ልትዳሰስ

በአህያ ላይ ተቀምጠህ አገኘንህ ቤተ መቅደስ፡፡