፻፴፬ ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ ላይ በቅዱስነታቸው የተላለፈ አባታዊ መልእክት
፻፴፬ ኛው የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ምልአተ ጉባኤ ላይ በቅዱስነታቸው የተላለፈ አባታዊ መልእክት
ሚያዝያ ፳፳/፳፻፲፰ ዓ.ም
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ የግንቦት ርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
መልእክተ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ ኣምላክ ኣሜን!
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፤
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ ኣባላት፣
በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦
ማሕየዊት በምትሆን ሞቱ ሰማያውያንና ምድራውያንን ያስታረቀ፣ በቅድስት ትንሣኤውም የሙታንን ሕይወት በተስፋ ያለመለመ ጌታችን፣ ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ እንኳን ለዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አደረሰን አደረሳችሁ!
“እስመ ተዋለጠ እግዚአብሔር ዓለመ በክርስቶስ አናኅስዮ ኃጢአቶሙ ወኢነጺሮ ጌጋዮሙ፤ ወረሰየ ላዕሌነ ቃለ ሥምረቱ፤ ወወሀበነ መልእክተ ሣህሉ፤ እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና በደላቸውን አይቈጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ” (2ኛቆሮ. 5፥19)
የእግዚአብሔርም ልጅ፣ የሰውም ልጅ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሰው ሆኖ ሲገለጽ ግልጽ የሆነ ዓላማና ግብ እንደነበረው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤ እርሱም በሰማይም፣ በምድርም ያሉትን በሙሉ ማስታረቅ፣ ማገናኘትና አንድ ማድረግ ነበረ፤
ጌታችን ይህንን ሲያደርግ ሰማያውያኑንና ምድራውያኑን የለያየውን ምክንያት በማስወገድ ነው፤ የመለያየቱ ምክንያት ክፉ ኅሊና አምጦ የወለደው በደልና እርሱን ተከትሎ የተከሠተው ኃጢኣት ነበረ፤ በኃጢኣት ምክንያት የገባው ሞት ደግሞ የቅጣቱ ማሳያ ፍርድ ነበረ።
የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በፈጸሙት ስሕተት መነሻነት ምድርንና ምድራውያንን ለከባድ ቅጣትና መርገም የዳረገው ይህ መለያየት ለሰማያውያኑም ተርፎአል።
ምክንያቱም መለያየቱ በእግዚአብሔርና በሰው፣ በመላእክትና በሰው፣ በሰውና በሰው፣ በነፍስና በሥጋ ጭምር የጥል ግድግዳን ገንብቶ እስከ ክርስቶስ ዕለተ ስቅለት መዝለቁን በቅዱስ መጽሐፍ የምናውቀው ስለሆነ ማለት ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
ቀዳማዊና ዘላለማዊ የሆነው ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ሰብእናችንን ተዋሕዶ በዚህ ዓለም የተገለጸው ሰማያውያንንና ምድራውያንን የለያየው የጥል ግድግዳን ለማፈራረስ ነው።
ለመለያየት ምክንያት የሆነችውን ኃጢኣት በሰውነቱ በመቅጣት የሕግን ትእዛዝ ከፈጸመ በኋላ የዕርቁን ተግባር በወሳኝ መልኩ አከናውኖታል።
በክርስቶስ ቤዛነት የሆነው ይህ ዕርቅ በእግዚአብሔር ዘንድ እጅግ የተወደደ ነበረና እሱ ራሱ በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር አስታረቀ።
ለዚህም ነው ተበዳይ እርሱ፣ ቤዛዊ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበው እርሱ፣ ኣስታራቂ እርሱ፣ ታራቂ እርሱ ሆኖ የምናገኘው፤ ለእርሱ የሚሳነው ነገር የለምና ለእኛ ግር የሚል ቢመስልም ለእርሱ ቀላል ነበረ።
በዚህ የዕርቅ ተግባር ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክት፣ ሰውና ሰው፣ ነፍስና ሥጋ ታርቀው በይፋ ተገናኙ፤ በኅብረትና በአንድነትም መኖር ቻሉ፤ በቀኙ ለተሰቀለው ወንበዴ “ዛሬውኑ ከእኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” የሚለው ቃለ ምሕረትና “አባት ሆይ፥ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” የሚለው ቃለ አማኅፅኖ የዕርቁ፣ የግንኙነቱና የኣንድነቱ ማሳያ ኣስረጅ ናቸው።
ስቅለተ ክርስቶስ ነፍሶቻችን ወደ ግዞት ቤት ሳይሆን ወደ ገነት እንዲገቡ፣ የሚቀበላቸውም ራሱ እግዚአብሔር እንዲሆን ያስቻለ ታላቅ መለኮታዊ ፍጻሜ ነው።
እኛ “ክርስቶስ መድኃኒታችን ነው፤ አድኖናል” ብለን በፍጹም ልባችን አምነን የምንመሰክረው፣ እርሱም በመስቀል ላይ ውሎ “ሰላሜን ሰጠኋችሁ” በማለት በመስቀሉ ስላዳነን አጽናኝ መንፈስ ቅዱስንም ስለላከልን ነው።
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
የድኅነታችንና የሰላማችን መሠረት የሆኑትን የክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ለዓለም ማኅበረሰብ የማብሰርና የማሥረጽ ተግባር የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቍጥር አንድ ተልእኮ ነው፤
ነገረ ሞቱና ነገረ ትንሣኤው በአስተውሎት፣ በጥልቀትና በተመሥጦ ስናስተምር በውስጡ የምናገኘው የዕርቅ፣ የሰላምና የኣንድነት ምስጢር ነው፤
እንደ እውነቱ ከሆነ እኛ የክርስቶስ መልእክተኞች እንደ ቃሉ ራሳችንን ክደን በሚጠበቀው መጠን ተልእኮኣችንን መወጣት ብንችል ኖሮ፣ ኣሁን በዓለማችን የተፈጠረው መለያየትና ግጭት አይኖርም ነበር።
ችግሩን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ባንችልም በእጅጉ መቀነስና ዓቅሙን ማዳከም እንችል ነበር፤ ነገር ግን ተልእኮአችንን በአግባቡ አለመወጣት ኣንድ ነገር ሆኖ የዓለሙ መሣሪያ ሆነን መገኘታችን “በዕንቅርት ላይ…” ሆኖ ይስተዋላል።
ይሁንና አሁንም ሕዝቡን ወደ አንድነት፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ ሰላም፣ ወደ ዘላቂ የጋራ ጥቅምና ወደ ፈሪሀ እግዚአብሔር ማምጣት የጉባኤያችን ዐቢይ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ እነዚህ ካሉ የምናጣውም ሆነ የሚያመልጠን የለምና ነው፤
ሀገርን በኀላፊነት ተረክባችሁ በላዕላዊ፣ በማእከላዊና በታሕታዊ መዋቅር የምትገኙ፣ እንደዚሁም አማራጭ ሐሳብ አለን ብላችሁ የምትንቀሳቀሱ ልሂቃነ ሀገር ፣ ሁላችሁም እግዚአብሔርን ከሚያውቅ፣ ከሚያመልክና ከሚፈራ ሕዝብ የተገኛችሁ ናችሁና በልባችሁ እግዚአብሔርን ፍሩ፤ ድምፁንም ስሙ፤ የእርሱ ገንዘብ በሆኑ ፍጡራንም አትጨክኑ፤ ሰውን መያዝ የሚቻለው ኅሊናን በመርታት እንጂ በሌላ አይደለምና፣
የሕዝቡን ፍላጎትና የልብ ትርታ በሚገባ አዳምጡ፤ ሕዝቡ የሚፈልገው በአንድነትና በእኩልነት መኖር፣ በሰላም ወጥቶ መግባት፣ ፍትሕን ማስፈን፣ ለኑሮው የሚበቃ ምጣኔ ሀብትን ማግኘት፣ የእምነት ነፃነትና እኩልነት መረጋገጥ የመሳሰሉት ናቸው።
ሕዝቡ እነዚህ ከተሟሉለት ተደመጠ ማለት ነው፤ ከተደመጠ ደግሞ እርሱም በበኩሉ ያደምጣል፤ ይከተላልም።
ስለሆነም ለሁሉም ልጆቻችንና ወገኖቻችን የምናስተላልፈው ወቅታዊ ጥሪ ሁሉንም ችግሮቻችንን በሰላም ብቻ ለመፍታት ተባበሩ የሚል ነው፤ ከዚህ ውጭ የሚደረገው አማራጭ ሁሉ ለዘላቂ ሰላማችን አይበጅም እንላለን።
በመጨረሻም፦
በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የሚካሄደው ዓመታዊው የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት የተጀመረ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑና ለመላው ኢትዮጵያውያን እናበሥራለን!!!
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤
አሜን!!!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ
ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤
ሚያዝያ ፳፰ ቀን ፳፻፲፰ዓ.ም
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
ዘገባው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት ነው።
