ሰማዕታት ቅድስት ኢየሉጣ እና ሕፃን ቂርቆስ

ቅድስት ኢየሉጣ በሮም ግዛት በሚገኝ አንጌቤን በሚባል አገር በፈሪሃ እግዚአብሔር፣ በክርስትና ሃይማኖት እና በበጎ ምግባር ጸንታ ትኖር የነበረች ደግ ሴት ነበርች፡፡ በሥርዓት ያሳደገችው ቂርቆስ የሚባል ሕፃን ልጅም ነበራት፡፡ ይህቺ ቅድስት የዘመኑን አረማዊ መኰንን እለእስክንድሮስን በመፍራቷ ከልጇ ጋር ከሮም ወደ ጠርሴስ በተሰደደች ጊዜ መኰንኑ እነርሱ ከሚገኙበት አገር ገብቶ ክርስቲያኖችን እያሳደደ መግደል ጀመረ፡፡ የንጉሡ ወታደሮችም እግዚአብሔርን እንዲክዱ፣ ለጣዖት እንዲሰግዱ ቅድስት ኢየሉጣንና ቅዱስ ቂርቆስን አስፈራሯቸው፡፡ ቅዱሳኑ ግን ሃይማኖታቸውን ለመለወጥ ፈቃደኛ አልሆኑም ነበር፡፡ በዚህም መኰንኑ ተቈጥቶ በዓይንና በአፍንጫቸው ውስጥ ጨውና ሰናፍጭ በመጨመር፤ በጋሉ የብረት ችንካሮች በመቸንከርና መላ ሰውነታቸውን በመብሳት በብዙ ዓይነት መሣሪያ አሠቃያቸው፡፡ እግዚአብሔርም የጋሉ ብረቶችን እንደ ውኀ ያቀዘቅዝላቸው፤ ሥቃያቸውንም ያቀልላቸው ነበር፡፡

በሌላ ጊዜም በገመድ አሳሥሮ ንጉሡ ሲያስጨንቃቸው ከቆየ በኋላ ራሳቸውን ከቆዳቸው ጋር አስላጭቶ እሳት አነደደባቸው፡፡ ዳግመኛም ከትከሻቸው እስከ እግራቸው ድረስ በሚደርሱ ችንካሮች ቸነከራቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ ከሥቃያቸው አድኗቸዋል፡፡ አሁንም ቀኑን ሙሉ በልዩ ልዩ የሥቃይ መሣሪያዎች ቢያስጨንቃቸውም የእግዚአብሔር ኃይልና የቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት አልተለያቸውም ነበርና ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰባቸውም፡፡ እንደ ገናም በመጋዝ ሰንጥቀው በብረት ምጣድ በቆሏቸው ጊዜ ጌታችን ከሞት አነሣቸውና በመኰንኑ ፊት ድንቅ ተአምራትን አደረጉ፡፡ ከተአምራቱ መካከልም ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ የመኰንኑን ጫማ በጸሎት ወደ በሬነት እንዲቀየር ማድረጉ ተጠቃሽ ሲሆን፣ መኰንኑ በተአምራቱ ተቈጥቶ የቅዱስ ቂርቆስን ምላስ አስቈርጦታል፤ ጌታችንም ምላሱን አድኖለታል፡፡

ዳግመኛም በፈላ የጋን ውኀ ውስጥ ቅዱሳን ቂርቆስና ኢየሉጣን ሊጨምሯቸው ሲሉ ቅድስት ኢየሉጣ በፈራች ጊዜ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ ያረጋጋትና በተጋድሎዋ እንድትጸና ወደ እግዚአብሔር ይጸልይላት ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ተያይዘው ወደ ጋኑ ውስጥ ገቡ፡፡ ውኀውም እንደ ውርጭ ቀዘቀዘ፡፡ ደግሞም ወታደሮቹ መንኰራኵር ባለበት የብረት ምጣድ ውስጥ አስገብተው ሥጋቸው እስኪቈራረጥ ድረስ በጎተቷቸው ጊዜ ቅዱስ ገብርኤል አድኗቸዋል፡፡ በመጨረሻም ከእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ተቀብለው በመንፈቀ ሌሊት አንገታቸውን ተቈርጠው በሰማዕትነት ጥር ፲፭ ቀን ዐርፈዋል፡፡ እስከ ሞት ድረስ በታመኑበት ተጋድሏቸውም ከእግዚአብሔር ዘንድ የሕይወትን አክሊል ተቀብለዋል፡፡

ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ የዚህን ዓለም ጣዕም በመናቅ ‹‹ሞት ቢሆን÷ ሕይወትም ቢሆን÷ መላእክትም ቢሆኑ÷ ግዛትም ቢሆን÷ ያለውም ቢሆን÷ የሚመጣውም ቢሆን÷ ኃይላትም ቢሆኑ÷ ከፍታም ቢሆን÷ ዝቅታም ቢሆን÷ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ እግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ›› (ሮሜ. ፰፥፴፰) በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ቃል በተግባር በማሳየት ለክርስቶስ ፍቅር ሲሉ ራሳቸውን ለመከራና ለሞት አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ ቅዱሳኑ ተጋድሏቸውን እስኪፈጽሙ ድረስም ቅዱስ ገብርኤል አልተለያቸውም፡፡ በቅዱስ ገብርኤል ተራዳኢነት ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ ብቻ ሳይሆኑ ዐስራ አንድ ሽህ አራት ሰዎች ሰማዕታት ሆነዋል፡፡

እኛም በሃይማኖታችን ምክንያት መከራ ባጋጠመን ጊዜ ቈራጥ ልብ ያለው ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ‹‹እናቴ ሆይ አትፍሪ›› እያለ እናቱን በመከራ እንድትጸና እንዳረጋጋትና ለሰማዕትነት እንድትበቃ እንዳደረጋት ሁሉ፣ ዘለዓለማዊውን የእግዚአብሔርን መንግሥት በአንድነት ለመውረስ እንድንችል አይዞህ! አይዞሽ! አትፍራ! አትፍሪ›› በመባባል በዚህ ዓለም የሚገጥመንን መከራ ታግሠን፣ እስከ ሞት ድረስ በሃይማኖታችን ጸንተን መኖር ይገባናል፡፡ ክርስትና ለብቻ የሚጸደቅበት መንገድ ሳይሆን በጋራ ዋጋ የሚያገኙበት የድኅነት በር ነውና፡፡ ከዚሁ ሁሉ ጋርም ቅዱስ ቂርቆስንና ቅድስት ኢየሉጣን የተራዳው የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ገብርኤል በአማላጅነቱ እንዲጠብቀን ‹‹በተአምኖ ንሴፎ ትንባሌ ዚአከ መዓልተ ወልሊተ፤ በእግዚአብሔር ታምነን በቀንም በሌሊትም የአንተን ልመና ተስፋ እናደርጋለን›› እያልን ዘወትር ልንማጸነው ያስፈልጋል፡፡ እርሱ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር በተሰጠው ቃል ኪዳን መሠረት ከሚደርስብን ልዩ ልዩ መከራና ሥቃይ ያድነናልና፡፡ ‹‹የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሠፍራል፤ ያድናቸውማል›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (መዝ. ፴፬፥፯)፡፡ ይህን እንድናደርግም የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ የቅዱስ ገብርኤል፣ ቅድስት ኢየሉጣ እና ቅዱስ ቂርቆስ ጸሎታቸው፣ ምልጃቸው ይጠብቀን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር