ጾም ምንድን ነው?
…በመ/ር ቅዱስ ያሬድ…
ጥያቄ፡- የጾምን ምንነትና ዓይነቶቹን ጠቅለል አድርገው ቢገልጹልን?
መምህር ቅዱስ ያሬድ፡- በመጀመሪያ ጾም ‹‹ጾመ›› ጾመ /ጦመ/ ታቀበ፣ ታረመ፣ ተወ፣ ተከለከለ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሃይማኖት ምክንያት ምግብና መጠጥ መተው፤ ወይም ከምግብና ከመጠጥ መከልከል፤ ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከክፋትና ሥጋን ደስ ከሚያሰኝ ነገር ሁሉ መታቀብና መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾም በታወቀው ዕለትና ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው /አስ. 4፥16፤ ዳን.10፥2፤ ፍት. መን. አን 15/፡፡
በተጨማሪም ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት የምትጠቅም የስሜት ልጓም፤ እንዲሁም ኃይለ ፍትወትን የምናደክምባት መሣሪያ ናት፡፡ ‹‹ጾም ትፌውስ ቍስለ ነፍስ፤ ወታፀምም ኩሎ ፍትወታተ ዘሥጋ፡፡ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና፤ ጾም የነፍስ ቁስልን ታደርቃለች፤ ተድላ ሥጋን ታጠፋለች፣ ለወጣቶች ርጋታን /ጭምትነትን/ ታስተምራለች» እንዳለ /ቅዱስ ያሬድ/፡፡ በሌላ በኩል ጾም ደካማው ሥጋ በነፍስ ላይ እንዳይሠለጥን የተሠራ ድንበር ነው፡፡ ምጽዋት በነዳያን በኩል የምታልፍ የገንዘብ ግብር እንደ ሆነች ሁሉ ጾምም ለአምላካችን ለንጉሠ ሰማይ ወምድር የምትቀርብ የሥጋ ግብር ናት፡፡ ‹‹ጾምሰ ጸባሕተ ሥጋ ውእቱ፤ በከመ ምጽዋት ጸባሕተ ንዋይ ይእቲ፤ ምጽዋት በነዳያን በኩል የምታልፍ የገንዘብ ግብር እንደ ሆነች ሁሉ ጾምም ለአምላካችን የምትቀርብ የሥጋ ግብር ናት» እንዲል /ፍት. መን. አንቀጽ 15/፡፡