ቅዳሜ

ቅዳሜ

ከመምህር አዲሱ በዛብህ

የትንሣኤ ሳምንት ቅዳሜ ቅዱሳት_አንስት_ይባላል።

በወንጌል ተጽፎ እንደምናነበው ፍቅሩን በማሰብ ጨለማውን ሳይፈሩ ወደ መቃብር ስለመጡት መግደላዊት ማርያም እና ማርያም ባውፍልያ በስፋት ቤተክርስቲያን እንድናስብ ስለምታስተምረን ቅዱሳት አንስት ተብሏል።

ወንጌሉ ስለዚህ ዕለት እንዲህ ብሎ ይገልጻል: – “ከሳምንቱም በፊተኛው ቀን መግደላዊት ማርያም ገና ጨለማ ሳለ ማለዳ ወደ መቃብር መጣች ድንጋዩም ከመቃብሩ ተፈንቅሎ አየች።እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ፦ ጌታን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው።

“ስለዚህ ጴጥሮስና ሌላው ደቀ መዝሙር ወጥተው ወደ መቃብሩ ሄዱ። ሁለቱም አብረው ሮጡ፤ ሌላው ደቀ መዝሙርም ከጴጥሮስ ይልቅ ፈጥኖ ወደ ፊት ሮጠና አስቀድሞ ከመቃብሩ ደረሰ፤ ዝቅም ብሎ ቢመለከት የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ነገር ግን አልገባም። ስምዖን ጴጥሮስም ተከትሎት መጣ ወደ መቃብሩም ገባ፤ የተልባ እግሩን ልብስ ተቀምጦ አየ፥ ደግሞም በራሱ የነበረውን ጨርቅ ለብቻው በአንድ ስፍራ ተጠምጥሞ እንደ ነበረ እንጂ ከተልባ እግሩ ልብስ ጋር ተቀምጦ እንዳልነበረ አየ። በዚያን ጊዜ አስቀድሞ ወደ መቃብር የመጣውም ሌላው ደቀ መዝሙር ደግሞ ገባ፥ አየም፥ አመነም፤ ከሙታን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው የሚለውን የመጽሐፉን ቃል ገና አላወቁም ነበርና። ደቀ መዛሙርቱም ወደ ቤታቸው ደግሞ ሄዱ።

“ማርያም ግን እያለቀሰች ከመቃብሩ በስተ ውጭ ቆማ ነበር። ስታለቅስም ወደ መቃብር ዝቅ ብላ ተመለከተች፤ ሁለት መላእክትም ነጭ ልብስ ለብሰው የኢየሱስ ሥጋ ተኝቶበት በነበረው አንዱ በራስጌ ሌላውም በእግርጌ ተቀምጠው አየች።

“እነርሱም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም፦ ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው። ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።

“ኢየሱስም፦ አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት።

“እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሏት፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው።

“ኢየሱስም፦ ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ፦ ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም፦ መምህር ሆይ ማለት ነው።

“ኢየሱስም፦ ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ፦ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዐርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።

መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።” (ዮሐ. ፳፥፩-፲፰)

የሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት ስም ዝርዝራቸውንና መታሰቢያ ቀናቸው፤

ተ.ቁስምየመታሰቢያ ቀናቸው
1  ኤልሳቤጥ            የካቲት 16 
2  ሐናመስከረም 7 ቀን
3  ቤርዜዳን ወይም ቤርስትታኀሣሥ 10 ቀን
4  መልቲዳን ወይም ማርናጥር 4 ቀን 
5 ሰሎሜግንቦት 25 ቀን    
6 ማርያም መግደላዊትነሐሴ 6 ቀን
7 ማርያም እንተ ዕፍረት እኅተ አልዓዛርየካቲት 6 ቀን
8 ሐና ነቢይትየካቲት 20 እና ጥቅምት 6 ቀን
9 ማርያም እሞሙ ለደቂቀ ዘብዴዎስጥር 18 ቀን
10 ሶፍያ (በርበራ)ጥር 30 ቀን
11 ዮልያና (ዮና)ኅዳር 18 ቀን
12 ሶፍያ (መርኬዛ)ጥር 30 ቀን      
13 አውጋንያን (ጲላግያ)ጥቅምት 11 ቀን
14 አርሴማግንቦት 11 ቀን         
15 ዮስቲናጥር 30 ቀን              
16 ጤግላነሐሴ 6 ቀን                
17 አርኒ (ሶፍያ)ኅዳር 10 ቀን    
18 ዕሌኒጥር 29 ቀን                
19 ኢዮጰራቅሊያ መጋቢት 26 እና ነሐሴ 2 ቀን  
20 ቴዎክላ (ቴኦድራ)ጥር 4 ቀን        
21 ክርስቲያና (አጥሩኒስ)ኅዳር 18       
22 ጥቅሞላ (አሞና)ጥር 30 ቀን         
23 ጲስጥር 30 ቀን
24 አላጲስ                            ጥር 30 ቀን
25 አጋጲስ                  ጥር 30 ቀን
26 እርሶንያ (አርኒ)           ጥር 30 ቀን
27 ጲላግያጥር 30 እና ጥቅምት 11 ቀን   
28 አንጦልያ (ሉክያ)የካቲት 25 ቀን      
29 አሞን (ሶፍያ)ጥር 15 እና ነሐሴ 3 ቀን         
30 ኢየሉጣነሐሴ 6 ቀን                       
31 መሪናሐምሌ 27 ቀን           
32 ማርታ እኅተ አልዓዛር                                   ጥር 18  እና ግንቦት 27 ቀን 
33 ማርያም የማርቆስ እናትጥር 30 ቀን
34 ሣራ (ሶፍያ) የይሁዳ እናትጥር 30 ቀን    
35 ዮሐና (ዮላና) የኩዛ ሚስትታኅሣሥ 26 ቀን  
36 ሶስናግንቦት 12 ቀን
ምንጭ ነገረ ቅዱሳን

ከቅዱሳት አንስት ምን እንማራለን?

እነዚህ “ቅዱሳት አንስት” በታሪክ ብቻ የሚታወቁ ሰዎች አይደሉም፤ ዛሬም ለእኛ የሕይወት መንገድ የሚያሳዩ መምህራን ናቸው።

📖 እነሱ ጌታን ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ ተከትለው ነበር፤ ብዙዎች በፍርሃት ሲሸሹ እነሱ ግን በመስቀል ሥር ቆመው ታማኝነታቸውን አሳዩ።

ይህ የሚያስተምረን —እውነተኛ እምነት በጥሩ ጊዜ ብቻ ሳይሆን፤ በመከራ ጊዜ እንደሚፈተን ያስተምረናል።

📖 እነሱ በፍቅር ተነሥተው ወደ መቃብር ሄዱ፤ “ማን ድንጋዩን ያነሳልናል?” ብለው ወደ ኋላ አልተመለሱም።

ይህ የሚያስተምረን —ፍቅር ፍርሃትን እንደሚያሸንፍ። እግዚአብሔርን በእውነት ከወደድን ምንም ከባድ ነገር እንኳን አያስቆመንም።

📖 እነሱ በትሕትና አገልግለዋል፤ ስማቸው እንዲታወቅ አልፈለጉም። ነገር ግን እግዚአብሔር ከፍ አደረጋቸው፤ የትንሣኤን ዜና በመጀመሪያ ሰሙ ፣ ነጋሪዎችም ሆኑ።

         ይህ የሚያስተምረን —ትሕትና ወደ ክብር እንደሚመራ ያሳያል።

📖 እነሱ በሐዘን ወደ መቃብር ሄዱ፤ በደስታ ተመለሱ።

          ይህም የሚያሳየን —ከመስቀል በኋላ ሁሌ ትንሣኤ እንዳለ ነው።

📖 ሴቶች በቤተክርስቲያን አገልግሎት ያላቸው ሱታፊ እጅግ ትልቅ እንደሆነ ያስገነዝበናል። አምላካችን በደቀ መዛሙርቱ ላይ ወድቆ የነበረው የኃዘንና የተስፋ መቁረጥ ጭጋግ በትንሣኤው ዜና እንዲገለጥ ያደረገው በነዚህ ቅዱሳት አንስት ነው። ይህንን የጌታ አብነት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀብላ ዛሬም ቤተ ክርቲያን ለሴቶች ተገቢውን ቦታ ሰጥታ ታከብራቸዋለች፤ እነርሱንም በሚመለከት የአገልግሎት ዘርፍ ታሰማራቸዋለች፤ ከአምላክ እናት ከድንግል ማርያም ወላዲተ አምላክ፤ የአምላክ እናት ከፈጣሪ በታች ከፍጥረታት ሁሉ በላይ ብላ ስሟን ከፍ በማድረግ ጀምራ፣ ሌሎች በቁጥር የናይወሰኑ በርካታ ሴቶችን በቀኖና ቅዱሳት በማለት ቀንና በአምላክ ቤት ለዘለዓለም የማይጠፋ ስም ሰጥታ ታከብራቸዋለች፤ ስለዚህም በዓለም ላይ ከአሥራ ስድስተኛው ምዕት ዓመት ጀምሮ የተነሳው ፌሚኒስት ንድፈ ሐሳብ፤ (Feminist theory) ቅድስት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንን ሊገዳደር አልቻለም።

በመሆኑም ይህቺን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አብነት አድርጋችሁ ሴቶችን እያሳተፋችሁ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የምታገለግሉ የግቢ ጉባኤ ልጆች የበለጠ አጠንክራችሁ እንድታስቀጥሉት ደግሞ እመክራለሁ።

ስለዚህ እንዳጠቃላይ ክርስቲያኖች የግቢ ጉባኤ ልጆች ሆይ ፦

– በመከራ ጊዜ አንሸሽ።

– በፍቅር እንኖር።

– በትሕትና እናገልግል።

– ተስፋችንን አንተው።

“ክርስቶስ ተነሥቷል!” — “በእውነት ተነሥቷል!” አሜን።

   ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር ይቆየን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *