“ዓይናቸውም ተከፈተ ዐወቁትም” (ሉቃ. ፳፬፥፴፩)
ከመምህር ተፈሪ መንገሻ
በክርስቶስ ትንሣኤ ብርሃን የምትመላለሱና በትንሣኤው ኃይል የታደሳችሁ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች፣ እንደምን ሰነበታችሁ? ይህ ሰሞን በቤተክርስቲያናችን ሥርዓት መሠረት የበዓለ ትንሣኤ ሦስተኛው እሑድ ሲሆን ይህም በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ ፳፬ ላይ የተመዘገበው “የኤማሁስ መንገደኞች” ድንቅ ምሥጢር የሚዘከርበት ሳምንት ነው።
በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የምናገኘው የሰው ልጅ ከጥርጣሬ ወደ እምነት፣ ከኀዘን ወደ ደስታ፣ እንዲሁም ከሞት ወደ ትንሣኤ የሚያደርገው ታላቅ የሕይወት ጉዞ ታሪክ ነው። ይህንን እንደሚከተለው እንመለከታለን።
➜ ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማሁስ፦ የሽሽትና የተስፋ መቁረጥ ጉዞ
ወደ ኤማሁስ የሚደረግ ጉዞ የሚጀምረው በሁለት ደቀ መዛሙርት የሽሽት ሕይወት መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል፤ “ከእነርሱም ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደምትርቅ ኤማሁስ ወደምትባል መንደር ይሄዱ ነበር” (ሉቃ. ፳፬፥፲፫) ኢየሩሳሌም የክርስቶስ የድኅነት ሥራው መከወኛ ማእከል፣ የተስፋው መፍለቂያና የትንሣኤው ከተማ ናት። በዕለተ ዓርብ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በደረሰው ሥቃይና ሞት ምክንያት በእነዚያ ደቀ መዛሙርት ልብ ውስጥ ኀዘንና ተስፋ መቁረጥ ስለነገሠ፣ ፊታቸውን ከኢየሩሳሌም አዙረው ወደ ኤማሁስ ሄዱ።
ኤማሁስ ማለት በሥጋዊ ትርጓሜው “የሞቀ ምንጭ” ማለት ቢሆንም፣ በመንፈሳዊ ትርጓሜው ግን የመሸሸጊያ፣ የብቸኝነትና “ነገሮች አልሆኑም” ብሎ የመቀበልና የተስፋ መቁረጥ ምሳሌ ናት። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እነሣለሁ” የሚለውን ቃል ችላ ብለው በቀቢፀ ተስፋ ኮብልለውበታልና።
ዛሬም ብዙዎቻችን በሕይወታችን ፈተና ሲገጥመን፣ ጸሎታችን ሳይመለስ ሲቀር ወይም እንደ ሀገርና እንደ ወገን ብሎም እንደ ቤተክርስቲያን መከራ ሲበዛብን፣ ፊታችንን ከእምነት አዙረን ወደ ዓለማዊ መጽናኛ፣ ጊዜያዊ የሞቀ መዝናኛ እንጓዛለን። በተለይም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የምትገኙ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች፦ በትምህርት ጫና፣ በብቸኝነትና በነገው ሕይወት ሥጋት ውስጥ ስትሆኑ፣ የኤማሁስ መንገድ የእናንተም መንገድ ይሆናል። ጌታ ግን በዛው በሸሸንበት መንገድ ላይ አብሮን ይጓዛል።
➜ ተስፋ የሚሰጥ የሕያው ክርስቶስ ትምህርት
ጌታ በመካከላቸው ተገኝቶ ስለ ምን እንደሚያወሩ በጠየቃቸው ጊዜ፣ “እኛስ እስራኤልን ይቤዣል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” እያሉ የልባቸውን ጭንቀት ነገሩት። (ሉቃ. ፳፬፥፳፩)
ይህ ዐረፍተ ነገር በውስጡ ትልቅ ትካዜን ይዟል። “ነበር” የሚለው ቃል ተስፋ መቁረጥን ይገልጻል። ዛሬም በሀገራችን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት፣ ብዙዎቻችን “ሀገራችን ሰላም ትሆናለች ብለን ተስፋ አድርገን ነበር”፣ “ሕይወታችን ይቃናል ብለን ተስፋ አድርገን ነበር” ወዘተ እያልን በኀዘን ፊት ለፊት እንቆማለን። ይህንንም ስንመለከተው ደቀ መዛሙርቱ የሚያወሩት ስለ “ሞተው” ኢየሱስ ነበር፤ አብሯቸው እየተጓዘ ያለው ግን በሥጋ ሞቶ የነበረው ሕያው የሆነው እርሱ ነው።
እኛም በችግራችን መሐል “እግዚአብሔር የት አለ?” ብለን ስንጠይቅ፣ እርሱ ጥያቄያችንን አብሮን እየሰማ መሆኑን ማወቅ አለብን። ጌታ ግን በዚያው በኀዘናቸው መሐል “እናንተ የማታስተውሉ፣ ነቢያትም የተናገሩትን ሁሉ ልባችሁ ከማመን የዘገየ” ብሎ ገሠጻቸው (ሉቃ. ፳፬፥፳፭) ይህ ተግሣፅ የጥላቻ ሳይሆን፣ ካለማወቅ ወደ ማወቅ የሚመልስ የአባትነት ተግሣፅ ነው።
“ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እርሱ በመጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን ተረጎመላቸው” (ሉቃ. ፳፬፥፳፯) እዚህ ጋር ነው ትልቁ ምሥጢር ያለው። ብሉይ ኪዳን ያለ ክርስቶስ ትርጉም አልባ፤ ፊደል ብቻ ሆኖ ይቀራል። ዛሬ በየግቢ ጉባኤያችሁ መጻሕፍትን ስታጠኑ፣ በጭንቅላታችሁ መረጃን ከመሰብሰብ ባለፈ ወደ ሕይወት ተግባር የማትቀይሩት ከሆነና በሕይወታችሁ በሚገጥማችሁ ቀላል ፈተና የምትንገዳገዱ ከሆነ፤ ዛሬ አንብባችሁ ሳይሆንላችሁ ቀርቶ ዝቅ ያለ ውጤት አምጥታችሁ ይህንን ወደሚያስረሳችሁ የምሽት ክለብ የምትሄዱ ከሆነ የኤማሁስ መንገደኞች እናንተ ናችሁ።
በመጻሕፍት ውስጥ ያለውን ለእኛ ተስፋ መቁረጥ መድኃኒት ሆኖ የተሰጠንን ማስተዋል ይገባናል። ያም መድኃኒት “ኢየሱስ ክርስቶስ” ነው።
➜ የልብ መቃጠልና የዓይን መከፈት
ጌታችን ያስተማራቸው ትምህርት በውስጣቸው ድንቅ ነገርን ፈጠረ። በኋላ ላይ “በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?” ተባባሉ (ሉቃ. ፳፬፥፴፪) ይህ የልብ መቃጠል የፍቅር እሳት ነው።
ቃለ እግዚአብሔር ሲሰማ፣ የልብ ዝገት ይለቃል፣ የኀዘን በረዶ ይቀልጣል። ውድ ወጣቶች በዚህ የትንሣኤ ዘመን ልባችሁ የሚቃጠለው በምን ይሆን? በዓለማዊ ዜና ነው ወይስ በቃለ እግዚአብሔር? በዩቲዩብና በሶሻል ሚዲያ ትርክት ነው ወይስ በወንጌል እውነት? እውነታው ግን ልባችሁ በቃሉ ካልተቃጠለ በዓለም ክፋት መቃጠሉ አይቀርም።
የኤማሁስ መንገደኞች ጌታን ለማቆየት “ከእኛ ጋር እደር” ብለው ለመኑት። ይህ ትልቅ ጸሎት ነው። መሸትሸት ሲል የሕይወት ጨለማ ሲመጣ ጌታን ወደልቡና ደጃችን ማስገባት ያስፈልጋል፤ “እነሆ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ፤ ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ፥ ወደ እርሱ እገባለሁ፤ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ፤ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።” (ራእ. ፫፥፳) እንዲል ደጃፍ ልቡናችንን ለእርሱ ልንከፍትለት ይገባል።
“ከእነርሱ ጋር በማዕድ ተቀምጦ ሳለ ኅብስቱን አንሥቶ ባረከው፥ ቆርሶም ሰጣቸው። ዓይናቸውም ተከፈተ፤ ዐወቁትም” (ሉቃ. ፳፬፥፴-፴፩) ቃሉን መስማት ልባችን በፍቅረ እግዚአብሔር እንዲቃጠል ያደርጋል። እሳት ያቃጠለው እርሻ ጥሩ ቡቃያ እንዲያበቅል፣ እርሻ ልባችን በእሳት ቃለ እግዚአብሔር ሲቃጠል ችግኝ ፈሪሃ እግዚአብሔርና ምግባር ይበቅልበታልና።
➜ አዲስ ኃይልና ወደ ኢየሩሳሌም መመለስ
ታሪኩ የሚጠናቀቀው በታላቅ ለውጥ ነው። ዓይናቸው ሲበራ ጌታ ከዓይናቸው ተሠወረ። ነገር ግን የጌታ መሰወር የእርሱ አለመገኘት ሳይሆን በውስጣቸው በጸጋ መኖሩን የሚያረጋግጥ ነው። “በዚያችው ሰዓት ተነሥተው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ” (ሉቃ. ፳፬፥፴፫) አስቡት ስድሳ ምዕራፍ ተጉዘው ደክመው የነበሩ ሰዎች፣ ጌታን ሲያዩ ግን ድካማቸው ጠፋ። ዛሬም እኛ በኃጢአት፣ በድካም ወይም በትምህርት ጫና ደክመን ከሆነ፣ ክርስቶስን ስናገኘው አዲስ ኃይል እናገኛለን።
ወጣቶች፣ በተለይም በግቢ ጉባኤያት የምትገኙ፣ ከኤማሁስ ተስፋ መቁረጥ ወጥታችሁ ወደ ኢየሩሳሌም ምስክርነት የምትመለሱበት ሰዓት አሁን ነው። ሀገራችን በብዙ ፈተና ውስጥ ባለችበት በዚህ ጊዜ፣ እንደ ኤማሁስ መንገደኞች “ነገሮች ተበላሽተዋል” ብሎ መደምደም ክርስቲያናዊ አይደለም። ይልቁንም “ጌታ ተነሥቷል፣ እርሱ በመካከላችን አለ” ብሎ የምሥራቹን ማብሠር ይገባል።
ማጠቃለያ
ይህ ዘመን ዘመነ ትንሣኤ ነው፤ የሞት ኃይል የተሸነፈበት፣ የሕይወት ብርሃን የበራበት ጊዜ። የኤማሁስ መንገድ የሁላችንም የዘወትር ታሪክ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ጌታ በሥውር አብሮን ነው። በታላቅ ተአምር ወይም በመብረቅ ሳይሆን፣ በመንገድ ላይ እንደ መንገደኛ ሆኖ ያገኘናል። በሰው ርዳታ፣ በጓደኛ ምክር፣ አልፎ ተርፎም በገጠመን ፈተና ውስጥ እርሱ አለ። አለመታወቁ አለመኖሩን አያሳይም። ስለዚህ በዚህ ጊዜ መንገድህ የቱንም ያህል ጨለማ ቢሆን፣ አብሮህ የሚጓዝ ጌታ እንዳለ አትዘንጋ። ቃሉን አንብብ – ልብህ ይቃጠላል፤ ወደ ማዕዱ ቅረብ – ዓይንህ ይከፈታል።
በኤማሁስ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ አትቀመጥ፤ ይልቁንም ወደ ኢየሩሳሌም ቅድስት ቤተክርስቲያንህ ተመለስና ለወንድሞችህ “ጌታ በእውነት ተነሥቷል” ብለህ መስክር።
ጌታችን በኤማሁስ መንገድ ላይ የገለጠውን ምሥጢር በልባችን ይሳልብን፤ ዓይናችንን ለብርሃን፣ ልባችንን ለቃሉ እሳት ያዘጋጅልን። ለሀገራችን ሰላምን፣ ለሕዝባችን ፍቅርን፣ ለተማሪዎቻችን ማስተዋልን ይስጥልን።
“ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ! ትንሣኤህን ለምናምን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን!”
ስብሐት ለእግዚአብሔር፣ ወለወላዲቱ ድንግል፣ ወለመስቀሉ ክቡር! አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!