“በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው” (ሐዋ. ፪ ፥፬)
ከመምህር ተፈሪ መንገሻ
የተወደዳችሁ የክርስቶስ ቤተሰቦች እንደምን ሰነበታችሁ? አሜን፣ የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን። እንኳን ለበዓለ ሃምሳ (በዓለ ጰራቅሊጦስ) አደረሳችሁ።
ቅዱስ ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ ላይ እንደጻፈልን፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከተነሣ በኋላ ለዓርባ ቀናት ለደቀ መዛሙርቱ እየተገለጠ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነገራቸው። በዓርባኛው ቀን ሲያርግ እንዲህ አላቸው፦ “ወናሁ አነ እፌኑ ተስፋሁ ለአቡየ ላዕሌክሙ ወአንትሙሰ ንበሩ ሀገረ ኢየሩሳሌም እስከ ትለብሱ ኃይለ እምአርያም፤እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።” (ሉቃስ ፳፬፥፵፱)
እነርሱም የታዘዙትን ጠብቀው፣ በሃምሳኛው ቀን (በዓለ ጰንጠቆስጤ) በማርቆስ እናት በቅድስት ማርያም ቤት በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት ሳሉ፣ ድንገት እንደ ዓውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ መጣ፤ የእሳት ላንቃዎችም በእያንዳንዳቸው ላይ ዐረፉ። መጽሐፉ እንደሚለን፦ “በሁሉም መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው።”
ሀ. በመንፈስ ዘንድ መድልዎ የለም
በዚያች ዕለት መለኮታዊው እሳት የወረደው በጥቂቶቹ ላይ ብቻ አይደለም፤ “በሁሉም” ላይ ነው እንጂ። ይህም መለኮታዊ ጸጋ በዘር፣ በባህል፣ በጾታ ወይም በማኅበራዊ ደረጃ ሳይገደብ ለሰው ልጆች ሁሉ በነጻ የተሰጠ መሆኑን ያሳያል። ነቢዩ ኢዩኤል በትንቢቱ ላይ፦ “ከዚህም በኋላ እንዲህ ይሆናል፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ” (ኢዩ. ፪፥፳፰) እንዳለ፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ሁሉ ጸጋውን አበዛ።
በተለይ ከተለያየ አካባቢና ባህል የመጣችሁ ወጣቶችና ምእመናን፣ በመንፈስ ቅዱስ ጥላ ሥር ሁላችንም እኩል መሆናችንን ማወቅ አለብን።
በክርስቶስ ቤት ማግለል የለም፣ ሁላችንም በጥምቀት አንድ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ተቀበልን የአንድ አባት ልጆች ነን።
ለ) ጎዶሎዎቻችን
እኛስ? ጎዶሏችንን በምን እየሞላን ነው?
በዕለተ ጰራቅሊጦስ ሐዋርያት በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው በደስታና በኃይል ሲመሰክሩ፣ በውጭ የነበሩት ሰዎች አላስተዋሏቸውም ነበር፤ ይልቁንም ፦ “ሌሎች ግን እያፌዙባቸው፦ ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።” (ሐዋ. 2፥13) ተብሎ ተጽፏል። ቅዱስ ጳውሎስም ይህንን ምሥጢር ሲተረጉም ፦ “በመንፈስ ተሞሉ እንጂ በወይን ጠጅ አትስከሩ ይህ ማባከን ነውና” ይላል።(ኤፌሶን ፭፥፲፰)
ይህ ጥልቅ ምሥጢር ነው። የሰው ልጅ በውስጡ ተፈጥሮአዊ የሆነ የመለኮታዊ ደስታ ጥማት አለው። ይህንን ጥማት ግን በምድራዊ ሱሶች (በአልኮል፣ በዕፅ፣ በቁማር፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ሱስ፣ በዝሙት ወዘተ) ለመሙላት ሲሞክር ሕይወቱን ያባክናል። የመንፈስ ቅዱስ ሙላት ግን የሰውን ውስጣዊ ጥማት መለኮታዊ በሆነ ሰማያዊ ደስታ ስለሚሞላው፣ ሰውየው ምድራዊውን ሱስና የኃጢአት ሕይወት ሙሉ በሙሉ እንዲጠላና ነጻ እንዲወጣ ያደርገዋል። ዓለም በሐሰተኛ ወይን ታሰክራለች፤ ጰራቅሊጦስ ግን በእውነተኛ የሕይወት ደስታ ይሞላል!
ሐ. አንድነትና ስምምነት
ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከመውረዱ በፊት “በአንድ ልብ ሆነው በአንድነት” ተሰብስበው ነበር። ይህ የሚያሳየው መንፈስ ቅዱስ የሚሠራውና የሚሞላው መለያየትና ክፋት ባለበት ቦታ ሳይሆን፣ ሰዎች በፍቅር፣ በይቅርታና በአንድነት ሲቆሙ መሆኑን ነው። ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ፦ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ” (ኤፌ. ፬፥፫) በማለት ያሳስበናል። በማኅበራችን፣ በቤታችንና በጉባኤያችን ውስጥ ክፋትንና መለያየትን አውጥተን ስንጥል፣ ያን ጊዜ መለኮታዊው እሳት በውስጣችን ያድራል።
መ. አዲስ ልሳንና የቋንቋ መታደስ
በብሉይ ኪዳን የሰው ልጅ እግዚአብሔርን ለመፎካከር የባቢሎንን ግንብ በገነባ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ቋንቋቸውን ደባልቆ በተበተኑ ጊዜ ቋንቋ የቅጣት ምልክት ነበረ።(ዘፍ.፲፩÷፩-፰) ነገር ግን በዕለተ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ሲወርድ ቋንቋዎችን አላጠፋቸውም፤ ይልቁንም ሐዋርያት ከተለያየ ዓለም በመጡ ሕዝቦች ቋንቋ እንዲናገሩ አደረገ። “…እኛ እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን?” ይላል።(ሐዋ. ፪፥፰)
ይህ ምሥጢር ምን ያሳየናል? መንፈስ ቅዱስ የሰውን ልጅ ማንነትና ባህል አያጠፋም፣ ይቀድሰዋል እንጂ። ዛሬ በሀገራችን በብሔርና በባህል ልዩነት ምክንያት ሰይጣን ትውልዱን በሚያባላበት ዘመን፣ ጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ልዩነቶቻችንን ሳያጠፋ በፍቅር ልዩነትን ውበት የሚያደርግ የመለኮታዊ አንድነት ኃይል ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት ሰው የሌላውን ልዩነት እንደ መለኮታዊ ስጦታ እንጂ እንደ ጠላትነት አይመለከትም።
ሠ. የፍርሃት መወገድ
ከመንፈስ ቅዱስ መውረድ በፊት ደቀ መዛሙርቱ በአይሁድ ፍርሃት ዝግ በሆነ ቤት ውስጥ ተሸሽገው ነበር። ሐዋርያት ጌታቸውን አይተውታል፣ ትንሣኤውን አውቀዋል፤ ነገር ግን በውስጣቸው መንፈሳዊው ኃይል ስላልነበረ በፍርሃት ቆፈን ተይዘው በቤት ውስጥ ተሸሽገው ነበር። ዛሬም ብዙ ክርስቲያኖችና ወጣቶች ስለ ነገ ሕይወታቸው፣ ስለ ሥራ ማጣት፣ ስለ በሽታና ስለ ሞት በፍርሃት ዝግ በሮች ጀርባ ተቀምጠዋል።
መንፈስ ቅዱስ ሲሞላባቸው ግን ፍርሃታቸው ተወግዶ በሕዝብ ፊት ወጥተው በድፍረት መመስከር ጀመሩ። ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት፦ “እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሃት መንፈስ አልሰጠንምና” ይላል። (፪ኛ ጢሞ. ፩፥፯)።
የእሳት ላንቃዎች በእያንዳንዳቸው ላይ ባረፉ ጊዜ፣ ያ አይሁድን ይፈራ የነበረው፣ ጌታውን የካደው ቅዱስ ጴጥሮስ፣ ዝግ የነበሩትን በሮች ከፍቶ ወጣ!
በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁድ በነበሩበት አደባባይ ላይ ቆሞ፣ ድምፁን ከፍ አድርጎ በድፍረት መመስከር ጀመረ። (ሐዋ. ፪፥፲፬) ይህ የሚያሳየው ፍርሃት የሚወገደው በመለኮታዊው እሳት መሆኑን ነው። መንፈስ ቅዱስ ወደ ልብ ሲገባ ፍርሃት ቦታ የለውምና ተበትኖ ይጠፋል።
ወጣቶች ሆይ በመንፈስ ቅዱስ ራሳችንን እንግዛ!
ፍርሃት አእምሮን ያውካል፤ የተሳሳተ ውሳኔ እንድንወስንም ያደርገናል። ይህ መንፈስ ግን ለአእምሯችን መረጋጋትን፣ ማስተዋልንና ሰላምን ይሰጠናል። በማንኛውም ሁከት ውስጥ ሆነን ነገሮችን በእግዚአብሔር መነጽር እንድንመለከት ያደርገናል።
ስለዚህ ዛሬ በዚህ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ልባችንን ለእግዚአብሔር መንፈስ እንክፈት። ጎዶሏችንን በዓለማዊና ጊዜያዊ ከንቱ ነገሮች ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ እንሙላ፤ ልዩነቶቻችንን በፍቅር አውርደን በአንድነት እንቁም፤ የፍርሃትንም ሰንሰለት ሰብረን በመንፈስ ቅዱስ በሚገኝ ኃይል፣ ፍቅርና ራስን በመግዛት እውነተኛ ነጻነትን እንኑር።ለዚህም አምላካችን እግዚአብሔር በቸርነቱ ያግዘን፡፡አሜን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!