መንፈሳዊ ሰው እና ሳይንሳዊ ምርምር (ክፍል አንድ)

“መንፈሳዊ ሰው መሆን ሳይንሳዊ ምርምርን ለማከናወን አይመችም፡፡ መንፈሳዊ ሰው ተመራማሪ መሆን አይችልም፡፡” በማለት የሚናገሩ አካላት አሉ፡፡ በእርግጥ መንፈሳዊ ሕይወት ሳይንሳዊ ምርምር ለማከናወን እንቅፋት ሊሆን ይችላል? ለመንፈሳዊ ሰውስ ምርምር ምን ይጠቅመዋል? በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከእንግዳ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንግዳችን ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ናቸው፡፡

ጥያቄ ፩፡ በመንፈሳዊ ሰው እይታ ሳይንሳዊ ምርምር ማለት ምን ማለት ነው?

 ዲ/ን ያረጋል፡- ሳይንሳዊ ምርምር በራሱ ሊታይ የሚገባው እንጂ መንፈሳዊ ለሆነ ላልሆነ ተብሎ የሚከፈል አይመስለኝም፡፡ በራሱ ሳይንሳዊ ምርምር ምንድነው? የሚለውን ማየት እና ከዛ በኋላ ግን በዚህ ሳይንሳዊ ምርምር ወይም ሳይንሳዊ የዕውቀት ማግኛ መንገድ በሚባለው ውስጥ ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጐኖች ማየቱ የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ሳይንሳዊ ምርምር የሚለውን አሳብ ከማየታችን በፊት ምርምር ምንድነው? የሚለውን ማየት ይገባል፡፡ ምርምር ማለት የራቀውን ለማቅረብ፣ የረቀቀውን ለማጉላት፣ የተሠወረውን ለማግኘት የሚደረግ ጥረት ወይም ሒደት ነው፡፡

መመራመር ለሰው የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ ሰው በራሱ ያገኘው አይደለም፡፡ ለምሳሌ፡- እንስሳት አይመራመሩም፤ በደመ ነፍስ የተቀመጠላቸውን፣ ከጥንት ጀምሮ ያገኙትን እየተገበሩ ይኖራሉ (ሣር የሚነጨውም ሣር ይነጫል፤ በበረሀ የሚኖረው በበረሀ ይኖራል)፡፡ ሰው ግን በብዙ መንገድ ይመራመራል፤ ኑሮውን በየጊዜው ይለውጣል፤ ያሳድጋል፡፡ ይህ ከእግዚአብሔር ለሰው የተሰጠ ጸጋ ነው፡፡ እግዚአብሔር “ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” ብሎ በታላቅ ጸጋና በሕያዊት ነፍስ አክብሮታል፡፡ “በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር” የሚለው ቃል ሰው ዐዋቂ መሆኑን ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር በባሕርዩ ዐዋቂ ነው፡፡ ሰውም ከእግዚአብሔር የማወቅ ሀብት ተሰጥቶታል፡፡ ማወቅ ማለት አንድ የተቀመጠን እውነት ብቻ ሳይሆን መጨመርንና ማሳደግንም ያሳያል፡፡

እግዚአብሔር ሰውን በገነት ሲያስቀምጠው “ገነትን ተንከባከባት” ብሎታል፡፡ ገነትን መንከባከብ ለኑሮ የግድ አስፈላጊ ሆኖ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም በገነት መራብ፣ መጠማት አልነበረምና፡፡ ነገር ግን ሰው በተሰጠው ጸጋ እንዲሠራ ገነትን ተንከባከባት፡፡ መሥራት ቁሳዊና ጉልበታዊ ብቻ ሳይሆን አእምሮአዊም ነው፡፡ ስለዚህ በእግዚአብሔር የተሰጠን ጸጋ መጠቀም ምርምር ነው፡፡

ሳይንሳዊ ምርምር ዕውቀት የሚገኝበት አንድ መንገድ ነው፡፡ ዕውቀት የሚገኘው በማየት፣ በመመልከት፣ በማስተዋል፣ በመሞከር፣ በምልከታና ከሚገኙ መረጃዎች ወይም ከክስተቶች በመነሣት ነው፡፡ እንዲህ ባለ መንገድ የሚያድገው እውነት የሚለካ ነው፤ የሚለካውም አሐዛዊ (Empirical፣ Mathematical፣ Quantitative) በሆነ መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ ሳይንሳዊ ምርምር አንድ የዕውቀት መንገድ ነው፡፡

ሳይንሳዊ ምርምር ችግር የሚሆንበት መንገድ አለ፡፡ ለዚህም ቢያንስ ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ማንሣት እንችላለን፡፡ አንደኛው ሳይንሳዊ መንገድ “ብቸኛው የእውነትና የዕውቀት መንገድ ነኝ” ሲል ነው፡፡ ምክንያቱም ሳይንስ ራሱን የቻለ አካል ከሕልውና ያለው ግለሰብ አይደለም፡፡ ነገር ግን የራሱ አቀራረብና ዘዴዎች አሉት፡፡ አቀራረቡና ዘዴውም እንደማንኛውም አቀራረብና ዘዴ የራሱ የሆነ ጠንካራና ደካማ ጐን አለው፡፡

ሳይንስ ብዙ ዕውቀቶችን አስገኝቷል፡፡ ነገር ግን ፍጹምና ብቸኛ የዕውቀት መንገድ አይደለም፡፡ ዕውቀትን፣ ምርምርን ሁሉ ከሌላው ነጥቀው፥ ለእርሱ ብቻ በመስጠት ፍጹም (Perfect) እና ብቸኛ መንገድ እንደሆነ ማቅረብ ስሕተት ነው፡፡ በሳይንስ መንገድ ያሉ ሰዎችም፥ ሳይንስ ከብዙ አስተሳሰቦች አንዱ እንጂ ብቸኛ አለመሆኑንና ምርጡም ሳይሆን አንዱ አማራጭ መሆኑን በተለይ በ20ኛው መ/ክ/ዘ የተነሡ ፈላስፎች ተናግረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ፓውል ፋየራባንድ፣ “ሳይንስ የዕውቀት ማግኛ አንድ መንገድ እንጂ ብቸኛ መንገድ አይደለም፡፡ ጥንቱንም ሲጀመር ሳይንስ የሰዎችን አስተሳሰብ ነጻ አውጥቶ በትክክለኛው ወይም ነጻ በሆነ መንገድ እንዲያስቡ፤ ዕውቀትን እንዲፈልጉ ለማድረግ ነበር፡፡ በኋላ ግን ሳይንስ የዕውቀት ብቸኛው መንገድ የእኔ ነው በሚል ሌሎችን ጨቋኝ ሆኗል፡፡ ሌላው ሳይንስ በእኔ መንገድ ካልመጣ ብቻ ስለሚል ከእርሱ ውጭ ያሉ፤ ሊገኙ የሚችሉ ዕውቀቶችንና አማራጭ መንገዶችን በመዝጋት ዕውቀትን አቀጭጯል፡፡ ስለዚህ ኅብረተሰባችን ከዚህ ነጻ መውጣት አለበት፡፡ ልክ ዓለማዊ (Secular) በሆኑ ሀገራት ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ እንደሆኑ ሁሉ አሁንም ሳይንስ ከመንግሥት መነጠል አለበት፡፡ ሳይንስ እንደማንኛውም የዕውቀት ማግኛ መንገድ መሆን አለበት እንጂ እንደ ብቸኛ መንገድ ተቆጥሮ ነገሮች ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያልፉ መደረግ የለበትም” በማለት ተናግሯል፡፡

ፓውል ከላይ ላነሣው አሳብ ብዙ ማሳያዎችን ያቀርባል፡፡ ለምሳሌ የኮፐርኒከስ “ቲዎሪ” እንደገናም ጋሊሊዮ ያረጋገጠውና ያጠናከረው “መሬት በፀሐይ ዙሪያ ትዞራለች (Moving Earth)” የሚለው አስተሳሰብ አንዱ ነው፡፡ ኮፐርኒከስም ሆነ ጋሊሊዮ በጊዜው ይኼን “ቲዎሪ” ሲያመጡ ከነበረው ሳይንሳዊ መንገድ አፈንግጠው ነው፡፡ ምክንያቱም በጊዜው የተለያዩ ሙከራዎች ነበሩ፡፡ ለዚህም ፀሐይ ትዞራለች የሚለው የአርስቶትልና የኘቶሎሚ ወይም የበጥሊሞስና የአርስጣጣሪስ ቲዎሪ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሙከራቸውንም ከማማ ላይ ድንጋይ ወደ መሬት በመጣል አካሔዱ፡፡ በሙከራቸውም “መሬት የምትንቀሳቀስ ከሆነ ከማማ ላይ የሚጣለው ድንጋይ ቀጥታ ወደታች ሳይሆን ወደ ጎን መሆን አለበት፡፡ ምክንያቱም ድንጋዩ ሲወረወር ከነበረው የመሬት አቅጣጫ አንጻር መሬቷ ስለምትሔድ ወደ ፊት እልፍ ማለት አለበት፡፡ ነገር ግን ድንጋዩ እዛው ቁልቁል የተጣለበት ቦታ ላይ ካረፈ መሬት አትንቀሳቀስም ማለት ነው፡፡” በዚህ መንገድ የኮፐርኒከስና የጋሊሊዮ ሙከራ ትክክል አልነበረም፡፡ ነገር ግን ኮፐርኒከስም ጋሊሊዮም ከዚህ ሳይንሳዊ መንገድ ወጥተው በሌላ መንገድ አሳባቸውን አቀረቡ፡፡ ለዚህ ነው ፓውል መጽሐፉን “Against Method” በማለት የሰየመው፡፡ ያ ቀመር በኋላ ትክክል ሆኗል፡፡ ነገር ግን በጊዜው በነበረው አስተሳሰብ ስህተት ነበር፡፡ ስለዚህ ሳይንሳዊ ምርምር የዕውቀት ማግኛ አንድ መንገድ እንጂ ብቸኛ መንገድ አይደለም፡፡ ስለሆነም የሳይንስ አንዱ ችግር ብቸኛ የዕውቀት መንገድ የእኔ ነው የሚለው ነው፡፡

ሁለተኛው ሳይንስ ነገሮችን የሚያጠናው የሚለኩ፣ የሚመዘኑ ከሆኑ ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጭ እውነታ የለም፤ እኔ ያላጠናሁት ነገር እውነት ሊሆን አይችልም ብሎ መደምደም ግን አይችልም፡፡ ይህ አስቀድሞ ነገሮች ሁሉ የሚለኩ፣ የሚታዩ፣ የሚጨበጡ፣ የሚዳሰሱ ናቸው ብሎ መደምደምን ያመጣል፡፡ ስለዚህ ራሱ ከፈጠረው እምነት ተነሥቶ መነሻውን እንደ ማስረጃ አድርጎ መውሰድ የለበትም፡፡ ይህ የራስን በራስ ማረጋገጥ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ከዛ ውጪ የሆኑ እውነታዎች አለመኖራቸውን በዚህ መንገድ ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ነገሮች ሁሉ የሚለኩ ናቸው ብሎ ከተነሣ፤ ከዚህ ውጪ ያለውን ነገር እሱ ማጥናት ስለማይችል ብቻ የሉም ከሚል መደምደሚያ መድረስ ትክክል አይደለም፡፡ ስለዚህ ሳይንሳዊው መንገድ ችግር የሚሆነው እንደ አንድ አቀራረብ፣ እንደ አንድ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉ ሳይሆን እሱ እንደ መነሻ ያደረገውን ነገር እንደ እውነት እና የነገሮች ሁሉ መመዘኛ አድርጐ ማቅረቡ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሳይንሳዊ መንገድ መመራመር እግዚብሔር ለሰው የሰጠው ጸጋ ነው፡፡

ጥያቄ ፪፡ አንድ መንፈሳዊ ሰው አላፊ፣ጠፊ ስለሆነው ስለዚህ ዓለም እንዴት በጥልቀት ሊመረምር ይችላል? መመርመር የሚችል ከሆነስ እንዴት ነው ማሰብ የሚኖርበት?

 ዲ/ን ያረጋል፡- በእርግጥ የአንድ መንፈሳዊ ሰው ዓላማው መንፈሳዊውን ዓለም መውረስ ነው፡፡ ስለሆነም አንድ መንፈሳዊ ሰው በዚህ ዓለም እግዚአብሔር በሰጠው ጊዜ ሲኖር በዚህ ዓለም ያለውን ነገር ማጥናት እና መንፈሳዊ በሆነ መንገድ መሳተፍ አለበት፡፡ ይኼ የሚሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች ሲኖሩ ከእነዚህም ውስጥ ዐራት መሠረታዊ ነጥቦች እንመለከታለን፡-

፩ኛው፡- ስለ እግዚአብሔር አሠራር፣ ስለመግቦቱ፣ ስለሀልዎቱ፣ ወዘተ ሁሉ የምናውቀው እግዚብሔር ያስቀመጠውን ዕውቀትና ጥበብ ስንመረምር ነው፡፡ “የማይታየው እግዚብሔር በሥነ ፍጥረቱ ይታወቃል” እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ፡፡ እግዚአብሔርን በባሕርዩ ማንም አላየውም፡፡ በባሕርዩ የማይታየው እግዚአብሔር ራሱን ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ በሥነ ፍጥረት ነው፡፡ ከደቃቅ ፍጥረታት ጀምሮ ግዙፍ ፍጥረታት ሁሉም አእምሮን ጐትተው ወደ እግዚአብሔር ያደርሳሉ፡፡ ለዚህ ነው መዝሙረኛው ዳዊት “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፥ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል።” በማለት የዘመረው (መዝ ፲፱፥፩)፡፡

እግዚአብሔር አስቀድሞ ያስተማረው ከመጽሐፍ ይልቅ በሥነ ፍጥረት ነው፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ የሚያገኘው የተማረ፣ ሀብት ያለው፣ ማንበብ የሚችል ሰው ነው፡፡ ሥነ ፍጥረት ግን ፊደል የቆጠረ ያልቆጠረ፤ ሀብታም ደሀ አይልም፤ ሁል ጊዜ የተዘረጋ መጽሐፍ ነው፡፡ ሥነ ፍጥረትን ማንበብ ማለት የእግዚአብሔርን ሥራ ማንበብ ነው፡፡ ጠርጠሉስ የተባለ ሊቅ “እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት የሚያጽፈውን እውነት አስቀድሞ በሥነ ፍጥረት ውስጥ ጽፎታል፡፡” ብሏል፡፡ አንድ ፈላስፋ ቅዱስ እንጦንዮስን “ባሕታዊ እንጦንዮስ ሆይ ከምንድነው የምትማረው?” በማለት ሲጠይቀው “ፈላስፋ ሆይ የእኔ መጽሐፍ ሥነ ፍጥረታት ናቸው” በማለት መለሰለት፡፡ ሥነ ፍጥረት ትልቅ መጽሐፍ ነው፡፡ ከዚህ የተነሣ የቀደሙና ዛሬም የሚገኙ ታላላቅ አባቶች ሥነ ፍጥረትን እያደነቁ እግዚአብሔርን ያመሰግናሉ፡፡ መጽሐፍ “ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር” እንዲል (ዘፍ.፳፬፥፷፫)፡፡  በእርግጥ ይስሐቅ ኢያውብርን እየጠበቀ ነበር፤ ከዚሁ ጋራ ግን በመሸ ጊዜ ሥነ ፍጥረትን እየተመለከተ ያሰላስል ነበር፡፡ ሥነ ፍጥረትን ካላነበብን እግዚብሔር በዛ ውስጥ የጻፈውን ሀልዎቱን ፣ መግቦቱን፣ ፈጣሪነቱንና ጥበቡን ልናውቅ አንችልም፡፡

ፍሪትዝ ሻፈር (The 3rd most quoted chemist in the world) የሚባል ሊቅ “በሳይንስ ወይም በምርምር ውስጥ ደስታ የማገኘው አዲስ ነገር በድንገት ሳገኝና ‘አሀ ለካ እግዚአብሔር የሠራው እንደዚህ ነው’ የምልበት ነገር ሳገኝ ነው፡፡ ዓላማዬ የእግዚአብሔርን አሠራር አንዷን ጥግ እንኳ ለመረዳት መሞከር ነው፡፡” በማለት ተናግሯል፡፡ በፊዚክስ፣ በኬሚስትሪ፣ በባዮሎጂ፣ … ባለን የዕውቀት መንገድ ሁሉ ብንሔድ የምናየው የእግዚአብሔርን አሠራር ነው፡፡ ስለሆነም ሥነ ፍጥረትን መመርመር በጣም ጠቃሚ ነው፡፡

፪ኛው፡- በዚህ ዓለም ያለውን ነገር የምንመረምርበት ምክንያት እግዚአብሔር በፍጥረቱ ውስጥ ያስቀመጠውን ሀብት ፈልጎ ለማግኘትና ጥቅም ላይ ለማዋል ነው፡፡ እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ስንኖር እንድንቸገር አይፈልግም፡፡  እንጠቀምበት ዘንድ በዚህ ዓለም ያስቀመጠው እምቅ ሀብት አለ፡፡ ልክ እውቀታችንና ፍላጐታችን የሚፈለግበት ደረጃ ሲደርስ የሚያስፈልገንን ሀብት ብቅ እያደረገ ይሰጠናል፡፡ ማንም ሳይንቲስት አዲስ ነገር አያገኝም፤ የነበረውን ያገኛል፡፡ እግዚብሔር በምድር ውስጥ ነዳጁን፣ ጋዙን፣ የመሳሰሉትን ሁሉ አስቀመጠ፡፡ መኪናና የመሳሰሉት ነገሮች ሲመጡ አስገኛቸው፡፡ ሰው ቀድሞ ፔትሮሊየም ወይም የተፈጥሮ ጋዝን ቢያገኝ ለምን ጥቅም ያውለው ነበር? ነገር ግን የሚያስፈልገው ነገር ሲመጣ ለዚያ የሚሆነውን ነገር አዘጋጀ፡፡ አንድ አባት ለልጁ የሚያስፈልገውን ነገር በባንክ አደራ እንደሚያስቀምጥ ማለት ነው፡፡ አባት ልጁ ሲያድግ እንደሚያስፈልገው መጠን ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ ምርምር የተሠወረውን ሀብት የምናገኝበት፣ ኑሮን ለማቅለል የምንጠቀምበት ነው፡፡

፫ኛው፡- የሰው ልጅ በታሪክ ሒደት ውስጥ የራሱ ድርሻ ስላለው ሥነ ፍጥረትን እናጠናለን፡፡ ሰው እግዚአብሔር የሚያደርገውን ብቻ ዝም ብሎ እንደሚያይ ግዑዝ ፍጥረት አይደለም፡፡ ሰው በታሪክ ሒደት የራሱ ድርሻ እና ሚና ያለው ፍጥረት ነው፡፡ ድርሻችንን የምንወጣው ደግሞ በሥራ ነው፡፡ የምንሠራው ደግሞ አጥንተን እንጂ በግምት፣ በግብታዊነት ወይም በደመ ነፍስ አይደለም፡፡

፬ኛው፡- እውነትን ለመጠበቅ እና ለመግለጥ ነው፡፡ ሰው በዚህ ዓለም ያለውን ነገር ማወቅና ማጥናት የሚገባው እውነትን ለመግለጥ፤ የተሠወረውን ገልጦ “በልዎ ለእግዚአብሔር ግሩም ግብርከ” እንደተባለው እግዚብሔርን እንዲያመሰግን ነው፡፡ እውነቱ ካልተገለጠ ሐሰት ቦታ እየያዘ፣ በውሸትና በግምት ከመደጋገሙ የተነሣ እውነት እየመሰለ የሰዎችን ልቦና ያሳስታል፡፡ ለምሳሌ እንደ ዝግመታዊ ለውጥ (Evolution) ዓይነት ያሉት፡፡ እንዲህ ዓይነት ግኝቶች እውነት መስለው፣ ተፈርተውና ተከብረው ዓለምን ሲያሳስቱ የኖሩ ናቸው፡፡ ግኝቶቹ ካልተጠኑ ዝም ብሎ በመቃወም፣ በማኩረፍ ወይም በመጥላት ብቻ እውነቱን ልንገልጠው አንችልም፡፡ አሁን ላይ በእግዚብሔር የሚያምኑ ብቻ ሳይሆኑ በእግዚአብሔር የማያምኑ ሳይንቲስቶች ሳይቀሩ እንደ ዝግመታዊ ለውጥ እና የመሳሰሉትን ቲዎሪዎች ይተቻሉ፡፡ ምርምር የሚጠቅመው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ስለዚህ ሥነ ፍጥረትን መመርመር ለአንድ እውነተኛ መንፈሳዊ ሰው አስፈላጊ ነው ፡፡

ይቀጥላል…

ምንጭ፡- ጉባኤ ቃና ልዩ ዕትም

መስከረም ፳፻፰ ዓ.ም.