በዓለ ሃምሳና ተግዳሮቶቹ
ከመምህር ተፈሪ መንገሻ
ከሁሉ አስቀድመን እንኳን ለጌታችንንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ በማለት መንፈሳዊ ሰላምታችንን እናቀርባለን።
አሁን የምንገኝበት ወቅት በዓለ ሃምሳ ነው። ይህ ወቅት የሞት ኃይል የተሰበረበት፣ የሰው ልጅ ነጻነት የታወጀበትና የመቃብር ድንጋይ ተንከባሎ የሕይወት ብርሃን የበራበት ነው።
ሆኖም ግን፣ ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ወይም ለክርስቲያን ወጣቶች ይህ ወቅት ሌላ ፈተና ይዞ መጥቷል። ዓቢይ ጾምን በከፍተኛ ተጋድሎ፣ በለቅሶና በጸሎት ያሳለፉ ወጣቶች፤ ዛሬ ጾሙ ሲፈታ መንፈሳዊነታቸው አብሮ የተፈታ ይመስል በስካርና በስንፍና፣ በስውርና በግልጥ ኃጢአት ማዕበል እየተወሰዱ ያሉት በርካቶች ናቸው። በዓለ ኀምሳ የነፍስ ደስታ እንጂ የሥጋ ማድለቢያና የዲያብሎስ ፈቃድ መፈጸሚያ እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።
1.1. በዓለ ሃምሳ ምንድ ነው?
በዓለ ሃምሳ ማለት ከጌታችን ትንሣኤ ጀምሮ እስከ ጰራቅሊጦስ (የመንፈስ ቅዱስ መውረድ) ድረስ ያለው የ፶ ቀናት ታላቅ የደስታ ወቅት ነው። ቤተ ክርስቲያን በዚህ ወቅት አዳም ወደ ቀደመ ክብሩ መመለሱን ለማብሠር እንዲሁም በመንግሥተ ሰማያት ጻር ድካም የለም ስትል ጾምና ስግደት እነዳይኖር አድርጋለች።
ነገር ግን ይህ ደስታ “መንፈሳዊ” መሆኑን አንርሳ። ሐዋርያት በዚህ ወቅት በፍርሃት ተቆልፎባቸው ከነበረበት ቤት ወጥተው፣ ትንሣኤውን እያደነቁ በጸሎትና በምስጋና ይተጉ ነበር። በዓለ ሃምሳ የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ ነው። በመንግሥተ ሰማያት ደግሞ ቅድስና እንጂ ርኩሰት የለም። ነገር ግን “ጾም የለም” በሚል ሰበብ ነፍሳቸውን ለሰይጣን አሳልፈው እየሰጡ ያሉ ወጣቶች ጥቂቶች አለመሆናቸውን የሁላችንም ልባችን የሚያውቀው እውነት ነው።
መንፈሳዊ በዓላት መንፈሳዊነታችንን የምናጣባቸው ሊሆን ይገባ ነበርን?!
“ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ/ነጻነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ …. ” እንዲል ቅዱስ ጳውሎስ። (ገላ ፭፥፲፫)
1.2. በዓለ ሃምሳን እንዴት ማሳለፍ ይኖርብናል?
1.2.1. እንደማንኛውም ጊዜ ቤተ ክርስቲያን መሔድን በማዘውተር
ወጣቶች ሆይ! ጾም ሲኖር ብቻ ደጅ የምትጠኑ፣ ጾም ሲፈታ ግን ቤተ ክርስቲያንን እንደ ባዕድ አገር የምትረሱ “ወቅታዊ ክርስቲያኖች” አትሁኑ።
“ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ ባሉኝ ጊዜ ደስ አለኝ” (መዝ. ፻፳፩፥፩)
ያለውን የዳዊትን ቃል ትታችሁ፣ “ወደ መዝናኛ ካፌ፣ ወደ ፊልም ቤት፣ ወደ ጫት ቤት እንሂድ ወዘተ” ሲሏችሁ ደስ የሚላችሁ ከሆነ፣ እናንተ ገና የትንሣኤው ብርሃን አልተገለጸላችሁም።
ጌታችን በመጽሐፍ ቅዱስ “እስከ መጨረሻው የሚጸና እርሱ ይድናል” (ማቴ. ፲፥፳፪) እንዳለ፣ ጽናት በጾም ብቻ ሳይሆን ከጾም ውጭም ይፈተናል።
1.2.2. በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ጽሙድ በመሆን
በጾመ ዓርባ ወቅት የግቢ ጉባኤ መድረኮች በአገልጋዮች ተጨናንቀው፣ መዝሙሩ ፣ ጥናቱ …. ተጠናክሮ እናያለን። ትንሣኤው ሲበሠር ግን አገልጋዩ እንደ ጢስ በኖ፣ እንደ ጉም ተኖ ይጠፋል።
በግቢ ጉባኤያችሁ ውስጥ ያላችሁ አገልግሎት በትንሣኤ ማግስት መዝለፍለፍ የለበትም። በጾም ወቅት መዘምራንና አገልጋዮች ሞልተው፣ አሁን ግን ዐውደ ምሕረቱ የሚቀዘቅዝ ከሆነ አገልግሎታችሁ ለወቅታዊ ስሜት እንጂ ለዘላለማዊው ለክርስቶስ እንዳልሆነ ማረጋገጫ ነው።
“ለሥራ ከመትጋት አትለግሙ፤ በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ፤ ለጌታ ተገዙ” (ሮሜ ፲፪፥፲፩)
የሚለውን የጳውሎስን ቃል መመሪያችሁ አድርጉ። አገልግሎት በወቅትና በጊዜ አይገደብምና።
የአገልግሎት ጽሙድነት ማለት በምቾትም በችግርም፣ በጾምም በበዓልም የማይናወጥ ጽናት ማለት ነው። “በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” እንዲል ጳውሎስ። ፪ኛ ጢሞ ፬፥፪።
ቅዱስ እስጢፋኖስ ድንጋይ እየወረደበትም አገልግሎቱን/ ምስክርነቱን አልተወም (ሐዋ. 7)። እኛ ግን ድንጋይ ቀርቶ ለምግቡ፣ ለመጠጡ ለምቾቱ ወዘተ” ስንል አገልግሎታችንን የምንረሳ ከሆነ፣ የቆምንበት መሠረት ምንኛ የላላ ነው!
አንድ ወታደር ጦርነቱ ካበቃ በኋላ የሚዘናጋ ከሆነና ጸንቶ ካልቆመ፣ ጠላት በድል በዓሉ መሐል መጥቶ ይገድለዋል።
እኛም በጾም ሰይጣንን ድል አድርገን፣ በበዓለ ሃምሳ ብንሰንፍ፣ ሰይጣን በደስታችን መሐል መጥቶ ነፍሳችንን ይማርካታል። ከዚህ ይጠብቀን።
ስለዚህ ወጣቶች ትንሣኤው በሥራ ይገለጥ! በመንፈስ የጀመራችሁትን በዝለት አታበላሹት። (ገላ. ፫፥፫)።
1.2.3. በምክረ ካህን በፈቃደ ካህን በመጓዝ
መሪ የሌለው መርከብ ወዴት ይጓዛል?!
የግቢ ጉባኤ ወጣቶች በዚህ በበዓለ ሃምሳ ወቅት ሊዘነጉት የማይገባ ታላቅ መመሪያ ቢኖር በምክረ ካህንና በፈቃደ ካህን የመመላለስ መንፈሳዊ ጥበብ ነው። የዩኒቨርሲቲ:የኮሌጅ ሕይወት በዕውቀት ባሕር ላይ እንደመጓዝ ቢሆንም፣ ያንን ባሕር ያለ መሪ (ካህን) ለመሻገር መሞከር ግን ነፍስን ለጽኑ ማዕበል አሳልፎ መስጠት ነው።
ፈቃደ/ምክረ ካህን ማለት ለአንድ ክርስቲያን ወጣት የጥበቃ አጥር ነው። አጥር ያለው ተክል እንስሳት እንደማይጎዱት ሁሉ፣ በፈቃደ ካህን የሚኖር ወጣትም የዚህ ዓለም ክፉ ፈተናዎች አያሸንፉትም። የትንሣኤው ደስታ ትርጉም የሚኖረው በካህኑ ቡራኬና መመሪያ ሲቃኝ ነው።
በጾም ወቅት ብቻ “ቀኖና ስጡኝ” እያሉ ደጅ የጠኑ፣ ዛሬ ግን ጾሙ ሲፈታ ፊታቸውን ከካህኑ አዙረው ወደ ሥጋዊ ፈቃዳቸው የሮጡ ወጣቶች፤ ሳያስተውሉት ነፍሳቸውን ለተኩላ አሳልፈው የሰጡ በጎች ናቸው!
በበዓለ ሃምሳ ወቅት “ጾም የለም” ብለው የልባቸውን ክፋት ሁሉ ሲፈጽሙ፣ ያለካህኑ ምክር ሲኖሩ፤ ጌታችን “እናንተን የሚሰማ እኔን ይሰማል፤ እናንተንም የጣለ እኔን ይጥላል” (ሉቃ. ፲፥፲፮) ብሎ የተናገረውን ቃል ራሳቸው ላይ እየፈረዱበት ነው።
በበዓለ ሃምሳ ወቅት “ጾም አበቃ” በሚል ስሜት ከካህን መራቅ ሳይሆን፣ ይልቁንም ያገኙትን መንፈሳዊ ድል ለማጽናት ወደ ካህኑ ይበልጥ መቅረብ ይኖርባቸዋል። በፈቃደ ካህን የሚጓዝ ወጣት በዓለ ሃምሳን በቅድስና የማሳለፍ ልዩ ጸጋ ይታደላል።
እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አለኝታዎች የሆኑ ወጣቶች፣ የካህናትን ምክር እንደ ኋላ ቀርነት ሳይሆን እንደ ሰማያዊ ጥበብ ሊመለከቱት ይገባል።
ስለዚህ ወጣቶች ሆይ በዚህ የደስታ ወቅት ከሰይጣን ወጥመድ የምታመልጡት በካህን ምክር ስትጓዙ ብቻ ነው። ካህኑን መፈለግ ያለባችሁ ኃጢአት ስትሠሩ ብቻ ሳይሆን፣ ቅድስናችሁ እንዳይጎድል ጭምር መሆን አለበት።
መረሳት የሌለበት ነገር በግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ዘንድ የሚታየው አንዱ ትልቅ ተግዳሮት “ምክረ ካህንን” ከ “ንስሓ” (ከኃጢአት መታጠብና ከቀኖና) ጋር ብቻ አያይዞ መመልከት ነው።
ንስሓ ውድቀት ከተከሠተ በኋላ ነፍስን የምታክም መድኃኒት ብትሆንም፣ ምክረ ካህን ግን ውድቀት ሳይመጣ፣ ኃጢአት ሳይሠሩ፣ ነፍስ እንዳትቆስል የሚደረግ “መከላከያና ቅድመ ጥንቃቄ” ነው። ወጣቶቹ ኃጢአት ሲሠሩ ብቻ ወደ ካህን የሚሮጡ ከሆነ፣ መንፈሳዊ ሕይወታቸው ሁልጊዜ በውድቀትና በጸጸት የተሞላ ይሆናል።
እንደ ግቢ ጉባኤ ተማሪነታቸው በትምህርት፣ በጓደኝነትና በወደፊት የሕይወት አቅጣጫቸው ላይ የካህን ምክር ያስፈልጋቸዋል። ካህናት “መንፈሳዊ አባቶች” ናቸው። አባት ደግሞ ልጁ ሲበድል ብቻ ሳይሆን፣ ልጁ ትክክለኛውን መንገድ ይዞ እንዲያድግ ሁልጊዜ ምክር ይለግሰዋል።
ጠቢቡ ንጉሥ “መካሪ የሌለው ሕዝብ ይወድቃል፤ በመካሪዎች ብዛት ግን ደኅንነት ይሆናል” ብሎ እንደተናገረው (ምሳሌ 11፥14)
ውድቀት (ኃጢአት) ሳይመጣ በፊት ደኅንነትን (ድልን) ለማግኘት የመካሪ አስፈላጊነትን ይገልጻል። ወጣቶቹ በምክረ ካህን ጥላ ሥር ሲሆኑ ከውድቀት ይጠበቃሉ እንጂ ውድቀትን አይጠብቁም።
ማጠቃለያ
በዓለ ሃምሳን በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ስንመለከተው፣ የክርስቶስ ትንሣኤ ለሰው ልጅ የሰጠው ነጻነት በኃጢአት ባርነት እንድንመላለስ ሳይሆን፣ በጽድቅ ብርሃን እንድንመላለስ መሆኑን እንረዳለን። የግቢ ጉባኤ ወጣቶች ከጾም ማግስት የሚገጥማቸውን መንፈሳዊ ዝለት አሸንፈው፣ ይህን ታላቅ ወቅት በቅድስና ሊኖሩ ይገባቸዋል።
“በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደ ገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።” ገላትያ ፭፥፩
ነጻ ያወጣችሁ ጌታ በነጻነቱ ያጽናችሁ፤ በነፍሳችሁ ላይ የታተመው የትንሣኤው ብርሃን ደግሞ በኃጢአት ዝገት እንዳይጠፋ በጸሎትና በምክረ ካህን ጠብቁት።
ስብሐት ለእግዚአብሔር!

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!