ጾም ምንድን ነው?

…በመ/ር ቅዱስ ያሬድ…

ጥያቄ፡- የጾምን ምንነትና ዓይነቶቹን ጠቅለል አድርገው ቢገልጹልን?

መምህር ቅዱስ ያሬድ፡- በመጀመሪያ ጾም ‹‹ጾመ›› ጾመ /ጦመ/ ታቀበ፣ ታረመ፣ ተወ፣ ተከለከለ ከሚለው የግእዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም በሃይማኖት ምክንያት ምግብና መጠጥ መተው፤ ወይም ከምግብና ከመጠጥ መከልከል፤ ጥሉላት መባልዕትን ፈጽሞ መተው፤ ሰውነትን ከክፋትና ሥጋን ደስ ከሚያሰኝ ነገር ሁሉ መታቀብና መጠበቅ ማለት ነው፡፡ ‹‹ጾምሰ ተከልኦተ ብእሲ እመብልዕ በጊዜ ዕውቅ በውስተ ሕግ፤ ጾም በታወቀው ዕለትና ሰዓት ሰው ከምግብ የሚከለከለው መከልከል ነው /አስ. 4፥16፤ ዳን.10፥2፤ ፍት. መን. አን 15/፡፡

በተጨማሪም ጾም ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት የምትጠቅም የስሜት ልጓም፤ እንዲሁም ኃይለ ፍትወትን የምናደክምባት መሣሪያ ናት፡፡ ‹‹ጾም ትፌውስ ቍስለ ነፍስ፤ ወታፀምም ኩሎ ፍትወታተ ዘሥጋ፡፡ ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና፤ ጾም የነፍስ ቁስልን ታደርቃለች፤ ተድላ ሥጋን ታጠፋለች፣ ለወጣቶች ርጋታን /ጭምትነትን/ ታስተምራለች» እንዳለ /ቅዱስ ያሬድ/፡፡ በሌላ በኩል ጾም ደካማው ሥጋ በነፍስ ላይ እንዳይሠለጥን የተሠራ ድንበር ነው፡፡ ምጽዋት በነዳያን በኩል የምታልፍ የገንዘብ ግብር እንደ ሆነች ሁሉ ጾምም ለአምላካችን ለንጉሠ ሰማይ ወምድር የምትቀርብ የሥጋ ግብር ናት፡፡ ‹‹ጾምሰ ጸባሕተ ሥጋ ውእቱ፤ በከመ ምጽዋት ጸባሕተ ንዋይ ይእቲ፤ ምጽዋት በነዳያን በኩል የምታልፍ የገንዘብ ግብር እንደ ሆነች ሁሉ ጾምም ለአምላካችን የምትቀርብ የሥጋ ግብር ናት» እንዲል /ፍት. መን. አንቀጽ 15/፡፡

Read more

መንፈሳዊ ሰው እና ሳይንሳዊ ምርምር (ክፍል ሁለት)

ጥያቄ ፫፡-  ሳይንሳዊ የምርምር ዘዴ ብዙ ጊዜ መነሻው ጥርጥር ነው፡፡ ማለት በአንድ ጉዳይ ላይ፣ በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ የሆነ የታወቀ ነገር ስለሌለ ከዛ ጥርጥር በመነሳት ነው ያን ነገር ወደ ማጥናት፣ አዲስ ግኝት ወደማግኘት የሚኬደው፤ ለአንድ መንፈሳዊ ሰው ዶግማዊ በሆኑ ነገሮች ተምሮ የአባቶቹን ትውፊት ተቀብሎ ከሚኖር መንፈሳዊ ሰው በነገሮች ላይ ከጥርጥር መነሣት አይከብደውምን? አያስቸግረውምን?

ዲ/ን ያረጋል፡- በመጀመሪያ የሳይንሳዊ ምርምር መነሻው ጥርጥር ነው የሚለው ከፊል እውነታ ነው ልንል  እንችላለን፤ የተወሰነ እውነታ አለው፡፡ ሙሉ ገጽታውና እውነታው ግን ይኼ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ምርምር ሳይንሳዊም ብንለው የሚነሣው ከእምነት ነው፡፡ የሆነ ነገርን ተቀብሎ ነው የሚነሣው እንጂ መቶ በመቶ ሁሉን ነገር አረጋግጦ የሚራመድ ምንም ሳይንሳዊ ዕውቀት የለም፡፡ የሚነሣው ምንም ከማይጠየቁ ነገሮች ነው፡፡ እነዚህ “አግዚየምስ” ይባላሉ፤ “ፖስቹሌት”ም ይባላሉ፤ እንደ ማኅበራዊ ሳይንስ ባሉት “ቲዎሪዎች” ደግሞ “አሳምፕሽን” ይባላሉ፡፡ እነዚህ ተቀምጠው በዛ መሠረት ነው “ቲዎሪ” የሚዳብረው፡፡ ያለ ምንም “አሳምፕሽን” “ቲዎሪ” ሊኖር አይችልም፡፡ እነዛ “አሳምፕሽኖች” የተረጋገጡ አይደሉም፤ እውነት መሆናቸው አይታወቅም፡፡ ምክንያቱም ማንም እውነታን “እንዲህ ብለን እናስብ” ብሎ መውሰድ አያስፈልገውም፡፡ ፀሐይ በምሥራቅ ትወጣለች ብሎ “አስዩም” ማድረግ ማንም አያስፈልገውም፡፡ ነገር ግን ያለነዚያ “አሳምፕሽኖች” ምንም ነገር ማውራት፣ ምንም ማድረግ ስለማይቻል የሆኑ ነገሮችን እንቀበል ብሎ ይነሣና ከዚያ በኋላ ነው ወደ ቀጣይ የሚሄደው፡፡ ስለዚህ ምንም ነገር መሠረቱ እምነት ነው፡፡ በየትኛውም መንገድ ቢሆን የሆነ ነገርን ከመቀበል ነው የሚነሣው፡፡ Read more

መንፈሳዊ ሰው እና ሳይንሳዊ ምርምር (ክፍል አንድ)

“መንፈሳዊ ሰው መሆን ሳይንሳዊ ምርምርን ለማከናወን አይመችም፡፡ መንፈሳዊ ሰው ተመራማሪ መሆን አይችልም፡፡” በማለት የሚናገሩ አካላት አሉ፡፡ በእርግጥ መንፈሳዊ ሕይወት ሳይንሳዊ ምርምር ለማከናወን እንቅፋት ሊሆን ይችላል? ለመንፈሳዊ ሰውስ ምርምር ምን ይጠቅመዋል? በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከእንግዳ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ እንግዳችን ዲ/ን ያረጋል አበጋዝ ናቸው፡፡

ጥያቄ ፩፡ በመንፈሳዊ ሰው እይታ ሳይንሳዊ ምርምር ማለት ምን ማለት ነው?

 ዲ/ን ያረጋል፡- ሳይንሳዊ ምርምር በራሱ ሊታይ የሚገባው እንጂ መንፈሳዊ ለሆነ ላልሆነ ተብሎ የሚከፈል አይመስለኝም፡፡ በራሱ ሳይንሳዊ ምርምር ምንድነው? የሚለውን ማየት እና ከዛ በኋላ ግን በዚህ ሳይንሳዊ ምርምር ወይም ሳይንሳዊ የዕውቀት ማግኛ መንገድ በሚባለው ውስጥ ያሉትን ጠንካራና ደካማ ጐኖች ማየቱ የተሻለ ይመስለኛል፡፡ Read more