ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ


ከመምህር ተፈሪ መንገሻ

ቅዱስ ጊዮርጊስ “የሰማዕታት ኮከብ” ተብሎ ይጠራል። እርሱ በምድራዊ ሥልጣኑና በሀብቱ ሳይወሰን፣ እውነተኛውን የክርስቶስን ፍቅር በመከራ ውስጥ ሆኖ መስክሯል። “እስከ ሞት ድረስ የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” (ራእ. ፪፥፲) የሚለው መለኮታዊ ቃል በሕይወቱ ተተርጉሞ እናገኘዋለን።
​ለዛሬው የግቢ ጉባኤ ተማሪ፣ የሰማዕቱ ጊዮርጊስ ገድል ትልቅ ትርጉም አለው። ግቢ ውስጥ የሚገጥሙን ልዩ ልዩ የሐሳብ፣ የሱስና የግብረገብነት ፈተናዎች እኛን ከእምነታችን ሊለዩን ሲሞክሩ፣ የሰማዕቱ ጽናት “እኔ ክርስቲያን ነኝ” ብሎ በድፍረት ለመቆም ጉልበት ይሆነናል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገሥታት ፊት የጸናው ለክርስቶስ ባለው ፍቅር እንደሆነ ሁሉ፣ እኛም በትምህርትና በማኅበራዊ ጫናዎች መካከል ሆነን ለሃይማኖታችን የታመንን እንድንሆን ያስተምረናል።
ይህንንም እንደሚከተለው በዝርዝር እንመለከታለን።

  1. የቅዱስ ጊዮርጊስ የተጋድሎ ታሪክ
    የሰማዕቱ ገድል እንደሚነግረን ቅዱስ ጊዮርጊስ መከራን የተቀበለው በፈቃዱ ነው፤ ይህም ለክርስቶስ ካለው ፍቅር የተነሣ ነው። ስለ ክርስቶስ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ. ፲፭፥፲፫) ተብሎ እንደተጻፈ፣ ሰማዕቱም ለክርስቶስ ያለውን ፍቅሩን በመከራ አሳይቷል። እነዚህ በቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ የደረሱ ሥቃዮች እንኳን ሊቀበሏቸው ለመነገር የሚከብዱየሰው ልጅ በራሱ ኃይል ሊወጣቸው የማይችላቸው ቢሆኑም፣ በሰማዕቱ ጽናት የአምላክ ኃይል ተገልጦባቸዋል።
    1.1. በመንኰራኩር መፈጨት :- ገድሉ እንደሚነግረን፣ ጨካኙ ንጉሥ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከእምነቱ ሊያስወጣው ባልቻለ ጊዜ፣ ልዩ በሆነ የማሠቃያ መሣሪያ መከራ እንዲያጸኑበት አዘዘ። ይህ መሣሪያ ጫፎቹ ስለት ያላቸው ጦሮች የተሰኩበት መንኰራኩር ነበር። ቅዱሱ በዚህ መሣሪያ ላይ ተጥሎ ሥጋው እስኪበታተን ድረስ ተቆራረጠ።
    በሰውኛ ሲታይ በሕይወተ ሥጋ ይቆያል ተብሎ የማይታሰብ ሁሉ ነገር ያበቃለት የሚመስልበት አስከፊ ሥቃይ ነበር።
    ይህ መፈጨቱ ግን ክርስቶስን ከመውደድ አላስቆመውም። ቅዱስ ጳውሎስ “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ ነው ወይስ ጭንቀት?…” (ሮሜ ፰፥፴፭) እንዳለው፣ የሰማዕቱ የቅዱስ ጊዮርጊስ እምነት ከመንኰራኩሩ ስለት በላይ የጠነከረ ነበር።
    በዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ሥጋን ሳይሆን መንፈሳዊ ማንነትን የሚፈጩ “ዘመናዊ መንኰራኩሮች” አሉ። እነዚህም የማይጠቅሙ የጓደኛ ግፊቶች፣ የሱስ ፈተናዎች፣ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጡ የትምህርት ጫናዎች ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህ ነገሮች ማንነታችሁን ሊያደቅቁ ሲሞክሩ፣ ማሸነፊያው መንገድ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በእምነት ጸንቶ መቆም ነው።
    1.2. በብረት ምጣድ ሥጋው መቆላት
    ​ ነገሥታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን በመንኰራኩር ከፈጩት በኋላ፣ አሁንም እምነቱን እንዲክድ ለማስገደድ በጋለ የብረት ምጣድ ላይ አድርገው ሥጋውን እንደ እህል ቆሉት። ይህ መከራ የቅዱስ ጴጥሮስን ቃል በተግባር ያሳየ ነው፦ “በእሳት እንደሚፈተን ወርቅ… እምነታችሁ ለምስጋናና ለክብር ይሁን” (፩ ጴጥ. ፩፥፯) ቅዱስ ጊዮርጊስ በእሳቱ ውስጥ አልጠፋም፤ ይልቁንም እንደ ንጹሕ ወርቅ ተፈትኖ ነጠረ።
    1.3. ሦስት ጊዜ ሞቶ አምላኩ እንዳስነሣው
    ​ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባቱ ዓመታት በተቀበላቸው መከራዎች ውስጥ ሦስት ጊዜ ለሞት ቢበቃም፣ አምላኩ ግን ለስሙ ክብርና ለከሐድያን ነገሥታት ተግሣፅ ይሆን ዘንድ ከሞት አስነሥቶታል። ጌታችን በዮሐንስ ወንጌል ፲፩፥፳፭ ላይ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ” እንዳለ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስም መነሣት ሞት የማይበግረው ኃያል አምላክ መኖሩ የሚገለጥበት ሆነ። በዚህም ብዙዎች በቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ አመኑ፤ በሰማዕትነትም ሞቱ። እምነት ካለ ሞት ራሱ የድል መጀመሪያ እንጂ የጉዞ ማብቂያ እንዳልሆነ ከዚህ እንረዳለን።
    ውድ የግቢ ተማሪዎች ሆይ! በትምህርት ውድቀት ወይም በሕይወት ፈተና ውስጥ ስትሰጥሙ “ሁሉ ነገር አበቃለት” ብላችሁ ተስፋ አትቁረጡ፤ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ እናንተንም ከውድቀት የማንሣት ኃይል አለውና። ጽናታችሁ ካላበቃ፣ ተስፋችሁ አይሞትም!
    1.4. በሰይፍ መቆረጥ
    ​ከሰባት ዓመታት መከራና ሥቃይ በኋላ፣ ነገሥታቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጽናት አፍረው በመጨረሻ በሰይፍ እንዲቀላ ፈረዱበት። ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሚያዝያ ፳፫ ቀን አንገቱን ለሰይፍ በመስጠት ምድራዊ ሩጫውን በድል አጠናቀቀ።
    “እስከ ሞት የታመንህ ሁን የሕይወትንም አክሊል እሰጥሃለሁ” (ራእ. ፪፥፲) ቅዱስ ጊዮርጊስ ለክርስቶስ ያለው ፍቅር በቃላት ብቻ ሳይሆን እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት የደረሰ እውነተኛ መሆኑን በዚህ አረጋገጠ።
    ሰባቱ ዓመታት ለሰማዕቱ ጊዮርጊስ የፍቅር መፈተኛ እንጂ የድካም ዘመናት አልነበሩም። አንገቱን ለሰይፍ ሰጥቶ፣ የሰማያዊውን መንግሥት አክሊል ተቀበለ።
    ብዙዎቻችሁ ትምህርታችሁን ወይም መንፈሳዊ ጉዟችሁን በመልካም ትጀምሩና መጨረሻው ላይ ስትደርሱ ትዝላላችሁ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ግን ለሰባት ዓመታት ታግሦ እስከ መጨረሻው ጸና።
    በግቢ ሕይወታችሁ ውስጥ “የመጨረሻው ውጤት” ላይ እስክትደርሱ ድረስ በማንነታችሁና በእምነታችሁ አትደራደሩ። ጅማሬያችሁ ብቻ ሳይሆን አጨራረሳችሁም ያማረ ይሁን።
  2. የቅዱስ ጊዮርጊስ ተአምራት
    የተአምራቱ ዓላማ ሰዎችን ለማስገረም ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ኃይል ከሰው ልጆች ድካም በላይ መሆኑን ለማሳየትና ከሐድያንን ወደ እውነት ለመመለስ ነው። ቅዱስ ዳዊት “እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው” እንዳለ። (መዝ. ፷፯፥፴፭)
    2.1. እንደ አምላኩ ሙት ማስነሣቱ
    ከሐድያን ነገሥታት ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመፈተን “አምላክህ እውነት ከሞት የሚያስነሣ ከሆነ፣ እነዚህን ጥንታውያን መቃብሮች ከፍቶ ሙታኑን ያስነሣልን” የሚል ጥያቄ አቀረቡለት። ቅዱስ ጊዮርጊስም በጸለየ ጊዜ መቃብራቱ ተከፍተው ሙታኑ ተነሥተው ወጥተዋል።
    ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው አልዓዛርንና የኢያኢሮስን ልጅ እንዳስነሣ ሁሉ፣ ለቅዱሳኑም ይህንኑ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ጌታችን “ሙታንን አስነሡ” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ትእዛዝና ሥልጣን ሰጥቷል። (ማቴ. ፲፥፰) እንዲሁም “በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል” በማለት ለሰጠው የተስፋ ቃል ማረጋገጫ ነው።(ዮሐ. ፲፬፥፲፪)
    ​ይህ ተአምር የተደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያመልከው አምላክ የሕያዋንና የሙታን ጌታ መሆኑን ለነገሥታቱና ለሕዝቡ ለማስረዳት ነበር። በመጽሐፈ ገድሉ እንደተጻፈ ይህን ድንቅ ያዩ ብዙዎች በክርስቶስ አምነው ለሰማዕትነት በቅተዋል።
    2.2. የደረቁ የዕንጨት ወንበሮችን ማለምለሙ
    ​ነገሥታቱ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመፈተንና በእርሱ ለማሾፍ፣ ከተለያዩ ዕንጨቶች ተጠርበው የተሠሩና ለረጅም ጊዜ የደረቁ ወንበሮች እንዲያለመልም ጠየቁት። ቅዱሱ በጸለየ ጊዜ እነዚያ ደረቅ ወንበሮች ወዲያውኑ ለምልመውና አብበው ታይተዋል። በዚህም አሳፍሯቸዋል።
    በትምህርትህ ወይም በሕይወትህ “የደረቀና ተስፋ የሌለው” የሚመስል ነገር ቢገጥምህ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ያንን ነገር ዳግም የማለምለም ኃይል አለው።
    2.3. የመበለቲቱን ቤት ምሰሶ ማለምለሙ
    ቅዱስ ጊዮርጊስ በእስርና በመከራ መካከል እያለ፣ ነገሥታቱ ለአንድ ሌሊት በአንዲት ድሃ መበለት ቤት እንዲታሰር አደረጉ። በዚያም ቅዱሱ በጸለየ ጊዜ፣ የቤቱ ደረቅ ምሰሶ ወዲያውኑ ለምልሞ፣ አብቦና ፍሬ አፍርቶ ታይቷል። ይህም አምላካችን እግዚአብሔር በምድረ በዳ ምንጭን እንደሚያፈልቅና የደረቀውን እንደሚያለመልም ያሳያል (ኢሳ. ፵፩፥፲፰) በእኛም ሕይወት የደረቁ የበረከት የመንፈሳዊነት ምንጮቻችንን በሰማዕቱ ጸሎት ያለምልምልን።
    2.4. በጣዖቱ አጵሎን ላይ ያደረውን ርኩስ መንፈስ ማስወጣቱ
    ንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስ ቅዱስ ጊዮርጊስን ወደ ጣዖት ቤት ወስዶ ለአጵሎን እንዲሰግድ በጠየቀው ጊዜና ቅዱሱ በፊቱ ቆሞ በጸለየ ጊዜ በውስጡ ተደብቆ የነበረው ርኲስ መንፈስ እየጮኸ እንዲወጣ አድርጓል። በዚህም ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ በስሙ አጋንንትን እንዲያወጡ የሰጣቸው ሥልጣን በሰማዕቱ ላይ ተገልጧል፡፡ (ማር. ፲፮፥፲፯)
    2.5. ዕውር፣ ዲዳ፣ ደንቆሮና ሽባ የነበረ የመበለቲቱን ልጅ ማዳኑ
    ቅዱሱ በእንግድነት ባደረበት ቤት የነበረው የመበለቲቱ ልጅ ደንቆሮ፣ ዲዳና ሽባ ነበረ። ቅዱስ ጊዮርጊስም በጸሎቱ ልጁን ፈውሶታል። ይህም የእግዚአብሔር ርኅራኄ በቅዱሳኑ በኩል ለተቸገሩት እንደሚደርስ ያሳያል።
    ብዙዎቻችሁ በአካል ጤነኞች ብትሆኑም፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችሁ ግን እንደ መበለቲቱ ልጅ የእግዚአብሔርን ቃል ለመስማት ጆሮአችሁ የተዘጋ (ደንቆሮ)፣ ስለ እምነታችሁ ለመመስከርና ለማመስገን ደግሞ አንደበታችሁ የተሳሰረ (ዲዳ) ሆኖ ይገኛል። በግቢ ሕይወት ውስጥ በጓደኛ ግፊትና በዓለማዊ ጩኸት ተውጣችሁ የኅሊናችሁን ድምፅ እንዳትሰሙ ተከልክላችኋል።
    ልጁ በቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎት እንደተፈወሰ፣ እናንተም ከዚህ መንፈሳዊ ድንቁርናና ዲዳነት ለመውጣት ወደ ቅዱሳኑ አማላጅነትና ወደ ንስሐ ሕይወት ቅረቡ። የቅዱስ ጊዮርጊስ አምላክ ዛሬም የልባችሁን ጆሮ የመክፈትና አንደበታችሁን የመፍታት ኃይል አለው።
    2.6. ያሠቃዩት የነበሩ ሰዎችን በጌታ ስም ማሳመኑ
    ይህ ምናልባትም ትልቁ ተአምር ነው፤ ምክንዪቱም የሰዎች ልብ ተለውጦ ወደ እውነት የሚመጣበት ነውና። ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲያሠቃዩ የነበሩ ወታደሮች፣ መኮንኖችና ንግሥቲቱ ራሷ (ንግሥት አሌክሳንድራ) የእርሱን ጽናትና ተአምራት አይተው በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ለሰማዕትነት በቅተዋል።
    ቅዱሱ በጽናቱ አማካኝነት የሰዎችን ልብ ከጣዖት አምልኮ ጨለማ ወደሚደነቅ ወደ ክርስቶስ ብርሃን አውጥቷል። ይህም ሰማዕትነት ሰውን የመግደል ሳይሆን፣ ሰውን የመማረክና የመለወጥ ኃይል እንዳለው ያሳያል።
  3. ቅድስናና ክብሩ
    የቅዱስ ጊዮርጊስ ቅድስናና ክብር፣ ለሰባት ዓመታት ላሳለፈው መከራና ለጸናበት እምነቱ በአምላኩ ዘንድ የተሰጠው ሰማያዊ ምላሽ ነው።
    3.1. የክብር አክሊላት
    ቅዱስ ጊዮርጊስ በምድር ላይ የነበረውን የሹመት ልብስና የወርቅ ካባ ስለ ፍቅረ ክርስቶስ አውልቆ ቢጥልም፣ በሰማይ ግን ከአምላኩ እጅ የማይጠፉ ሰባት የብርሃን አክሊላትን ተቀዳጅቷል። እነዚህ አክሊላት ዝም ብለው የጌጥ ዘውዶች ሳይሆኑ፣ ሰማዕቱ ላሳለፋቸው ሰባት የመከራና የሥቃይ ዓመታት ለጠበቀው ቅድስናና ጽኑዕ ተጋድሎ የተሰጡ የድል ምልክቶች ናቸው።
    ቅዱስ ጳውሎስ “የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል” (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፰) ብሎ እንደተናገረው፣ ይህ ሰማያዊ ሽልማት ቅዱስ ጊዮርጊስ ላሳየው ተጋድሎና ለጠበቀው ሃይማኖት የታመነ ምስክርነት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ሩጫውን በድል እንደጨረሰ ሁሉ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስም ለሰባት ዓመታት የደረሰበትን እልህ አስጨራሽ መከራ በትዕግሥት አልፎ “መልካሙን ገድል” በመጋደሉ፣ ጻድቅ ፈራጅ ከሆነው ከጌታ ዘንድ ሰባቱን የማይጠፉ የብርሃን አክሊላትን ተቀዳጅቷል። ይህም አክሊል እንዲሁ የሚሰጥ ሳይሆን፣ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ አገላለጽ እስከ መጨረሻው ለጸናና ሃይማኖቱን ለጠበቀ የሚሰጥ የድል ምልክት በመሆኑ፣ የሰማዕቱ ጽናት የጳውሎስን ትምህርት በተግባር የገለጠ ነው።
    በዚህም በቤተክርስቲያናችን ሰማዕቱ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት የሥቃይ ብዛት የተነሣ ሊቀ ሰማዕታት በመባል ይጠራል።
    3.2. ቃልኪዳን
    ሰማዕቱ ባደረገው ጽኑዕ ተጋድሎ ምክንያት ከእግዚአብሔር ዘንድ ባለመዋዕልነትን በማግኘት በእርሱ አማካኝነት ሰዎች የሚጠቀሙበት ቃል ኪዳንን ሰጥቶታል።
    ጌታችን ለቅዱስ ጊዮርጊስ “ስምህን የጠራውን፣ መታሰቢያህን ያደረገውን፣ በስምህ ለተቸገረ ምጽዋት የሰጠውን ሁሉ እምርልሃለሁ፤ ከጭንቅም አወጣዋለሁ” የሚል ታላቅ የተስፋ  ቃልኪዳን ገብቶለታል።
    ይህም ጌታችን በማቴዎስ ወንጌል (፲፥፵፩) ላይ “ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢዩን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል” ብሎ ያስተማረውን መለኮታዊ ሕግ ያረጋግጥልናል።
    ይህ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቃል ኪዳን ለተጨነቁት መውጫ፣ ለታመሙት ፈውስ፣ ለተማሪዎችም ረድኤት የሚሆን የመንፈሳዊ መጠበቂያ ነው።
    እኛስ?
    የቅዱስ ጊዮርጊስ የሰባት ዓመታት ተጋድሎ ለሁሉም ክርስቲያኖች በተለይ ለዘመኑ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችና ወጣቶች እንዲሁ የታሪክ ማስታወሻ ሳይሆን፣ በፈተና ለተከበበው ማንነታቸው ሕያው የጽናት መመሪያ ነው።
    ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምን እንማር?
    ፩. የማንነት ኩራትና በራስ መተማመን
    ቅዱስ ጊዮርጊስ በንጉሥ ዲዮቅልጥያኖስና በ፸ው ነገሥታት ፊት ሲቆም፣ መኮንንነቱንና ምድራዊ ክብሩን ሳይሆን ቀድሞ የተናገረው “እኔ ክርስቲያን ነኝ” የሚለውን ማንነቱን ነበር። ይህም በታላቅ ድፍረትና በራስ መተማመን የተገለጠ ማንነት ነው።
    አንተም አንቺም በግቢ ቆይታህ/ሽ የተለያዩ የርእዮተ ዓለም ግፊቶች፣ “ዘመናዊነት” ተብለው የሚቀርቡ ግን እምነትንና ማንነትን የሚያጥላሉ ሁኔታዎች ሊገጥሙ ይችላሉ። ተማሪዎች እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማንነታቸውን ሳይደብቁ፣ በእምነታቸውና በመልካም ባህላቸው ኮርተው እንዲኖሩ ያስተምራቸዋል።
    ይህ የማንነት ኩራት በግቢ ሕይወት ውስጥ “ብቸኛ” ለመሆን ድፍረት ይሰጣል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ለብቻው በብዙዎች ፊት መቆሙ፣ ዛሬ ተማሪዎች ከጓደኛ ግፊት (Peer Pressure) ወጥተው ለራሳቸው ዕሴት ታማኝ እንዲሆኑ ትልቅ ትምህርት ነው።
    ፪. ለእውነት መቆም
    ቅዱስ ጊዮርጊስ በነገሥታት ፊት የቆመው ለግል ጥቅሙ ሳይሆን ለተገለጠለት እውነት (ለክርስቶስ) ነው። ነገሥታቱ በሐሰተኛ ክስና በጣዖት አምልኮ ሊያውኩት ሲሞክሩ እርሱ ግን “እውነት” ዋጋ እንደሚያስከፍል እያወቀ አልተረበሸም።
    “እውነትንም ታውቃላችሁ እውነትም አርነት ያወጣችኋል” (ዮሐ. ፰፥፴፪) እንዲል።
    ​ተማሪዎችም በግቢ ሕይወት ውስጥ የሐሰት ወሬዎች፣ ኩረጃና ኢ-ፍትሐዊ አሠራሮች እንደ ትክክለኛ መንገድ ሊቆጠሩ ይችላሉ። ተማሪዎች አካሄዳቸው ከብዙኃኑ ጋር ባይገጥም እንኳ፣ እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለኅሊና እውነትና ለሃይማኖታዊ ዕሴቶቻቸው ጸንተው በመቆም የሐሰትን ማዕበል መቋቋም እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል።
    ፫. በትዕግሥት መጽናት
    ሰባት ዓመት ሙሉ በመንኮራኩር መፈጨት፣ በኖራ ጉድጓድ መጣልና ልዩ ልዩ ሥቃዮችን ማሳለፍ የሚቻለው ከተራ ሰው በላይ በሆነ ትዕግሥት ነው። ይህ ጽናት መከራውን ወደ ድል የቀየረበት ጥበቡ ነው።
    ለእውነት መቆም ማለት ማንኛውም ዓይነት መሥዋዕትነትን ስንከፍልለት የዚያን እውነት ምንነት አውቀነዋል ማለት ነው። ስለዚህ ለመሥዋዕትነቱ ጽናትና ትዕግሥት ያስፈልጋል።
    ጌታችንም “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” (ማቴ. ፲፥፳፪) በማለት ተናግሯል።
    ዛሬም ተማሪዎች የትምህርት ጫና፣ የውጤት መዛባትና የኑሮ ውድነት ወዘተ. ተማሪዎችን ለተስፋ መቁረጥ ሊዳርጓቸው ይችላሉ። ቅዱስ ጊዮርጊስ በመከራው ውስጥ እንዳልተሸነፈ ሁሉ፣ ተማሪዎችም ፈተናዎችን እንደ ስብእና መገንቢያ ወይም እንደ የማንነት መብሰያ በመቁጠር፣ በጸሎትና በጥንካሬ እስከ መጨረሻው እንዲጸኑ ትልቅ የሞራል ጉልበት ይሰጣቸዋል።
    ፬. ቅድሚያ የሚሰጠውን ነገር ማወቅ
    ቅዱስ ጊዮርጊስ የሀብትና የሹመት ባለቤት ነበረ፤ ነገር ግን ከምድራዊ ክብር ይልቅ ሰማያዊውን፣ ከጊዜያዊ ደስታ ይልቅ ዘላለማዊውን መርጧል። “ቅድሚያ የምሰጠው ለአምላኬ ነው” በማለት ዓላማውን ለይቷል።
    ጌታችን በወንጌሉ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ፥ ይህም ሁሉ ይጨመርላችኋል” (ማቴ. ፮፥፴፫) ብሎ እንደተናገረው።
    በተለይ በዚህ ዘመን በግቢ ውስጥ ትኩረትን የሚሰርቁ ብዙ ነገሮች (ሱስ፣ ከንቱ መዝናኛዎችና ዓላማ ቢስ ግንኙነቶች፣ መገናኛ ሚዲያዎች ወዘተ) አሉ። ተማሪዎች እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባውን “ዋና ዓላማቸውን” (ትምህርታቸውንና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን) በመለየት፣ ሁለተኛ ደረጃ ለሆኑ ነገሮች ውድ ጊዜያቸውንና ማንነታቸውን አሳልፈው መስጠት እንደሌለባቸው ያሳያል።
    ​፭. ለሌሎች መድረስ
    ቅዱስ ጊዮርጊስ የሞተውን በማንሣት፣ የታመመውን በመፈወስና መበለቶችን በመርዳት የታወቀ ነው። የገዛ ሥቃዩ ሳይበግረው ለሌሎች መዳን ምክንያት ሆኗል።
    እኛም የወጣትነት ጉልበትና ዕውቀት ለራስ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ሊተርፍ ይገባል። ተማሪዎች በግቢ ቆይታቸው እርስ በርስ በመረዳዳት፣ የተቸገሩትን በማገዝ (Tutorial በመስጠትም ይሁን በምክር) እና የወጣትነት ትኩሳታቸውን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማዋል የጊዮርጊስን ፈር እንዲከተሉ ይመክራቸዋል።
    የሊቀ ሰማዕታት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጸሎቱ፣ አማላጅነቱ፣ በረከቱ አይለየን። ስብሐት ለእግዚአብሔር🙏🙏🙏
0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *