‹‹የምንጾመው ለምንድን ነው?›› የጾም ጥቅም፣ ዓላማና አስፈላጊነት

ለሜሳ ጉተታ

ጾም፣ ጸሎትና የንስሐ ሕይወት የማይነጣጠሉ የክርስትና ሕይወት መሠረቶች ናቸው፡፡ ጾም በሃይማኖትና በምግባር ለመጽናት ከክፉ አሳብና ምኞት እንዲሁም ተግባር ለመጠበቅ የምግባር ፍሬንም ለማፍራት ይረዳል፡፡ ጾም ፍትወተ ሥጋን፣ የዓለምን ሀሳብ፣ ምኞትና ተግባሩን ለመጥላት የመንፈስ ፍሬን ለማፍራት ከሥጋ ፍሬ ራስን ለመጠበቅ መንግሥቱን ለመውረስ የእርሱ ጥበቃን ለማግኘት ይረዳል፡፡ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን፣ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት ይረዳል፤ ምሥጢር እንዲገለጥልንም ያደርጋል፡፡ ጾም የመንፈሳዊ ተግባራትና የበጎ ሥራዎች ሁሉ መነሻ መሠረት/መገኛና መጀመሪያ ነው፡፡

ጾም ሥጋን ለመንፈስ ለማስገዛት፣ በመንፈሳዊ ሕይወትና በአገልግሎት ለመበርታት ለመጽናት፣ ለእግዚአብሔርም ለመገዛት ይረዳል፡፡  ያለ ጾም በመደዳ መብላትና መጠጣት፣ ያለ ልክና አግባብ ሥጋን ያበረታል፤ በአንጻሩ መንፈስን ደግሞ ያዳክማል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ኃጢአትና በደልን ክፋትን ያሠራል፤ ለዓለምና ለሥጋ ሀሳብ ፍላጎትና አምሮትም ያስገዛል ፍላጎታችን ፤ ሥጋችን እና አሳባችን በነፍሳችን ላይ እንዲሠለጥን ያደርጋል፡፡ ጾም ከዚህ ሁሉ ይጠብቃል፡፡ ጾም ለትሩፋት ያተጋል፡፡ አብዝቶ መብላትና መጠጣት ለፍትወት ያነሣሣል፡፡ ይህ ደግሞ የሰው መልአካዊና ሰማያዊ ብሎም መንፈሳዊ ማንነቱን ንጽሕናና የቅድስና ሕይወቱን ለማቆሸሽ ይዳርጋል፡፡ ክርስቲያን ሕይወቱን በጾም በጸሎትና በንስሐ የሚመራ መንፈሳዊ ሰው መሆን አለበት፡፡ ሮሜ.7፡1፡፡          

ይህ እየታወቀ ግን አሁንም ትውልዱ ‹‹ለምን እንጾማለን?›› በሚል ጥያቄ ተወጥሯል፡፡ ያለንበት ወቅት እና የምንኖርባት ዓለም በልዩ ልዩ ጥያቄዎች የተሞላች ምድር ናት፡፡ ደግነትም ክፋትም የሚንጸበረቅባት ዓለም ናት፡፡ ክርስቲያን  ሁሉን የማወቅ የመመርመር መልካሙን እና ክፉዉንም የመለየት መልካሙንም የመምራጥ ግዴታ እና ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥም መጠየቅ ከክፋት ራስን ለመጠበቅ ብሎም በጎዉን ለመሥራት ይረዳል፡፡ ለዚህ ነዉ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም መርምሩ መልካሙንም ያዙ’’ የሚለን (1ተሰ.5፥20-21)፡፡

አይታይ፣ አይጨበጥ፣ አይዳሰስ፣ አይነገር፣ አይተረክ የነበረው ይህ ዓለም ለምን እንዲታይ እንዲዳሰስ እንዲተረክ ሆነ ብሎ መጠየቅ  አላዋቂ አያሰኝም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የፍጥረተ ዓለምን ዓላማ  ለመረዳት፣ ተረድቶም ድርሻን ለመወጣት እስከሆነ ድረስ ተገቢ ነውና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለምን እንደሚጾም ለሚጠይቅ ሰውም ግልጽ ማብራርያ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡- ጾም ለክርስቲያኖች  መንፈሳዊ ተግባር እና ግዴታ መሆኑን፣ መንፈሰዊ ሰው እንደሚያደርግ፣ ከፈተና እንደሚጠብቅ፣ በሃይማኖት እና በምግባርም እንደሚያጸና፣ ለአገልግሎት እንደሚያተጋ፣ ሰውነትን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት ራስንም ከኃጢአት ከክፋት ከደበል ለመጠበቅም እንደሚረዳ፣ ከፈቃደ ሥጋ፣ ከተግባረ ዓለም፣ ከከንቱ ምኞት እና ሃሳብም እንደሚጠብቅ፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችንም እንድናፈራ እንደሚያግዘን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ጾም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው፡፡ ጾም ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ተግባርና ሕግ እንዲሁም ግዴታቸውም ጭምር ነው፡፡ ያለጾም ክርስቲያንና መንፈሳዊ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም የሃይማኖት መገለጫ እና መሠረት ነው፡፡ ጾም ለግል ሕይወት ለሀገር ለቤተ ክርስቲያን ለቤተሰብ ብሎም ለዓለም ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

እናም በአጭሩ፡-

  1. ጾም ሥጋን ለነፍስ ለማስገዛት ይረዳል፡፡

ሥጋችን ሁሉ ጊዜ ምቾትና ድሎትን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሥጋ ከመንፈስና ከነፍስ በላይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሥጋ ሲሠለጥንብን የመንፈስ ተግባርን መሥራት ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን መወጣት መተግበር ንስሐ መግባት፤ ምሥጢራት ላይ መሳተፍ በጎና መልካም ሥራን መሥራት ቃለ እግዚአብሔርን መማር፤ መተግበር ያዳግተዋል፡፡ ይህ በተራው ነፍስንና መንፈስን ያቀጭጫል፤ ሕይወትንም ያሳጣል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ሁሉ ጥፋት ለመዳን ጾም ትልቅ ልጓም በመሆን ያገለግላል፡፡ ጾም ሥጋን ለነፍስ ያስገዛል፡፡ ሁልጊዜ ስለነገረ እግዚአብሔር፣ ስለ መንፈሳዊነት እንድናስብ፣ ስለ ሕይወትና ሞት፣ ስለመልካም ሥራ፣ ስለ ቅድስና እና ስለ በረከት እንድናስብ ያደርጋል፡፡ ንስሐ እንድንገባ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን ሁሉ ሕይወቱን በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሕይወት መምራት አለበት፡፡ ገላ.5፡16-17፣ ሮሜ.8፡5-6፡፡

የሥጋ ፈቃድ እና ተግባርን የሚፈጽሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይችሉም፡፡ ከዚህ ለመውጣት መንግሥቱን ለመውረስ ደግሞ ሕይወትን በጾም መምራት ያስፈልጋል፡፡ ሕይታቸውን ያለ ጾም ጸሎት እና ንስሐ የሚመሩ ሰዎች  የእነሱ ሕይወት መጨረሻው የዘለዓለም ሞት ነው፡፡ እናም ራስን ለመጠበቅ እናም መንግሥቱን ለመውስ መጾም ይኖርብናል፡፡

  1. ጾም ከእግዚአብሔር የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ ይረዳል፡፡

ክርስቲያን ያለ ጾም  ሕይወቱ ባዶ ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር የምንፈልጋቸው ነገሮችን ለማግኘት እርሱን በጾም እንማጸናለን፡፡ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ቸርነትን፣ ይቅርታን፤ ጤናን፤ በረከትን፤ የእርሱን ጠብቆቱን እንለምንበታለን፡፡ ከኃጢአት እንዲጠብቀን፣ በሃይማኖት እንዲያጸናን፣ በምግባር፤ በመንፈሳዊ ሕይወትና በአገልግሎት፤ በምግባር እንዲያበረታን እርሱን እንማጸናለን፡፡ የሳሙኤል እናት ሐና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሰውን የሚያክብር፣ ታማኝ ታዛዥ ቅን ትሁት የሆነ ልጅን ያገኘችው በጾምና በጸሎት ሕይወት ነው፡፡ በቤቱ በመመላለስ ደጅ በመጥናት ሳትሰለች፣ ተስፋም ሳትቆርጥ በጽናት በእምነት በመለመን ነው፡፡ እኛም ከእርሱ የምንፈልገውን ነገር ማግኘት የምንችለው ያለ ትዕቢት በትዕግሥት በመለመን፣ በጽናትና በተስፋ በቤቱ በመጽናት ስንለምን ብቻ ነው 1ኛ.ሳሙ.2፡1፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን የሆነውን ታቦትን የተቀበለው ከዐርባ ቀናት የጾምና የጸሎት ሕይወት በኋላ ነው፡፡ ዘጸ.34፡1-31፡፡ እኛም ዛሬ ለብዙ ችግሮቻችን ከእርሱ መልስን ለማግኘት ሕይወታችንን በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሕይወት መምራት ይኖርብናል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ እና ዳንኤል ሃይማኖትን በምግባር ገልጸው ከሞት ባሕር የተሻገሩት ሕይወታቸውን በጾምና በጸሎት፣ እግዚአብሔርንም በመፍራት ይመሩ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬም እኛ ከማናውቃቸው ክፉ ነገሮች እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ ሕይወትን በጾምና በጸሎት መምራት ያስፈልጋል፡፡

ጾም የልባችንን መሻት ለእግዚአብሔር ለመግለጽ ይረዳል፡፡ ስናውቅም ሆነ ሳናውቅ የምንሠራው ኃጢአት ከእግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ከረድኤተ እግዚአብሔር፣ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያራቁታል፡፡ ስለዚህም ለምሕረት፣ ለቸርነት እና ለይቅርታ ማልቀስ ይኖርብናል፡፡ ጾም ከበደልና ከኃጢአት እንመለስ ዘንድ ንስሐን በመግባት ከእግዚአብሔር ምሕረት፤ ቸርነትና ይቅርታን ለማግኘት የምንፈጽመው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ ጾም በሃይማኖት ያበረታል፤ ከመከራ ሥጋና ነፍስም ያሻግራል፤ በጎ ምግባርንም ለመሥራት ያተጋል፡፡

ማጠቃለያ ፡-

የጾም መሠረታዊ ዓላማ ከምግብ ዓይነት መቆጠብ ከመመገብ እና ካለመመገብ ጋር የሚያያዝ ብቻ ሣይሆን ከምግብ በመራቅ በሚገኘው ውጤት ላይ ነው፡፡ ውጤቱም ፈቃደ ሥጋን በማሸነፍ መንፈሳውያን መላእክትን  መስሎ መኖር ወይንም መሆን ነው፡፡ እንዲሁም ራስን፣ ዓለምን፣ ክፉ ሃሳብ፣ ተግባር እና ምኞትን በማሸነፍ መንፈሳዊ መሆን፣ ራስንም ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡

ከጾም ዋጋን ለማግኘት በዋናነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾማችንንም በፍቅር፣ በምግባር፣ በሃይማኖት እና በእምነት ልንፈጽመው ይገባል፡፡ ለተራቡት ማሰብ፣ ለተጨነቁት መድረስ፣ ተሰፋ ላጡትም ተሰፋ መሆን ይኖርብናል፡፡ ጾማችንንም በንሰሐ ሕይወትና በጸሎት ልንፈጽመው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ፈቃደ ሥጋን በማሸነፍ፣ ይልቁንም ከትዕቢት በመራቅ፣ ትሕትናንም ገንዘብ በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡ ጾሙን ጹመን ለመንግሥቱ እንዲያበቃን ከክፉ ነገርም እንዲጠብቀን  የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡

የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜ እና ፍችዎቻቸው

በገብረ እግዚአብሔር ዘይኵኖ

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስሙ ጐልቶ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ በዐቢይ ጾም ውስጥ ለሚገኙ ሳምንታት የየራሳቸው መጠሪያ በመስጠቱ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለሳምንታቱ ስያሜዎችን ሲሰጥ ጌታችን የሠራቸውን የቸርነት ሥራዎችን፣ ያስተማራቸው ትምህርቶችን፣ ተጠቅሟል፡፡ በአጠቃላይ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ሳምታት ሲሆኑ ስያሜአቸውን እና ትርጓሜያቸውን  በሚከተለው መልኩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

  1. ዘወረደ

የጌታችንና የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ወደ ምድር መውረድ በሥጋ ብእሴ መገለጽ የሚነገርበት፣ የሚታሰበብበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ የሚሰበከው ምስባክ፤ የሚነበበቡት ምንባባት እንዲሁም የሚተረጎመው ወንጌል ይህንኑ ኹኔታ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

በዘወረደ ሳምንት ከሚነበበው ምንባብ ወንጌልን ብንመለከት በዋናነት የዮሐንስ ወንጌል ተጠቃሽ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹…. ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው›› (ዮሐ.3፥12-13) የሚለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ›› ተብሎ የተጠራው በተለየ አካሉ ሰው ኾኖ የተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ከመንጸፈ ደይን ለማዳን ወደ ምድር የወረደ፤ ይፈጽመው ዘንድ ያሰበውን ኹሉ አካናውኖ ወደ አባቱ ያረገ መኾኑ በንባቡ ተረድተናል፡፡ በአጠቃላይ የዘወረደ ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መውረድና መወለዱ የሚነገርበት፣ የሚታሰብበት ነው፡፡ ፈጣሪያችን በፍጹም ፍቅር እና በትሕትና ወደዚህች ምድር መውረዱን፣ መከራ መሰቀሉን እያሰብን  እኛም በበደል  የሚገኙትን ኹሉ በመናቅ እና በማቃለል ሳይሆን በፍቅር ልንቀርባቸው እና ልናገለግላቸው እንደሚገባ እናስተውላለን፡፡

  1. ቅድስት

ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት የሰጠው ስያሜ “ቅድስት” የሚል ነው፡፡ ቅድስት ‹‹ቀደሰ›› ከሚለው ሥርወ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ቀደሰ፣ ለየ፣ አከበረ የሚል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቅድስት የሚለው ቃል የተለየች ክብርት ንጽህት የሚል ትርጔሜ ይሰጠናል፡፡ ቅዱስ የሚለው ቃል የባሕርይ ቅድስና ካለው ከእግዚአብሔር  በጸጋ የቅድስና ሀብት ለተሰጣቸው አካላት ኹሉ ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ፡- ቅዱሳን ሰዎች፣ ቅዱሳን መላእክት፣ ቅዱሳት መካናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እና ቅዱሳት ዕለታት ይገኙበታል፡፡ በዚሁ መሠረት የሰንበትን ቅድስና አስመልክቶ ጌታችን ያስተማረው ትምህርት በዜማ (በምስባክ) እንዲሁም በንባብ እየተነበበ በዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሣምንት ይተረጎማል፡፡

“እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፤ አሚን መሠናይት ቅድሜሁ፤ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፤ ምስጋናና ውበት በፊቱ፣ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው” (መዝ. 95፥5-6) ከሚለው የዳዊት መዝሙር ተወስዶ የሚሰበከውን ምስባክ መምህራን እየተረጎሙ ያስተምሩበታል፡፡ “ቅድስት” በተሰኘች የዐቢይ-ጾም ሳምንት ማቴ. 6 ከቁጥር 16-25 ያለው የጌታችን ትምህርት ይነበባል፤ በሊቃውንት ተተርጎሞ ትምህርት ይሰጥበታል፡፡

  1. ምኩራብ

አምልኮተ እግዚአብሔር ለመፈጸም አይሁድ ከሚሰባሰቡባቸው ስፍራዎች ዋነኛው ምኩራብ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ያሬድም ሦስተኛዋን የዐቢይ ጾም ሳምንት “ምኩራብ” በሚል ስያሜ የሰየመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ውስጥ ተገኝቶ የቤተ መቅደስን ክብር ማስጠበቁን በማሰብ ነው፡፡ በዚህች ሳምንት የሚሰበከው የዳዊት መዝሙር “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዐሌየ፤ ወቀጻእክዋ በጾም ለነፍስየ” የሚለው ነው ፡፡ ይኸውም “የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና፣ ነፍሴንም በጾም ቀጣኋት” ማለት ነው (መዝ.68፥9-10)

ቤተ ጸሎት የተባለች ምኩራብን ከግብሯ ውጪ ለመነገጃና መለወጫ ተግባር ያዋሏትን ነጋዴዎችና ለዋጮች ጌታቸን በጅራፍ እየገረፈ ርግቦችንና ሌሎች እንስሳትን ከቤተ መቅደስ በኅይል ሥልጣኑ አስወጥቷል (ዮሐ.2፥12- ፍ.ም)፡፡ ከዚሁ አንፃር አማናዊና ሕያው “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ” የተባለ ሰው ልጅ ሰውነት ከተፈጠረበት ዓላማ ውጭ ሌላ ተግባር ቢፈጸምበት እግዚአብሔር እንደሚቀጣ የሚስያገነዝቡና በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡ ኃይለ ቃላት  እየተነበቡ የሚተረጎሙበት ሳምንት ነው፡፡(1ኛ ቆሮ.6፥16-17)

  1. መፃጉ

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የማዳኑ ጉዳይ ጎልቶ ከሚነገርባቸው ጊዜያት አንዱ ይህ “መፃጉ’’ የተሰኘው ሳምንት ነው፡፡ “መፃጉ” ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ አምላካችን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዚህች ምድር ሲመላለስ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ የገላገላቸው መኾኑን የሚያሰረዱ የምስክርነት ቃሎች የሚሰሙበትን ጊዜ ቅዱስ ያሬድ “መፃጉ” በማለት ጠርቶታል፡፡

በመፃጉ ሳምንት የሚሰበከው ምስባክ፡- ‹‹እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እም ደዌሁ፤ አንሰእቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ›› የሚለው ነው ፡፡ በመዝሙር 40 ላይ የሚገኘውን ይህንን ቃል ዲያቆኑ ከፍ ባለ ዜማ ከሰበከ በኋላ በዮሐንስ  ወንጌል ምዕራፍ 5 ላይ  ያለው ይነበባል፤ ይተረጎማል ፡፡ በደዌ ሥጋም ኾነ በደዌ ነፍስ የተያዝን የሰው ልጆች የፈጣሪያችንን ምሕረትና ቸርነቱን እንደምናገኝ ተሰፋ የምናደርግባቸው ገቢረ ተአምራት ይሰማሉ፡፡

በአጠቃላይ እኛም ከዚህ ታሪክ ብዙ ነገሮችን እንማራለን፡፡ የመጀመርያው ሰውን መውደድን ማፍቀርን፣ ለሰው ድኅነት ብሎ ዝቅ ማለትን፣ ትሕትናን እንማራለን፡፡ የክርስትና ሕይወት የፍቅር፣ የሠላም፣ የአንድነት ሕይወት ነው፡፡ ለራስ ብቻ የሚኖሩት ሕይወት ሳይሆን ለሌሎችም መዳን ዝቅ ማለት ነውና እኛም ይህን በዓልን ስናከብር ጾሙንም ስንጾም ይህን ታሳቢ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

  1. ደብረ ዘይት

“ደብረ ዘይት” የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ተራራ ማለት ነው፡፡ በዚያ ተራራ ላይ የወይራ ዛፍ በብዛት ስለሚበቅል ስያሜውንም በዚያው አንጻር አግኝቷል፡፡ በደብረ ዘይት ላይ የዓለም ፍጻሜ ምን እንደሚመስል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ “እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ቀርበው ንገረን  ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው“ ? አሉት /ማቴ 24፡3/ የዓለም ኅልፈት መቼ እንደሆነና ምልክቱ ምን እንደሆነ ለተጠየቀው ጥያቄ ጌታችን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የዓለም ኅልፈት በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የምትታወቅ እንጂ ቀኒቱ ለሰው ልጅ ተለይታ የማትታወቅ መሆኗን ተናግሯል፡፡

ኅልፈተ ዓለም መቼ ይሆናል ?

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ምጽአት ቀንና ሰዓት ከመግለጹ ባሻገር “ያን ግን እወቁ፤ ባለቤቱ ከሌሊት በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ፣ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” በማለት አሳስቧል (ማቴ. 24፥43-44)፡፡  በቤቱ ያለውን ንብረት እና ሀብት ዘርፎ እንዳይወስድበት ባለቤቱ ነቅቶ እንደሚጠብቅ በሌባ የተመሰለ መልአከ ሞት የምእመናን ሕይወት በንሰሐ ሳይዘጋጅ እንዳይነጥቅ በንሰሐ፣ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲሁም በሥርዓተ ቍርባን ተወስኖ መቆየት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡  በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች እግዚአብሔር ለንስሐ ብሎ በሰጣቸው አንድ መቶ ሃያ ዓመታት መጠቀምን አልወደዱም፤ ይልቁንም ሌላ ኃጢአት ለመፈጸም ጊዜውን ሲከፋፍሉት ታይተዋል፡፡ በመቶ ዓመታት ፈቃደ ሥጋን ፈጽመው በቀረው ሃያ ዓመት ንስሐ እንደሚገቡ ሲያቅዱ ታይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የንፍር ውኃ ድንገት ከሰማይ ወርዶ አጥፍቷቸዋል፡፡ መቅሰፍቱ የኖኅ ዘመን ሰዎችን ድንገት እንዳገኛቸው መልአከ ሞትም ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሏል (ማቴ. 24፥44)

የኅልፈተ ዓለም ምልክቱ ምንድን ነው?

ጌታችን ኅልፈተ ዓለምን አስመልክቶ ከቀረቡለት ጥያቄዎች  ከዳግም ምጽአት በፊት ከሰባት በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች በምልክትነት የሚታዩ መሆናቸውን ገልጾአል፡፡ ከዚህም መካከል፡- የሀሰተኞች ነቢያት መነሣት፣ የጥፋት ርኲሰት በተቀደሰው ስፍራ መታየት፣ የፍቅር መቀዝቀዝ እንዲሁም ጦርና የጦር ወሬ መስማት በምልክትነት ከቀረቡት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ምስባክና ወንጌል

ደብረ ዘይት የሚሰበከው ምስባክ ‹‹እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይወጣል፤ አምላካችን ይመጣል፣ ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል” (መዝ 49-3) የሚለው ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ያለው ገጸ ንባብም እየተተረጎመ ትምህርት ይሰጥበታል፡፡

  1. ገብር ኄር

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት የሚጠራበት ስያሜ  “ገብር ኄር” የሚል ነው፡፡ መልካም የኾነ  አገልግሎትን ፈጽመው ከፈጣሪያቸው ምስክርነት የሚያገኙ ሁሉ በዚህ ስም ይጠሩበታል፡፡ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍርድ ቀን “ኑ፣ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፡- ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥት ውረሱ” ብሎ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባቸው የታመኑ አገልጋዮችን መሆኑ ታውቋል (ማቴ.25፥34)፡፡

መልካም አገልጋዮች የተባሉት (የሚባሉት) በሃይማኖት ጸንተው በፈጸሟቸው በጎ ሥራዎች ነው፡፡ ማለትም “ይህ ፈጣሪአችን እንፈጽመው ዘንድ ያዘዘን የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ በእርሱ እርዳታና ቸርነት ይህን ሥራ ሠርተን ዋጋ  እናገኝበታለን፣ እንጠቀምበታለን” በሚል እምነት በጎ ሥራ ሠርተው የሚወርሱት ነው፡፡ “መልካም አገልጋይ” ተብሎ በእግዚአብሔር ዘንድ መመስገንም ኾነ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ በፈጣሪ ቸርነት ብቻ ሳይሆን በሠሩት ክርስቲያናዊ የተቀደሰ ተግባርም ነውና፡፡

የሚያስመሰግነው ክርስቲያናዊ ተግባር

ማንኛውም ክርስቲያን ሃይኖማቱን የሚገልጠው  በበጎ ሥራው ወይም በአኗኗሩ ጭምር ነው፡፡ ማመኑ ብቻውን አያስመሰግነውም፡፡ ይልቁኑ ከበጎ ሥራ የተለየ ሃይኖማትን ብቻ ቢይዝ ምንም እንደማይረባው በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጦ ይገኛል፡፡

የክርስትና ሃይማኖት ደግሞ በጎ ሥራን ጭምር ይጠይቃል እንጂ ከሥራ የተለየ እምነት ብቻ  ክርስቲያን አያደርግም፡፡ ትእዛዛቱንና ሕጉን ሁሉ መፈጸም እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” በማለት አሳስቧል (ያዕቆ.1፥22)፡፡  ስለሆነም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያበቃውንና በሃይማኖት መፈጸም ያለበትን በጎ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ ስለዚህ ነው፡- ‹‹የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም›› (ማቴ. 7 21) በማለት ጌታችን ያስተማረው፡፡

መንግሥተ ሰማያትን መውረስ

 ክርስቲያኖች ሁሉ የተጋድሎአቸው ውጤቶችና የተፈጠሩበትንም ዓላማ የሚያሳኩት  መንግሥተ እግዚአብሔርን በመውረስ ነው፡፡ የተጋድሏቸው ዓላማ እግዚአብሔርን ማስደሰት፣ ግቡም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነው፡፡ “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፣ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ” ተብሎ እንደተነገረላቸው (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)፡፡ እንግዲህ  ከገቡ የማይወጡባት፣ ካገኙ የማያጡባት፣ ኀዘን፣ መከራና ሞት የመሳሰሉ ችግሮች የማይታወቁባት የእግዚአብሔር  መንግሥት  የምትወረሰው በበጎ ሥራና በድካም ነው፡፡ “ወደ እግዚአብሔር  መንግሥት  በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” የሚለውም የሐዋርያት ቃል የሚስረዳው መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ስሚጠበቅብን ተግባር ነው፡፡ (የሐዋ. ሥራ 14፥21)፡፡

ምስባክ እና ወንጌል

በገብር ኄር ሰንበት የሚሰበከው ምስባክ መዝሙር 39 ላይ ያለው ነው፡፡ ይኸውም “ከመ እንግር ፈቃድከ መከርኩ አምላኪየ፤ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፤ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ” የሚለው ሲሆን የአማርኛ  ትርጉምም “አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፤ በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ” ማለት ነው (መዝ.39፥8-9)፡፡ በዚሁ ጊዜ የሚነበበው ወንጌል በሐዋርያው እና በወንጌላዊው  በቅዱስ ማቴዎስ የተጻፈው  ምዕራፍ 25 ከቍጥር 14-31 ያለው ነው::

  1. ኒቆዲሞስ

ቅዱስ ያሬድ የዐቢይ ጾምን ሳምንታት ሲሰይም ታሳቢ ካደረጋቸው ኹኔታዎች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር የተደረገላቸውና ትምህርት የተከታተሉትን ግለሰቦች መኾኑ ግልጥ ነው፡፡ ለምሳሌ መፃጒ እና ኒቆዲሞስ የሚሉ ስያሜዎች ይጠቀሳሉ፡፡ መፃጒም ድውይ ማለት መሆኑን በአራተኛው ሳምንት ስያሜ ላይ መነሻ አድርገን ተመልክተናል፡፡ ሰባተኛው ሳምንትም የአይሁድ መምህር ሲሆን ሌሊት ሌሊት ከጌታችን ዘንድ እየመጣ ይማር በነበረው ኒቆዲሞስ በተባለው ሰው ስም ተሰይሟል፡፡

ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን የኾነና የአይሁድ አለቃ የነበረ ሰው ነው፡፡ አለቅነቱም በትምህርት፣ በሹመት እና በባለጸነት ሲሆን ከጌታችን ዘንድ እየቀረበ በሌሊት የሚማር ሰው ነበር፡፡ የሚያስፈልገውን የሚሻ ትጉህና የሃይማኖት ሰውነት በኒቆዲሞስ ሕይወት ውስጥ ተገልጠው የሚታዩ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ በዚሁ አግባብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ምእመናንን ትጋታቸውን  በኑሯቸው ኹሉ ይገልጡ ዘንድ ታስተምራለች፡፡

ካለው ነገር ይልቅ የሚያስፈልገውን የሚሻ ኒቆዲሞስ

ምንም እንኳ በተማረው ትምህርት፣ በሰበሰበው ሀብት እና በያዘው ሥልጣን የአይሁድ አለቃ ቢኾንም ከኹሉ በላይ እርሱ የሚያስፈልገውን ለማግኘት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኼድን ያዘወትር የነበረ ሰው ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ብዙ ነገሮች ያሉት ሰው ቢመስልም ትልቋ ሀብት ግን አልነበረችውም፤ ይህችውም ሀብት የልጅነት ጸጋ የምታሰጥ ጥምቀት ናት፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ዓለሙን ኹሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? (ማቴ.16፥26) በማለት እንዳስተማረው በነፍሱ እንዳይጎዳ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የምታሰጠውን  ጥምቀተ ክርስትናን የሚሻ ሰው ነበር፡፡ በሰበሰበው ሀብት፣ በያዘው ሥልጣንና በተማረው ትምህርት ላይ ብቻ ተመሥርቶና እርካታ ተሰምቶት የሚኖር ሰው አለመሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ ይልቁኑ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታስገባውን ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምታሰጠውን ጥምቀት አብዝቶ የሚፈልግ ኾኖአል፡፡ ይህም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” (ፊልጵ. 3፥13) በማለት የተናገረውና ከማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ፍለጋ ነው፡፡

ትጋት በኒቆዲሞስ ሕይወት

ያለ መታከትና  ያለ መሰልቸት ሌሊት ሌሊት ከጌታችን ዘንድ እየሔደ ትምህርተ ወንጌል የሚማረው ኒቆዲሞስ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሰብአ እስራኤልን ሰብስቦ የሚያስተምር ሀብቱን የሚያስተዳደር ሰው ነበር፡፡  ምንም እንኳ ሌሎችን በማስተማር ሀብቱንና ቤተሰቡን በማስተዳደር ቀኑን ቢያሳልፍም ድካሙን ታግሦ የሕይወት ፍሬ ወደ ኾነው ወደ ጌታ  መገስገስን አላቌረጠም፡፡  የኒቆዲሞስ  ትጋት ወደ ጌታችን  ሳይታክት በመመላለሱ ብቻ የሚገለጥ አይደለም፤ ይልቁኑ ረቂቅ የኾነውን ነገረ ጥምቀትንና በጥምቀት የሚገኘውን ሀብት ግልጥ ኾኖ  እስኪረዳው በትጋት በመማሩ እንጂ፡፡ እናም በማንኛውም ምእመን ሕይወት እንዲኖር የሚያስፈልገውን ትጋት ኒቆዲሞስ ይዞ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ትጋቱ  የቤተ ክርስቲያን አባል፣ የክርስቶስ አካል በመኾን የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል ስለ ትጋት አስፈላጊነት መላልሶ አስተምሯል (ሉቃ. 18፥1፣ ማቴ. 26፥38፣ ማር. 13፥33)፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም  የጌታዋን ቃል ይዛ ልጆቿ በበጎ ሥራ ተግተው እንዲኖሩ ትመክራለች፡፡ (የሐዋ.20፥3 ፤ ሮሜ.12፥3) ፡፡

ሃይማኖት በኒቆዲሞስ ሕይወት

በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ማመኑን በተመለከተ ኒቆዲሞስ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡- “ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ቀርቦ ‹ከእግዚአብሔር አብ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ተወልደህ ልታስተምር እንደመጣህ እናውቃለን” ዮሐ 3፡2 በማለቱም ይህን እንረዳለን፡፡ ጌታችንም ሃይማኖትን ፍጹም የምታደርግ ጥምቀትን በሰበከለት ጊዜ ቀድሞ ካወቀው ምጡቅ እውቀት ይልቅ ለድኅነት የምታበቃው ሃይማኖት እንደምትበልጥ አውቆ ያንኑ ተቀብሏል፡፡

ምስባክ እና ወንጌል

በኒቆዲሞስ ሰንበት የሚሰበከው ምስባክ “ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፤ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመ ሕያው፤ በሌሊትም ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፤ የሰውን ሥራ አፌ አንዳይናገር” (መዝ.16፥3-4) የሚለው ነው፡፡ ወንጌሉም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፥1-12 ነው፡፡

  1. ሆሣዕና

 “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ልጅ ሆይ እልል በይ፤ እነሆ ንጉሥሽ አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾኖ በአህያም፣ በአህያዪቱም ግልገል በውርንጫዪቱ ላዩ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡ ሠረገላውንም ከኤፍሬም፣ ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል፡፡›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ንጉሠ ነቢያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ ፋጌ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ዕለት ማለትም መጋቢት 22 ቀን በ33 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

‹‹ሆሣዕና›› ማለት አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ‹‹ማዳን የባሕርይህ የሆነ መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ መጥተህ እድነን›› እያሉ የአዳም ልጆች ሁሉ የጸለዩበትን ጸሎት የያዙትን ሱባኤ ያመለክታል፡፡ በቀድሞ ዘመን በሰረገላ እና በፈረስ የሚቀመጥና ገስግሶ የሚሄድ ጦረኛ ነው፡፡ ጌታ ግን በአህያ ላይ ተቀምጦ መጓዙ የሰላም አምላክ፣ ሰላምን ለዓለም የሚሰጥ፣ ይቅርታውን ለአዳም የሚያደርግ መኾኑን ለማብሰር ነው፡፡

በዕለተ ሆሣዕና  የእናታቸውን ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ሳይቀሩ በትህትና ዝቅ ብሎ በአህያ ጀርባ ወደ ኢየሩሳሌም የገባውን የባሕርይ ንጉሥ አመስግነውታል፡፡ ይኸውም ይህ ከመሆኑ ከአንድ ሺ ዓመታት በፊት ቅዱስ ዳዊት “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ›› በማለት በተናገረው ትንቢት መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ እንኳን ሕፃናት ይቅርና ግእዛን የሌላቸው የቢታንያ ድንጋዮችም ጭምር ‹‹በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ቡሩክ አምላክ ነው›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ (መዝ. 8፥2-3)

የሆሣዕና ምስባክ እና ወንጌል

ምስባኩ በመዝ. 146፥ 12-13 ላይ፡- ‹‹ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚእብሔር፤ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፤ እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ›› ተብሎ የተነገረው ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመሰግኝ፤ ጽዮንም ለአምላክሽ እልል በይ፤ የደጆችሽን መወርወርያ አጽንቶአልና›› የሚል ነው፡፡ የሚነበቡትንም ሊቃውንት ከአራቱ ወንጌላውያን የሚያዘጋጁ ሲሆን ዕለቱን የተመለከተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱና በውርንጫይቱ ጀርባ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የመግባቱን ነገር የሚያወሱ ምንባባት ይነበባሉ፣ ይተረጎማሉ (ማቴ. 21፥1-16)፡፡

በእንተ ጾም፣ ጌታችን የጾመበት ምክንያት

በገብረ እግዚአብሔር ዘይኵኖ

 ለቸርነቱ ወሰን የሌለው፣ በኃይለ ረድኤቱ  ያልተለየን ምስጉንና ክቡር የኾነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቸር አባቱ ከእግዚአብሔር አብ እና ከባሕርይ ሕይወቱ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጋራ ምስጋና ይግባው፡፡ መዋዕለ ጾማችንም ባርኮ ቀድሶ  እንዳስጀመረን በሰላም እንዲያስፈጽመን፤ ጾሙንም የኃጢአት መደምሰሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ አድርጐ በቸርነቱ ይቀበልልን፤ ለአገራችን ሰላምን ለሕዝቧም ፍቅር፣ አንድነትን ያድልልን አሜን፡፡

በዚህ ጽሑፍ የጾምን ምንነትና አስፈላጊነት፣ የጌታችንን ጾም እና የመጾሙን ምክንያት በአጭሩ እንመለከታለን፤ ልዑል አምላካችን በቅዱስ ቃሉ የሚገባንን ይግለጥልን አሜን፡፡

የጾም ምንነት

ጾም መተውን፣ መከልከልን የሚያጠይቅ መንፈሳዊ ተግባር ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን የሕግና የሥርዓት መመሪያ የኾነው ፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ሲገልጽ “ጾምስ የሥጋ ግብር ነው፤  ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ፡ ነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ ነው” ብሏል፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 15)፡፡ ጾም የጸሎት እናት፣ የአርምሞ እኅት፣ የእንባ መሠረት ናት፡፡ በተጨማሪም የመልካም ተጋድሎ ኹሉ መነሻ ጾም መኾኗ በቅዱሳት መጻሕፍት የተረዳ፣ የታወቀ፣ ጉዳይ ነው ፡፡

በሌላ በኩል ጾም ወደ ፈጣሪአችን የምንመለስባት (የምንቀርብባት) መንፈሳዊት መንገድ መሆኗ በመጽሐፍ ቅዱስ  ተገልጧል፡፡ ይህም ሊታወቅ ልዑል እግዚአብሔር በነብዩ አድሮ “በፍጹም ልባችሁ በጾምም በለቅሶ እና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ” ብሏል (ኢዩ. 2፥12) ፡፡ “ወደ እኔ ተመለሱ ’’ በሚለው ቃል ውስጥ ወደ ፈጣሪአችን  የምንመለስባቸው መንገዶች ጾም እና ንሰሐ መኾናቸው ታውቋል፡፡ የንሰሐ  ሕይወት ያለ ጾም፣ ጸሎት  ያለ ንሰሐ አይፈጸሙምና ፡፡

የጾም አስፈጊነት

ከመንፈሳውያን  ሀብቶቻችን  አንዷ ጾም ለነፍስ ብቻ  ሳይሆን ለሥጋም  የምትሰጠው ጥቅም  አላት፡፡ ጾም ወደ ፈጣሪአችን የምንመለስባት መንፈሳዊት መንገድ ናት፡፡  እንዲህም ከኾነ  በበደል፣ በኃጢአት እና በአመጻ ምክንያት ከፈጣሪው የተለየ የሰው ልጅ በጾም፣ በጸሎት እና በንሰሐ ሕይወት ዳግም ወደ አምላኩ ይመለስበታል፡፡ ጾም ወደ ፈጣሪአችን ፈቃድና አሳብ የምንደርስበት መንፈሳዊ መንገድ መኾኗ ቀደም ብለን አይተናል፡፡ ከዚህ አንጻር ቸር እና መሐሪ ወደ ኾነው አምላካችን እንድንቀርብ የምታስችል ናትና ጾም የሰው ልጅ ወደ ፈጣሪው የሚሳብባትና የሚቀርብባት መልካም ጎዳና ኾና  ታገለግላለች፡፡

ጾም ኃይል መንፈሳዊን ታቀዳጃለች

ፈቃደ ሥጋን፣ እኩያን ፍትወታት፣ እኩያት ኀጢውዕን ድል ለመንሣትና መንፈሳዊ ኃይልን ለመቀዳጀት የጾም እርዳታ ከፍተኛ ነው፡፡ ሐዋርያው “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ ደግሞ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛለሁ” (1ኛ ቆሮ. 9፥27) እንዳለ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት የጾም አስተዋጽኦ ከፍ ያለ መኾኑ ታውቋል፡፡ ፈቃደ ሥጋው በጾም፣ በጸሎት እና በሰጊድ እንዲሁም በመሳሰሉት መንፈሳዊ ተግባራት ታግዞ መግራት ያልቻለ እንዴት መንፈሳዊ ኃይልን መቀዳጀት ይቻለዋል? እንኳን  ለሌሎች ሊተርፍ ለራሱም መሆን አይቻለው ፍትሕ መፈሳዊ በጾም ከሚገኙ ረቦች (ጥቅሞች) አንዱ መንፈሳዊያንን  መላእክትን መምሰል መኾኑን አስረድቷል፡፡

መንፈሳዊያን የምንላቸው ቅዱሳን መላእክት እና ቅዱሳን ሰዎች ነው፡፡ ከቅዱሳን  አባቶቻችን እንዱ ቅዱስ ጰውሎስ  ለቆሮንቶስ ምእመናን ካሳሰባቸው ጉዳዮች  አንዱ እርሱን እንዲመስሉ  ነው፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ“ በማለት (1ቆሮ፡ 11፡1)፡፡  እንግዲህ ቅዱሳንን  ከምንመስልባቸው ጉዳዮች አንዱ ጾም መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ “ጾም  ይረባናል›› ብለን ከመጾማችን የተነሳ መንፈሳዊያንን እንመስላለን፡፡ እነርሱን ከመሰልናቸውም ደግሞ  እነርሱ የሚመስሉትን ክርስቶስን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም  ጿሚው  የረሃብን ችግር ያውቅ ዘንድ፣  ለተራቡት እና ለሚለምኑት ሁሉ ይራራላቸው  ዘንድ ነው ፡፡ (ፍትሕ መንፈሳዊ 574)

ጌታችን ዐርባ መዓልት እና ዐርባ ሌሊት ለምን ጾመ?

የጾም ምክንያት ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል “ራስን ለመግራት’’ (ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ለማስገዛት) መንፈሳዊ ኃይልን ለመቀዳጀት መኾኑ ከዚህ በላይ ተገልጿል፡፡ ይኹንና ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ  ዐርባ መዓልት፣ ዐርባ  ሌሊት የመጾሙ ምክንያት ግን ከዚህ በላይ ለሰው ልጆች ጾም የተጠቀሱትን ምክንቶች ለማሟላት አይደለም፤ እርሱ ጌታችን ኃይል መንፈሳዊውን የሚሰጥ እንጂ የሚቀበል አይደለምና፡፡  ታዲያ ጌታ ለምን ጾመ?

፩. በጾሙ ጾማችንን ሊባርክ ጾመ፡፡

አስቀድሞ በቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን ሲፈጸም የቆየውን ጾም ኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አጽንቶታል፡፡ ጌታችን የመጾሙ ምክንያት ኃይል  መንፈሳዊ ለማግኘት አስቦ ወይም ያልከፈለው እዳ ኖሮበት ለማስደምሰስ ሳይሆን በጾሙ ጾማችንን ሊባርክልን ነው፡፡ በባህረ ዮርዳኖስ፣ በዕደ ዮሐንስ ተጠምቆ የእኛን ጥምቀት እንደባረከልን፤ በገዳም ጾሞ ጾማችንን ባርኮልናል፡፡ ሥርዓቱን ኹሉ የሠራው በተግባር ጭምር እንጂ በቃሉ ትእዛዝ ብቻ አይደለምና፡፡

. በጾም ጸሎት አርዕስተ ኅጣውእን ድል ማድረግ እንደሚቻል ሊያስገነዝበን ነው፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐርባ መዓልት ከዐርባ ሌሊት ከጾመ በኋላ ፈታኝ ይዞአቸው የመጣውን ፈተናዎች ሁሉ ድል ነሥቷል፤ ጠላት ዲያቢሎስንም አሳፍሮ መልሶታል፡፡ የሰው ልጆችን ሕይወት የሚፈታተኑ የኃጢአት ራሶች የተባሉትም ሦስቱ  ስስት፣ ትዕቢት እና ፍቅረ ንዋይ ናቸው፡፡ በስስት የመጣውን በትዕግሥት፣ በትዕቢት የመጣውን በትህትና እንዲሁም በፍቅረ ንዋይ ለመጣው ፈተና በጸሊአ ንዋይ ድል አድርጓል፡፡

፫. አብነት ሊሆነን

በቅዱስ ወንጌል ላይ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ጻፎችና ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር ተቀምጠዋል፡፡ ስለዚህ ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ፣ ጠብቁትም፡፡ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ፡፡ ከባድና አስቸጋሪ ሸክም ተብትበው በሰው ትከሻ ይጭናሉ፤ እነሱር ግን በጣታቸው ሊነኩት አይወዱም›› ብሏል፡፡ (ማቴ. 23፥2-4)

ከዚህ የጌታችን ትዕዛዝ ቢያንስ ሦስት ጉዳዮችን መረዳት ይገባል፡- እነርሱም ጸሐፍት ፈሪሳውያን በሙሴ ወንበር እስከተቀመጡ የሚናገሩትን መስማት እንደሚገባ፣ የጸሐፍት ፈሪሳውያን ተግባር ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ በመኾኑ በተግባር እነርሱን መምሰል እንደማይገባ  እና በሦስተኛ ደረጃ የጸሐፍት  ፈሪሳውያን ጠባይ መታወቁ ነው፡፡

ከሚናገሩት የእግዚአብሔር ቃል አንዱንም እንኳ አይፈጽሙምና የእነርሱን አብነት ከመከተል ይልቅ ከእርሱ መማር እንዲገባን “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እነ ኑ፤ እኔም አሳርፋችኋለሁ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና” (ማቴ. 11፥28) ሲል ጌታችን ነግሮናል፡፡

እንደ ጸሐፍት ፈሪሳውያን ሳይሆን በፍጹም ትህትና ዝቅ ብሎ የአገልጋዮቹን እግር እያጠበ ጭምር ተግባራዊ ትምህርትን ያሳየንን ጌታችንን በጾሙም ጭምር እንመስለው ዘንድ ሥርዓተ ጾምን በተግባር ሠርቶልናል፡፡

፬. ጾምን የሥራችሁ መጀመሪያ አድርጓት ሲል ነው፡፡

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተጠመቀ በኋላ ሳይውል ሳያድር ነው ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ የገባው፡፡ ይኸውም አብነት ነው፡፡ ጌታችን ከጥምቀት በኋላ ወንጌልን ወደ መስበክ፣ ተአምራትን ወደ ማድረግ አልተሰማራም፡፡ እንግዲህ እኛም ከኹሉ ተግባራችን አስቀድመን መጾም መጸለይ እንዳለብን በዚሁ የጌታቸን ተግባር እንረዳለን፡፡

 ማጠቃለያ ፡-

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ አድሮ “ለእናንተ የማስባትን አሳብ እኔ አውቃለሁ፤ ፍጻሜና ተስፋ እሰጣችሁ ዘንድ የሰላም አሳብ ነው እንጂ የክፉ ነገር አይደለም” ብሏል (ኤር.29፥11)፡፡ በዚሁ መሠረት በቀደሙት ወላጆቻችን (በአዳም በሔዋን) ዘመን ጀምሮ የምትረባንን ሥርዓተ ጾም ሠርቶልናል፡፡ ይህም ሊታወቅ አዳምና ሔዋን  በገነት ሲኖሩ እፀ በለስ እንዳይበሉ  መታዘዛቸው አንድም  ሥርዓተ ጾምን ሲያስተምራቸው ነው፡፡

ከዚያም በኋላ  በዘመነ አበው፣ በዘመነ ነቢያት በልዩ ልዩ መልክ ሥርዓተ ጾምና ጸሎት ሲፈጸም ቆይቷል፡፡ ከኹሉ በላይ በደገኛው የምሕረት ዘመን (በሐዲስ ኪዳን) ራሱ ጌታችን በዓት አጽንቶ በፍጹም ትዕግስት ጾሟል፡፡ እንግዲህ እነዚህን ኹሉ አብነት አድርገን ጌታችና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንድም በትምህርት፣ አንድም በተግባር ስለ ጾም ያስተማረንን አብነት ወስደን በፍጹም ፍቅርና አንድነት ልንጾም ያስፈልገናል፡፡ ስለኹሉ የልዑል እግዚአብሔር ቸርነት፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ጸሎት አይለየን አሜን፡፡

ፈተና በክርስቲያናዊ የአገልግሎት ሕይወት

ለሜሳ ጉተታ

ክርስትና የተግባር ሕይወት ነዉ ፡፡ የክርስትና ሕይወት ተራ ኑሮ ብቻም ሳይሆን ዘለዓለማዊ ዓላማ ያለው ሕይወትም ጭምር ነዉ፡፡ በተጨማሪም የክርስትና ሕይወት እግዚአብሔርን እና ቅዱሳንን የምንመስልበት ሕይወት እንዲሁም ቅዱስ የምንሆንበት ሕይወት ነዉ፡፡ ቅዱሳንን እንድንመሰል የሚያደርገን የክርስትና ሕይወትን በሕይወት፣ በፍቅር፣ በቅድስና፣ በትዕግስት፣ በታማኝነት፣ በንጽህና መኖር እና መግለጥ ሲቻል ብቻ  ነዉ፡፡  ለዚህ ነዉ ሐዋርያው ቅዱስ ጰዉሎስ እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እናንተም እኔን  ምሰሉ ያለን፡፡

የክርስትና ሕይወት  በመንፈሳዊነት ይገለጣል፡፡ ቃሉን በመማር፣ በመስማት፣ በሕይወትም በመግለጥ (በመኖር) ይገለጣል፡፡ “የክርስትና ሕይወት የቅድስና ሕይወት ነዉ”  ስንል ቅድስናዉ የሚገለጠዉ በአገልግሎት ሕይወት፣ ትጋት እና ፍቅር ነዉ፡፡ ክርሰትና አገልጋይነት ነዉ፤ ያዉም በታማኝነት እና በመንፈሳዊነት የምናከናውነው፡፡

አገልግሎት ለቅድስና ሕይወት ያበቃል፡፡ ከኃጢአት፣ ከክፋት፣ ከበደል፣ ከክፉ ምኞት ሐሳብ እና ተግባርም ይሠዉራል፡፡ ለፀጋ እግዚአብሔር፣ ለመንግሥቱና ለርሰቱም ያበቃል፡፡ ለበለጠ ፀጋ እና ክብርም ያደርሳል፡፡ ሰማያዊና ምድራዊ፣ መንፈሳዊ ሀብትን እና ክብርንም ያሰጣል፡፡ ማቴ ፡25፡ 14-30. መንፈሳዊ አገልግሎት፣ መንፈሳዊነት እና ክርሰትና ራስን መካድን፣ ራስን ማሸነፍን፣ ዓለምን መጥላትን/መተዉን፣ ለእግዚአብሔር ራስን አሳልፎ ማስገዛትን/መስጠትን ይፈልጋል፡፡ ‹‹ኑሮዬ ይበቃኛል›› ማለትን ይፈልጋል፡፡ ምክንያትን ማሸነፍን፣ ትዕግሰትን እና ማስተዋል ይጠይቃል ፡፡

የክርስትና ሕይወት በአገልግሎት ይገለጣል ስንል አገልግሎት ፈተና እንዳለዉም ደግሞ መርሳት የለብንም፡፡  መንፈሳዊ አገልግሎት መከራ ይበዛበታል፣ መዉጣት እና መዉረድ መዉደቅ እና መነሳትም አለው፡፡ ያለ ክርስትና ሕይወት መንፈሳዊነት የለም፤ የእግዚአብሔር ሰውም መሆን አይቻልም፡፡

እዉነተኛ አገልገሎት፣ የክርስትና ሕይወት እና  መንፈሳዊነት  ባለበት ቦታ ሁሉ መከራ እና ፈተና አለ፤ ያለ ፈተናም ጸጋን መቀበል አይቻልም፡፡ ለዚህም ነዉ ሐዋርያት በራሳቸው የተፈተነ ሕይወት ተግባራዊ ማሳያነት “ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” እያሉ ያስተማሩት (የሐዋ.14፡21-22)፡፡ ይህም መከራ የደረሰባቸው በደስታ የሚቀበሉትና በመንፈስ የሚበለጽጉበት ሆኖላቸዋል፤ “… ቃሉን በብዙ መከራ ከመንፈስ ቅዱስ  ደስታ ጋር ተቀብላችሁ እኛና ጌታን የምትመስሉ ሆናችሁ፡” (1ተሰ. 1፡6) እንዲል፡፡

ቅዱስ ጳዉሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈዉ መልእክቱ በመከራ ስለሚገኝ በረከት እንዲህ ያስተምረናል። “በብዙ መከራ ተፈትነው ሳሉ የደስታቸዉ ብዛትና የድኅነታቸው ጥልቀት የልግስናቸው ባለጠግንት አብዝቶአል።” (2ኛ ቆሮ.8፡2)፡፡ ፈተና በተለያዩ መንገዶች በተለያዩ ምክንያቶችም ሊመጣብን ይችላል፡፡  ለመባረክና  ለመዳንም በፈተና መጽናት ያስፈልጋል፡፡  ለዚህ ነዉ መጽሐፍ ቅዱሰ በተደጋጋሚ ‹‹እሰከ መጨረሻዉ የሚጸና እርሱ ግን ይድናል›› በማለት አጽንቶ የሚመክረን (ማቴ 10፡ ማቴ 24፡ ማር 13)፡፡

ፈተና የክርሰትያናዊ ሕይወት አንዱ መገላጫ ነዉ ፡፡ ያለፈተና በአገልግሎት እና በመንፈሳዊ ሕይወት ያለፉ ቅዱሳን የሉም፡፡ ይህን ሲያስረዳ ቅዱስ ጰዉሎስ 2ኛቆሮ. 11፡22-29 ላይ፡- “—–በድካም አብዝቼ፣ በመገረፍ አብዝቼ፣ በመታሰር አትርፌ፣ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ፡፡ አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ፡፡ ሦስት ጊዜ  በበትር ተመታሁ፤  አንድ  ጊዜ  በድንጋይ  ተወገርሁ፤  መርከቤ ሦስት  ጊዜ  ተሰበረ፤  ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ  ኖርሁ። ብዙ ጊዜ  በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ  ፍርሃት፣ በወንበዴዎች  ፍርሃት፣  በወገኔ በኩል ፍርሃት፣  በአሕዛብ  በኩል  ፍርሃት፣  በከተማ ፍርሃት፣  በምድረ በዳ ፍርሃት፣  በባሕር ፍርሃት፣  በውሸተኞች  ወንድሞች በኩል ፍርሃት  ነበረብኝ፡፡ በድካምና በጥረት፣  ብዙ ጊዜም  እንቅልፍ  በማጣት፣  በረሀብና  በራቁትነት ነበርሁ። የቀረዉንም  ነገር ሳልቆጥር ዕለት ዕለት  የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው”  በማለት ስለ ክርሰቲያናዊ የአገልግት ሕይወት እና የመከራን ጥብቅ ቁርኝት ያስረዳናል ፡፡

የክርስቲያን  መንፈሳዊ የሕይወት ጉዞ  በድሎት እና በምቾት የተሞላ አይደለም፡፡ ይልቁንም በማያቋርጡ ተጋድሎዎች የተሞሸረ ነዉ እንጂ፡፡ ክርሰቲያናዊ ሕይወት ቅዱሳንን የምንመሰልበት እና ቅዱስ የምንሆንበት ሕይወት ነዉ፡፡ መከራ እና ፈተና የክርሰትና  የሕይወት ቅመም ነዉ፡፡ ከጸጋ ወደ ጸጋ ያሳድጋል፣ ያተጋል፣ ያበረታል፣ ለንሰሐ ሕይወት ያበቃል፣ ወደ ጾም እና ጸሎት ይመራል፡፡ ሁል ጊዜ ወደ ቤተ እግዚአብሔርም እንድንሄድ ሕይወታችንን በእርሱ ፍቃድ፣ ትእዛዝ እና ሀሳብም እንድንመራ ያደርጋል፡፡  ያለ ፈተናና  መከራ የክርስትና ሕይወት፣ ድኅነት እና ጽድቅ አይገኝም፡፡ መከራ ሲባል ደግሞ ልንችለዉና ልናሸንፈዉ ከምንችለዉ በላይ እንደማንፈተን መጽሐፍ እንዲህ ይነግረናል፡- ‹‹ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነዉ፤ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናዉ ጋር መዉጫዉን ደግሞ ያደርግላችኋል፡፡” (1ኛ ቆሮ 10፡13)

ክርስቲያን ለማመን ብቻ አልተጠራም፡፡ ለማገልገል፣ የቅድስና ሕይወትንም ለመኖር፣ ለመልካም ሥራ እና የእግዚአብሔርንም መንግሥት ለመዉረስ ጭምር ነዉ እንጂ፡፡ ለዚህ ነዉ መጽሐፍ ‹‹እግዚአብሔር ለቅድስና ጠርቶናል›› የሚለን (1ኛ ተሰ.4፡7)፡፡

ዳግመኛም የተጠራነው በስሙም መከራን ለመቀበል እና ለመፈተንም ጭምር ነው፡- ቅዱስ ጰዉሎስ ‹‹ስለ እርሱ መከራን ደግሞ ልትቀበሉ እንጅ በእርሱ ልታምኑ ብቻ አልተጠራችሁም››  በማለት ያሰተማረንም ይህንን ያስረዳል፡፡ ፊልጵ.(1፡29)

ሁሉም የሚደርስብን ፈተና ግን  በእግዚአብሔር ሰለአመንን በመልካም ሥራችን ነዉ ብሎ መዉሰድ ደግሞ አግባብነት የለውም፡፡ ከእግዚአብሔር የሚመጣብን ፈተና ከእምነታችን ጽናት፣ ከፍቅሩ  ጥልቀት እና ስፋት፣ ለበለጠ ፀጋ  እና ክብር እንበቃ ዘንድ በመንፈሳዊ ሕይወታችን  ጥንካሬ  ደረጃ የሚመጣብን ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ የአባታችን የአብርሃም  ፈተና እና የትዕግስተኛዉ አባታቸን ኢዮብ ዓይነት ፈተና ማለት ነዉ ፡፡

ግን በእኛ ስህተት፣ በኃጢአታችን ብዛት፣ ለትምህርት እና ለቅጣትም ጭምር  የሚመጣም ፈተና አለ፡፡  በዚህ ጊዜ ከኃጢአት መመለስ፣ ማዘንና ማልቀስ፣ ንሰሐም መግባት፣ መጾም እና መጸለይም  ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ቅዱስ ያዕቆብ፡- ‹‹ማንም ሲፈተን በእግዚዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈትንምና፡፡ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም፤ ነገር ግን እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብ እና ሲታለል ይፈተናል ፡፡ ከዚህ በኋላ ምኞት ፀንሳ ኃጢአትን ትወልዳለች፣ ኃጢአትም ካደገች በኋላ ሞትን ትወለዳለች›› በማለት ይመክረናል፡፡ ያዕ. 1፡13.

ስለዚህ ክርስቲያን ሲኖር እንዴት መኖር አለበት? ስንል፡- ‹‹ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፡፡ በበጎነትም እዉቀትን፣ በእዉቀትም ራስን መግዛትን፣ ራስንም በመግዛት መጽናትን፣ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰልን፣ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማች መዋደድ፣ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ›› የሚለንን ቃሉን መሠረት እና የሕይወታችን መመርያ በማድረግ መኖር አለብን፡፡ (2ኛ ጴጥ ፡ 1፡5-8)

የክርስትና ሕይወት  ማስተዋል፣ እምነት እና ትእግስትን ይጠይቃል፡፡ ዝም ብሎ በሰዉ ከመነዳት መጠበቅ አለብን፡፡ የዓላማ ሰዉ መሆን ይኖርብናል ፡፡ የተፈጠርንበትን ዓላማ እና ክብርንም መርሳት የለብንም፡፡ የስም ሳይሆን የተግባር እና የሕይወት ክርሰቲያን ሆነን  ክርስትናንም በሕይወት ገልጠን  ለመንግሥቱ እና ለክብሩ እንዲያበቃን የእርሱ የአምላካችን መልካም ፍቃድ ይሁንልን፤ አሜን ፡፡

መለያየት- ከክርስቶስ የመለየት ምልክት ነው!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከእውነተኛ መምህራቸው እና አምላካቸው ክርስቶስ ይልቅ የእርሱን ቃል ባስተማሯቸው ሰዎች ማንነት በመመካት እርስ በርስ ሲከፋፈሉ ለነበሩት የገላትያ ምእመናን፡- “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና። አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁ። “ ብሎ ነግሯቸዋል፡፡ (ገላ. 3:27 -28)

ከዚህ መልእክት የምንረዳው እውነት የአንድነታችን መሠረቱ በጥምቀት አማካይነት፣ በእምነት በኩል  የክርስቶስ አካል መሆናችን ነው፡፡  ይህም ሲባል ክርስቲያኖችን ሁሉ አንድ ያደረጋቸው በክርስቶስ ማመናቸውና በእምነት አንድ መሆናቸው እንጂ እንደማንኛውም ሰው በመልክ፣ በባህል፣ ተወልደው ባደጉበት ቦታና በትምህርት ደረጃቸው አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ ይታወቃል፡፡ ይልቁንም ኦርቶዶክሳውያን የሆንን ሁላችን እንደማንኛውም ሰው አስቀድመው በተጠቀሱት በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ልንለያይ ብንችልም እንኳን አንድ አምላክ ብለን ስለምናምን፣ ከአንዲት ማኅጸነ ዮርዳኖስ እና ከአንዱ አብራከ መንፈስ ቅዱስ በአንዲት ጥምቀት አማካይነት ተወልደን የአንዱ የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን፣ የክርስትና ሃይማኖትን በአንድነት ስለምንቀበል፣  በአንዲት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለምንኖር አንድ ነን፡፡

እናም በአንዲት ጥምቀት አንዱን ክርስቶስን የለበሱ ክርስቲያኖች በሚለብሷቸው ባህላዊ አልባሳት ምክንያት ሊለያዩ አይችሉም፤ ምድራዊው መገለጫ ከሰማያዊው ሊበልጥባቸው አይችልምና፡፡ በአንድ የፍቅር ገመድ የተሳሰሩ ምእመናን በቋንቋቸው መለያየት ምክንያት አንድነታቸው ሊፈተን አይገባውም፤ የክርስቲያኖች ዋነኛው መግባቢያ ፍቅር እንጂ ቋንቋ አይደለምና፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ በገላትያ ምእመናን አማካይነት ‹‹አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም›› ብሎ ሲመክረን የትውልድ ዜግነታችንን ለማስካድ አይደለም፤ ከተወለድንበት ቦታ ይልቅ ክርስቲያን ሆነን፣ የክርስትናን ምግባራት ሁሉ ፈጽመን ከምንወርሳት ሰማያዊት አገር በእጅጉ እንደሚያንስ ለማጠየቅ እንጂ፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ‹‹ባሪያ ወይም ጨዋ የለም›› ሲልም በወቅቱ ሰዎች እርስ በርሳቸው የተከፋፈሉባቸውን ኩነቶች ከመግለጡም ባሻገር ‹‹በክርስትና ሰው ሁሉ ሰው በመሆኑ ብቻ እኩል ነው እንጂ መበላለጥ አለመኖሩን›› ለማስረዳት ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ በክርስትና የሚገኘው አንድነት ‹‹ወንድ›› ወይም ‹‹ሴት›› የሚባል የጾታ ልዩነትን እንኳን የሚያስረሳ፣ ፍጹም አንድ አካል መሆንን እንደሚያረጋግጥ ሐዋርያው አስረግጦ የተናገረው ተፈጥሮን ለመካድ አይደለም፤ በክርስቶስ አንድ የሆነ ክርስቲያን እንኳንስ በሰው ሰራሽ ነገሮች መለያየት ቀርቶ የተፈጥሮ ድንበር እንኳን ረቂቁን መንፈሳዊ አንድነት ሊያፈርሰው እንደማይቻለው ለማሳየት እንጂ፡፡

በዚሁ መሠረት ‹‹አንድ›› መንጋ የሆነው መንፈሳዊ ቤተሰብ ደግሞ እንደ አንድ ልብ መካሪ፣ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ በፍጹም የአንድነት መንፈስ ጸንቶ ይኖራል እንጂ ዘመን በተቀየረ፣ ወሬ በተወራ ቁጥር በሆነው ባልሆነው ሁሉ አይለያይም፡፡ ሐዋርያው በክርስቲያኖች መካከል አንድነት እንጂ መለያየት ፈጽሞ መኖር እንደሌለበት በተማጽኖ ቃል ‹‹ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ሁላችሁ አንድ ንግግር እንድትናገሩ በአንድ ልብና በአንድ አሳብም የተባበራችሁ እንድትሆኑ እንጂ መለያየት በመካከላችሁ እንዳይሆን በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምናችኋለሁ።›› ሲል የሚናገረውም ለዚሁ ነው (1ቆሮ.1:10)፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ለክርስቲያኖች የሚሰጠው በአንድነት ሕይወት ውስጥ መሆኑ በሐዋርያት ኑሮ ተረጋግጧል፡- በጽርሐ ጽዮን ‹‹…ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው፣ አብረው ሳሉ…›› መንፈስ ቅዱስ እንደወረደላቸውም ቅዱስ መጽሐፋችን ይመሰክራልና (ሥራ. 2፡1)፡፡ ደግሞም፡- «በሰላም ተሳስራችሁ ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኘውን ለመጠበቅ ትጉ። በተጠራችሁ ጊዜ ለአንድ ተስፋ እንደተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ። እንዲሁም አንድ ጌታ አንድ እምነት እና አንድ ጥምቀት አለ። ደግሞም  ከሁሉ በላይ የሆነ በሁሉም የሚሠራ፤ በሁሉም የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።»  ተብለን እንደተመከርን (ኤፌ4፤3-7) ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም፡፡

በጋራ በምንጸልየው ጸሎተ ሃይማኖታችንም ውስጥ፡- «ሐዋርያት በሰሯት በአንዲት ቅደስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን» እንላለን፤ የቤተ ክርስቲያን ልዩ መገለጫዋ አንድነቷ ነውና፡፡ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ በዋናነት በምድር ያሉት ምእመናንና ተጋድሏቸውን የፈጸሙ ቅዱሳን ኅብረት ወይም አንድነት ናት፡፡ “እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አእጹቂሃ..፤ ሥሮቿ በምድር፣ ቅርንጫፎቿም በሰማይ ያሉ” የሚለው የቅዱስ ያሬድ ትምህርትም ለዚህ ትልቅ አስረጂ ነው፡፡

ከምንም በላይ ደግሞ አማናዊውን የክርስቶስን ሥጋና ደም የተቀበሉ ሁሉ የአንዱ ክርስቶስ አካል ብልቶች ሆነዋልና አንድ ናቸው፡፡ “…ይዌልጦሙ በቅጽበት አባላተ ክርስቶስ ይኩኑ፤ በኃይለ ጥበቡ መንክር ወዕጹብ ኪኑ፤ ድንቅና ዕፁብ በሆነ በጥበቡ ኀይል የክርስቶስ አካላት ይሆኑ ዘንድ በቅጽበት ይለውጣቸዋል፡፡” እንዲል መልክአ ቁርባን፡፡ በዚህ መልኩ አንድ የሆኑ ክርስቲያኖች የአንዱ ወይን ግንድ (የክርስቶስ) ልዩ ልዩ ቅርንጫፎች ናቸው እንጂ የተለያዩ ተክሎች አይደሉም (ዮሐ.15፡5)፡፡ እናም በክርስቶስ ክርስቲያኖች የተሰኙ ሁሉ በአንድ አማናዊ እረኛ የሚመሩ አንድ መንጋ ናቸው እንጂ የሚለያዩ አይደሉም (ዮሐ.10፡16)፡፡

እንዲህ ዓይነቱ የአንድነት መንፈስ ደግሞ የሚገኘው ሥጋዊና ደማዊ እውቀት አይደለም፤ ይልቁንም በእምነት እንጂ፡፡ ለዚሁም ነው ‹‹ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፣ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን….እስክንደርስ ድረስ…›› ተብሎ የተገለጸው (ኤፌ.4፡12-13)፡፡ ምንጊዜም ክርስቲያን ሆኖ ከምእመናን አንድነት በመነጠል ‹‹ሙሉ›› ሊሆን የሚችል እንደማይኖር በዚህ ተገልጧል፡፡

እኛ ክርስቲያኖች ‹‹አንዲት ቤተ ክርስቲያን›› ብለን የምናምነው በሰማይ ካሉት መላእክትና በአጸደ ነፍስ ካሉ ደቂቀ አዳም ጋር ጭምር አንድነት ያገኘንባትን መንፈሳዊ ኅብረት ነው፡፡ በምድር ካሉና ዕለት ዕለት ከምናያቸው ወንድሞቻችና እኅቶቻችን ጋር ያለንን ኅብረት በማቋረጥ ፈጽሞ ከማናያቸው ከእግዚአብሔር እና ቅዱሳኑ ጋር ኅብረት አለን ብንል ዘበት ይሆናል፤ ‹‹…ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?›› እንዲል (1ዮሐ.4፡20)፡፡

በምንም ሒሳብ አብረውን ከሚያገለግሉና መንግሥተ እግዚአብሔርን ለመውረስ አብረውን ከሚደክሙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ኅብረት መነጠል ጤነኛነት ሊሆን አይችልም፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ በአንድነት ውስጥ የሚሰጥ መሆኑን አስቀድመን ተመልክተናል፤ በተቃራኒው ደግሞ መለያየትን የሚዘራውና አንድነትን በመፈታተን ደስ የሚለው ቢኖር ጠላታችን ሰይጣን ብቻ ነው፡፡ ስለዚህም አንዴ በቋንቋ፣ ሌላ ጊዜ በዘውግ፣ ከዚያ ሲያልፍም በትውልድ መንደር እየተከፋፈሉ መናቆሩ ማንን እንደሚያስደስት ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ ከምንም በላይ ኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ መሆን መቼም ሊበጠስ በማይችል መንፈሳዊ የፍቅር ገመድ እርስ በርስ ሊያስተሳስረን ይገባል፤ ከዚህ የወጣ ክርስትና የለምና፡፡

ምንጭ፡- የጉባኤ ቃና መጽሔት መልእክት (መጋቢት 2010 ዓ.ም)

ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? (ክፍል ሁለት)

በመ/ር ኃ/ሚካኤል ብርሃኑ

ቤተ ክርስቲያን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ እግዚአብሔርን በማመን የጸኑ በሥራቸው የተመሠከረላቸው የእውነተኛ አማኞች ማኅበር ናት፡፡ በምድር ላይ ከተመሠረቱ ማኅበራት ሁሉ ይልቅ አምሳያ የሌላት በእግዚአብሔር ፈቃድ ለእግዚአብሔር ዓላማ በእግዚአብሔር የተመረጡና የተጠሩ ሰዎች ጉባኤ በመሆኗ ከሁሉ የተለየች ተብላለች፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም እንደጻፈው ”እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህንም ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው” (ሮሜ 8÷30) ይላልና፡፡

Read more

ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? (ክፍል አንድ)

በመ/ር ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

«ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ካሃል» (Qahal) እና «ኤዳህ» (Edah) ተብሎ ይተረጐማል፡፡ ሐዲስ ኪዳን በተጻፈበትና ሰብአ ሊቃናት (Septuagint) ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ በተረጐሙበት ትርጒም አቅሌሲያ (akklesia) በሚል ቃል ተጽፏል፤ ወደ ግእዝ ሲተረጐምም ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተተርጉሟል፡፡

Read more

‹‹ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ ይሁን›› ፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፵ (የመጨረሻ ክፍል)

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ማኅበራዊ የመገናኛ ብዙኀንን ስንጠቀም መልካሙን ከክፉ መለየት፣ ከአስተምህሮአችን ጋር ከሚቃረነው መራቅ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ መንፈሳዊ እና ሃይማኖታዊ መልእክቶችን በማኅበራዊ የመረጃ መረቦች በምናስተላልፍበት ወቅት የሚከተሉትን ሥርዓታዊ አካሄዶች መከተል አለብን፡፡

Read more

‹‹ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ ይሁን›› ፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፵ (ክፍል ሁለት)

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፋቸው መልእክታት መካከል ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ላይ እንዳስቀመጠው፡ ‹‹ነገር ግን ሁሉ በአግባብ እና በሥርዓት ይሁን›› 1ኛ ቆሮ. ፲፬፤፵ ብሏል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን መልእክት መሠረት አድርጋ  ልጆቿን ታስተምራለች፡፡ በሁሉም የአምልኮ ዘርፍ ሥርዓት መሥርታ ሕግጋተ እግዚአብሔርን እያጣቀሰች ምእመናን በቀና መንገድ እንዲመሩ ታሳስባለች፡፡ ያላመኑትን ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር በማምጣት፤ ያመኑትን በእምነት በማጽናት፤ የጸኑትን ደግሞ በመባረክ እና በመቀደስ ለማያልፈው ዘለዓለማዊ መንግሥት እንዲበቁ የንስሓ ትምህርትን በማስተማር ለንስሓ ሕይወት ታዘጋጃለች፡፡ ከሕግ እና ከሥርዓት ብሎም ከትክክለኛ አስተምህሮዎቿ የሚርቁ፤ የሚሸሹ እና የሚቃወሙትን ደግሞ በምክረ ካህን ታስተምራለች፤ እምቢ አሻፈረኝ ያሉትን ደግሞ  ታወግዛለች፡፡

Read more

‹‹ሁሉ በአግባቡ እና በሥርዓቱ ይሁን›› ፩ኛ ቆሮ.፲፬፥፵ (ክፍል አንድ)

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር እንዲል እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የሚሠራበት ጊዜ አለው፡፡ ዓለምን ሲፈጥር፣ ሙታንን ሲያስነሣ፣ ድዉያንን ሲፈውስ፣ የተሰደዱትን ሲመልስ፣ ያዘኑትን ሲያረጋጋ እርሱ ጊዜ አለው፡፡ ሁሉንም በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው እንዲል ለሥራው ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር የተፈጠረ፣ እርሱ የሠራለትን ሥርዓት ተከትሎ የሚኖር እንደመሆኑ ለእንቅስቃሴው ሁሉ ጊዜ አለው፡፡ የሰው ልጅ በጨለማ የኖረበት ጊዜ አለው፤ በብርሃን ውስጥ ያለፈበትም ጊዜ አለው፡፡ የሰው ልጅ በድንቁርና የኖረበት ጊዜ አለ፤ በዕውቀት ብርሃን የተመላለሰበት ጊዜ አለ፡፡ የሰው ልጅ በጥበብ ሰክኖ ፈጣሪውን ያመሰገነበት ጊዜም አለው፡፡ የሰው ልጅ ባልተጻፈ ሕግ የተመራበት ጊዜ አለው፤ በተጻፈ ሕግም የተመራበት ጊዜ አለው፡፡

Read more