ቤተ ክርስቲያን ማን ናት? (ክፍል አንድ)

በመ/ር ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

«ቤተ ክርስቲያን» የሚለው ቃል የግእዝ ቃል ሲሆን መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ በተጻፈበት በዕብራይስጥ ቋንቋ «ካሃል» (Qahal) እና «ኤዳህ» (Edah) ተብሎ ይተረጐማል፡፡ ሐዲስ ኪዳን በተጻፈበትና ሰብአ ሊቃናት (Septuagint) ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ በተረጐሙበት ትርጒም አቅሌሲያ (akklesia) በሚል ቃል ተጽፏል፤ ወደ ግእዝ ሲተረጐምም ቤተ ክርስቲያን ተብሎ ተተርጉሟል፡፡

ቤተክርስቲያን የሚለው ቃል ከሁለት ጥምር የግእዝ ቃላት፤ማለትም ቤተ እና ክርስቲያን ከሚሉት ሁለት ቃላት የተገኘ ነው፡፡ ትርጒሙም ቤተ ማለት አደረ፤ ክርስቲያን ማለት ደግሞ የክርስቶስ ማደሪያ፣ የክርስቶስ ሕዝብ፣ የክርስቶስ ተከታይ ማለት ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ የሚለው ቃል ወገንን፣ ነገድን ያመለክታል፡፡ ይህም ቤተ ያዕቆብ፣ ቤተ እስራኤል፣ ቤተ አሮን የሚለው ቃል የእስራኤልን ሕዝብ፣ የእስራኤልን ወገን የሚያመለክት እንደሆነ ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የሚለውንም ቃል እግዚአብሔር በክርስቶስ የጠራውና ለእግዚአብሔር የተለየ አካል፣ ለእግዚብሔር የተለየ ሕዝብ እና ለእግዚአብሔር አምልኮ የተለየ ቦታ የሚል ትርጒም አለው፡፡

    በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን የሚለው ቃል በዘይቤም በምሥጢርም ሦስት ዐይነት አወጣጥ አለው፡፡ የመጀመርያው ፍቺ ፡- ከውሃና ከመንፈስ /ከማኅፀነ ዮርዳኖስ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ/ የተወለደ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆነ አካል፤

ሁለተኛው አፈታት፡- ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ የተወለዱ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ የሆኑ የክርስቲያኖች አንድነት ጉባኤ፣

ሦስተኛው፡- ለአምልኮተ እግዚአብሔር የተለየ (የተመረጠ) ቦታን ያመለክታል፡፡ ይህም ክርስቲያኖች የሚሰባሰቡበት ምሥጢራቱ የሚፈጸሙበት ሕንፃ ቤተ መቅደስ ነው፡፡

ይህንን ምሥጢራዊ ትርጉም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳትሆን አምስቱም አኃት አብያተ ክርስቲያናት የሚቀበሉት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አሳብ ነው ፡፡ ስድስቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት በአምልኮተ እግዚአብሔርና ዶግማዊ በሆነ ሥርዓት አንድ ናቸው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቃል ከላይ በጠቀስነው መሠረት ትርጒሙን ይስማሙበታል፡፡

    ቤተ ክርስቲያን ሲባል አንዳንድ ሰዎች ትርጒሙን ሳይረዱት አንደኛውን ትርጉም ብቻ ይዘው ማለትም ለአምልኮተ እግዚአብሔር የተለየ ምሥጢራቱ የሚፈጸሙበትን በእግዚአብሔር ፈቃድና በሰዎች ጥበብ የታነጸን ቤተ መቅደስ ብቻ በማሰብ  አጥብበው እንደሚያዪት አይደለም፡፡ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ውጭ ያሉት ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቃል ለራሳቸው ሰውነት ብቻ በመስጠት ሕንጻ ቤተ መቅደስን ሲነቅፉ ይደመጣሉ፡፡ ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን ጥልቅ የሆነ መለኮታዊ ምሥጢር የተሸከመች እጅግ የሚደንቁ ባሕርያት ያሏት በእጅ ከመዳሰስና በዐይን ከመታየትም ያለፈ የረቀቀ የእግዚአብሔር የምሥጢር ግምጃ ቤት ናት፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *