መናፍቃን የሚስቱባቸውና የሚያስቱባቸው መንገዶች (ክፍል አንድ)
ዳዊት አብርሃም
ነገረ ድኅነትን (የመዳን ትምህርትን) በተሳሳተ መንገድ የሚያስቡና ስሕተት የሆነን ትምህርት ከማስተማር አልፈው ትክክል የሆነውን የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የሚቃወሙ ወገኖች እዚህ አቋም ላይ ሊደርሡ የቻሉበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ከብዙዎቹ ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹን በመለየት ቀለል ያለውን መንገድ መርጠን ለማየት እንሞክራለን፡፡ የስሕተቶቹ መነሻ በመጠኑ ሲዳሰስ የሚከተለውን ይመስላል፡፡
- በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ መመሥረት
በማንኛውም የትምህርት መስክ አንድ አቋም ላይ ለመድረስ በቂ የሆነ መረጃ መያዝ እንደሚያስፈልግ የጥናትና ምርምር ሕግ ግድ ይላል፡፡ ዓለማዊ ወይም ምድራዊ ነገር ይህን ያህል ጥንቃቄ የሚያስፈልገው ከሆነ ሰማያዊው የነገረ መለኮት ዕውቀት ደግሞ የቱን ያህል ጥንቃቄ፣ የቱንስ ያህል ትዕግሥት ይሻ ይሆን? በተለይ የሰው ልጆችን ዘለዓለማዊ ሕይወትና ዘለዓለማዊ ጥፋት በቀላሉና በችኮላ፣ በተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ብቻ በመመሥረት ለማወቅና እውነቱ ይህ ብቻ ነው ብሎ ለመደምደም መሞከር ከባድ ስሕተት ላይ መጣሉ አይቀርም፡፡ ብዙዎቹ መናፍቃን ግን በጥቂት ጥቅሶች ላይ ከመመሥረት አልፈው በሁለትና በሦስት ጥቅሶች ላይ ብቻ ተመሥርተው ይደመድማሉ፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፤ በጣም በሚገርም ኹኔታ በአንዲት ነጠላ ጥቅስ ላይ ብቻ ተመሥርተው ትልቅ ነገር መለኮታዊ ግንብ ለመገንባት ይጥራሉ፤ ወይም የተገነባውን ታላቅ ግንብ ለመናድ ይሞክራሉ፡፡ አንዳንዶች አንዲትን ቃል መዘው በመያዝ መዳን በጌታ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፤ ቀጥለውም ቅዱሳን ለመዳን ምንም ሚና ሊኖራቸው አይገባም በማለት ይደመድማሉ፡፡