“ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ፤ የማትረግፍ አበባ” (ቅዱስ ያሬድ)

በዲ/ን ሕሊና በለጠ

በቤተ ክርስቲያናችን ከመስከረም ሃያ ስድስት እስከ ኅዳር አምስት ያለው ዓርባ ቀናትን የያዘው ጊዜ ዘመነ ጽጌ፣ ወርኃ ጽጌ በመባል የሚታወቅ ነው። ከዋክብትን ለሰማይ ውበት የፈጠራቸው አምላካችን እግዚአብሔር አበቦችን ደግሞ ምድርን ያስጌጧት ዘንድ ፈጥሯቸዋል። አበቦች ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ላይ መታየት የጀመሩት በዕለተ ሠሉስ፣ በሦስተኛው የፍጥረት ዕለት ነው። ይህንን የመዘገበልን ሙሴ በኦሪት ዘፍጥረት ላይ እንዲህ ይለናል፡ ‹‹ምድርም ዘርን የሚሰጥ ሣርንና ቡቃያን እንደ ወገኑ ዘሩም ያለበትን ፍሬን የሚያፈራ ዛፍን እንደ ወገኑ አበቀለች። እግዚአብሔርም ያ መልካም እንደ ሆነ አየ››። (ዘፍ.፩፡፲፪)።

ጊዜን በወቅቶች ከፍሎ፡ በየትኛው ጊዜ ምን ዓይነት ምስጋናን ማቅረብ እንደሚገባን ሥርዓትን በመጻሕፍቱ የሠራልን ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ፡ በዚህ የሙሴ ቃል ላይ ተነሥቶ በድጓ ዘጽጌ እንዲህ ይለናል፡- ‹‹በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ ወሤሞ ለፀሐይ ውስተ ጠፈረ ሰማይ ወርእየ ከመ ሠናይ ወካዕበ ይቤ ለታውፅዕ ምድር ጽጌያተ ዘበድዱ ወፍሬያተ ዘበበዘመዱ – በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ሠራ፤ ፀሐይንም በጠፈር ላይ አሠለጠነው፤ የሠራው ሁሉ መልካም እንደ ሆነ እግዚአብሔር አየ። ዳግመኛ ምድር አበቦችን በየግንዱ ፍሬዎችን በየነገዱ ታውጣ እንዳለ››። (ድጓ ዘጽጌ)። እግዚአብሔር ሰውን በዕለተ ዓርብ የፈጠረው ሰማይን በከዋክብት፣ ምድርን በዕፅዋት አስጊጦ ከፈጸመ በኋላ ነው። ቅዱስ ያሬድ በዚሁ በጽጌ ድጓው እንዳለውም ‹‹ወወሀበ ገነተ ምስለ ጽጌያት – ገነትንም በአበቦች እንዳሸበረቀች ሰጠው›› እንዲል።

አንድ ደጋሽ ምግቡን አዘጋጅቶ፣ መጠጡን አሰናድቶ፣ ቤቱን አስውቦ የከበረ እንግዳውን በመጨረሻ እንደሚጠራው፡ እግዚአብሔር አምላክም ከፍጥረታት ይልቅ የከበረውን ሰው ሁሉን አሰናድቶ ከፈጸመ በኋላ ፈጠረውና በሁሉ ላይ ሾመው። አዳም ይኖርባት ዘንድ የተሰጠችው ገነትም ያማረችና የተዋበች ነበረች። ለዚህ ነው አምላካችን ‹‹ወይቤሎ ለአዳም ወሀብኩከ ርስተ ገነተ ትፍሥሕት በጽጌ ሥርጉተ ወበፍሬ ክልልተ- ለአዳም ‹አዳም ሆይ በፍሬ የተከበበች በአበባ የተሸለመች የደስታ ገነትን ለአንተና ለልጆችህ ርስት ትሆንህ ዘንድ ለርስትነት ሰጠሁህ›› በማለት ገነትን ‹‹የደስታ ገነት›› ብሎ የሰጠው። (ድጓ ዘጽጌ)። አዳም በበደለ ጊዜ ግን ባሕርይው ጎሰቆለ። ከገነት ወጣ፤ ስደተኛ ሆነ፤ ምድርም በአዳም ምክንያት ተረገመች። ዕፀ በለስን በመብላት መዋቲነትን መረጠ። ምንም እንኳን ለዘላለም ሕይወት ቢፈጠርም በበደሉ ምክንያት የሚሞት ሆነ። እንደ አበባ ሊያብብ ቢፈጠርም ባለመታመኑ ምክንያት ጠወለገ። አበባ እሳት ሲያቃጥለው፣ ፀሐይን ሲያጣ ወይም ሙቀቷ ሲበረታበት፣ ውኃን ሲጠማ፣ ውጫዊ ኃይል ሲያርፍበትና ከግንዱ ሲለይ ይጠወልጋል፣ ይረግፋል። አዳምም ከጕንደ ወይኑ ከእግዚአብሔር ተለይቶ ጠወለገ፤ ሥጋው በመቃብር ነፍሱ በሲኦል ረገፈ። መልሶ እንዲያብብ ‹‹የሕይወት ውኃ›› የተባለ ‹‹ፀሐየ ጽድቅ›› ክርስቶስ ያስፈልገው ነበር። ለዚህ ደግሞ ለድኅነቱ ምክንያት የሆነችው ንጽሕት እመቤት ድንግል ማርያም ታስፈልገው ነበር። ለዚህ ነው ቅዱስ ያሬድ እንዲህ ሲል የገለጻት፡- ‹‹እስመ ርእየ ሕማማ ለአመቱ ወገብረ ኃይለ በመዝራዕቱ… መዝገቡ ለቃል ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ መድኃኒተ ሕዝብ – የባርያይቱን መዋረድ አይቷልና ኃይልን በክንዱ አደረገ፤ የማትረግፈውን አበባ የዓለም መድኃኒት የቅዱሳን መዓዛ እንድትሆን አደላት›› (ድጓ ዘጽጌ)።

ቅዱስ ያሬድ ‹‹የማትረግፈው አበባ›› ያላት የማይረግፍ ዘላለማዊ ክብርና ቅድስና ያላትን እመቤታችንን ነው። ስለ እርሷ ‹የማይረግፍ አበባነት› ከማየታችን በፊት ግን፡ ሊቁ በአበባ ከመሰላቸው መካከል ከእመቤታችን ጋር ዐቢያን አምሳላት የሚባሉት መስቀሉ እና ቤተ ክርስቲያንም ይህ ”ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ፤ የማትረግፍ አበባ” ዐውደ ስብከት ዲ/ን ኅሊና በለጠ ቅዱስ ያሬድ ጥቅምት/ ፳፻፲፫ ዓ.ም 5 ቅጽል ይገባቸዋልና የእነርሱንም ‹የማይረግፍ አበባነት› በጥቂቱ ልናይ ይገባናል። ይልቁንስ ከጠቀስናቸው ከሦስቱም ይልቅ በአበባ ከሚመሰሉት ከዐራቱ ዐቢያን አንዱ የሆነው ጌታችን፡ ‹‹የማይረግፍ አበባ›› ነው፤ ሌሎቹም ይህን ጸጋ ያገኙት ከእርሱ ሥር ተጠልለው ነውና ከሁሉ አስቀድሞ የእርሱን አበባነት ማየቱ ተገቢ ነው። የጌታችን አበባነት ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ ‹‹ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፥ ከሥሩም ቍጥቋጥ ያፈራል›› ሲል የጌታችንን ከእመቤታችን መወለድ ገልጾአል። (ኢሳ. ፲፩፡፩)። ‹‹በትር›› የተባለችው ያለ ዘር የጸነሰችውና ከእሴይ የዘር ሐረግ ሥር የተገኘችው ድንግል ማርያም ስትኾን ከበትሩ ላይ ያቆጠቆጠው አበባ ደግሞ ጌታችን ነው። ይህንን ሲያስረዳ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ‹‹ትወፅዕ በትር እምሥርወ ዕሴይ ወየዐርግ ጽጌ እምኔሃ… ይእቲ በትር አምሳለ ማርያም ቅድስት ይእቲ ወጽጌ ዘወፅአ እምኔሃ አምሳሉ ለወልድ – ከእሴይ ሥር በትር ትወጣለች፤ አበባም ከእርሷ ያቆጠቁጣል፤ ይህች በትር ቅድስት ማርያም ናት፤ ከእርሷ የወጣው አበባም የወልድ ምሳሌ ነው››። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የማርያም አበባ ነው። ከእርሷ በትርነት የተገኘ አበባ ነው።

ጠቢቡ ሰሎሞን በመኃልየ መኃልይ ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› ማለቱን ሊቃውንት ከጌታችን ጋር አያይዘው ተርጉመውታል። (መኃ.፪፡፩)። ሳሮን (Sharon) በይሁዳ የሚገኝ ሸለቆ ነው። ብዙ ውኃ ያለበትና መለምለም የሚችል ሥፍራ ነው። ነገር ግን በግብፅና በሶሪያ መካከል እንደ መንገድ የሚጠቀሙበት ጠባብ ሥፍራ በመኾኑ አበቦች የሉበትም። ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› በሚለው ጥቅስ ላይ ሳሮን የሕዝበ እስራኤል፣ ቆላ ደግሞ የአሕዛብ ምሳሌ ናቸው። በእስራኤልም ሆነ በሕዝብ መካከል ፍሬ ድኅነት አልተገኘባቸውም ነበር፤ ድኅነትን የሚሰጠውን አበባ፣ ማለትም ክርስቶስን አላገኙም ነበርና። የማርያም አበባ የሆነው ጌታችን በተወለደ ጊዜ ግን በሳሮን ለተመሰሉት ለእስራኤላውያን ጽጌረዳ፣ በቆላ ለተመሰሉት አሕዛብም አበባ ሆነላቸው። ያውም በጊዜ ብዛት የማያልፍና የማይጠወልግ፣ የማይረግፍም አበባ። ‹‹እኔ የሳሮን ጽጌ ረዳ የቈላም አበባ ነኝ›› ያለው ጌታችን በጠቢቡ አንደበት ቀጥሎም ‹‹በእሾህ መካከል እንዳለ የሱፍ አበባ፥ እንዲሁ ወዳጄ በቈነጃጅት መካከል ናት›› ይላል። (መኃ.፪፡፪)።

ይህን ያብራሩ ሊቃውንት ‹‹እርሱ የቆላ አበባ እንደ ሆነው ሁሉ የሚወዳቸው ሁሉ የእርሱን ምሳሌነት ተከትለው አበባ እንዲኾኑ ይፈልጋል። ማለትም የእርሱን መንገድና ምሳሌነት የሚከተል ነፍስ ሁሉ አበባ ይኾናል›› ይላሉ። በእሾህ እንደ ተከበበች የሱፍ አበባ ወዳጄ ብሎ የገለጻት የሰው ነፍስን ነው። ይህን ክፍል በተረጎመበት ትምህርቱ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ‹‹ነፍስ ወደ መሲሁ የምትናፍቅ አበባ ናት፤ የዚህን ዓለም ፈተና ሁሉ ድል አድርጋ ወደ እርሱ የምትጓጓ አበባ ናት›› ይላል። (A Patristic Commentary on The Song of Songs; Fr. Tadros Y. Malaty;) የቅዱስ መስቀሉ አበባነት አበው ‹‹በሴት ጠፋን በሴት ዳን›› እንደሚሉት ሁሉ ‹‹በዕፅ ጠፋን በዕፅ ዳን››ም ይላሉ። ያጠፋን ዕፅ ዕፀ በለስ ሲኾን ያዳነን ዕፅ ደግሞ ዕፀ መስቀሉ ነው። የመስቀሉ ጠላቶች የሚበሰብስ መስሏቸው ዕፀ መስቀሉን ከመሬት ሥር ለሦስት መቶ ዓመታት ቀብረውት ቢቆዩም ‹‹የማይረግፈው አበባ›› መስቀሉ ግን ምንም ሳይኾን በቅድሰት ዕሌኒ ምክንያት ተገኝቷል።

ዛሬም ማዕተብና መስቀሉ የሚወክለው ክርስትናን ጨርሶ ለመቅበር የሚጥሩ ሰዎች የማይሳካላቸው መስቀሉ ‹‹የማይረግፍ አበባ›› ስለ ሆነ ነው። ውኃ የማይጠጣ ተክል ይጠወልጋል፤ መስቀሉ ግን ‹‹እኔ ከምሰጠው ውኃ የሚጠጣ ሁሉ ግን ለዘላለም አይጠማም፥ እኔ የምሰጠው ውኃ በእርሱ ውስጥ ለዘላለም ሕይወት የሚፈልቅ የውኃ ምንጭ ይሆናል እንጂ›› ያለውን የክርስቶስን ደም ‹ጠጥቶ› ስለ ለመለመ የሚጠወልግ አይደለም – የማይረግፍ አበባ ነው እንጂ። (ዮሐ.፬፡፲፬)። ቅዱስ ያሬድም ‹‹በከመ ይቤ ሰሎሞን በእንተ ማርያም ንዑ ንትፈጋዕ ወኢይኅልፈነ ጽጌ ደመና መስቀል ዘዮም አብርሃ በሥነ ማርያም – ሰሎሞን ስለ ድንግል ማርያም ሲናገር እነሆ ክረምቱ አልፎ በረከት ተተካ እንዳለ የክርስቶስ መስቀል ከድንግል ማርያም ባሕርይ በተገኘው (በተወለደው በክርስቶስ) ዛሬ አብርቷልና የበረከት አበባ ሳያልፈን ኑ እንደሰት›› ይላል። (ድጓ ዘጽጌ)። ለዚህም ነው መዘምራን የመስቀል በዓል ሲደርስ ‹‹መስቀል አበባ ነህ ውብ አበባ አደይ አበባ ነህ ውብ አበባ›› እያሉ የሚዘምሩት። የቤተ ክርስቲያን አበባነት ቅዱስ ያሬድ የቤተ ክርስቲያንን አበባነት ሲመሰክር እንዲህ አለ፡- ‹‹ልዑለ ረሰዮ ለመሠረትኪ አረፋትኪ ዘመረግድ ደቂቅኪ ምሁራን በኀበ እግዚአብሔር…- የተለየሽ ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ሆይ መሠረትሽን ከፍ ከፍ አደረገው። ግድግዳዎችሽን በመረግድ በወርቀ ደማቸው። ልጆችሽ በእግዚአብሔር ዘንድ የሠለጠኑ ናቸው። በምድረ በዳ እንዳለች የሱፍ አበባ ለጋ የሆነ የወይን አበባ ሽታን ትሸቻለሽ። የበረከትንም ፍሬ ታፈሪያለሽ››። ዳግመኛም በዚሁ በድጓ ዘጽጌው ‹‹ሐረገ ወይን እንተ በምድር ሥረዊሃ ወበሰማይ አዕፁቂሃ እንተ በሥሉስ ትትገመድ ወታፈሪ ለነ አስካለ በረከት ሲሳዮሙ ለቅዱሳን – ሥሯ በምድር ጫፏ በሰማይ የሆነች በፈቃደ ሥላሴ ተገርዛ የምትለቀም የበረከት ፍሬን የምታፈራልን የወይን ሐረግ የተለየች ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ናት›› ይላል። ቤተ ክርስቲያን ‹‹ፍሬ›› የተባለ የክርስቶስን ሥጋ ወደሙን ዘወትር የምትሰጠን የማትረግፍ አበባ ናት። ብዙዎች ሊያረግፏትና ሊያጠወልጓት ለዘመናት ቢዘምቱባትም፣ ዲያቢሎስ ጦሩን ሁሉ ቢወረውርባትም፡ ልክ ለምለም አበባ በረጅም ሥሩ ውኃን ከመሬት እየሳበ የበለጠ እንደሚያብበው ‹‹የውኃ ግድግዳ የደም መሠረት›› እያልን የምንዘምርላት ቤተ ክርስቲያንም የበለጠ አበበች እንጂ አልጠወለገችም። አትጠወልግምም።

የእመቤታችን አበባነት ‹‹የማኅጸንሽ ፍሬ ቡሩክ ነው›› ለተባለው ለእውነተኛው ፍሬ መገኛ የሆነችው እመቤታችን የማትረግፍና ዘወትር የምታብብ አበባ ናት። እመቤታችን በማይጠወልግና በለምለም ተክል መመሰሏ ነገረ ማርያምን ለተማረ ሰው አዲስ አይደለም። ሙሴ በሲና ተራራ ላይ እሳቱ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው፣ ሐመልማሉም እሳቱን ሳያጠፋው ያየው ምሥጢር ለእሳተ መለኮትና ለትሥብእት ተዋሕዶ ምሳሌ ነው። ‹‹የእግዚአብሔርም መልአክ በእሳት ነበልባል በእሾህ ቍጥቋጦ መካከል ታየው እነሆም ቍጥቋጦው በእሳት ሲነድ ቍጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ››። (ዘፀ. ፫፡፪)። እሳት ተዋሕዶት ያልጠወለገው ሐመልማል ለእመቤታችን ምሳሌ እንደ ሆነ ሊቁ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ ሲያስረዳ ‹‹ጌታችን ክርስቶስን በወለደችው ጊዜ ከእርሷ ወደ ሰው ሕይወት የበራው የመለኮት ብርሃን ሐመልማሉን አላቃጠለውም። በተመሳሳይም በእርሷ ውስጥ ያለው የድንግልናዋ አበባም አምላክን በወለደችው ጊዜ አልረገፈም›› ይላል። ሌሎች እናቶች ሲያገቡና ሲወልዱ ጽጌ ድንግልናቸው ይወገዳል፤ የማትረግፈው አበባ ድንግል ማርያም ግን ወልዳም ጽጌድንግልናዋ አልተለወጠም። የኢየሩሳሌምን ጥፋት እንዳያይ እግዚአብሔር በእንቅልፍ ምክንያት የሠወረው አቤሜሌክ፡ ከቀጠፋት ከስልሳ ስድስት ዓመት በኋላ ሳትጠወልግና ሳትደርቅ ወተቷ ሲንጠባጠብ የተገኘችው የበለስ ቅጠል ምሳሌነቷ ለእመቤታችን እንደ ሆነ ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አመሥጥረው ያስረዳሉ። (ተረ. ባሮ. ፫)። ይህች ቅጠል ተቀጥፋ ከስልሳ ስድስት ዓመታት በኋላም ከነ ልምላሜዋ መገኘቷ የእመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና፣ ንጽሕናና ቅድስና የሚያሳይ ነው።

“የማኅጸንሽ ፍሬ ቡሩክ ነው” ለተባለው ለእውነተኛው ፍሬ መገኛ የሆነችው እመቤታችን የማትረግፍና ዘወትር የምታብብ አበባ ናት። የካህኑ አሮን የደረቀ በትር መለምለሙም ለእመቤታችን ሌላው ምሳሌ ነው። ‹‹እንዲህም ሆነ በነጋው ሙሴ ወደ ምስክሩ ድንኳን ውስጥ ገባ እነሆም፥ ለሌዊ ቤት የሆነች የአሮን በትር አቈጠቈጠች፥ ለመለመችም፥ አበባም አወጣች፥ የበሰለ ለውዝም አፈራች››። (ዘኁ. ፲፯፡፰)። ይህም አስቀድመን እንዳየናቸው ምሳሌዎች ሁሉ መጠቀስ የሚችል ነው። ‹‹በሰላመ ገብርኤልን›› አዘውትሮ የሚጸልይና ለእመቤታችን ልዩ ፍቅር የነበረው አንድ አስቴራስ የተባለ ዲያቆን ነበር። ይህም ዲያቆን ወደ ሩቅ አገር እየሔደ ሳለ ጨካኞች በመንገድ አገኙትና ገድለውት ሳይቀብሩት ከመንገድ ዳር ትተውት ሔዱ። ነገር ግን ሌሎች መንገደኞች ሲያልፉ አይተውት ከዚያው ከመንገዱ ዳር ቀብረውት ሔዱ። ከሦስት ቀንም በኋላ በዚያ አቅራቢያ ባለ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለሚያገለግል አንድ መልካም ዲያቆን እመቤታችን በራእይ ትገለጣለች። ጓደኞቹን አስተባብሮም የዲያቆን አስቴራስን አስከሬን ከመንገዱ ዳር በማውጣት በቤተ ክርስቲያን ግቢ እንዲቀብሩት ታዛቸዋለች። ዲያቆኑም እመቤታችን እንዳዘዘችው ሌሎች ዲያቆናትን ይዞ ወደ ቦታው በመጓዝ አስከሬኑን ቢያወጡት ርሔ እንደሚባል ሽቱ መዓዛው እጅግ ደስ የሚያሰኝ ከአስከሬኑ የበቀለ የጽጌሬዳ አበባን አገኙ። በዚህም እየተደነቁ አስከሬኑን በክብር ገንዘውት በታዘዙት ሥፍራ ቀበሩት። ይህን የተአምረ ማርያም ታሪክ አባ ጽጌ ድንግል እንዲህ ተቀኝቶበታል፡- “ጽጌ አስተርአየ ሠሪጾ እምዐፅሙ፣ ለዘአምኀኪ ጽጌ ለገብርኤል ምስለ ሰላሙ፣ ወበእንተዝ ማርያም ሶበ ሐወዘኒ መዓዛ ጣዕሙ፣ ለተዐምርኪ አሐሊ እሙ፣ ማሕሌተ ጽጌ ዘይሰመይ ስሙ። ትርጉም፡- የክርስቶስ እናቱ የሆንሽ ድንግል ማርያም ሆይ መልአኩ ገብርኤል ደስ ይበልሽ እያለ ካቀረበልሽ ሰላምታ ጋር አበባን ይዞ እጅ ከነሣሽ ሰው ዐፅም የጽጌሬዳ አበባ በቅሎ ታየ ስለዚህም የተአምርሽ ዜና ባስደሰተኝ ጊዜ ስሙ ማኅሌተ ጽጌ የሚባል ምስጋናን አመሰግንሻለሁ። (ማኅሌተ ጽጌ) (ሊቀ ጠበብት አስራደ ባያብል፣ የማሕሌተ ጽጌ ትርጉምና ታሪክ፣ ፳፻፬፣ ፳)፡፡

አንድ ሌላ የእመቤታችን ወዳጅ የሆነ ዲያቆንም እንዲሁ በግፍ ተገድሎ በተቀበረ በአራተኛ ቀኑ፡ በመቃብሩ ላይ ፈርከሊሳ የተባለ አበባ ይበቅላል። የአበባው ቅጠል ላይም ዲያቆኑ በሕይወት እያለ ዘወትር ይጸልየው የነበረው ‹‹በሰላመ ገብርኤል›› ጸሎት ተጽፎበት ተገኝቷል። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫም በመልክአ ውዳሴው፡- ማርያም ጽጌ ዘትምዕዚ እምፈርከሊሳ፣ ይማዖ ጽድቀ ዚአኪ ለዘዚአየ አበሳ፣ ከመአራዊተ ይመውእ አንበሳ። ትርጉም፡- ፈርከሊሳ ከምትባል የሽቱ እንጨት መዓዛ ይልቅ አንበሳ አራዊትን እንደሚያሸንፍ ጽድቅሽ፣ መዓዛ ቅድስናሽ የኔን በደል ያጥፋው። (መልክአ ውዳሴ) በማሕሌተ ጽጌም ይህንና ይህን የመሰለውን ሁሉ በማንሣት እመቤታችንንና ጌታችንን በአበባ እየመሰሉ ካህናቱና ምዕመናኑ ሲያመሰግኑ ያድራሉ። ማጠቃለያ፡- የዚህ ዓለም ሀብትና ጊዜ እንደ ጤዛ የሚረግፉ፣ እንደዚህ ዓለም አበባ የሚጠወልጉ ናቸው። የሰው ልጅ በዚህ ምድር ቢያዝን ኀዘኑ ዘላለማዊ አይደለም። ቢደሰትም የዚህ ምድር ደስታና ፈንጠዝያ የሚያልፍ ነው።

የሰው የጉብዝና ዘመንና የምድር ሕይወት እንኳን የሚረግፍ ነው። ነቢዩ የሰው ልጅን እንደ ሣር መጠውለግ ሲገልጽ ‹‹የማጽናናችሁ እኔ ነኝ፥ የሚሞተውን ሰው እንደ ሣርም የሚጠወልገውን የሰው ልጅ ትፈራ ዘንድ አንተ ማን ነህ?›› ይላል። (ኢሳ.፶፩፡ ፲፪)። የሰው ልጅ ከሚጠወልግ ከዚህ ምድር ሕይወቱ ይልቅ ዘላለማዊውን የማይረግፍ ሕይወት ያገኝ ዘንድ ‹‹የማይረግፉ አበቦች›› ያልናቸውን ሊጠጋ ይገባዋል። የጌታችንን ሥጋውን ሊበላ ደሙን ሊጠጣ፣ ጌታችን ራስ ለሆነላት ለአካሉ ለቤተ ክርስቲያን ብልት ለመኾን ሊፋጠን፣ በእመቤታችን አማላጅነትና በመስቀሉ መማጸኛነት አምኖና ተመርኩዞ መንፈሳዊ ሕይወቱን ሊያበረታ ይገባዋል። ይህን በማድረግም ‹‹የክርስቶስ አበባ›› የተባለች ነፍሱን ከመጠውለግና ከመርገፍ ይታደጋታል። ‹‹ጽጌ እንተ ኢትትነገፍ – የማትረግፍ አበባ›› ብሎ ቅዱስ ያሬድ የጠራት እመቤታችን ሁላችንንም ከመከራ ትጠብቀን። አሜን፡፡

ምንጭ፡- ሐመር መጽሔት ጥቅምት ፳፻፲፪ ዓ.ም

የአብነት ትምህርት ለግቢ ጉባኤያት ያለው ጥቅም

በመጋቤ ሃይማኖት መ/ር ይላቅ ሻረው

 (የጅማ ሐ/ኖ/ቅ/ኪ/ም/ ቤተ ክርስቲያን ስ/ወ/ክ/ ኃላፊ)

ትምህርት መንፈሳዊ ከጥቅሙ በስተቀር ጉዳት የሚባል አንዳችም የጎንዮሽ ችግር የለበትም፡፡ ለዚያውም አብነት ትምህርትን መማር የሞራልም ጥቅም አለው፡፡ ምክንያቱም ፈሊጣዊና ምሳሌአዊ ንግግሮች ከአብነት ትምህርት ማግኘት ስለሚቻል፡፡ ከቃሉ ስንነሣ እንኳን “አብነት” ማለት መሠረት፣ መነሻ፣ መጀመሪያ፣ የሚቀድመው የሌለ የሁሉም የበላይ ማለት ነው፡፡ አብነት ትምህርትን ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ማስተማር ማለት አማራጭ የሌለው ትልቁ ምርጫ ነው፡፡ በተግባርም በቆየንባቸው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢዎች ባሉ አብያተ ክርስቲያናት የምናገለግል አገልጋዮች ተማሪዎች የመማር ጥቅሙን አይተናል፡፡

ለዚህም የጅማ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ እንደምስክርነት ሆኖ ቢቀርብ የሚያስመሰግን ነው፡፡ በቃል የማንዘረዝራቸው (ስማቸውን የማንጠራቸው) ለሀገርም፣ ለቤተክርስቲያንም ልዩ ጥቅም የሚሰጡ ከዲቁና እስከ ቅስና ድረስ፡- “ቀሲስ ዶክተር፣ ቀሲስ ኢ/ር” የምንላቸውን ውድ ልጆች አፍርቷል፡፡ “ባንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” የሚባለውም ይህንን ይመለከታል፡፡ በሁለት አፍ የተሳለ ሰይፍ ሆነው እንዲወጡ ከተፈለገ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎችን አብነት ትምህርት ማስተማር ላይ ከበፊቱ ይልቅ መትጋት ያስፈልጋል፡፡ ምናልባት ለጊዜው ጥቅሙን ላናውቅ እንችል ይሆናል ካለፈ በኋላ ግን ስለሚቆጨን ከወዲሁ መበርታት ይመከራል፡፡

በተለምዶ የቆሎ ትምህርት ቤት እያልን የምንጠራውን አብነት በተናጠል ለመማር ከአለንበት ተነሥተን አብነት ትምህርት ቤት ፍለጋ የምንከራተትበትን ውጣ ውረድ የሚያውቅ ያውቀዋል፡፡ ግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ግን በአንድ የመማሪያ ተቋም ተሰብስበው ሲገኙ “ከመጣሽ ማርያም ታምጣሸ” ነውና አብነቱን አስተምሮ ሁለተኛ ጥቅማቸውን በማረጋገጥ የማኅበረ ቅዱሳን ትጋትና አስተዋፅኦ በቃላት የሚገለጥ አይደለም፡፡ ሀገራዊ ተቋማትና ቅድስት ቤተክርስቲያንም፣ ዛሬ ላይ እየተጠቀሙባቸው ያሉ ብዙ ምሁራን አብነት ትምህርት ቤት የተማሩት ናቸው፡፡ ለዚህ ግቢ ጉባኤን አብነት ትምህርት ማስተማር ከራስ አልፎ ለቤተሰብ፣ ከቤተሰብ ለአካባቢ፣ ከአካባቢ ለሀገር … ጥቅሙ በቀላሉ የሚገመት ስላልሆነ የተማሪዎች ቤተሰብም ጥቅሙን ለልጆቻቸው ቢያስተምሩ የወደፊት መልካም ዜጋ ማግኘት ይቻላል፡፡

 ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች አብነት ትምህርት መማራቸው ምን ይጠቅማል?

ሀ. ዘመኑን  ለመዋጀት

ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የአብነት ትምህርት መማር ከከንቱ አስተሳሰብና ከስንፍና እንዲርቁ በክፉዎቹም ቀናት መካከል ያለውን መንፈሳዊ ሕይወታቸውን  ከክፉ ይጠብቁ ዘንድ ዘመኑን እንዲዋጁ ብርቱና ጠንካራዎችም እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡ ይህም ስንፍናቸውን እያራቀ ለጸሎትም እያተጋ ዘወትር በእግዚአብሔር ቤት እንዲኖሩ ያበረታቸዋል፡፡ “ከእንቅልፍ የምትነሡበት ሰዓት አሁን እንደደረሰ ዘመኑን ዕወቁ፣ ካመንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደእኛ ቀርቦአልና” የሚለውን የቅዱስ ጳውሎስን መልእክት በተግባር የምናየው የአብነት ትምህርትን የተማሩ ተማሪዎች በግቢ ጉባኤ ቆይታቸው መገንዘብ ስለቻልን ነው፡፡ (ሮሜ 13፥11)

ለምሳሌ በቅዱሳት ሥዕላት፣ በኪነ ጥበብ፣ በሥነ ጽሑፍ በመሳሰሉት ሁሉ ብርቱና ጠንካራ ተማሪዎችን ስንመለከት የቤተ ክርስቲያን ተስፋዋ መለምለሙን ያሳየናል፡፡ ዘመኑን የሚዋጅ፣ ጥበብን የሚወድ፣ ትውልድን የሚቀርፅ፣ ዜጋ ለመፍጠር በግቢ ጉባኤያት  የአብነት ትምህርት ማስተማር አማራጭ የሌለው ምርጫ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደ ሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ፡፡” በማለት የመከረን መንፈሳዊ ሕይወት ለዓለም ማሳያ መስታውት፣ በጥበብም ለሚመላለሱ ብልህ ሰዎች ጥቅም መሆኑን ሲያመለክተን  ነው፡፡ (ኤፌ. 5፥15)

ለ. ከክፉ የጎልማሳነት  ምኞት ለመራቅ

ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች በግቢ ጉባኤያት ቆይታቸው የአብነት ትምህርትን መማራቸው  እግዚአብሔርን ባለመፍራት በሥጋ ፈቃድ ከሚመላለሱበት ክፉ ዘመን እንዲርቁ  ይረዳቸዋል፡፡  ለምሳሌ፡- ከልዩ ልዩ ሱሶች፣ ከዝሙትና ከክፉ ሁሉ አስተሳሰብ ይጠብቃቸዋል፡፡ በመሆኑም የአብነት ትምህርትን  መማሩ ጥቅሙ የጎላ ነው፡፡ ከሀገራችን  ከልዩ ልዩ አካባቢዎች  የመጡ ወጣቶች የአብነት ትምህርትን እንዲማሩ መደረጉ ከክፉ ልማዳዊና ጎጂ ድርጊቶች እንዲታቀቡ ከማድረጉም  ባሻገር እርስ በእርስ በመንፈሳዊ ወንድማማችነት እንዲቀራረቡ፣ አንዱ ለሌላው መልካሙን እንዲያስብ ፣ ከክፉ የጎልማሳነትም ምኞት  በመራቅ በትምህርታቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ላይ እንዲያተኩሩ፣ በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር እንዲከትሙም ያስችላቸዋል፡፡

. መንፈሳዊ ሰይፍን  ለመታጠቅ

ቅዱስ ጴጥሮስ “በዘፈንም፣ ያለ ልክ በመጠጣት፣ ነውርም ባለበት በጣዖት ማምለክ የተመላለሳችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃል፡፡ በማለት እንደተናገረው (፩ኛ ጴጥ 4፥3) አብነት ትምህርትን መማር ተማሪዎች በማወቅም ባለማወቅም ያለ ልክ የኖሩበትን ዘመን በቃን ብለው ከሥጋዊ አስተሳሰብ በመለየት ጠላትን ድል የሚያደርጉበት የመንፈስን ሰይፍ እንዲታጠቁ የሚያደርጋቸው መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ፡- “የመዳንን ራስ ቁር፣ የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ፣ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው” ተብሎ እንደተጻፈ መንፈሳዊ ሰይፍ ማለት የጾም፣ የጸሎት፣ የስግደት፣ የምጽዋት እንዲሁም የመታዘዝ፣ የመገዛትና የቅንነት በአጠቃላይ የበጎ ምገባር ትጥቅ ማለት ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ የተነገረውም ይህ ነው፡፡(ኤፌ.6፥1-12)

. ሃይማኖትን በሚገባ ለመረዳት

ሃይማኖታዊ ዕውቀት ስንል መንፈሳዊ ዕውቀትን ነው፡፡ መንፈሳዊ ዕውቀት ደግሞ የነፍስ ዕውቀት እንጂ የሥጋ ዕውቀት አይደለም፡፡ ስለዚህ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን የአብነት ትምህርት ማስተማሩ ወይም እንዲማሩ ማድረጉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ አስተምሮዋን እንዲረዱ ያስችላቸዋል፡፡ ይህም አገልግሎቷን የተሟላ እንዲሆን ያደርገዋል፡።

ከዕውቀቶች ሁሉ ታላቁ ዕውቀት የእግዚአብሔርን የባሕርይ አምላክነት የምናውቅበት መንፈሳዊ ዕውቀት ነው፡፡ “ነፍስ ዕውቀት የሌላት ትሆን ዘንድ መልካም አይደለም” እንዲል፡፡ (ምሳ.19፥2) ይህም የሚሆነው ተማሪዎች ከተለያዩ ቦታዎች ስለሚመጡ በውስጣቸው ብዙ ጥያቄዎች ይፈጠርባቸዋል፡፡ የእነዚያንም ጥያቄዎች መልስ ለማወቅ ካላቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሣ ደጋግመው ይጠይቃሉ፡፡ በሚሰጣቸው ምላሽ በሚያውቁት ዕውቀትም ግልጽ መረዳት የሚኖራቸው በአብነት ትምህርት ማለፍ ሲችሉ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን ወይም በተዋሕዶ ሃይማኖታችን ትልቁ ዕውቀት የሚባለው የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት መረዳት፣ የተረዱትንም  ሳይጠራጠሩ ማመን ነውና፡፡

በመጽሐፍ እውነተኛ “አምላክ ብቻ የሆንክ አንተ የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይቺ የዘለዓለም ሕይወት ናት” ተብሎ የተጻፈውን እውነት ለመረዳት መሠረቱ አብነት ትምህርት ነው፡፡ (ዮሐ.17፥3)

ሠ.ተፅዕኖ  ፈጣሪ ለመሆን

የአብነት ትምህርት መማር ለግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በሌሎች ጓደኞቻቸውም ዘንድ ሆነ በማኅበረሰቡ ዘንድ የመሰማት፣ የመደመጥ፣ የማሸነፍ፣ የሐሳብ የበላይነት እንዲኖራቸውና ተጽዕኖ መፍጠር እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡ በጠቅላላው ትምህርቱ በቃል የሚያዝ ትምህርት ስለሆነ አብነት ትምህርት የተማረ ሰው ምን እናገራለሁ ብሉ አይጨነቅም፡፡ ከአንደበት ላይ ቅኔ የሚነጥቁ  ምሁራን የሚፈጠሩትም በዚሁ በአብነቱ ካለፉት መምህራን መካካል ነው፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን በተለይም የጸሎትና የዜማ መጻሕፍትን በአእምሮ የመወሰንና፣ ያለመርሳት ጸጋ የሚታደልበት በዚሁ በአብነት ትምህርት ቤት ነው፡፡

በጥቅሉ ብዙ ትምህርቶችን ሰብስቦ በጭንቅላት ማከማቸት፣ ለትውልድ ማድረስ፣ ለቤተሰብ ማውረስ፣ የረሱትን ማስታወስ ማለት ነው፡፡ የተፅዕኖ ፈጣሪነት ጸጋውም የሚመጣው ከማስታወስ፣ ካለመዘንጋት የተነሣ ስለሆነ የአብነት ትምህርት ለግቢ ጉባኤ ማስተማር ማለት ሙሉ ሃይማኖቱን በሰው ልቡና ወይም አእምሮ ውስጥ እንደሚቀመጥ ትልቅ መዝገብ ወይም ግምጃ ቤት ይቆጠራል፡፡

           ወስብሐት  ለእግዚአብሔር

“መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሀ በሰው ፊት ይብራ((ማቴ፭፥፲፮)

                                                                       / ቢትወድድ ወርቁ

ክርስቲያኖች በዓለም ስንኖር ሌሎችን ወደ ሃይማኖት ሊያመጣ ወደ እግዚአብሔር ሊያቀርብ የሚችል የሚገባ መልካም አኗኗር ሊኖረን እንደሚገባ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስተምሩናል፡፡ ተግባራዊ የክርስትና ሕይወት በቃል ከምንመሰክረው በላይ በሌሎች  አርአያነት ተጽዕኖ አለውና፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብፁዓን የተራራው ስብከቱ ለጊዜው ለቅዱሳን ሐዋርያቱ በፍጻሜው እስከ ዓለም ፍጻሜ ለሚነሡ ክርስቲያኖች ሊኖረን ከሚገባን አኗኗር አንጻር ክርስቲያኖችን በአራት ነገሮች መስሎ አስተምሯል፡፡

                የምድር ጨው ናችሁ (ማቴ፭፥፲፫)

ጌታችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ   ክርስቶስ   በቅዱስ ወንጌሉ  ”እናንተ የምድር ጨው ናችሁ ጨው አልጫ ቢሆን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጭ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም‘  በማለት እንደተናገረው ጨው የገባበት ነገር ሁሉ ይጣፍጣል፡፡ክርስቲያኖች ይልቁንም በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም እንዲሁ የዓለሙን ሕይወት የሚያጣፍጡ ሊሆኑ እንደሚገባቸው ሲያስተምር ”የምድር ጨው ናችሁ‘  አለ፡፡ ጌታችን  ” እናንተ የምድር ጨው ናችሁ‘ ብሎ መናገሩ የሰው ልጅ በሙሉ  ከኃጢአቱ የተነሣ ጣዕም አጥቶ አልጫ ሆኖ እንደነበር ሲያስገነዝብ ነውና፡፡

ስለዚህ  እንደዚህ በኃጢአት ምክንያትም  አልጫና ጣዕም አልባ የሆነውን የሰውን ልጅ መምራት ይቻላቸው ዘንድ እንዲህ ያሉ ምግባራትን ከደቀ መዛሙርቱ (ከክርስቲያኖች)  እንደ ግዴታና ቅድሚያ እንደሚፈለግባቸው እንረዳለን፡፡ አስቀድሞ የዋህና ለጋሽ የሆነ የሚምር ስለ ጽድቅ የሚራብና የሚጠማ ሰው እነዚህን ደገኛ ምግባራት  ለሌሎች ሰዎችም እንደ ጅረት ውኃ ይፈስሱ ዘንድ ያደርጋቸዋል እንጂ መልካም ምግባራትን  ”ለእኔ ብቻ‘  አይልምና፡፡ ዳግመኛም በልቡ ንጹሕ የሆነ፣ የሚያስታርቅ፣ ስለ እውነት ብሎም የሚሰደድ ሰው ሕይወቱን በአግባቡ የሚመራው ለሌሎች ጭምር ነው፡፡

ጨው ባይጣፍጥ አልጫ ቢሆን ምን ያደርጋል ? ቢክቡት ይናዳል ቢንተራሱት ራስ ይቆርቁራል፡፡ ከተክል ቦታ ቢያደርጉት ተክል ያደርቃል ብለው ሰዎች እንደሚጥሉት እንደሚረግጡትም ክርስቲያኖችም ለሌሎች አብነት ካልሆንን ማን ይሆንላቸዋል? ለሌሎች አብነት መሆን ካልቻልንም ለራሳችንም ሆነ ለሌላው አንጠቅምምና፡፡ጨው ካልጣፈጠ ወደ ውጭ እንደሚጣል እኛንም ሌሎች ከልቡናቸው አውጥተው ይጥሉናል፡፡በክፉ አኗኗራችን ሌሎች ሰዎችን በማሰናከላችን እግዚአብሔር ከመንግሥተ ሰማያት ውጭ ያደርገናል፡፡

ጨው ሦስት ተግባራት አሉት፡፡ ያጣፍጣል፣ቁስል ያደርቃል፤እንዲሁም ሥጋን እንዳይፈርስ አንዳይተላ ይጠብቃል፡፡ ክርስቲያኖችም የሌሎችን ሕይወት ማምረር ሳይሆን በመልካምነት ማጣፈጥ አለብንና ጌታችን ይህን አስተማረን፡፡ ጨው ቁስል እንደሚያደርቅ ክርስቲያኖችም በኃጢአትና በርኲሰት ተስፋ በመቁረጥና በክሕደት የቆሰለ ዓለምን በወንጌል የተገለጠ መልካም አኗኗርን ገንዘብ በማድረግ ቁስሉን እንድንፈውስለት ጌታችን አስተማረን፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያቱ ክርስቶሳዊነትንና አርአያ ክህነትን ይዘዋልና “ጌታችን እስከምድር ዳርቻ ድረስ ለማዳን ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ ብርሃን አድርጌሃለሁ ብሎ አዞናል፡፡” በማለት ያስተማሩትንና የሰሙትን ሆነው በመገኘት በተግባር አሳይተው በቃልም መሰከሩ፡፡ ጨው ሥጋን እንዳይተላና እንዳይፈርስ እንደሚጠብቅ ክርስቲያኖችም ይህ ዓለም በእኩይ ምግባር እንዳይፈርስ በዚህም በትል የተመሰሉ አጋንንት እንዳይሠለጥኑበት በአርአያነት አብዝቶ በመብላትና በመጠጣት ሳይሆን በመጾም፤ አብዝቶ በመቀባጠርና ነገረ ዘርቅ በማብዛት ሳይሆን በአርምሞና አብዝቶ በመጸለይ የአጋንንትን ኃይላቸውን የማድከም ጸጋና ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡ (ማር. ፱፥፵፫)

               ለእናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ (ማቴ.፭፥፲፬

ጌታችን  መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” በማለት ያስተማረው ትምህርት ክርስቲያኖች በዓለም ሊኖራቸው የሚገባውን የምሳሌነት (የአርአያነት) ሚናና ድርሻ በሚገባ ያመለክታል፡፡ ክርስቲያኖች አኗኗራችን የክርስትናውን ሚዛን በሳተ ከወንጌል መንገድም ባፈነገጠ ልክ የዓለሙም የበጎነትና የመልካምነት ነገር መስመር ይስታል፡፡ብርሃን ሲጠፋ ጨለማ እንደሚነግሥ በብርሃን የተመሰሉ ክርስቲያኖችም ጨለማ በተባለ ክፉ ሥራ በተዘፈቅን ቁጥር ኃጢአት፣ የፈሪሐ እግዚአብሔር መታጣት፣ ሕገ ወጥነትና ሌሎች እኩይ ምግባራት ይሠለጥናሉ፡፡

ሰዎች ወደ አምልኮተ እግዚአብሔር ከመምጣት ይልቅ ወደ አምልኮ ባዕድ፤ ወደ ጽድቅ ከማዘንበል ይልቅ ወደ ኃጢአት፣ ወደ ንስሓ  ከመቅረብ ይልቅ ወደ ዓመፅ ይተማሉ፡፡ ይህ በሆነ ቁጥርም ዓለም የጭንቀትና የኃዘን የጦርነትና የሁከት ዋሻና መድረክ ትሆናለች፡፡የቤተክርስቲያን አገልጋዮችና ምእመናን አብነትነታቸው በብዙ ወገን ነው፡፡ ስካር፣ ዝሙት፣ ሴሰኝነት፣ ጉቦ መቀበል፣ ቅንአት፣ ቁጣ፣ አድመኝነት፣ መለያየት፣ ዘረኝነትና ጎጠኝነት ሰዎችን ወደ ጨለማ የሚወስዱ የጨለማ ሥራዎች እንደሆኑ በጎ ሥራዎችም ሰዎችን አማናዊ ብርሃን ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ የሚያመጡ የብርሃን ሥራዎች ናቸው፡፡ስለሆነም ጌታችን ለክርስቲያኖች በሙሉ ይልቁንም በየደረጃው ላሉ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እነርሱ የሚሠሩት በጎ ሥራ ሌሎች ገንዘብ ያደረጉትን ጨለማ የሆነ ክፉ አሳብ፣ ንግግርና ተግባራቸውን የሚያጠፋ ብርሃን መሆኑን አስተማራቸው (ሮሜ፲፫፥፰-፲፫) ፡፡

               ሐ. በተራራ ያለች ከተማና መቅረዝ (ማቴ፭፥፲፬፲፭)

አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖችን ”በተራራ ያለች ከተማ ልትሠወር አይቻላትም፡፡ መብራትንም አብርተው ከዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፡፡ በቤቱም ላሉ ሁሉ ያበራል‘  ብሎ በተራራ ባለች ከተማና በመቅረዝ ላይ በተቀመጠ መብራት መስሏቸዋል፡፡  ይህ የጌታችን ትምህርት ክርስቲያኖች ምንም ጊዜ በሰዎች ሁሉ ፊትና በዓለም የትርኢት ቦታ ላይ እንደቆምን ሆነን በማሰብ ልንመላለስ እንደሚገባን ያስተምረናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ይግባውና በመዋዕለ ሥጋዌው ክፉ ለሆኑትም ጭምር ልንጠነቀቅ እንደሚገባን አስተምሮናል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የወንጌል ትርጓሜ እንደሚያስተምረን በቃና ዘገሊላ  በሠርጉ ቤት እመቤታችን ድንግል  ማርያም ልጅዋን ”የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም‘  ባለችው ጊዜ ”ጊዜዬ ገና አልደረሰም‘  ብሎ ለጥቂትም ቢሆን ተአምራቱን ካዘገየባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ የይሁዳ በዚያ ቅጽበት በስፍራው አለመኖር ነው፡፡

እንደዚሁም ወደ ታቦር ተራራ ሲወጣ ዘጠኙን በተራራው ግርጌ ትቶ ሦስቱን ብቻ ወደ ተራራው ራስ ይዞ መውጣቱም በይሁዳ ምክንያት ነው፡፡ ይሁዳ ከቀድሞውም በክፉ አሳብ መያዙንና አሳልፎ እንደሚሰጠው እያወቀ ከደቀ መዛሙርቱ አልለየውም፡፡ ቢለየው ኖሮ ይሁዳ ጌታችንን አሳልፎ ለመስጠቱ  ”ከተአምራቱ፣ ከምሥጢራቱ ቢለየኝ ከሞቱ ገባሁበት‘  የሚል የመሰናከያ ምክንያት ያገኝ ነበርና፡፡

አይሁድ ጌታችንን ለመክሰስ ብሎም የመሰናከያ ነገርን ለማግኘት ብዙ ጊዜ ጥረዋል፡፡ ለምሳሌም ”መምህር ሆይ ይህች ሴት ስታመነዝር ተገኝታ ተያዘች ሙሴም እንደነዚህ ያሉት እንዲወገሩ በሕግ አዘዘን አንተስ ስለ እርስዋ ምን ትላለህ ?‘  ብለው የቀረቡት ለምን እንደነበር ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ሲነግረን ”የሚከሱበትንም እንዲያገኙ ሊፈትኑት እንዲህ አሉ‘ ብሎናል (ዮሐ፰፥፬-፮)፡፡

ምክንያቱም ጌታችን መድኃኒታችን  ኢየሱስ ክርስቶስ ”ተዉአት አትውገሯት‘ ቢላቸው  ”ሕግንና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም‘ ይላል ነገር ግን ደግሞ ይኽው የሙሴን ሕግ ይሽራል ሊሉት፤ ውገሯት ቢላቸውም ደግሞ ለኃጢአተኞች መጣሁ ይላል ነገር ግን ደግሞ አይራራላቸውም ብለው ሊከሱት አስበው መሆኑ በተረዳ ነገር የታወቀ ነው፡፡ በመሆኑም ውገሯትም፣ አትውገሯትም ሳይላቸው ጎንበስ ብሎ በምድር ላይ ከጻፈ በኋላ ”ከእናንተ ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ ይውገራት‘  አላቸው፡፡ እነርሱም የሚከሱበትንና የሚሰናከሉበትን ነገር አጥተው ሕሊናቸው ወቅሷቸው አንድ በአንድ እየወጡ ሄደዋል፡፡ የማያሰናክልና ለክስ የማይመች አኗኗርን ብንከተል እንኳን ዓለም ክርስቲያኖችን ለመክሰስ የሚያስችለውን ነገር ከመፈለግ ወደ ኋላ እንደማትል ይህ ታሪክ ምስክር ነው፡፡

እንኳን ክፉ ነገር ተፈልጎብን፤ ሳይፈለግብንም በክፋት የተሞላን ሰዎች ልንመለስና አኗኗራችንን ልናስተካክል ምንኛ ይገባን ይሆን ?  በብሉይ ኪዳን በናቡከደነጾር ቤተ መንግሥት ይኖሩ የነበሩ አለቆችና መሳፍንቱ በነቢዩ ዳንኤል ላይ በቅንአት ተነሣስተውበት ሊከሱትና ሊያስገድሉት ክፉ ምክንያት ይፈልጉ ነበር፡፡ መጽሐፍ ይህን ሲነግረን ”የዚያን ጊዜም አለቆችና መሳፍንቱ ስለ መንግሥቱ በዳንኤል ላይ ሰበብ ይፈልጉ ነበር፥ ነገር ግን የታመነ ነበረና ስሕተትና በደል ያገኙበት ዘንድ አልቻሉም እነዚያ ሰዎች ከአምላኩ ሕግ በቀር በዚህ በዳንኤል ላይ ሌላ ሰበብ አናገኝበትም አሉ ይለናል (ዳን.፮፥፬-፮)፡፡

ቀደምት አባቶቻችን ለሌላው እንቅፋትና የጥፋት መሰናክል ላለመሆን እንዲህ ተጠንቅቀው ኖረዋል፡፡ በዚህ ዘመን ላለን ክርስቲያኖች ይልቁንም ለቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ”ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን ብለውም አስተምረውናል ‘(፩ኛጴጥ.፪፥፲፪)

               የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን አማላጅነት የቅዱሳን ረድኤት አይለይን!!

“ጠፍተው የተገኙ”

                                                      በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

ስለ መጥፋት ስናነሣ በቅድሚያ አእምሮአችን ውስጥ የሚመጣው እና የመጥፋትን አስከፊነት የተማርንበት የሰው ልጅ ጥንተ ታሪክ ነው፡፡ በመላእክት ሥነ ተፈጥሮ ደግሞ ጠፍቶ መገኘትን፣ወድቆ መነሣትን፣ተሰብሮ መጠገንን ሳይሆን ጠፍቶና ተዋርዶ  መቅረትን ያየንበት ዲያብሎስ ነው፡፡ የሰው ልጅ ግን ጠፍቶ በመገኘት የመውጣት እና ተመልሶ የመግባት ዕድል ማግኘትን ያየንበት ታሪክ ነው፡፡ ይህም በሰው  ልጅ ሕይወት የአባታችን አዳም እና እናታችን ሔዋን መጥፋት የመጀመሪያው ነው፡፡ በዚህ መጥፋት ውስጥ  የሚከሠተው  የመጀመሪያው ወድቆ መሰበር ነው፡፡ እሱም ከብሮ መዋረድ፣አግኝቶ ማጣት፣ገብቶ መውጣት፣ነግሦ መሻር፣ሥቆ ማልቀስ፣ተደስቶ ማዘን፣ሕያው ሆኖ ተፈጥሮ መሞት ነው፡፡

አዳም እና ሔዋን ጠፍተው የተገኙ ናቸው፡፡ከጠፉበት ለመገኘት ደግሞ የፈላጊ መኖር የግድ ነው፡፡ ይህን ስንል ግን የጠፉት ለመገኘት ጠፊዎቹ ምንም ሚና የላቸውም ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም  የጠፉት ለመገኘት  መጥፋታቸውን ማመን፣መጸጸት፣ምሕረትን መሻት መሠረታዊ ጉዳይ ሲሆን የፈላጊያቸውን ድምጽ መለየት እና ወደሚፈልጋቸው ለመቅረብ ፈቃደኛ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር የጠፋውን መፈለግ፣የወደቀውን ማንሣት፣ያዘነውን ማጽናናት፣የተሰበረውን መጠገን አምላካዊ ባሕርዩ ነው፡፡ ለዚህም ነው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ ”እግዚአብሔር ይጠብቀኛል የሚያሳጣኝም የለም በለመለመ መስክ ያሳድረኛል በዕረፍት ውኃ ዘንድ አሳደገኝ ነፍሴን መለሳት ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ መራኝ በሞት ጥላ መካከል እንኳ ብሄድ አንተ ከእኔ ጋር ነህና ክፉን አልፈራም‘ በማለት እግዚአብሔር ፍጥረቱን የማይንቅ እና የሚጠብቅ መሆኑን የመሰከረው  (መዝ.፳፪፥፩) ፡፡

እግዚአብሔር ኃጢአተኛው እንኳ ቢሆን ተመልሶ ንስሓ እንዲገባ እና እንዲምረው (ምሕረት ማድረግን) የሚወድ አምላክ ነው እንጂ ጠፍተን እንድንቀር የሚፈቅድ አይደለም፡፡  በነቢየ እግዚአብሔር በሕዝቅኤል እንደተገለጸው  ” አንተም የሰው ልጅ ሆይ የእስራኤልን ቤት እናንተ በደላችንና ኀጢአታችን በላያችን አሉ እኛም ሰልስለንባቸዋል እንዴትስ በሕይወት እንኖራለን? ብላችሁ ተናግራችኋል በላቸው፡።  እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኀጢአተኛው ይሞት ዘንድ አልፈቅድም ይላል ጌታ እግዚአብሔር የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለ ምንስ ትሞታላችሁ ? በላቸው‘ ይላል፡፡ (ሕዝ.፴፫፥፲)

እግዚአብሔር የሰውን መዳን እንጂ መሞት የማይሻ ደግ አባት ነው፡፡ስለዚህ ስንጠፋ ይፈልገናል፤ስናዝን ያጽናናናል፤ ስንወድቅ ያነሣናል፤ ስንርቀውም በፍቅር እየተከተለ ይጠራናል፡፡ አዳምና ሔዋን በገነት ዕፀ በለስን በልተው ከክብር በተዋረዱ ሰዓት የሠሩት ኃጢአት ስላስፈራቸው በበለሶች መካከል ተደበቁ፡፡ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር በፍቅር እየተከተለ አዳም አዳም እያለ መጣራት ጀመረ፡፡  ሁል ጊዜ እግዚአብሔር ይፈልገናል፡፡ ይህም ፍፁም ፍቅሩን የሚያሳይ ነው፡፡

ለዚህም ነው  ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ”የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና‘ በማለት ራሱን የሰው ልጅ ሲል የገለጸው(ሉቃ.፲፱፥፲)፡፡

በዚህ ገጸ ንባብ ላይ  ሰው የሆነበትንም ዓላማ ሲጠቅስ የጠፋውን ሰው መፈለግ እና ማዳን መሆኑን አስረድቶናል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን እንዲሁ ስለወደደው ከጠፋበት ይፈልገው እና ያድነው ዘንድ የባሕርይ ልጁን እግዚአብሔር ወልድን ላከው፡፡ ይህም በእግዚአብሔር አብ ፈቃድ፣በእግዚአብሔር ወልድ ፈቃድ፣በእግዚአብሔር መንፍስ ቅዱስም ፈቃድ ምሥጢረ ሥጋዌ ተፈጽሞአል፡፡

በበደል ምክንያት ርስቱን ያጣውን እና ከፈጣሪው የተጣላውን የጠፋውን የሰውን ልጅ ፈልጎ ያገኘው እና ወደ ራሱ አቅርቦ ከራሱ ጋር በማስታረቅ  ልጅነቱን አግኝቶ ወደ ቀድሞ ክብሩ ይመለስ ዘንድ ቤዛነቱን የፈጸመለት  መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህንንም ሲያስረዳ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ጠፍተው የተገኙትን ነገሮች  በምሳሌ ያስረዳበት ትምህርቱ በግልጽ እንድንረዳው ያደርገናል፡፡ ጠፍቶ የነበረ ግን የተገኘ፣ወድቆ የነበረ ግን ታድሶ የተነሣ፣ በባርነት ተይዞ ተጎሳቁሎ የነበረ ግን ዳግም ልጅነትን አግኝቶ የከበረ መሆኑን ጠፍተው በተገኙ በተለያዩ ምሳሌዎች አስተምሮናል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ   ጠፍተው ስለ ተገኙት በምሳሌ እየተናገረ ያስተማረባቸው ምሳሌዎችም ከቤት ኮብልለው  በውጪ ስለጠፉት፡-  የጠፋው ልጅ ታሪክ( ሉቃ.፲፭፥፳፬) ፣ በቤት ውስጥ እያሉ ስለጠፉትም፡- በቤት ውስጥ ጠፍታ ስለተገኘችው ድሪም  (ሉቃ.፲፭፥፰) ፣  ከበጎች መካከል ተለይታ ስለ ጠፋቸው እና ስለተገኘችው በግ (ሉቃ.፲፭፥፩) ሲሆኑ እነዚህ ሁሉ ጠፍተው የነበሩ ቢሆንም ተፈልገው መገኘታቸውን እና ፈላጊያቸው(ባለቤታቸው) በመገኘታቸው መደሰቱን በምሳሌ አስተምሯል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእያንዳንዱ በሚገባው መንገድ ወንጌልን በምሥጢር፣በቀጥታ እና በምሳሌ አስተምሯል፡፡ የሰውን በሕይወት መኖሩን እንጂ ሞቱን የማይሻ በመሆኑ ላሉት ጠባቂ፣ለጠፉት ደግሞ ፈላጊ እውነተኛ እረኛ ነው፡፡ለዚህም ነው ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር ጥበቃ እንዳይለየን ስንለምን ከወደቅንበት ኃጢአት ደግሞ በምሕረቱ እንዲያነሣን ይቅርም እንዲለን የምንጠይቀው፡፡

በየትኛውም ስፋራ እና ሁኔታ ውስጥ ብንሆንም ጠባቂያችን አምላካችን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለዚህም ነው በወንጌል ”ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱን ይሰጣል‘ በማለት ያስተማረን(ዮሐ.፲፥፲፩)፡፡ ዓለም የእግዚአብሔርን ልጆች የምታስጨንቅበት የክፋት መረብ ስላላት በተለያየ መንገድ የጠፉ  አሉ፡፡ የጠፉትን ሁሉ ደግሞ የሚፈልግ እርሱ ቸሩ ጠባቂያችን እግዚአብሔር ነውና የፍለጋ ድምጹን ሰምተው በኃጢአታቸው የተጸጸቱ እና ምህረቱን የሚሹ ሁሉ ያገኙታል፡፡

ጠፍተው የተገኙ የተባሉትም በተለያየ በደልና ኃጢአት ምክንያት ከቅድስና ሕይወት ወጥተው በእምነታቸው ተጠራጥረው በምግባራቸው ደክመው የነበሩ ሁሉ ዳግም ወደ ልባቸው ተመልሰው በንስሓ ታድሰው ኃጢአታቸው ይቅር የተባለላቸው ናቸው፡፡የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን፡፡ አሜን

“ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ “ (ኤፌ ፭፥፲፮)

አዲሱ ዓመትን ለመሸጋገር በነፍስ ወከፍ አሰፍስፈንናል ምኑን ጥለን ምኑን አንጠልጥለን እንደምንሸጋገር ግን ብዙዎቻችን አናውቅም፤ ምናልባት ጥቂቶች ለባውያን (ልባሞች) ያውቁ ይሆናል ይህም ሲባል ባለፈው ዘመን ካከናወኑት ተግባር መካከል ወደ ኋላ የጎተታቸውንና ከዘመን ጋር ያጋጫቸውን ክፉ ነገር ትተው ወደ ፊት እንዲራመዱ ያደረጋቸውንና ከዘመን ጋር ያፋቀራቸውን ደግ ደጉን ይዘው መሸጋገርን ማለት ነው፡፡  ወይም ባለፈው ዘመን ከክፉ ሥራና ከስንፍና በስተቀር ጥቂት በጎ ሥራ እንኳን ያልሠሩበት ከሆነ ከወዲሁ ከአዲሱ ዘመን ዋዜማ ጀምሮ ንስሓ ገብተው ያንን ክፉ ሥራቸውንና ስንፍናቸውን ርግፍ አድርገው በመተው በጎ ሥራ ለመሥራት አቅደው መሸጋገርን ማለት ነው፡፡

ዘመን ተሸከርካሪ ነው ራሱ ሊሽከረከር አብሮት የሚሽከረከር ይፈልጋል፡፡ ጊዜና ውኃ ሙላት ሰውን አይጠብቅም›› እንደ እንደሚባለው ወደ ኋላ የሚጎተተውን ግን  ቀድሞት ይሄዳል እንጂ ከእሱ ጋር አብሮ በመጎተት አይጠብቀውም። ይህ ደግሞ  የዘመን ጉዳተኛ ሆኖ መቅረትን ያስከትላል። ነቢየ  እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ‹‹ሰነፍ በልቡ እግዚአብሔር የለም ይላል›› በማለት እንደተናገረው  ከስንፍናው ብዛት የተነሣ ሃይማኖቱን እስከመካድና እግዚአብሔር የለም እስከ ማለት ይደርሳል(መዝ፲፫፥፩) ይህ እንዳይሆን ግን  ዘመንን ቀድሞ  በመገኘት፣ የክብር አክሊልን መቀዳጀት የሰው ልጆች ግዴታ  አምላካዊ ትእዛዝም ነው ።

ሩጫችን ከዘመን ጋር መሆኑን  በአግባቡ መረዳት  ዘመንን ቀድመን መገኘት  ሲገባን  በዘመን ተቀድመን  መገኘት የለብንም ቅዱስ ጳውሎስ ዘመኑን ዋጁ ሲለንም  መልካም ስበእና መንፈሳዊ ትጋትና ንቃተ ሕሊና የዘመን ተግዳሮቶችን የሚያሻግር መንፈሳዊ ጥበብና ዕውቀት  ያለው ሰው ሁኖ መገኘት እንዳለብን  ሲመክረን ነው። ስለሆነም ዘመኑን በአዲስ የሥራ መንፈስ ልንቀበለው ይገባናል። በዘመኑ የሠራ በዘመን ይደሰታል።በዘመን የሰነፈ ደግሞ በዘመን ያዝናል።ያለፈውን ዘመን ያልሠራበትና በእንቅልፍ ወይም በወሬ ብቻ ያሳለፈው ሰነፍ አዲስ ዘመን በመለወጡ ብቻ አዲስ ነገር ሊያገኝ አይችልም። አሮጌውም አዲሱም ነገር ያለው ከራሱ ነው፤ ደስታውም ሆነ ኅዘኑ የሚመነጨው እሱ ራሱ በሠራው ሥራ እንጂ ከዘመን መለወጥ የሚገኝ ምንም ነገር የለም ዝም ብሎ የሚገኝ ድህነት ብቻ ነው። እሱም ቢሆን በቂ ምክንያት አለው፣ ይኸውም የአስተዳደር ድክመንት ወይም የዕውቀት ማነስ አለዚያም እንዲሁም ጦርነትና መቅሰፍት በታዘዘ ጊዜ  ሊሆን ይችላል፣ ከዚህ ሁሉ ውጭ ምንም ነገር የለም፡፡

ዘመንን በዘመናችን እንደታዘብነው የራሱ የሆነ ጫና አለው በአንዱ ዘመን ድርቅና ጦርነት ይበረታል። ለሌላው ዘመን  ዳግመ አዳዲስ የበሽታ ዓይነቶች ሊከሠቱ  ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ እንደ ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ማለት ነው። በፖለቲካ ቀውስ ምክንያትም ሕዝቦች የችግር ሰለባ የሚሆንበት ዘመን አለ። ይህም ሁሉ አልፎ በሌላው ዘመን ደግሞ ጦርነትና በሽታም  ከምድር  ይጠፋና ሰው ልጆች  የሰላምና የጤና ባለቤት የሚሆኑበት ዝናመ ምሕረቱ፣ ጠለ በረከቱ  የሚወርድበት የምድር በረከትም የሚትረፈረፍበት ፤ሕዝቡ ረኀብ ቸነፈርም ከሰው ልጆች  የራቀበት ዘመን ይመጣል ታዲያ በእንዲህ ያለው ደግ ዘመን ያተረፈበት ብልህ ደግሞ አልፎ አልፎ የሚከሠተውን የመከራ ዘመን በሰላምና በጤና ይሸጋገራል፣ በመልካሙ ዘመን ያገኘው በረከት ለመከራው ዘመን ይረዳዋልና፡፡

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ ዘመን ወይም የዘመን አቆጣጠር ሥርት  መሠረት  ዘመን ጉዞውን የሚገፋባቸው የተለያዩ ስያሜዎች አሉት። ማቴዎስ፣ ማርቆስ ሉቃስና ዮሐንስ የሚባሉ አራቱ ወንጌላውያን እየተፈራረቁ የዘመንን ጉዞ ይቆጣጠራሉ፣ሄልሜል ሜሌክ ብርኤል ምልኤልና ናፔኤል የሚባሉ አራት ከዋክብትም እየተፈራረቁ የዘመንን ጉዞ በየተራ ይመራሉ። ክረምት፣ ሐጋይ፣ መፀውና ፀደይ የሚባሉት ወቅቶች ደግሞ ዓመቱን ለአራት ተከፋፍለው የያዙ የዘመን መረማመጃዎች ናቸው። ሁሉም ተደምረው በየተመደቡበት ወራት የየራሳቸውን ኃላፊነትና ድርሻ ይወጣሉ። በኃጢአታችን ምክንት የእግዚአብሔር መቅሰፍት በእኛ ላይ ካልሆነ በስተቀር የተጠቀሱት ሁሉ የተመደቡበትን ኃላፊነት ቸል ብለውት አያውቁም፤ ሁሉም የየራሳቸውን ተልእኮ በሚገባ ይፈጽማሉ፡፡

የዘመንን ዑደት ተቁጣጥሮ ሥራ ለመሥራት ሥልጣን የተሰጠው የሰው ልጅ ይህን የተሰጠውን ዘመን በሥራ ሊዋጀው ይገባዋል።የተወደዳችሁ ምእመናን ዘመን በወለዳቸው የጥላቻ እና የዘረኝነት ክፋቶች እንዲሁም የመጤ ባሕሎችነ አስተሳሰቦች ሰዎች ሳንሆነ ዘመንን  በመዋጀት  ክፉዎቹነ ቀኖች  አልፈን መልካም ቀኖችን  ለማየት  ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “ሕይውትን ሊወድ መልካም ቀኖችንም ሊያይ የሚሻ ምላሱነ  ከንፈሮችንም ተንኮልን ከመናገር ይከልከል ከክፉ ነገር ፈቀቅ በል  መልካም ያድርግ ሰላምንም ይሻ ይከተለውም “በማላት እንተናገረው ዘመንን ቀድመን በቅንነት መትጋት ይኖርብናል (፩ጴጥ፫፥፲) አዲስን ዓመት ስንቀበል ከክፉ ሥራዎች በመራቅ የተጣላነውን ታርቀን የቀማነውንም መልሰን በንስሓ ሳሙና ታጥበን ሥጋውንና ደሙን በመቀበል አዲሱን ዓመት መልካም ዘመን እንዲሆንልን አምላካችን እግዚአብሔርን በጸሎት በመጠየቅ እንጂ በጭፈራ  በዘፈን መሆን የለበትም (፩ጴጥ፬፥፫)

አዲሱን ዓመት እውነተኛ አዲስ ዓመት እንዲያደርግልንና ዘመኑን እንድንዋጀው በሀገራችን ኢትዮጵያ ጦርነት ረኀብ ስድትና በሽታ የሚያበቃበት ሰላም ደስታ የሚበሠርበት ዘመን ይሆንልን ዘንድ  የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃዱ ይሁልን፡፡

“ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” (ዮሐ.፫፥፲፫)

 በቀሲስ ኃይለሚካኤል ብርሃኑ

ቃሉን የተናገረው ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይድረሰውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ነው፡፡ አንዳንዶች ይህንን ቃል ለምን እንደተነገረና ምን ማለት እንደሆነ ባለመረዳት ሲሰነካከሉበት ይስተዋላል፡፡ ለስህተታቸውም እንደ ማስረጃ ለመጠቀም ይሞክራሉ፡፡ በተለይ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዕርገት ሲነሣ  የሚረብሻቸው  የዲያብሎስ የግብር ልጆች ከሞት አልተነሣችም አላረገችም ለማለት ሲጠቀሙበት ይታያል፡፡ ነገር ግን ይህ ቃል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እና ሌሎችም ቅዱሳን ስለ ማረጋቸው የሚያስረዳ እንጂ አለማረጋቸውን የሚገልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ከሌሎቹ የሚለይ መሆኑን የሚያስገነዝብ ነው፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ፣ወእግዚእነ በቃለ ቀርን፣ ዘምሩ ለአምላክነ ዘምሩ፤ እግዚአብሔር በዕልልታ ጌታችንም በመለከት ድምፅ ዐረገ ዘምሩ ለአምላካችን ዘምሩ”(መዝ፵፮፥፭)፡፡ በማለት በምን ሁኔታ እንዳረገ በመግለጽ ተቀኝቶለታል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ የደቀ መዛሙርቱን ልብ እያጸና ተስፋቸውን እየነገረ ትንሣኤውን በግልጽ እንዲረዱ በአካል እየተገለጠላቸው በመካከላቸውም እየተገኘ አስተማራቸው፡፡  ግብረ ሐዋርያት በተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል እንደተጻፈው፡- “ሕማማትን  ከተቀበለ በኋላ ብዙ ተአምራት በማሳየት ዐርባ ቀን ሙሉ እየተገለጠላቸው ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየነገራቸውና እያስተማራቸው ሕያው ሆኖ ራሱን ገለጠላቸው” (ሐዋ.፩፥፫) ይላል፡፡

ከማረጉም አስቀድሞ እንደነገራቸው የሚያጸናቸውን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል እስኪቀበሉ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ  ነግሮአቸዋል፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ሲገልጽ  ‘እነሆ እኔ የአባቴን ተስፋ ለእናንተ እልካለሁ እናንተ ግን ከአርያም ኃይልን እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ተቀመጡ’’( ሉቃ.፳፬፥፵፱) በማለት እንደነገራቸው ጽፎልናል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአርያም ኃይልን እስኪለብሱ ድረስ  በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ ማዘዙ ዳግም ወደ ምርኮ እንዳይመለሱ ነው፡፡ ምክንያቱም አጽናኙን መንፈስ ቅዱስን ካልተቀበሉ መፍራት፣ መጠራጠር፣ መጨነቅ ሊመጣ ስለሚችል ከዚህ ሁሉ ፍርሃትና ጭንቀት የሚታደጋቸውን የመንፈስ ቅዱስን ኃይል መልበስ ስለሚኖርባቸው ነው፡፡

ይህን ካላቸው በኋላ በንፍሐተ ቀርን እጁን ጭኖ ባረካቸው፡፡ እያዩትም ከፍ ከፍ አለ ከዐይናቸውም በርቀት ሳይሆን በርኅቀት ተሠወረ፡፡ የክብሩ መገለጫ የሆነችው ደመና ተቀበለችው፡፡ የመላእክትም ምስጋና እና የመለከት ድምጽ ይሰማ ነበር። ደቀ መዛሙርቱም   ሲያርግ  በአንክሮ  ይመለከቱት ነበር፡፡ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት መላእክትም እንዲህ አሏቸው፡፡ “እናንተ የገሊላ ሰዎች ሆይ ወደ ሰማይ እያያችሁ ለምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ ያረገው ኢየሱስ ከእናንተ ወደ ሰማይ ሲያርግ እንዳያችሁት እንዲሁ ዳግመኛ ይመጣል አሏቸው” (ሐዋ.፩፥፲፩)፡፡

በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ የነገረ ሥጋዌው  ምሥጢር  በልደቱ ይጀምርና በዳግም ምጽአቱ ይጠናቀቃል፡፡ ይኸውም ተወለደ፤ ተጠመቀ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ፤ ተቀበረ፤ ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በክብር በምስጋና ዐረገ፤ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል፤  የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ነው በኪዳን ጸሎታችን መጀመሪያ ላይ “ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተወልደ እማርያም እምቅድስት ድንግል ተሣሃለነ እግዚኦ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተጠምቀ በዮርዳኖስ ወተሰቅለ ዲበ ዕፀ መስቀል ተሣሃለነ እግዚኦ፣ ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን አመሣልስት ዕለት በከመ ጽሑፍ ውስተ ቅዱሳት መጻሕፍት ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽእ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ተሣሃለነ እግዚኦ”  (ጸሎተ ኪዳን)፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ተወለደ ብለን ተጠመቀ ማለትን፣ ተሰቀለ ብለን ሞተ ማለትን፣ ተቀበረ ብለን ተነሣ ማለት፣ ዐረገ ብለን ዳግመኛ በሕያዋንና በሙታን ይፈርድ ዘንድ ይመጣል በማለት የዚህን ዓለም ሥርዓት እንጠቀልላለን፡፡

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱ ከሌሎች ቅዱሳን ዕርገት ይለያል፡፡ ለዚህም ነው በወንጌሉ “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው” በማለት የነገረን (ዮሐ.፫፥፲፫)፡፡

በመጽሐፍ ቅዱስ ከምድር ወደ ሰማይ የተወሰዱ ቅዱሳን፣ ከሰማይም ለምሕረትም ሆነ ለመዓት ወደ ምድር የተላኩ ቅዱሳን መላእክት አሉ፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ዕርገት ከእነዚህ ሁሉ ቅዱሳን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? ብለን ከጠየቅን በዝርዝር ማየት ያሻልና ለአብነት ያህል ጥቂቶችን እንመልከት፡-

፩ኛ. ከሰማይ ከወረደው በቀር ሲል፡-  አካላዊ ቃል  ወደዚህ ዓለም ከመምጣቱ አስቀድሞ የነበረበት አምላካዊ አነዋወር እና የቅዱሳን መላእክት አነዋወር ይለያያል፡፡ እርሱ በፈጣሪነቱ የሚመለክ  እነርሱ ደግሞ በፍጡርነታቸው የሚያመሰግኑ፣ የሚያገለግሉ፣ የሚገዙ ናቸው፡፡ የእርሱ በከበረ ዙፋኑ ከፍከፍ ብሎ የሚኖር  የልዑላን ልዑል፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ ሲሆን ሰውን ለማዳን ከሰማያት ወርዶ ወደዚህ ዓለም መምጣቱ “ከሰማይ የወረደ” ያሰኘዋል፡፡

ለሰማያውያን ሰማያቸው ወይም ሀገራቸው የሆነ አምላክ በሥጋ ማርያም ተገልጦ መታየቱ ልዩ ነውና ከእርሱ ወደ ምድር መምጣት(መውረድ) እና ወደ ሰማይ ከማረግ ጋር የቅዱሳን መላእክት ለምሕረትም ሆነ ለመዓት ወደዚህ ምድር መላካቸው  የሚነጻጸር አይደለም፡፡ በመሆኑም “ከሰማይ ከወረደው ከሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም” አለ ፡፡

፪ኛ. ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከቅድስት ድንግል ማርያም የተወለደና የማዳኑን ሥራ ሁሉ ፈጽሞ  ሰውንም ወደ ቀደመ ክብሩ መልሶ ወደ ሰማያት ዐርጎ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠ  እርሱ ብቻ ነውና ፡፡

፫ኛ. በሕይወተ በሥጋ እያሉ ያረጉ ቅዱሳን፡- በመጽሐፍ ቅዱስ በሕይወተ ሥጋ እያሉ ያረጉ ቅዱሳን መኖራቸው ተጽፎአል፡፡ ከእነርሱም ውስጥ ሄኖክና ኤልያስ ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ቅዱሳን ማረጋቸው እውነት ቢሆንም ዕርገታቸው ግን ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገት ጋር አይነጻጸርም፡፡ ምክንያቱም የእነርሱ አሳራጊ እርሱ ስለሆነ እርሱ ግን በሥልጣኑ ዐረገ፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ስለ ሄኖክ ሲጽፍልን “ሄኖክም እግዚአብሔርን ደስ ስላሰኘው አልተገኘም እግዚአብሔር ሠውሮታልና” (ዘፍ.፭፥፳፬) ይላል፡፡ ሄኖክን እግዚአብሔር ሠውሮታል ይላል እንጂ በሥልጣኑ ተሠወረ አይልም፡፡

እንደዚሁም ኤልያስም በምን መልኩ እንዳረገ ስንመለከት “ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን አለው” (፪ኛነገ.፪፥፱) ይላል፡፡ ኤልያስ እንደተናገረው ሳልወሰድ ማለቱ የሚወስደው ኃይል እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ ስለዚህ ዕርገቱ በእግዚአብሔር እንጂ በራሱ ሥልጣን እንዳልሆነ በግልጽ የሚያስረዳ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ዐረገ ስንል ያረገው በሥልጣኑ ነው፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- “እግዚአብሔር በእልልታ፣ ጌታችንም በመለከት ድምጽ ዐረገ” በማለት የተቀኘለት ነውና ዕርገቱ ልዩ ነው፡፡

፬ኛ. ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያረገው ወደ ሰማየ ሰማያት ወደ መንበረ ክብሩ ነው፡፡ ሄኖክና ኤልያስ ግን ያረጉት ወደ ብሔረ ሕያዋን ነውና የጌታችን የምድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዕርገቱ ከቅዱሳን ዕርገት ጋር ሊነጻጸር አይችልም ፡፡ እርሱ በመለከት ድምጽ በመላእክት ምስጋና  በክብር ያረገ፤ በአባቱም ቀኝ የተቀመጠ፤ የዘለዓለም ንጉሥ ነው፡፡ ወነበረ በየማነ አቡሁ ዳግመ ይመጽዕ በስብሐት ይኮንን ሕያዋነ ወሙታነ ወአልቦ ማኅለቅት ለመንግሥቱ’’   (ጸሎተ ሃይማኖት) እንዲል፡፡

በመሆኑም “ከሰማይ ከውረደው በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም’” ተብሎ የተጻፈው የወረደው ሌላ የወጣው(ያረገው) ደግሞ ሌላ ነው የሚሉ መናፍቃን ስለ ነበሩ የሰው ሥጋን በመዋሐድ አዳምና ልጆቹን ለማዳን የወረደው አካላዊ ቃል የመጣበትን የማዳን ሥራ ፈጽሞ “አባ ወአቡየ ግብረ ዘወሀብከኒ ፈጸምኩ ፤አባት ሆይ የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜአለሁ” በማለት ያረገው ያው ሥጋን ተዋሕዶ ሰው የሆነው አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ለማጠየቅ እንደሆነ ሊቃውንት ያስረዳሉ ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የብዙኃን ማርያም

መ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ብዙኃን ማርያም የተባለበት ምክንያት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ፫፻፲፰ቱ ሊቃውንት በንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ጥሪ መሠረት አርዮስን ለማውገዝ ሚያዚያ ፳፩ ቀን ጉዞ ጀምረው መስከረም ፳፩ ቀን በኒቂያ ስለተሰበሰቡ ብዙኃን ማርያም ተብሏል፡፡ እመ ብዙኃን የሚለውም የሊቃውንቱን ብዛት ያመለክታል፡፡ እንዲሁም እመቤታችን የብዙዎች እናት ናትና እመ ብዙኀን ተብላለች፡፡ (መድብለ ታሪክ)፡፡

ስለዚህ መስከረም ፳፩ ቀን የሚከበረው የእመቤታችን በዓል የብዙኃን ማርያም ይባላል፡፡ ይህም የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግማደ መስቀል ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ መግባቱን ተከትሎ ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን ከሰሜን ከደቡብ፣ ከምሥራቅ፣ ከምዐራብ ከሁሉም የሀገራችን ክፍሎች ቅዱስ መስቀሉን ለማክበር የሚሰባሰቡበት፣ እንዲሁም በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም የታነፀችው ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ቤት በድምቀት የተከበረበት ቀን ነው፡፡
በዕለተ ዓርብ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ ከመስቀሉ ሥር የነበረችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እናት አድርጎ በወንጌላዊው በቅዱስ ዮሐንስ አማካኝነት ሰጥቶናል፡፡ ይህች ቀን የቤታችን እና የኑሮአችን በረከት ለሕይወታችን የድኅነት ምክንያት በሆነችን በቅድስት ድንግል ማርያም ስም ተሰባስበን ዕለቱ የመስቀሉን በረከት የምንሳተፍባት ቀን በመሆኗም ከላይ እንደጠቀስነው የብዙኃን ማርያም ብለን እናከብራታለን፡፡

ይህም ዐፄ ዳዊት ቅዱስ መስቀሉ እንዲሰጣቸው ለእስክንድርያና ለኢየሩሳሌም ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቀኝ እጁ ያረፈበት ግማደ መስቀሉ ለኢትዮጵያ ተሰጠ፡፡ ዐፄ ዳዊት ግን ቅዱስ መስቀሉን ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ እግዚአብሔር በመረጠው ሥፍራ ሳያስቀምጡት በድንገት ዐረፉ፡፡
ልጃቸው ዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ቅዱስ መስቀሉ ተቀብሎ በመስከረም ፲ ቀን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ በማድረግ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከሆነው በኋላ “አንብር መስቀልየ በዲበ መስቀል፤ መስቀሌን በመስቀልኛ ቦታ አስቀምጥ” በተባለው መሠረት መስቀለኛ መልክአ ምድራዊ አቀማመጥና አንድ መግቢያ መንገድ ብቻ ባለው በግሸን ደብረ ከርቤ መስከረም ፳፩ ቀን ፲፬፻፵፮ ዓ.ም በክብር እንዲያርፍ ተደርገል፡፡ በዚህም ምክንያት መስቀሉ በግሸን ተራራ ባረፈበት በመስከረም ፳፩ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡

እንዲሁም በዚህች ዕለት የተፍጻሜተ ሰማዕት ቅዱስ ጴጥሮስ ደቀ መዛሙርት ከነበሩትና በዕውቀታቸው ብዙ ከተጓዙት መካከል እለእስክንድሮስ፣ አኪላስ እና አርዮስ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በአንደበተ ርቱዕነቱና በፍልስፍናው ጎበዝ የተባለው አርዮስ በፈጠረው የክሕደትና የምንፍቅና ትምህርቱ ከራሱ አልፎ ሌሎችንም እስከማጠራጠር ደርሶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በማወኩ የተነሣ ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “አስተጋብኦሙ እምበሐውርት እም ጽባሕ ወእም ዓረብ ወመስዐ ወባሕር፤ ከምሥራቅ ከምዕራብ፣ ከሰሜንና ከደቡብ ከሁሉም ክፍላተ ዓለም አሰባሰባቸው” በማለት እንደተናገረው ታላቁ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ በ፫፻፳፭ ዓ.ም በልዩ ልዩ ክፍላተ በዓለም ያሉ ፫፻፲፰ የቤተ ክርስቲያን አበው ሊቃውንት በኒቂያ ሰብስቧቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ሊቃውንቱን በዚህ ቀን አርዮስን ለይተው በማውገዝ ሃይማኖትን አጽንተው ሥርዓት የሠሩበት ቀን በመሆኑ የሚከበር በዓል ነው፡፡ የቅዱሳን አባቶቻችን የጸናች ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በልባችን ታትማ ለዘለዓለም ትኑር አሜን፡፡

መስቀል የበረከት ዐውድ

ቅዱስ አግናጥዮስ ዘአንጾኪያ /፻፲-፻፲፭/ በነበረው ጊዜ ሰማዕትነትን ሊቀበል ሲወስዱት የሚከተለውን የኑዛዜ ቃል ተናገረ፡- “ከሶሪያ እስከ ሮም ድረስ ከአውሬዎች ጋር በባሕርና በየብስ እየተዋጋሁ እስከዚህች ሰዓት ደርሻለሁ፤ ቀንና ሌሊት በዐሥር አናብስት እጠበቅ ነበር” ብሏል፡፡ ይህ ቃል የወታደሮቹን የሚያስጨንቅ አያያዛቸውን፣ ክፋታቸውንና ጭካኔያቸውን የሚያሳይ ነበር፡፡

በመቀጠልም እንዲህ አለ፡- “እነርሱ አላስፈላጊ የሆነ መከራን ባጸኑብኝ መጠን እውነተኛ ደቀ መዝሙርነት ምን ማለት እንደሆነ ተምሬያለሁ፡፡ እንዲያውም መከራ ሲጨምሩብኝ የምቀበለውን የሕይወት አክሊል እያሰብሁ በርኅራኄ ሳይሆን በፍርሐት በእኔ ላይ የሚያጸኑትን መከራ እንዳይቀንሱ አሳስባቸው ነበር፡፡ እነርሱ ይኽንን ነገር በእኔ ላይ እንዲፈጽሙ ሰውነቴን ለመከራ አሳልፌ ሰጠሁ፡፡ ለእኔ የሚጠቅመኝ ምን እንደሆነ አውቄያለሁ፡፡ አሁን ደቀ መዝሙር መሆን ጀምሬያለሁ፡፡ ከዚህም በላይ የሚታይና የማይታይ መከራን ያድርሱብኝ፣ በእኔ ላይ እሳትን ያምጡ፣ መስቀሉንም ያቁሙ፣ ለአውሬዎችም ይስጡኝ፣ አጥንቴንም ይሰባብሩት፣ ከንፈሬንም ይቁረጡት፣ ሰውነቴንም በሙሉ እንዳልበረ ያድረጉት፡፡ ነገር ግን ወደ ፈጣሪዬ ክርስቶስ የማደርገውን የእምነትና የነፃነት ጉዞ ሊያስተጓጉሉ አይቻላቸውም” ብሏል፡፡

ቅዱስ ጴጥሮስም “ነገር ግን ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ፣ የእግዚአብሔርም መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ፡፡ ከእናንተ ማንም ነፍሰ ገዳይ ወይም ሌባ ወይም ክፉ አድራጊ እንደሚሆን ወይም በሌሎች ጉዳይ ግን እንደሚገባ ሁኖ መከራን አይቀበል፣ ስለዚህ ስም እግዚአብሔርን ያመስግን፡፡ /፩ጴጥ.፬.፲፫-፲፭/ የሚለውን ቃል የክርስትና ጉዞ የመስቀል ጉዞ መሆኑን ያስረዳል፡፡

የልዑል እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በቀራንዮ የተተከለውን፣ በጎልጎታ የተቀበረውን፣ በተአምራት የወጣውን የጌታችን መስቀል ስታስብ እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍቅር ገመድ እየተጎተተ ከሊቶስጥራ ዐደባባይ እስከ ቀራንዮ ሲጓዝ በእምነት ትመለከታለች፡፡ የሕይወትና የክብር መገኛ አምላክ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ በክብር መንገሡን ትመለከታለች፡፡ የፍቅር ትርጉሙ ለሚገባቸው ሁሉ የቸርነት ተግባሩን ትናገራለች፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን የፍቅር ፍላጻው በልቡናው ውስጥ ሥር በሰደደ መጠን ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ ወዴት አለ? ሞት ሆይ መውጊያህ ወዴት አለ? እያለች የፍቅር ዜማን እያዜመች ምርኮን ሲበዘብዝ፣ ሲኦል ሲመዘበር እየተመለከተች /ኤፌ.፬.፰/ ከምድር እስከ ሰማይ በመስቀል ላይ ለነገሠው ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብር ጉልበት ሁሉ ሲንበረከክ ትመለከታለች፡፡ /ፊል.2.፲/፡፡

በቀደመ ርግማን ምክንያት “እሾህና አሜኬላ ያብቅልብሽ” ተብላ የተረገመች ምድር፣ በክብረ መስቀሉ ይህ የመከራ አረም ተወግዶ አዲስ የሆነ የድኅነት ተክል የተዘራባት ምድር ሆነች፡፡ ይህም ተክል ንጹሕ የሆነ የቅድስና ሕይወትን አስገኘ፡፡ እርሱም ክርስቶስ በቀራንዮ ዐደባባይ የነገሠበት የክብር ዙፋኑ ዕፀ መስቀሉ ነው፡፡

በመስቀሉ ፍጥረት ሁሉ አዲስ ሆነ፣ በመስቀሉ ሞትና ኃጢአት በመስቀሉ ሞትና ኃጢአት ተዘርቶበት የነበረው ዓለም በምትኩ ጽድቅና ሕይወት የተዘራበት ዓለም ሆነ፡፡ ጠቢቡ በምስጋናው እንዲህ አለ፡- “እነሆ ክረምትም አለፈ፣ ዝናቡም አልፎ ሄደ፣ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፣ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቁርዬው ቃል በምድራችን ተሰማ፡፡ በለሱ ጎመራ፣ ወይኖች አበቡ፣ መዓዛቸውንም ሰጡ” /መኃ.2.፲፩/ እንዲል፡፡

ይኽም ማለት ቀዝቃዛው የሞት ዘመን በክርስቶስ ቤዛነት አለፈ፣ በአዲስ ሕይወት ታደሰ፣ እርሱ ሁሉን አዲስ አደርጋለሁ እንዳለ ፍጥረትን አዲስ አደረገ፡፡ ይኽም በመስቀል ላይ ባደረገው ቤዛነት ነው፡፡ በሥጋ ሞትን የቀመሰ በትንሣኤው አበባ ምድርን አስጌጠ፣ ፍጥረትን አዲስ አደረገ፡፡ ሙታን አዲስ ሕይወትን ለበሱ፡፡ አበቦች ስለ ጎመሩ፣ ዛፉም መልካም ፍሬን ስለሰጠ ምድረ በዳውም ልምላሜ ጽድቅን ስለለበሰ፣ ፍጥረት ሁሉ ደስ ይለዋል፡፡

ሙሽራዪቱ ቤተ ክርስቲያን ለሙሽራው መድኃኔዓለም ክርስቶስ ክብር የተዘጋጀች ሁና ልትቀመጥ ይገባታል፡፡ ዳግመኛ በሚመጣበት ጊዜ እድፍና የፊት መጨማደድ ሳይኖርባት ለሙሽራው የተገባች ሁና ያገኛት ዘንድ በጽድቅ ለሚፈርደው በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ የተሸከመውን እርሱን /፩ጴጥ.2.፳፬/ ከፍ ከፍ ታደርገው ዘንድ፡፡

ዘወትር በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሚፈተተው በቀራንዮ ዐደባባይ በዕለተ ዐርብ በመስቀሉ ላይ የተዘጋጀው ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙ ነው፡፡ መስቀሉም በክርስቶስ ደም የታጠበ ነው፡፡ የክርስቶስ መስቀል መከራ በዓይነ ሕሊናችን ላይ በሚሣልበት ጊዜ ሁሉ መከራ የተቀበለበት መስቀልም በዓይነ ልቡናችን ዘወትር ይመላለሳል፡፡ እንደገናም ጽድቅን የሚራቡና የሚጠሙ ወገኖች በመስቀሉ ላይ የተፈተተውን ምግበ ሕይወት በመመገብ ነፍሳቸውን ያነጻሉ፡፡ ሞኞችና ማስተዋል የሌላቸው ወገኖች ዕለት ዕለት የሚፈተተውን ይህንን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደም መታሰቢያ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ጥበበኞችና ለድኅነት የተመረጡ ወገኖች ግን ይህ ቃል ከጦር ይልቅ የሚያስፈራ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ቃል በተነገረበት ቦታ ሁሉ የሚታሰባቸው ለሰይጣንና ለመልእከተኞቹ ወደተዘጋጀ ወደዘለዓለማዊ እሳት ሂዱ የሚለውን አስፈሪ የፍርድ ቃል ነው /ማቴ.፳፬.#1/፡፡ በእርግጥ ከባድና አስፈሪ ቃል ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስን መከራ በምትናገርበት ጊዜ ሁሉ ይኽንን የመጨረሻ የአዋጅ ቃል ታስተጋባለች፡፡

በመስቀል የተፈተነ ክርስትና

ሰማዕቱ ቅዱስ እስጢፋኖስ የሰው ልጆች ክርስቲያን የሆኑበትን ምሥጢር ሲያስረዳ እንዲህ አለ፡- “ጌታችን በመስቀል ላይ መስቀሉን እያሰቡ፣ ልባቸውን መስቀሉ የተቀበረበትን የጎልጎታ መቃብር አድርገው በፍጹም ፍቅሩ እንዲመላለሱ ነው፡፡ ከመስቀሉ ፍቅር ይልቅ የዚህ ዓለም ፍቅሩ ያየለባቸው ወገኖች ግን በኃጢአተኞች አኗኗር ልባቸው ስለቀና የእውነትን መንገድ ተቃዋሚና እንደ በሽተኞች መዋጋትን የሚናፍቁ ሆነዋል፡፡ እነዚህ ሰዎች የመስቀሉ ጠላት ሆነው ተነስተዋል፡፡ ይኽንንም ተቃውሞአቸውን የሚገልጹት፣ የማያምኑ መስለው ሳይሆን የሚያምኑ መስለው ስሕተታቸውን ይደግፍልናል የሚሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከተቀመጠበት ዓውድ በመለየት ለእነርሱ በሚመቻቸውና በሚፈልጉት ቦታ ላይ በማስቀመጥ ነው” ይላል፡፡

ክርስቲያን ከማያምኑ ሰዎች በበለጠ ይወደው ዘንድ የሚከተሉት ነገሮች በእርሱ ዘንድ አሉ፡፡ የሚያምን ሰው ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራን በመቀበሉ ፍላጎቱ፣ ተስፋው፣ እምነቱ ሁሉ እንደተፈጸመ በእምነት ያውቃል/ኤፌ.፫.፲9/፡፡ የተፈቀሩ ሰዎች ግን የተፈቀሩበትን የፍቅር መጠንና ያፈቀራቸውን ማንነት፣ ስለ ፍቅራቸውም የተከፈለውን ዋጋ በትክክል የተረዱ አይመስልም፡፡ /ሉቃ.፯፤፯/፡፡ ቤተ ክርስቲያን ግን ምን እንደተደረገላት በሚገባ ተገንዝባለችና “ነፍሴ የወደደችህ አንተ ንገረኝ፣ ወዴት ታሰማራለህ? በቀትርስ ወዴት ትመሰጋለህ? ትላለች”/መኃ.1.7/////////፡፡ መንጋዎቿንም በዕረፍት ውኃ በለመለመ መስክ ታሰማራለች፡፡ እረኛዋም የሠራዊት ጌታ ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡

በአጠቃላላይ ያለ ክብረ መስቀል ክርስትና፣ ያለ ክርስትናም ክብረ መስቀል አይኖሩም፡፡ አበው ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት፣ ዳገቱን የወጡበት፣ እሳቱን፣ ስለቱን ያለፉበት፣ መከራውን የታገሱበት፣ ተልእኮአቸውን የተወጡበት ዕፀ መስቀሉን ተመርኩዘው ነው፡፡ በመስቀሉ የተፈተኑ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች የበረከት ዐውድ የሆነውን የመስቀሉን በዓል በሥርዓተ እምነታቸው መሠረት ማክበር ይገባቸዋል፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፣ መስከረም ፲፮-፴ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም

ልብሳችሁን እጠቡ

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ልብስ የሚለውን ቃል በቀጥታ ስንመለከተው አካል የሚሸፈንበት እርቃንን የሚሸፍን፣ ከሌሊት ቁር ከቀን ሐሩር የሚከላከል ሲሆን የሰውነት ክፍልን ከመሸፈንም አልፎ ግርማ ሞገስንና ውበትን ያላብሳል፡፡ ይህም እንደየ ሀገሩ የአለባበሱ ሥርዓት ሊለያይ ይችላል፡፡ ያም ቢሆን ግን የወንድ ልብስ እና የሴት ተብሎ ይለያል፡፡ አሁን ላይ በአንዳንዶች የምንመለከተው የአለባበስ ሥርዓት ግን ወግን ባሕልን፣ ዕሤትን፣ ሃይማኖትን ማእከል ያደረገ አይደለም፡፡ በተለይ ደግሞ ወጣቱ ክፍል እየተሰነካከለበት ያለው አንዱ የአለባበስን ሥርዓት በማይጠብቁና ለውድቀት የሚጋብዙ የአካል መራቆቶችን በዓይኑ አይቶ በልቡ እንዲመኝ እናም እንዲያመነዝር የሚያደርጉ፣ ባሕልንና ዕሤትንም ያልጠበቁ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ማጠብ መታጠብ የሚለውን ቀጥታ ትርጉሙን ስንመለከት ዕድፍን፣ ቆሻሻን ማስወገድ፣ የቆሸሸን ነገር ማንጻት የሚያመለክት ሲሆን፣ ልብስ የሚለውን ቃል በሌላው ፍቺ ስንመለከት ደግሞ በሕይወታችን ወይም በማንነታችን የሚገለጠውን ውሳጣዊ እና አፍኣዊ ሥራችን ነው፡፡ ከዚሁ ተያይዞ ማጠብ መታጠብ የሚለውም በንስሓ መንጻት፣ መቀደስ፣ በደልን፣ ኃጢአትን መተው፣ ወደ እግዚአብሔር መመለስን ያሳያል፡፡

አባታችን ያዕቆብ “ልብሳችሁን እጠቡ” በማለት ለጊዜው የተናገረው በሥጋ ለወለዳቸው እና በኑሮ አብረውት ለነበሩት አገልጋዮቹ በአጠቃላይ ለቤተሰቦቹ ሲሆን፣ ፍጻሜው ግን በብሉይ ኪዳን በሃይማኖት አባት ለሆነላቸው ለቤተ እስራኤል (ለእግዚአብሔር ሕዝቦች)፣ በሐዲስ ኪዳን በክርስቶስ ክርስቲያን ለተባልን ለሐዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ነው፡፡  አባታችን ያዕቆብ ከመባረኩ አስቀድሞ ያዕቆብ እየተባለ ይጠራ የነበረ ቢሆንም ከተባረከ በኋላ እስራኤል ተብሏል፡፡ እስራኤል የሚለውም የመባረክ፣ የመመረጥ፣ የመቀደስ፣ የመክበር ስም ነው፡፡

እግዚአብሔር ሲያከብርና ሲቀድስ ስምንም ይለውጣል፡፡ ያዕቆብም ሌሊቱን ሙሉ ከእግዚአብሔር ጋር ሲታገል ያደረው ባርከኝ በሚል ልመናና ጸሎት ነበር፡፡ “እግዚአብሔርም አለው ስምህ ያዕቆብ አይባል ስምህ እስራኤል ይባል እንጂ ” ብሎታል (ዘፍ.፴፭፥፲)፡፡ ያዕቆብ የሚለው የቀድሞ ማንነቱ የተገለጠበት ስም ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን የቀድሞ ማንነቱን በበረከት ቀይሮለት ከባረከው በኋላ ያለውን ማንነት የሚገልጥ አዲስ ስም ሰጠው፡፡ ያዕቆብ የሚለው የስም ትርጉም፡-አዕቃጼ ሰኮና(ተረከዝ ያዥ)፣ አሰናካይ ማለት ሲሆን ቀድሞ በዚህ ግብሩ ይጠራ ነበር፡፡ ኋላ ግን እስራኤል ተብሏል፡፡

እስራኤል ማለትም የተባረከ የእግዚአብሔር ሕዝብ ማለት ነው፡፡ ሙሴ በመጽሐፉ እንዳሰፈረው ያዕቆብ ከወንድሙ ከዔሣው ቁጣ ለማምለጥ ወደ አጎቱ ላባ ሄዶ ብዙ ዘመን ከኖረ በኋላ ብዙ ሀብትና ንብረት አፍርቶ ልጆችን ወልዶ ቆይቶአል፡፡ ወደ አባቱና እናቱ ወደ ወንድሙም ለመመለስ ሲነሣ የወንድሙን ይቅርታ እንዲያገኝ ብዙ እጅ መንሻ ይዞ ተነሣ በዚህን ጊዜ እግዚአብሔር ምን ማድረግ እንዳለበት ነገረው፡፡

 “ተነሥተህ ወደ ቤቴል ውጣ በዚያም ኑር ከወንድምህ ከዔሳው ፊት በሸሸህ ጊዜ ለተገለጥሁልህ ለእኔ መሠውያን ሥራ”  እግዚአብሔር ይህን ካለው በኋላ መላው ቤተሰቡ እሱ በስደት ከኖረበት አገር መውጣት እንዳለባቸው፣ ሲወጡ ደግሞ ንጹሐን ሆነው መውጣት እንዳለባቸውና ልብሳቸውን ማጠብ እንደሚገባቸው ከመካከላቸውም እንግዶች አማልክትን ማስወገድ እንዳለባቸው ነግሯቸዋል፡፡ “ያዕቆብም ለቤተሰቡና ከእርሱ ጋር ላሉት ሁሉ እንዲህ አለ ከእናንተ ጋር ያሉ እንግዶች አማልክትን ከመካከላችሁ አስወግዱ፣ ንጹሓንም ሁኑ፣ ልብሳችሁንም እጠቡ፣ ተነሡና ወደ ቤቴል እንውጣ በዚያም በመከራዬ ቀን ለሰማኝ በሄድሁበትም መንገድ ከእኔ ጋር ለነበረው ከመከራም አድኖ ላሻገረኝ ለእግዚአብሔር መሠውያን እንሥራ”(ዘፍ.፴፭፥2-፫) በማለት ነግሯቸዋል፡፡

አባታችን ያዕቆብ ሲናፍቃት ወደ ነበረችው፣ እናት አባቱ ወዳሉባት፣ ወንድሙና የአባቱ የእናቱ ቤተሰቦች ወዳሉባት፣ ተወልዶ ወዳደገባት ሀገር ለመመለስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነለት በስደት እያለ ያፈራቸው እና ያገኛቸው ቤተሰቡ የቆዩበትን የኃጢአት ሥራ እንዲያስወግዱ ጣዖት አምልኮ ያደረጉበትን፣ በጣዖታት ፊት የተንበረከኩበትን፣ ያደፈ ልብሳቸውን እንዲያጥቡና እንዲያነጹ፤ ከዚያም ወደ አያቱ አብርሃም ወደ አባቱ ይስሐቅ መንደር (አገር) ወደተባረከችው ምድር በበረከት ወደሚኖርባት ሀገር ገብተው መኖር እንዲችሉ የሚያደርጋቸውን ቅድመ ሁኔታ በሚገባ አስተማራቸው፡፡

እነዚህም ከላይ የጠቀስናቸው  ሲሆኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ በሕገ ልቡና ለቅዱሳን አበው የገለጸላቸው ናቸው፡፡ ኋላም ለሙሴ በሲና ተራራ ላይ በሕገ ኦሪት እንዳዘዘው “እግዚአብሔርም ይህን ቃል ሁሉ እንዲህ ብሎ ተናገረ ከግብጽ ምድር ከባርነት ቤት ያወጣሁህ እግዚአብሔር አምላክህ እኔ ነኝ ከእኔ በቀር ሌሎችን አማልክት አታምልክ በላይ በሰማይ ካለው በታችም በምድር ከአለው ከምድርም በታች በውኃ ከአለው ነገር የማናቸውንም ምስል ለአንተ አምላክ አታድርግ”(ዘፀ.፳፥፩) የሚል ነውና ለእግዚአብሔር የተለየ ሕዝብ ያዕቆብ እንዳለው እንግዶች አማልክትን ከመካከላቸው እንዲያስወግዱ አደረገ፡፡

ዛሬም ቢሆን በአንዳንዶቻችን ዘንድ ነውር የሆነ ጣዖት አምልኮ በተለያየ መልኩ ሰልጥኖብን እያለ ከሰዎች እይታ ለመሰወር እውነተኛ መስሎ መታየት፣ ነውሩን እንደ ክብር የመቁጠሩ ነገር ይታያል፡፡ አባታችን ያዕቆብ ለቤተሰቡ እንግዶች አማልክትን አስወግዱ፣ ንጹሓን ሁኑ፣ ልብሳችሁን እጠቡ ያለው የተስፋዋን ምድር ለመውረስ የሚናፍቁትን ቤተሰቡን እንደሆነ ሁሉ ዛሬም ተስፋ ወደምናደርጋት ወደ ሰማያዊት ኢየሩሳሌም ለመግባት አምልኮ ጣዖትን ማስወገድ፣ ከበደል ርቀን ንጹሃን ሆነን መኖር፣ በንስሓ ዕንባ መታጠብ እና መንጻት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህም ነው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ “እንግዲህ ለአዲስ ቡሆ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ ከእናንተ አርቁ፣ ገና ቂጣ ናችሁና ፋሲካችን ክርስቶስ ተሠውቶ የለምን አሁንም በዓላችሁን አድርጉ ነገር ግን እውነትና ንጽሕና ባለው እርሾ ነው እንጂ በአሮጌው እርሾ በኃጢአትና በክፋት እርሾም አይደለም”( 1ኛቆሮ.፭፥7) በማለት ያስጠነቀቃቸው፡፡

ሐዋርያው እንዳስተማረን አሮጌ እርሾ ማለት የቀደመ በደላችን፣ ክፉ ሥራችን፣ በጨለማ የተመላለስንበት ማንነት፣ ከእግዚአብሔር ርቀን የኖርንበት ዘመን ነው፡፡ ለዚህም ነው በቤተ ክርስቲያን በምናደርገው ጉባኤ ላይ ተሰባስበን በኅብረትም ሆነ በግላችን የቀደመ በደላችንን አታስብብን፣ አቤቱ ይቅርታህ ፈጥኖ ይደረግልን እያልን የምንዘምረው፡፡

የቀደመ በደላችንን ለማስወገድ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በጅራፍ ተገረፈ፣ በጥፊ ተጸፋ፣ የእሾህ አክሊል ተደፋበት፣ በመስቀል ተሰቀለ፣ ነፍሱን በፈቃዱ ሰጠ፣ በሥጋው ተቀበረ፣ በነፍሱ ወደ ሲኦል ወርዶ ነጻነትን ሰበከ፣ ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት በከርሠ መቃብር  ቆይቶ ተነሣ፣ በዓርባኛው ቀን ዐረገ፣ በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፣ ዳግመኛም ዓለምን ለማሳለፍ በምስጋና ይመጣል፡፡ ክብር ይግባውና ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሁሉ የሆነው የቀደመ በደላችንን ሊያጠፋ ነው፡፡ ከቀደመ በደላችን ነጻ ካወጣን በኋላ፣ ከባርነት አላቆ በልጅነት ጸጋ እንድመላለስ ካደረገን በኋላ ዳግም የኃጢአት ባሮች ልንሆን አይገባም፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም በመልእክቱ፡- “የአሕዛብን ፈቃድ ዝሙትንና ምኞትን ስካርንና ወድቆ ማደርን ያለ ልክ መጠጣትንና ጣዖት ማምለክምን ያደረጋችሁበት ያለፈው ዘመን ይበቃችኋልና”(፩ኛጴጥ.፬፥፫) እንዳለው ሁሉ የቀደመ ክፉ ግብራችንን ማስወገድ ያለፈውን ዘመን ከነ ክፋቱ ጥሎ ማለፍና አዲሱን ዘመን በንስሓ በታጠበ ማንነት መኖር ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ነው አባታችን ያዕቆብ ወደ ቤቴል እንዲወጣ እና ከቤተሰቡ ጋር እንዲገናኝ በተጠራ ሰዓት በስደት ሀገር ያገኛቸው ቤተሰቡን የኖሩበትን የቀደመ በደላቸውን ትተው ልብሳቸውንም አጥበው መውጣት እንደሚገባቸው ያስተማራቸው፡፡

ውጫዊ ልብስ ሲቆሽሽ እንደሚታጠብ ሁሉ ውሳጣዊ ማንነታችንም በኃጢአት ሥራ ሲቆሽሽ በንስሓ ይታጠባል፡፡ ነገር ግን ባደፈ ልብስ ወደ ሠርግ አዳራሽ እንደማይገባ ሁሉ ንስሓ ባልገባ ማንነትም ወደ እውነተኛው ወደ ዘለዓለማዊው የሠርግ ቤት አዳራሽ መግባት አይቻልም፡፡ ንስሓ ኃጢአተኛውን ጻድቅ፣ ዘማዊውን ድንግል የሚያደርግ ነው ሲባል በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ሲመለስ በኃጢአት ይኖር የነበረ ሰው ኃጢአቱ ይቅር ይባልለታል፡፡ ዘማዊ የነበረውም በደሉ ተደምስሶለት ቅዱሳን ሊያገኙት ያላቸውን ጸጋና ክብር ያገኛል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሰውን ከመፍጠሩ አስቀድሞ እንደሚበድል ያውቅ ነበርና የሚጸጸትና ስለ ኃጢአቱ የሚያለቅስ በጎ ኅሊና ፈጥሮለታል፡፡ ለዚህም ነው ንስሓ ለእገሌ ወይም ለነእገሌ ተብሎ ሳይሆን ለሁሉም ሰው ያስፈለገው፡፡ ምክንያቱም ሰው በተለያየ መንገድ ስለሚበድል ኃጢአትን ስለሚሠራ እሱም፡- በአሳብ፣ በቃል፣ በተግባር የሚሠራ ኃጢአት ነው፡፡

ለሁሉም እንደየ ደረጃው ንስሓ ያስፈልገዋልና ለዚህም ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ፡- “ይህች መከራ ስለአገኘቻቸው እነዚህ ገሊላውያን ከገሊላ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ተለይተው ኃጢአተኞች የሆኑ ይመስሏችኋልን አይደለም እላችኋለሁ እናንተም ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ ወይስ እነዚያ በሰሊሆም ግንብ ተጭኖ የገደላቸው ዐሥራ ስምንቱ ሰዎች ከኢየሩሳሌም ሰዎች ይልቅ ተለይተው ኃጢአተኞች ይመስሏችኋልን አይደለም እላችኋለሁ   እናንተም  ንስሓ ካልገባችሁ ሁላችሁ እንደ እነርሱ ትጠፋላችሁ” በማለት ያስተማረው(ሉቃ.፲፫፥፩)፡፡

አባታችን ያዕቆብ ልብሳችሁን እጠቡ ያለው ለጊዜው ውጫዊ ልብሳቸውን ሲሆን በፍጻሜው ግን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መመለስን የሚያስተምር ነው፡፡ ሰው በኃጢአትና በበደል ምክንያት ከእግዚአብሔር እንደሚርቅ ሁሉ በንስሓ ሲመለስ ደግሞ ከእግዚአብሔር የተለየበት ኃጢአቱ ይቅር ተብሎለት ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል፡፡ ይህ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር መለየቱ  የሞት ሞት መሞቱን ሲያመለክተን በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መቅረቡ ደግሞ በዘለዓለማዊ ሕይወት የሚኖር መሆኑን ያስረዳናል፡፡

ከገቡ መውጣት፣ ካገኙ ማጣት የሌለባት የማታልፈውን ዘለዓለማዊ መንግሥቱን እግዚአብሔር ያወርሰን ዘንድ ያደፈው ማንነታችንን የተጎሳቆለ ሕይወታችን በንስሓ ልናጥበውና ንጹሕ ሆነን ምጽአቱን ልንጠብቅ ያስፈልጋል፡፡ መቼ እንደምመጣ አታውቁምና ተዘጋጅታችሁ ጠብቁኝ ብሎ የአመጣጡን ነገር እንዳስተማረን ሁሉ ተዘጋጅተን ልብስ የተባለ ሥራችንን መልካም አድርገን እንኖር ዘንድ በቸርነቱ ይርዳን፡፡ አሜን፡፡

‘‘እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት’’(ማቴ. ፲፭፥፲፪)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ የወይን ሐረግ ስለመሆኑና አምነው የተከተሉት ሁሉ ደግሞ ቅርንጫፎች እንደሆኑ በብዙ ምሳሌ ካስረዳ በኋላ ከላይ በርዕስ የተነሣንበትን ቃል ተናግሯል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ቃል በቃል ስንመለከተው “እኔ እንደወደድኋችሁ እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ የእኔ ትእዛዜ ይህች ናት፣ ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም፤ እናንተስ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ካደረጋችሁ ወዳጆቼ ናችሁ” (ዮሐ.፲፭፥፲፪-፲፭) ይላል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛ እርስ በእርሳችን እንዋደድ ዘንድ እንደሚገባ ከማዘዙ አስቀድሞ እርሱ እኛን የወደደበትን ፍጹም ፍቅሩ አብነት እንዲሆነን ጠቅሶልናል፡፡ እሱም ፍጹም አምላክ  ሲሆን ፍጹም ሰው ሆኖ በሥጋ የተመላለሰው እኛ የሰው ልጆች በግብራችን (በሥራችን) ደካሞች (ሰነፎች) ብንሆንም በነገር ሁሉ ብርቱ የሆነውን እርሱን ተመልክተን ከድካማችን እንድንበረታ ነው፡፡

ለዚህም ነው ጌታችን በወንጌሉ “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ ወደ እኔ ኑ እኔም አሳርፋችኋለሁ፣ ቀንበሬን በላያችሁ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ. ፲፩፥፳፰) በማለት ያስተማረን፡፡

እኛ ምንም ሳይኖረን ማለትም በበደላችን ምክንያት ከጸጋው ተራቁተን፣ በኃጢአት ተጎሳቁለን፣ ደስታ ርቆን በኀዘን ተውጠን ሳለ እንዲሁ የወደደን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ከእኛ ምንም አገኛለሁ ወይም እጠቀማለሁ ሳይል ሕመማችንን የታመመ፣ ስለ እኛ የቆሰለ፣ ሞታችንን ሞቶ ሕይወቱን ያደለን እርሱ ፍቅር ስለሆነ ነው፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያለ ዋጋ እንደ ወደደንና መተኪያ የሌለውን የደም(የሕይወት) ዋጋ ከፍሎልን ፍጹም ፍቅሩን እንዳሳየን ሁሉ እርስ በርሳችን እንዋደድ ዘንድ አዝዞናል፡፡

እርሱ እንደወደደን እርስ በርሳችን መዋደድ ማለትም፡ ጥቅምን፣ ዋጋን፣ ክፍያን፣ ውለታን ምክንያት ሳናደርግ እንዲሁ ያለ ዋጋ፣ ያለ ውለታ፣ ያለ ጥቅም መዋደድ ነው፡፡ ይህም ያለው ለሌለው፣ ያገኘው ላላገኘው፣ የተማረው ላልተማረው፣ የበረታው ለደከመው ነገ ይከፍለኛል ወይም ውለታዬን ይመልስልኛል ብሎ ሳያስብ እንዲሁ ያለ ዋጋ በነፃ የሚደረግ ስጦታ ከእውነተኛ ፍቅር የተገኘ ነው፡፡

እርስ በእርስ መዋደድ፡- ዘርን፣ ብሔርን፣ ቋንቋን ምክንያት ሳያደርግ ድሃ፣ ባለጠጋ ሳይል ሁሉን በእኩል ዓይን መመልከትና መውደድ ነው፡፡ አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ ከሰጠው ከዐሥሩ ትእዛዛት መካከልም አንዱ “ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” (ዘሌ. ፲፱፥፲፰) የሚል ነው፡፡

ስለዚህ ክርስትና ስለራስ ብቻ የሚኖሩበት፣ ስለራስ ብቻ የሚያስቡበት፣ ስለራስ ብቻ የሚጨነቁበት ሕይወት ሳይሆን ስለ ሌላውም የሚኖሩት፣ የሚያስቡበት፣ የሚጨነቁበት፣ የመረዳዳትና የመተሳሰብ ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ኢሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው፤ ኦሪትም ነቢያትም የሚያዝዙት ይህ ነውና” (ማቴ. ፯፥፲፪) በማለት ያሰተማረን፡፡

የክርስትና ሃይማኖት እርስ በእርስ የሚፋቀሩበት፣ የሚረዳዱበትና የሚተሳሰቡበት ሕይወት  ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንቅፋት የሚሆኑብንን ክፉ ምግባራት ከሕይወታችን ልናስወግዳቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ክፉ ምግባራት ራስን ከመጉዳታቸው በተጨማሪ በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ ክርስቲያናዊ የሆነ መልካም ግንኙነት እንዳይኖረንና እውነተኛ ፍቅር እንዳናሳይ የሚያደርጉ ናቸው፡፡ በመሆኑም እነዚህን የመልካምነት እንቅፋቶች የሆኑትን፣ ከክርስቲያናዊ ሕይወት ሊወገዱ የሚገባቸውን ክፉ ተግባራት ከብዙው በጥቂቱ ስንመለከት፡-

፩ኛ. ራስ ወዳድነት

ራስ ወዳድነት ሲባል ስለ ራስ ምቾትና ጥቅም ሲባል ብቻ በጣም ከማሰብ የተነሣ ስለ ሌሎች ሰዎች ወይም ስለ ማኅበረሰቡ ግዴለሽ መሆንና እንዲያውም ስለ ግል ጥቅም ሲባል የሌላውን ሰው መብት መጋፋት ማለት ነው፡፡ ስለ ሌላው ሰው ማሰብ ሲባል ደግሞ ሰው ለራሱ እንዲሆንለት ወይም እንዲደረግለት የሚፈልገውን ጉዳይ ለሌላም ሰው እንዲደረግለት መመኘት ወይም ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው፡፡ እንዲሁም በራስ ሊደርስ የማይፈለግ ድርጊት በሌላ ሰው ላይ እንዲደርስ አለመመኘት ነው፡፡

ይህንን በጎ ተግባርም የእምነት አባት አብርሃም በመፈጸሙ እንደ ምሳሌ ተጠቃሽ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነገረን አብርሃምና ሎጥ በቤቴል ሰፍረው ሳለ እግዚአብሔር በብዙ ባረካቸው እጅግ የብዙ መንጎች ባለቤትም ሆኑ ነገር ግን መንጎቻቸው ከመብዛታቸው የተነሳ የማሰማሪያ ስፈራ ስለ ጠበባቸው እረኞቻቸው መጋጨት ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ አብርሃም ሎጥን እኛ ወንድማማቾች ነንና በእኔና በአንተ፤ በእረኞቼና በእረኞችህ መካከል ጠብ እንዳይሆን እለምንሃለሁ…አንተ ግራውን ብትወስድ እኔ ወደ ቀኝ እሄዳለሁ አንተም ቀኙን ብትወስድ እኔ ወደ ግራ እሄዳለሁ በማለት የመረጠውን ይወስድ ዘንድ የወንድሙን ምርጫ አስቀደመ፡፡

ምንም እንኳ አብርሃም በታላቅነቱ ቅድሚያና መከበር የሚገባው ቢሆንም እርሱ ግን ምርጫን ለወንድሙ ልጅ ለሎጥ ትቶለት ከራስ ወዳድነት ሸሸ፡፡ ሎጥ ግን በወቅቱ የራሱን ምርጫ በማስቀደም የተሻለ መስሎ የታየውን  አቅጣጫ መረጠ፡፡ ከዚያ በኋላ ሎጥ የመረጠው ሀገር ሰዶምና ገሞራ እንዲጠፉ በተወሰነበት ጊዜ ከዚያች ተሰዶ ተንከራተተ፡፡ አብርሃምን ግን ባለበት ቦታ እግዚአብሔር ባረከው (ዘፍ. ፲፫፥፰)፡፡

ይህንን አስመልክቶ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በወንጌል “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት አስተምሮናል (ሉቃ. ፮፥፴፩)፡፡

ብዙዎች መንፈሳውያን ሰዎችም ከራሳቸው ክብርና ጥቅም ይልቅ የሌላውን ሰው ክብርና ጥቅም ያስቀድማሉ፡፡ በዚህ በጎ ተግባራቸውም እንደ አብርሃም ተባርከውበታል፡፡ በመሆኑም ለኔ ብቻ ይመቸኝ እንጂ ስለ ሌላው ምን ገዶኝ ከሚለው ራስ ወዳድነት ይልቅ ጸጋና በረከት የሚገኝበትን ለሌላ ሰው የማሰብን ጠባይ ቅዱሳን አባቶቻችን አብነት አድርገን ፈለጋቸውን እንከተል ዘንድ ያስፈልጋል፡፡

በመሁኑም  ክርስትና ስለ ራስ ብቻ ሳይሆን ስለ ሌላውም የሚኖሩበት ሕይወት ነው፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ስለ ራስ ብቻ በማሰብ፣ እኔን ከተመቸኝ፣ ለእኔ ከሆነልኝ፣ እኔን ከተስማማኝ፣ ለእኔ ከዘነበለልኝ በማለት ግላዊ ጥቅምንና የራስን ድሎት ብቻ በማስቀደም የሚኖሩት ሕይወት መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊ (ዓለማዊ) ኑሮ ነው፡፡ ለዚህም የሚጠቀስ አንድ አባባል አለ፡፡ እሱም፡- “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አለች አህያ” የሚል ነው፡፡ ይህንን ቃል አህያ አፍ አውጥታ ተናገረች ለማለት ሳይሆን ራሱን ብቻ የሚወድ ሰው ስለራሱ እንጂ ስለ ሌላው ምንም የማይገደው መሆኑንና ይህም ክፉ ጠባይ እንደሆነ ለማሳየት ነው፡፡

ራስ ወዳድ ሰው የራሱን ጥቅም ለማስከበር ሲል በወንድሙ ደም ይረማመዳል፡፡ ሌላውን ገፍትሮ ጥሎ ራሱ ብቻ ለመቆም ይጥራል፡፡ የሌላውን እድል ሰብሮ የራሱን ነገር ብቻ ያደላድላል፡፡ ይህ ደግሞ ከክርስቲያናዊ ሕይወት የማይጠበቅ እኩይ ተግባር ነው፡፡ ከቅዱሳን አባቶቻችን  ሕይወት እንደተማርነው ክርስትና ለራስ እየተራቡ ሌላውን ማብላት፣ ራስ እየሞቱ ሌላውን ማዳን፣ ለራስ እየተቸገሩ ሌላውን ከችግሩ ማውጣት፣ ለራስ ክብርን እያጡ ሌላውን ማክበር፣ ለራስ እየተጠሉ ሌላውን መውደድ፣ ለራስ እየተጨነቁ ሌላውን ከጭንቀት ማውጣት ወዘተ… እንደሆነ እናስተውላለን፡፡

፪ኛ. ስስታምነት

ስስታምነት ባለን ነገር አለመርካት፣ ተመስገን አለማለት፣ ያለንን ነገር ሳይሆን ሁልጊዜ የለኝም የምንለውን ነገር ማሰብ፣ ያለንን ብዙ ነገር ባለማስተዋል የሌለንን ጥቂት ነገር ባለማግኘታችን በእግዚአብሔር ላይ የሚደረግ ማጉረምረም ነው፡፡ አንድ ሰው በፊቱ ያለውን ሳያነሣ የጀርባውን የሚመኝ፣ የቆረሰውን ሳይጎርስ በሚመገበው ላይ ዓይኑን የሚጥል፣ የቀረበለትን ሳይበላ ነገ ስለሚቀርበለት የሚጨነቅ፣ የራሱ እያለው የሌላውን የሚመኝ ከሆነ ስስታም ይባላል፡፡

ስስት ለማኅበራዊ ኑሮም ሆነ ለመንፈሳዊ ሕይወት እንቅፋት ነው፡፡ ምክንያቱም ስስታም ሰው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት የለውም፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በዓይኑ ትዕቢተኛ የሆነውና ልቡ የሚሳሳው ከእኔ ጋር አይተባበርም”  (መዝ. ፩፻፩፥፭) ይላልና፡፡

ስስታምነት የሚመጣው ከሆዳምነት ወይም ከአልጠግብ ባይነት ነው፡፡ በመሆኑም መቀበል እንጂ መስጠት፣ መለመን እንጂ መለመን(እባክህ መባል) የማይወድ ሰው ስስታም ይባላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ቢበላም አይጠግብም፣ ቢጠጣም አይረካም፣ ቢለብስም አይሞቀውም፡፡ ምክንያቱም ስስት አንቆ ይዞታልና በጥቂትም ሆነ በብዙው ነገር መርካት አይችልም፡፡

ክርስቲያናዊ ሕይወት ግን ከእንዲህ ዓይነት ነገር የራቀ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ልጁ ጢሞቴዎስን ሲመክር “በቃኝ ከማለት ጋር እግዚአብሔርን ማምለክ ታላቅ ረብ ነው፡፡ ወደ ዓለም ያመጣነው የለንምና ከእርሱም ልንወስደው የምንችል የለንም፡፡ ምግባችንን እና ልብሳችንን ካገኘን ይበቃናል፡፡ ባለጸጋ ሊሆኑ የሚወዱ ግን በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን  በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” (፩ኛ ጢሞ. ፮፥፮) ብሏል፡፡

፫ኛ. ክፉ ቅንዓት

ክፉ ቅንዓት ለክርስቲያናዊ ሕይወት ጠንቅ ነው፡፡ ይህም በሌላው ማግኘት፣ መከበር፣ መበልጸግ፣ ማደግና ወደተሻለ ነገር መሸጋገር መናደድ ለምን እገሌ ተለወጠ? ለምን እገሊት ከፍ አለች? በሚል የክፋት አሳብ መያዝ ነው፡፡ ክፉ ቅንዓት በራስ ሳይሆን በሌላ ማግኘት መበሳጨት ነው፡፡ ምንም እንኳ ያ በክፉ ቅንዓት የተያዘ ሰው የማያገኘው ወይም የማይደርስበት ነገር ቢሆንም እንኳ ሌላው ሰው (አካል)እንዳያገኘው ወይም እንዳይደርስበት መፈለግ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ክፉ ጠባይ ለማኅበራዊ ኑሮም ሆነ ለመንፈሳዊ ሕይወት እንቅፋት ነው፡፡

ይህ ዓይነቱ ክፉ ቅንዓት ቃዔል በወንድሙ በአቤል ላይ እንደቀናበት ያለ ቅንዓት ነው፡፡ እንደምንመለከተው በዚህ ክፉ ቅንዓት ሰበብ ብዙ ወንድማማቾች ተለያይተዋል፣ ወዳጆች ወዳጅነታቸውን ሰርዘውበታልና ከክፉ ቅንዓት መራቅ ያስፈልጋል፡፡

፬ኛ ዘረኝነት

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝብና አሕዛብ የታረቁበት የሰላም ባለቤት ነው፡፡ ለሰው ልጅ ሕይወት እውነተኛ ሰላም ያደለው እርሱ ነው፡፡ ይህንን ያልተረዱ አንዳንድ ግለሰቦች ግን ዛሬም ድረስ የሀገሬ ልጅ፣ የወንዜ ልጅ እየተባባሉ ራሳቸውንም ሆነ ሌላውን የሚጎዱ ጥቂት የሚባሉ አይደሉም፡፡ የክርስትና ሃይማኖት የፀብ ግድግዳ የፈረሰበት ሁሉን በእምነት አንድ ወገን ያደረገ ሃይማኖት መሆኑን ያልተረዱ በየስፍራው አይታጡም፡፡ ዘረኝነትን ከውስጣችን ካላጠፋን ክርስቲያናዊ  ሕይወታችን በማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ መገለጥ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ዘረኝነት አንዱ ለክርስቲያናዊ ሕይወት እንቅፋት ስለሆነ፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ሰዓት እየተፈተነች ያለችበት አንዱ የዘረኝነት ጉዳይ ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የሥጋ ሥራ ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል አንዱ ይኸው ዘረኝነት ነው፡፡ “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና እርሱም ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ” የሚል ነው፡፡ ነገር ግን እርስ በርሳችሁ ብትነካከሱ ብትበላሉ እርስ በርሳችሁ እንዳትጠፋፉ ተጠንቀቁ ነገር ግን እላለሁ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ” (ገላ. ፭፥፲፬) እንዲል፡፡ በመሆኑም ዘረኝነትን ከመካከላችን አስወግደን እውነተኛ ፈቅርን ገንዘብ ማድረግ ለማኅበራዊ ኑሮአችን አስፈላጊ ነው፡፡     

፭ኛ. ሐሜት

ሐሜት፡- ስለ አንድ ሰው እርሱ በሌለበት የነቀፋ ወይም የስም ማጥፋት ወሬ መናገር ነው፡፡ ሐሜት በእውነት ወይም በሐሰት ላይ የተመሠረተ ሊሆን ይችላል፡፡ በእውነት ላይ የተመሠረተ በሚሆንበት ጊዜ የሚታማው ሰው የፈጸመውን ክፉ ድርጊት በማንሣት ባለቤቱም ሆነ ሌላው ሰው እንዲማርበት ተብሎ ሳይሆን በድክመቱ ሌላው ሰው እንዲዘባበትበት በማሰብ ሆን ተብሎ ለሌላው ወገን በነቀፋ መልክ መናገር ነው፡፡

ሐሜት በሐሰት ላይ የተመሠረተ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ‘‘ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ’’  እንደሚባለው ሁሉ ሆን ተብሎ የሰው ስም ለማጥፋት ወይም ለመጉዳት ሲባል የሚወራ ክፉ ወሬ ግን እርስ በርስ በመዋደድ ፍቅርን የሚያደርግ ሰው ከሐሜት ይርቃል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሕይወት ያለው ሰው ምንም እንኳ በዙሪያው ያሉ ሰዎች ኢ-ክርስቲያናዊ ተግባር የሆነውን የሐሜትን ቃል ቢናገሩም ሰምቶ እንዳልሰማ ዝም ይላል እንጂ ከእነሱ ጋር ለሐሜት አይተባበርም፡፡

ሐሜት በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ተግባር ከመሆኑ ባሻገር ለማኅበራዊ ኑሮ ጠንቅ ነው፡፡  በክርስቲያናዊ ሕይወትም አይፈቀድም፡፡ ለዚህ ነው ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር ሆይ ወደ መኖሪያህ መግባት የሚችል ማነው? የሌሎች ሰዎችን ስም የማያጠፋ… ጎረቤቶቹን የማያማ… እነዚህን ነገሮች የሚያደርግ ሰው ከማናቸውም ክፉ ነገር ተጠብቆ ይኖራል እንጂ ከቶ አይናወጥም” (መዝ. ፲፭፥፩) በማለት ስለ ሐሜት ነውርነት አስገንዝቧል፡፡

ስለዚህ ከሐሜት መራቅ የክርስያናዊ ሕይወት መገለጫ ሲሆን መልካም ለሆነ ማኅበራዊ ግንኙትም ወሳኝ ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህንና መሰል በጎ ተግባራን በመፈጸም ሕይወታችንን ልንመራ ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡

እነዚህንና መሰል የማይገቡ ክፉ ተግባራትን አርቀን መልካምነትን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የመልካምነት እንቅፋቶችም ከላይ የዘረዘርናቸው የሥጋ ሥራዎች ከላይ የጠቀስናቸውን እናንሳ እንጂ ፍቅርን ሊያቀዘቅዙ የሚችሉ በርካታ ናቸው፡፡ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ በማስገዛት የመንፈሳዊነታችን መገለጫ የሆነውን ፍቅርን ልናደርግ ይገባል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን እርስ በእርሳችን የምንግባባበትን እውነተኛ ፍቅር ለሁላችንም ያድለን አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር