የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜ እና ፍችዎቻቸው

በገብረ እግዚአብሔር ዘይኵኖ

ኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ስሙ ጐልቶ ከሚነሳባቸው ጉዳዮች አንዱ በዐቢይ ጾም ውስጥ ለሚገኙ ሳምንታት የየራሳቸው መጠሪያ በመስጠቱ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ለሳምንታቱ ስያሜዎችን ሲሰጥ ጌታችን የሠራቸውን የቸርነት ሥራዎችን፣ ያስተማራቸው ትምህርቶችን፣ ተጠቅሟል፡፡ በአጠቃላይ በዐቢይ ጾም ውስጥ የሚገኙ ዘጠኝ ሳምታት ሲሆኑ ስያሜአቸውን እና ትርጓሜያቸውን  በሚከተለው መልኩ ለማየት እንሞክራለን፡፡

  1. ዘወረደ

የጌታችንና የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ወደ ምድር መውረድ በሥጋ ብእሴ መገለጽ የሚነገርበት፣ የሚታሰበብበት ሳምንት ነው፡፡ በዚህ ሳምንት የሚዘመሩ መዝሙራት፣ የሚሰበከው ምስባክ፤ የሚነበበቡት ምንባባት እንዲሁም የሚተረጎመው ወንጌል ይህንኑ ኹኔታ የሚያስረዱ ናቸው፡፡

በዘወረደ ሳምንት ከሚነበበው ምንባብ ወንጌልን ብንመለከት በዋናነት የዮሐንስ ወንጌል ተጠቃሽ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹…. ስለ ምድራዊ ነገር በነገርኋችሁ ጊዜ ካላመናችሁ፤ ስለ ሰማያዊ ነገር ብነግራችሁ እንዴት ታምናላችሁ? ከሰማይም ከወረደ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ ማንም የለም እርሱም በሰማይ የሚኖረው የሰው ልጅ ነው›› (ዮሐ.3፥12-13) የሚለው ይገኝበታል፡፡ ‹‹የሰው ልጅ›› ተብሎ የተጠራው በተለየ አካሉ ሰው ኾኖ የተገለጸው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ከመንጸፈ ደይን ለማዳን ወደ ምድር የወረደ፤ ይፈጽመው ዘንድ ያሰበውን ኹሉ አካናውኖ ወደ አባቱ ያረገ መኾኑ በንባቡ ተረድተናል፡፡ በአጠቃላይ የዘወረደ ሳምንት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መውረድና መወለዱ የሚነገርበት፣ የሚታሰብበት ነው፡፡ ፈጣሪያችን በፍጹም ፍቅር እና በትሕትና ወደዚህች ምድር መውረዱን፣ መከራ መሰቀሉን እያሰብን  እኛም በበደል  የሚገኙትን ኹሉ በመናቅ እና በማቃለል ሳይሆን በፍቅር ልንቀርባቸው እና ልናገለግላቸው እንደሚገባ እናስተውላለን፡፡

  1. ቅድስት

ቅዱስ ያሬድ ለዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሳምንት የሰጠው ስያሜ “ቅድስት” የሚል ነው፡፡ ቅድስት ‹‹ቀደሰ›› ከሚለው ሥርወ ግስ የተገኘ ቃል ሲሆን ትርጉሙም ቀደሰ፣ ለየ፣ አከበረ የሚል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ቅድስት የሚለው ቃል የተለየች ክብርት ንጽህት የሚል ትርጔሜ ይሰጠናል፡፡ ቅዱስ የሚለው ቃል የባሕርይ ቅድስና ካለው ከእግዚአብሔር  በጸጋ የቅድስና ሀብት ለተሰጣቸው አካላት ኹሉ ያገለግላል፡፡ ለምሳሌ፡- ቅዱሳን ሰዎች፣ ቅዱሳን መላእክት፣ ቅዱሳት መካናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እና ቅዱሳት ዕለታት ይገኙበታል፡፡ በዚሁ መሠረት የሰንበትን ቅድስና አስመልክቶ ጌታችን ያስተማረው ትምህርት በዜማ (በምስባክ) እንዲሁም በንባብ እየተነበበ በዐቢይ ጾም ኹለተኛ ሣምንት ይተረጎማል፡፡

“እግዚአብሔርሰ ሰማያተ ገብረ፤ አሚን መሠናይት ቅድሜሁ፤ ቅድሳት ወዕበየ ስብሐት ውስተ መቅደሱ፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ፤ ምስጋናና ውበት በፊቱ፣ ቅዱስነትና ግርማ በመቅደሱ ውስጥ ናቸው” (መዝ. 95፥5-6) ከሚለው የዳዊት መዝሙር ተወስዶ የሚሰበከውን ምስባክ መምህራን እየተረጎሙ ያስተምሩበታል፡፡ “ቅድስት” በተሰኘች የዐቢይ-ጾም ሳምንት ማቴ. 6 ከቁጥር 16-25 ያለው የጌታችን ትምህርት ይነበባል፤ በሊቃውንት ተተርጎሞ ትምህርት ይሰጥበታል፡፡

  1. ምኩራብ

አምልኮተ እግዚአብሔር ለመፈጸም አይሁድ ከሚሰባሰቡባቸው ስፍራዎች ዋነኛው ምኩራብ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ ቅዱስ ያሬድም ሦስተኛዋን የዐቢይ ጾም ሳምንት “ምኩራብ” በሚል ስያሜ የሰየመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምኩራብ ውስጥ ተገኝቶ የቤተ መቅደስን ክብር ማስጠበቁን በማሰብ ነው፡፡ በዚህች ሳምንት የሚሰበከው የዳዊት መዝሙር “እስመ ቅንዐተ ቤትከ በልዐኒ፤ ትዕይርቶሙ ለእለ ይትዔየሩከ ወድቀ ላዐሌየ፤ ወቀጻእክዋ በጾም ለነፍስየ” የሚለው ነው ፡፡ ይኸውም “የቤትህ ቅንዓት በልታኛለችና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና፣ ነፍሴንም በጾም ቀጣኋት” ማለት ነው (መዝ.68፥9-10)

ቤተ ጸሎት የተባለች ምኩራብን ከግብሯ ውጪ ለመነገጃና መለወጫ ተግባር ያዋሏትን ነጋዴዎችና ለዋጮች ጌታቸን በጅራፍ እየገረፈ ርግቦችንና ሌሎች እንስሳትን ከቤተ መቅደስ በኅይል ሥልጣኑ አስወጥቷል (ዮሐ.2፥12- ፍ.ም)፡፡ ከዚሁ አንፃር አማናዊና ሕያው “የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ” የተባለ ሰው ልጅ ሰውነት ከተፈጠረበት ዓላማ ውጭ ሌላ ተግባር ቢፈጸምበት እግዚአብሔር እንደሚቀጣ የሚስያገነዝቡና በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡ ኃይለ ቃላት  እየተነበቡ የሚተረጎሙበት ሳምንት ነው፡፡(1ኛ ቆሮ.6፥16-17)

  1. መፃጉ

ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ድውያነ ሥጋን በተአምራት፣ ድውያነ ነፍስን በትምህርት የማዳኑ ጉዳይ ጎልቶ ከሚነገርባቸው ጊዜያት አንዱ ይህ “መፃጉ’’ የተሰኘው ሳምንት ነው፡፡ “መፃጉ” ማለት በሽተኛ ማለት ነው፡፡ አምላካችን በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ በዚህች ምድር ሲመላለስ ከደዌ ዳኛ ከአልጋ ቁራኛ የገላገላቸው መኾኑን የሚያሰረዱ የምስክርነት ቃሎች የሚሰሙበትን ጊዜ ቅዱስ ያሬድ “መፃጉ” በማለት ጠርቶታል፡፡

በመፃጉ ሳምንት የሚሰበከው ምስባክ፡- ‹‹እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዐራተ ሕማሙ፤ ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቤሁ እም ደዌሁ፤ አንሰእቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ›› የሚለው ነው ፡፡ በመዝሙር 40 ላይ የሚገኘውን ይህንን ቃል ዲያቆኑ ከፍ ባለ ዜማ ከሰበከ በኋላ በዮሐንስ  ወንጌል ምዕራፍ 5 ላይ  ያለው ይነበባል፤ ይተረጎማል ፡፡ በደዌ ሥጋም ኾነ በደዌ ነፍስ የተያዝን የሰው ልጆች የፈጣሪያችንን ምሕረትና ቸርነቱን እንደምናገኝ ተሰፋ የምናደርግባቸው ገቢረ ተአምራት ይሰማሉ፡፡

በአጠቃላይ እኛም ከዚህ ታሪክ ብዙ ነገሮችን እንማራለን፡፡ የመጀመርያው ሰውን መውደድን ማፍቀርን፣ ለሰው ድኅነት ብሎ ዝቅ ማለትን፣ ትሕትናን እንማራለን፡፡ የክርስትና ሕይወት የፍቅር፣ የሠላም፣ የአንድነት ሕይወት ነው፡፡ ለራስ ብቻ የሚኖሩት ሕይወት ሳይሆን ለሌሎችም መዳን ዝቅ ማለት ነውና እኛም ይህን በዓልን ስናከብር ጾሙንም ስንጾም ይህን ታሳቢ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

  1. ደብረ ዘይት

“ደብረ ዘይት” የሚለው የግእዝ ቃል ሲሆን ተራራ ማለት ነው፡፡ በዚያ ተራራ ላይ የወይራ ዛፍ በብዛት ስለሚበቅል ስያሜውንም በዚያው አንጻር አግኝቷል፡፡ በደብረ ዘይት ላይ የዓለም ፍጻሜ ምን እንደሚመስል ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሯል፡፡ “እርሱም በደብረ ዘይት ተቀምጦ ሳለ ደቀመዛሙርቱ ለብቻቸው ቀርበው ንገረን  ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው“ ? አሉት /ማቴ 24፡3/ የዓለም ኅልፈት መቼ እንደሆነና ምልክቱ ምን እንደሆነ ለተጠየቀው ጥያቄ ጌታችን ምላሽ ሰጥቷል፡፡ የዓለም ኅልፈት በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ የምትታወቅ እንጂ ቀኒቱ ለሰው ልጅ ተለይታ የማትታወቅ መሆኗን ተናግሯል፡፡

ኅልፈተ ዓለም መቼ ይሆናል ?

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዕለተ ምጽአት ቀንና ሰዓት ከመግለጹ ባሻገር “ያን ግን እወቁ፤ ባለቤቱ ከሌሊት በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ በነቃ፣ ቤቱም ሊቆፈር ባልተወም ነበር፡፡ ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፤ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና” በማለት አሳስቧል (ማቴ. 24፥43-44)፡፡  በቤቱ ያለውን ንብረት እና ሀብት ዘርፎ እንዳይወስድበት ባለቤቱ ነቅቶ እንደሚጠብቅ በሌባ የተመሰለ መልአከ ሞት የምእመናን ሕይወት በንሰሐ ሳይዘጋጅ እንዳይነጥቅ በንሰሐ፣ በጾም፣ በጸሎትና በስግደት እንዲሁም በሥርዓተ ቍርባን ተወስኖ መቆየት እንደሚገባ ተናግሯል፡፡  በኖኅ ዘመን የነበሩ ሰዎች እግዚአብሔር ለንስሐ ብሎ በሰጣቸው አንድ መቶ ሃያ ዓመታት መጠቀምን አልወደዱም፤ ይልቁንም ሌላ ኃጢአት ለመፈጸም ጊዜውን ሲከፋፍሉት ታይተዋል፡፡ በመቶ ዓመታት ፈቃደ ሥጋን ፈጽመው በቀረው ሃያ ዓመት ንስሐ እንደሚገቡ ሲያቅዱ ታይተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የንፍር ውኃ ድንገት ከሰማይ ወርዶ አጥፍቷቸዋል፡፡ መቅሰፍቱ የኖኅ ዘመን ሰዎችን ድንገት እንዳገኛቸው መልአከ ሞትም ድንገት እንዳይደርስባችሁ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ ብሏል (ማቴ. 24፥44)

የኅልፈተ ዓለም ምልክቱ ምንድን ነው?

ጌታችን ኅልፈተ ዓለምን አስመልክቶ ከቀረቡለት ጥያቄዎች  ከዳግም ምጽአት በፊት ከሰባት በላይ የሚሆኑ ጉዳዮች በምልክትነት የሚታዩ መሆናቸውን ገልጾአል፡፡ ከዚህም መካከል፡- የሀሰተኞች ነቢያት መነሣት፣ የጥፋት ርኲሰት በተቀደሰው ስፍራ መታየት፣ የፍቅር መቀዝቀዝ እንዲሁም ጦርና የጦር ወሬ መስማት በምልክትነት ከቀረቡት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ምስባክና ወንጌል

ደብረ ዘይት የሚሰበከው ምስባክ ‹‹እግዚአብሔር ግልጥ ሆኖ ይወጣል፤ አምላካችን ይመጣል፣ ዝምም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይቃጠላል” (መዝ 49-3) የሚለው ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 24 ላይ ያለው ገጸ ንባብም እየተተረጎመ ትምህርት ይሰጥበታል፡፡

  1. ገብር ኄር

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሳምንት የሚጠራበት ስያሜ  “ገብር ኄር” የሚል ነው፡፡ መልካም የኾነ  አገልግሎትን ፈጽመው ከፈጣሪያቸው ምስክርነት የሚያገኙ ሁሉ በዚህ ስም ይጠሩበታል፡፡ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፍርድ ቀን “ኑ፣ እናንተ የአባቴ ቡሩካን፡- ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ያዘጋጀሁላችሁን መንግሥት ውረሱ” ብሎ ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚያስገባቸው የታመኑ አገልጋዮችን መሆኑ ታውቋል (ማቴ.25፥34)፡፡

መልካም አገልጋዮች የተባሉት (የሚባሉት) በሃይማኖት ጸንተው በፈጸሟቸው በጎ ሥራዎች ነው፡፡ ማለትም “ይህ ፈጣሪአችን እንፈጽመው ዘንድ ያዘዘን የተቀደሰ ተግባር ነው፡፡ በእርሱ እርዳታና ቸርነት ይህን ሥራ ሠርተን ዋጋ  እናገኝበታለን፣ እንጠቀምበታለን” በሚል እምነት በጎ ሥራ ሠርተው የሚወርሱት ነው፡፡ “መልካም አገልጋይ” ተብሎ በእግዚአብሔር ዘንድ መመስገንም ኾነ መንግሥተ ሰማያትን መውረስ በፈጣሪ ቸርነት ብቻ ሳይሆን በሠሩት ክርስቲያናዊ የተቀደሰ ተግባርም ነውና፡፡

የሚያስመሰግነው ክርስቲያናዊ ተግባር

ማንኛውም ክርስቲያን ሃይኖማቱን የሚገልጠው  በበጎ ሥራው ወይም በአኗኗሩ ጭምር ነው፡፡ ማመኑ ብቻውን አያስመሰግነውም፡፡ ይልቁኑ ከበጎ ሥራ የተለየ ሃይኖማትን ብቻ ቢይዝ ምንም እንደማይረባው በቅዱሳት መጻሕፍት ተገልጦ ይገኛል፡፡

የክርስትና ሃይማኖት ደግሞ በጎ ሥራን ጭምር ይጠይቃል እንጂ ከሥራ የተለየ እምነት ብቻ  ክርስቲያን አያደርግም፡፡ ትእዛዛቱንና ሕጉን ሁሉ መፈጸም እንደሚያስፈልግ ሐዋርያው “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ራሳችሁን እያሳታችሁ የምትሰሙ ብቻ አትሁኑ” በማለት አሳስቧል (ያዕቆ.1፥22)፡፡  ስለሆነም የእግዚአብሔርን መንግሥት ለመውረስ የሚያበቃውንና በሃይማኖት መፈጸም ያለበትን በጎ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡ ስለዚህ ነው፡- ‹‹የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ ጌታ ሆይ ጌታ ሆይ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም›› (ማቴ. 7 21) በማለት ጌታችን ያስተማረው፡፡

መንግሥተ ሰማያትን መውረስ

 ክርስቲያኖች ሁሉ የተጋድሎአቸው ውጤቶችና የተፈጠሩበትንም ዓላማ የሚያሳኩት  መንግሥተ እግዚአብሔርን በመውረስ ነው፡፡ የተጋድሏቸው ዓላማ እግዚአብሔርን ማስደሰት፣ ግቡም መንግሥተ ሰማያትን መውረስ ነው፡፡ “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፣ ደማቸውን ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሡ” ተብሎ እንደተነገረላቸው (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)፡፡ እንግዲህ  ከገቡ የማይወጡባት፣ ካገኙ የማያጡባት፣ ኀዘን፣ መከራና ሞት የመሳሰሉ ችግሮች የማይታወቁባት የእግዚአብሔር  መንግሥት  የምትወረሰው በበጎ ሥራና በድካም ነው፡፡ “ወደ እግዚአብሔር  መንግሥት  በብዙ መከራ እንገባ ዘንድ ያስፈልገናል” የሚለውም የሐዋርያት ቃል የሚስረዳው መንግሥተ ሰማያትን ለመውረስ ስሚጠበቅብን ተግባር ነው፡፡ (የሐዋ. ሥራ 14፥21)፡፡

ምስባክ እና ወንጌል

በገብር ኄር ሰንበት የሚሰበከው ምስባክ መዝሙር 39 ላይ ያለው ነው፡፡ ይኸውም “ከመ እንግር ፈቃድከ መከርኩ አምላኪየ፤ ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፤ ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ” የሚለው ሲሆን የአማርኛ  ትርጉምም “አምላኬ ሆይ ፈቃድህን ለማድረግ ወደድሁ፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው፤ በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ” ማለት ነው (መዝ.39፥8-9)፡፡ በዚሁ ጊዜ የሚነበበው ወንጌል በሐዋርያው እና በወንጌላዊው  በቅዱስ ማቴዎስ የተጻፈው  ምዕራፍ 25 ከቍጥር 14-31 ያለው ነው::

  1. ኒቆዲሞስ

ቅዱስ ያሬድ የዐቢይ ጾምን ሳምንታት ሲሰይም ታሳቢ ካደረጋቸው ኹኔታዎች በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተአምር የተደረገላቸውና ትምህርት የተከታተሉትን ግለሰቦች መኾኑ ግልጥ ነው፡፡ ለምሳሌ መፃጒ እና ኒቆዲሞስ የሚሉ ስያሜዎች ይጠቀሳሉ፡፡ መፃጒም ድውይ ማለት መሆኑን በአራተኛው ሳምንት ስያሜ ላይ መነሻ አድርገን ተመልክተናል፡፡ ሰባተኛው ሳምንትም የአይሁድ መምህር ሲሆን ሌሊት ሌሊት ከጌታችን ዘንድ እየመጣ ይማር በነበረው ኒቆዲሞስ በተባለው ሰው ስም ተሰይሟል፡፡

ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን የኾነና የአይሁድ አለቃ የነበረ ሰው ነው፡፡ አለቅነቱም በትምህርት፣ በሹመት እና በባለጸነት ሲሆን ከጌታችን ዘንድ እየቀረበ በሌሊት የሚማር ሰው ነበር፡፡ የሚያስፈልገውን የሚሻ ትጉህና የሃይማኖት ሰውነት በኒቆዲሞስ ሕይወት ውስጥ ተገልጠው የሚታዩ መንፈሳዊ ሀብቶች ናቸው፡፡ በዚሁ አግባብ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆቿ ምእመናንን ትጋታቸውን  በኑሯቸው ኹሉ ይገልጡ ዘንድ ታስተምራለች፡፡

ካለው ነገር ይልቅ የሚያስፈልገውን የሚሻ ኒቆዲሞስ

ምንም እንኳ በተማረው ትምህርት፣ በሰበሰበው ሀብት እና በያዘው ሥልጣን የአይሁድ አለቃ ቢኾንም ከኹሉ በላይ እርሱ የሚያስፈልገውን ለማግኘት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መኼድን ያዘወትር የነበረ ሰው ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ብዙ ነገሮች ያሉት ሰው ቢመስልም ትልቋ ሀብት ግን አልነበረችውም፤ ይህችውም ሀብት የልጅነት ጸጋ የምታሰጥ ጥምቀት ናት፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሰው ዓለሙን ኹሉ ቢያተርፍ ነፍሱንም ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል? (ማቴ.16፥26) በማለት እንዳስተማረው በነፍሱ እንዳይጎዳ ዘለዓለማዊ ሕይወትን የምታሰጠውን  ጥምቀተ ክርስትናን የሚሻ ሰው ነበር፡፡ በሰበሰበው ሀብት፣ በያዘው ሥልጣንና በተማረው ትምህርት ላይ ብቻ ተመሥርቶና እርካታ ተሰምቶት የሚኖር ሰው አለመሆኑ በተግባር ታይቷል፡፡ ይልቁኑ ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታስገባውን ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና የምታሰጠውን ጥምቀት አብዝቶ የሚፈልግ ኾኖአል፡፡ ይህም ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” (ፊልጵ. 3፥13) በማለት የተናገረውና ከማንኛውም ሰው የሚጠበቅ ፍለጋ ነው፡፡

ትጋት በኒቆዲሞስ ሕይወት

ያለ መታከትና  ያለ መሰልቸት ሌሊት ሌሊት ከጌታችን ዘንድ እየሔደ ትምህርተ ወንጌል የሚማረው ኒቆዲሞስ በቀኑ ክፍለ ጊዜ ሰብአ እስራኤልን ሰብስቦ የሚያስተምር ሀብቱን የሚያስተዳደር ሰው ነበር፡፡  ምንም እንኳ ሌሎችን በማስተማር ሀብቱንና ቤተሰቡን በማስተዳደር ቀኑን ቢያሳልፍም ድካሙን ታግሦ የሕይወት ፍሬ ወደ ኾነው ወደ ጌታ  መገስገስን አላቌረጠም፡፡  የኒቆዲሞስ  ትጋት ወደ ጌታችን  ሳይታክት በመመላለሱ ብቻ የሚገለጥ አይደለም፤ ይልቁኑ ረቂቅ የኾነውን ነገረ ጥምቀትንና በጥምቀት የሚገኘውን ሀብት ግልጥ ኾኖ  እስኪረዳው በትጋት በመማሩ እንጂ፡፡ እናም በማንኛውም ምእመን ሕይወት እንዲኖር የሚያስፈልገውን ትጋት ኒቆዲሞስ ይዞ ተገኝቷል፡፡ በዚህም ትጋቱ  የቤተ ክርስቲያን አባል፣ የክርስቶስ አካል በመኾን የዘለዓለም ሕይወትን ለማግኘት በቅቷል፡፡ ጌታችን በቅዱስ ወንጌል ስለ ትጋት አስፈላጊነት መላልሶ አስተምሯል (ሉቃ. 18፥1፣ ማቴ. 26፥38፣ ማር. 13፥33)፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም  የጌታዋን ቃል ይዛ ልጆቿ በበጎ ሥራ ተግተው እንዲኖሩ ትመክራለች፡፡ (የሐዋ.20፥3 ፤ ሮሜ.12፥3) ፡፡

ሃይማኖት በኒቆዲሞስ ሕይወት

በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ማመኑን በተመለከተ ኒቆዲሞስ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡- “ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ ቀርቦ ‹ከእግዚአብሔር አብ ባሕርይ ዘእም ባሕርይ ተወልደህ ልታስተምር እንደመጣህ እናውቃለን” ዮሐ 3፡2 በማለቱም ይህን እንረዳለን፡፡ ጌታችንም ሃይማኖትን ፍጹም የምታደርግ ጥምቀትን በሰበከለት ጊዜ ቀድሞ ካወቀው ምጡቅ እውቀት ይልቅ ለድኅነት የምታበቃው ሃይማኖት እንደምትበልጥ አውቆ ያንኑ ተቀብሏል፡፡

ምስባክ እና ወንጌል

በኒቆዲሞስ ሰንበት የሚሰበከው ምስባክ “ሐወጽከኒ ሌሊተ ወፈተንኮ ለልብየ፤ አመከርከኒ ወኢተረክበ ዓመፃ በላዕሌየ፤ ከመ ኢይንብብ አፉየ ግብረ ዕጓለ እመ ሕያው፤ በሌሊትም ጎበኘኸኝ፤ ልቤንም ፈተንኸው፣ ዐመፅም አልተገኘብኝም፤ የሰውን ሥራ አፌ አንዳይናገር” (መዝ.16፥3-4) የሚለው ነው፡፡ ወንጌሉም የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3፥1-12 ነው፡፡

  1. ሆሣዕና

 “አንቺ የጽዮን ልጅ ሆይ እጅግ ደስ ይበልሽ፤ አንቺ የኢየሩሳሌም ልጅ ልጅ ሆይ እልል በይ፤ እነሆ ንጉሥሽ አዳኝ ነው፤ ትሑትም ኾኖ በአህያም፣ በአህያዪቱም ግልገል በውርንጫዪቱ ላዩ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል፡፡ ሠረገላውንም ከኤፍሬም፣ ፈረሱንም ከኢየሩሳሌም ያጠፋል፡፡›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት ንጉሠ ነቢያት ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ ፋጌ ወደ ኢየሩሳሌም በሄደበት ዕለት ማለትም መጋቢት 22 ቀን በ33 ዓ.ም ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡

‹‹ሆሣዕና›› ማለት አሁን አድን ማለት ነው፡፡ ‹‹ማዳን የባሕርይህ የሆነ መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ መጥተህ እድነን›› እያሉ የአዳም ልጆች ሁሉ የጸለዩበትን ጸሎት የያዙትን ሱባኤ ያመለክታል፡፡ በቀድሞ ዘመን በሰረገላ እና በፈረስ የሚቀመጥና ገስግሶ የሚሄድ ጦረኛ ነው፡፡ ጌታ ግን በአህያ ላይ ተቀምጦ መጓዙ የሰላም አምላክ፣ ሰላምን ለዓለም የሚሰጥ፣ ይቅርታውን ለአዳም የሚያደርግ መኾኑን ለማብሰር ነው፡፡

በዕለተ ሆሣዕና  የእናታቸውን ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ሳይቀሩ በትህትና ዝቅ ብሎ በአህያ ጀርባ ወደ ኢየሩሳሌም የገባውን የባሕርይ ንጉሥ አመስግነውታል፡፡ ይኸውም ይህ ከመሆኑ ከአንድ ሺ ዓመታት በፊት ቅዱስ ዳዊት “ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ›› በማለት በተናገረው ትንቢት መሠረት የተፈጸመ ነው፡፡ እንኳን ሕፃናት ይቅርና ግእዛን የሌላቸው የቢታንያ ድንጋዮችም ጭምር ‹‹በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ የዳዊት ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ቡሩክ አምላክ ነው›› እያሉ አመስግነዋል፡፡ (መዝ. 8፥2-3)

የሆሣዕና ምስባክ እና ወንጌል

ምስባኩ በመዝ. 146፥ 12-13 ላይ፡- ‹‹ትሴብሖ ኢየሩሳሌም ለእግዚእብሔር፤ ወሰብሒዮ ለአምላክኪ ጽዮን፤ እስመ አጽንዐ መናሥግተ ኆኃትኪ›› ተብሎ የተነገረው ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ኢየሩሳሌም ሆይ እግዚአብሔርን አመሰግኝ፤ ጽዮንም ለአምላክሽ እልል በይ፤ የደጆችሽን መወርወርያ አጽንቶአልና›› የሚል ነው፡፡ የሚነበቡትንም ሊቃውንት ከአራቱ ወንጌላውያን የሚያዘጋጁ ሲሆን ዕለቱን የተመለከተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያይቱና በውርንጫይቱ ጀርባ ሆኖ ወደ ኢየሩሳሌም የመግባቱን ነገር የሚያወሱ ምንባባት ይነበባሉ፣ ይተረጎማሉ (ማቴ. 21፥1-16)፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *