“ጾም ትፌውስ ቊስለ ነፍስ፤ጾም የነፍስን ቁስል ታድናለች” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ጾም:- ጾመ፤ ተወ፣ ታረመ፣ ታቀበ ከሚል የግእዝ ግሥ የተገኘ ሲሆን፣ ጾም ከመባልእት መከልከል ማለትም ለተወሰነ ሰዓት ከምግብ ተከልክሎ መቆየት እና ከጥሉላት ምግቦች ለአንድ ቀንም ሆነ ለሦስት ቀን፣ ለሳምንት፣ ለሁለት ሳምንት ለወርና ለሁለት ወር ወዘተ በመታቀብ  ስለ ፍቅረ እግዚአብሔር  ከላመ ከጣመ ምግብ መከልከል ማለት ነው፡፡ በዚህም ሁሉ ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ነው፡፡ ጾም ሥጋን አድልበው ለፈቃደ ሥጋ ከሚገፋፋ ስሜት ተላቆ ፍትወተ ሥጋን አጥፍቶ ለፈቃደ ነፍስ ማደር እንዲቻል የመንፈስን ጥንካሬ ገንዘብ ማድረጊያ የጽድቅ መሣሪያ ነው፡፡

የጾም መሠረታዊው ዓላማም ሕዋሳትን ሁሉ ለእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲኖሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያሬድ፡- “ይጹም ዐይን፣ ይጹም ልሳን፣ እዝንኒ ይጹም፣ እምሰሚዓ ኅሡም፤ ዐይን ይጹም፣ አንደበትም ይጹም፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ይጹም” በማለት የገለጸው (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)፡፡

ጾምን ፍጹም የሚያደርገው ከምግብ መከልከል በተጨማሪ ዐይን ክፉ ከማየት ተቆጥቦ የክርስቶስን መስቀል በመመልከት የእግዚአብሔርን ማዳን በመጠባበቅ ደጅ መጥናት ሲችል፣ ጆሮም ክፉ ከመስማት ርቆ መልካሙን የእግዚአብሔርን ቃል መስማት ሲችል፣ እጅ ክፉ ከማድረግ ተቆጥቦ ለምጽዋት ሲዘረጋ፣ የደከመውን ሲደግፍ፣ የወደቀውን ማንሣት ሲችል፣ እግር ወደ አልባሌ ስፍራ ከመሄድ ይልቅ በቅድስና ስፍራው ተገኝቶ በእግዚአብሔር ፊት መንበርከክ ሲችል፣ ልብም ክፉ ከማሰብ ይልቅ በጎ በጎውን በማሰብ ለእግዚአብሔር የተከፈተ በር፣ ለኃጢአት ግን የተዘጋ በር ሆኖ ለእግዚአብሔር የሚመች ሲሆን ነው፡፡ እነዚህን ሕዋሳት ስም ጠቅሰን ዘረዘርናቸው እንጂ ሰው እነዚህን ከላይ የዘረዘርናቸውን ሁሉ መጠበቅ፣ ሕዋሳቱን መግዛት፣ ስሜቱን መቆጣጠር ሃይማኖታዊም፣ ተፈጥሮአዊም ግዴታው ወይም ሓላፊነቱ ነው፡፡

ጾም ከእግዚአብሔር ጋር ታስታርቃለች፡፡ “ወታጸምም ኩሉ ፍትወታተ ዘሥጋ፤ የሥጋ ፍላጎትን ሁሉ ታጠፋለች” እንዲል፡፡ የሥጋ ፍላጎት ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ እንዲሁም “ትሜህሮሙ ለወራዙት ጽሙና፤ በወጣትነት ዕድሜ ያሉትን እግዚአብሔርን መፍራት ታስተምራቸዋለች”  እንዲል ቅዱስ ያሬድ፡፡  ጾም በበደል ምክንያት ከእግዚአብሔር የራቀን ሰው ወደ እግዚአብሔር ታቀርባለች፡፡ ምክንያቱም ጾም እንዲሁ በልማድ ከእህልና ከውኃ ለተወሰነ ጊዜ ተከልክሎ መቆየት ብቻ ሳይሆን ልማድነቱ ቀርቶ ፍጹም መፀፀት ያለበት ኃጢአትን፣ በደልን እያሰቡ በጸሎት የእግዚአብሔርን ምሕረት በመጠባበቅ በፍቅሩ ተማርኮ የሚጾሙት መሆን ሲቻል በእውነትም ከእግዚአብሔር ጋር መታረቂያ መንገድ፣ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ የሚያስችል የንስሓ ጉዞ ነው፡፡

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበጎ ምግባር መጀመሪያ ጾም እንደሆነ በመግለጽ በአብዛኛው በዓላቶቿን ከማክበሯ አስቀድማ ጾምን ታውጃለች እነዚህንም ለአብነት ያህል ጠቅሰን እንመለከታለን፡-

የትንሣኤን በዓል(ፋሲካን) ከማክበራችን አስቀድመን ዐቢይ ጾምን፣ ብርሃናተ ዓለም ጴጥሮስ ወጳውሎስን በማሰብ በዓለ ዕረፍታቸውን ከማክበራችን አስቀድሞ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላ አገልግሎታቸውን ከመጀመራቸው አስቀድሞ ሱባዔ እንደገቡና እንደ ጾሙ እኛም ጾመ ሐዋርያትን፣ የእመቤታችንን በዓለ ፍልሰት ከማክበራችን አስቀድሞ ቅዱሳን ሐዋርያት ዕረፍቷን ዓይተን ትንሣኤዋን እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ሳናይ ብለው ሱባኤ እንደ ገቡና እንደ ጾሙ እኛም በዓሏን ከማክበራችን አስቀድመን እንጾማለን፡፡ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓል ከማክበራችን አስቀድመን ቅዱሳን ነቢያት ይወርዳል ይወለዳል ብለው ትንቢት እየተናገሩ፣ ቅዱሳን አበው ሱባዔ እየቆጠሩ ሲጠብቁት እንደ ነበረ የተስፋው ፍጻሜ ሲደርስ በገባው ቃል መሠረት ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም መወለዱን እያሰብን ያን ያናገራቸውን የነቢያት ትንቢት እንደተፈጸመ እያሰብን ከበዓለ ልደት አስቀድመን እንጾማለን፡፡ በመሆኑም ጾምን የምግባራት ሁሉ መጀመሪያ ብላ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ለዚህ ነው፡፡

ጾም የሕግ መጀመሪያም ነው፡፡ ይህንንም ሊቀ ነቢያት ሙሴ የሥነ ፍጥረትን ነገር በአስተማረበት መጽሐፉ እንደ ጠቀሰው እግዚአብሔር አምላክ በኤዶም በስተ ምሥራቅ ገነትን እንደ ተከለ እና የፈጠረውን ሰው በዚያ እንዳኖረው ገልጾ አድርግ እና አታድርግ ወይም ብላ እና አትብላ የምትል የጾም ሕግን እንደሰጠው ይናገራል፡፡

“እግዚአብሔር አምላክም አዳምን እንዲህ ብሎ  አዘዘው በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ ብላ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና”(ዘፍ.፪፥፲፮) እንዲል፡፡  በዚህም ቃል መሠረት ጾም ትእዛዘ እግዚአብሔር፣ ሕገ እግዚአብሔር፣ ፍቅረ እግዚአብሔር እንደሆነና በጾም ሕግ ሕይወትና ሞት እንዳለ ተረዳን፡፡ ማለትም ጾምን ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ብለን ደስ ብሎን ብንጾም ሕይወትን እንደምናገኝ ሁሉ ጾምን እንደ ግዳጅ ወይም ግዳጅን እንደመወጣት መጾም ስላለብን ብቻ እና ስለ ታዘዝን ብለን ትእዛዝ ለመፈጸማችን ማረጋገጫ አድርገን ለይስሙላ የምንጾም ከሆነ ዋጋ አናገኝበትም፡፡ በሌላም መንገድ ጭራሽ የጾምን ሕግ በመጣስ ለጾም ያለን አመለካከት ዝቅተኛ ሆኖ ብንገኝ ሞትን እንደምንሞት ከእግዚአብሔር እንደምንለይ ከላይ የተመለከትነው በሙሴ መጽሓፍ የተጻፈው የእግዚአብሔር ቃል ያስረዳናል፡፡

በመጀመሪያ የጾምን አዋጅ ያወጀው የሁሉ ባለቤት የሆነው አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህም “መልካሙንና ክፉን ከሚያሳየውና ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ” ያለው ነው፡፡ ከዚህ ተነሥተው አበው ቅዱሳን ነቢያት፣ ካህናት፣ ሐዋርያት ሁሉ ጾምን ሰበኩ፡፡ በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር የተለየውን ሰው በጾም ወደ እግዚአብሔር አቀረቡት፡፡ እግዚአብሔርም በጾም፣ በጸሎት፣ በምጽዋት፣ በስግደት፣ በፍጹም ፍቅር እና ትኅትና ሆነው ለተመለሱት ቁጣውን በትዕግሥት፣ መዓቱን በምሕረት ይመልሳልና አባታችን አዳም በጾም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመመለሱ ከልጅ ልጁ ተወልዶ እንደሚያድነው ቃል ገብቶለት ጊዜው ሲደርስ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ አዳነው፡፡ “ነገር ግን ቀጠሮው በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፣ ከሴትም ተወለደ የኦሪትንም ሕግ ፈጸመ” (ገላ.፬፥፬)እንዲል፡፡

የነነዌ ሕዝቦችም እንዲሁ በነቢዩ ዮናስ ስብከት በጾም በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመመለሳቸው ከተቃጣባቸው መዓት ዳኑ (ዮና.፫፥፩ )፡፡ ሌሎችም በዚህ ክፍል ያልጠቀስናቸው ብዙዎች በጾም በጸሎት የእግዚአብሔር ምሕረት ተደርጎላቸዋልና ጾም ሰውና እግዚአብሔር የሚታረቁባት ደገኛ ሕግ ናት፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ኢዩኤል “በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምንም ቀድሱ፣ ምሕላንም ዐውጁ”(ኢዩ.፪፥፲፭) በማለት ለጾም ልዩ ፍቅር እንዲኖረን እና ስንጾም በደስታ ሆነን የእግዚአብሔር ፍቅር በልባችን ሞልቶ ምስጋናውን እያቀረብን መሆን እንዳለበት ያስረዳናል፡፡ ጾምን ከጸሎት፣ ከስግደት፣ ከምጽዋት፣ ከፍቅር፣ ከትኅትና ጋር አስተባብረን ብንጾም የኃጢአት ሥርየትን፣ የእግዚአብሔርም ጸጋ ይበዛልናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እንዴት እንጹም?

ክፍል ፪

የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤያት ድረ ገጽ ተከታታዮች “እንዴት እንጹም” በሚል ርእስ በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከሃይማኖተ አበው መጽሐፍ ስለ ጾም በጥቂቱ አቅርበንላችሁ እንደነበር ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከምትመራባቸው የሥርዓት መጻሕፍት መካከል በፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ከተደነገጉት መካከል በአንቀጽ ፲፭ ያገኘነውን እነሆ፡-

 • ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፤ በደሉን ለማስተሥረይ፣ ዋጋውን ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ፣ ለነባቢት ነፍስም ትታዘዝ ዘንድ፡፡
 • ለክርስቲያን ሁሉ የታዘዘውም ጾም ክብር ምስጋና ይግባውና ክርስቶስ የጾመው ጾመ ፵ ነው፡፡ ፍጻሜዋ ከፍሥሕ (የአይሁድ ፋሲካ) በፊት ባለው ዐርብ የሚሆን ነው፡፡ ከዚህም ቀጥሎ የስቅለት ሳምንት ነው፡፡ እነዚህም እስከ አስራ ሁለት ሰዓት ድረስ ይጾማሉ፣ ደም የሚወጣው እንስሳ፣ ከእንስሳትም የሚገኘው አይበላባቸውም፡፡
 • ዳግመኛም በየሳምንቱ ሁሉ ዐርብና ረቡዕን መጾም ነው፡፡ በዓለ ፶ የልደትና የጥምቀት በዓል የተባበሩባቸው ጊዜ ካልሆነ በቀር እንደተጻፈው እስከ ፱ ሰዓት ድረስ ይጹሟቸው፡፡
 • ጾምስ የሥጋ ግብር ነው፣ ምጽዋት የገንዘብ ግብር እንደሆነ፡፡ ሕግ ጾምን ያስወደደው የፈቲው ጾር ትደክም ዘንድ፣ ለነባቢትም ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ነው፡፡
 • ጾም ይረባናል ብለን ከመጾማችን የተነሣ መንፈሳውያን እንመስላለን፣ ከመሰልናቸውም የሚመስሉትን ለመምሰል ይቻላል፡፡ ዳግመኛም ጸዋሚው የረኃብን ችግር ያውቅ ዘንድ ለተራቡትና ለሚለምኑት ይራራላቸው፡፡ ዳግመኛም በጽኑ ፈቃድ ሁኖ ሊመገበው ሥጋውንና ደሙን ይቀበል ዘንድ ነው፡፡ መቀበሉም በሥጋዊና በነፍሳዊ ትጋት ይሁን፤ ዳግመኛም ከእንስሳዊ ባሕርይ ተለይቶ የጾምን ሥርዓት ጠብቆ ከሰው ወገን ደግሞ በጸሎት የተለየ ሁኖ ስለ አጽዋም በተሠሩት ሕጎች የፀና ሁኖ በሁለንተናው እግዚአብሔርን ያምልከው፡፡
 • ጾመ ፵ በእናንተ ዘንድ የከበረ ይሁን፤ መጀመሪያውም ከሰንበቶቹ ሁለተኛ የሆነው ሰኞ ነው፡፡ መጨረሻውም ከፍሥሕ አስቀድሞ ባለው በዕለተ ዐርብ ነው፡፡ ይህም ከፍሥሕ ሱባዔ በኋላ ያለ ሱባኤ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ከዐቢይ ጾም በኋላ የከበረ ሰሙነ ሕማማትን ትፈጽሙ ዘንድ ትጉ፡፡
 • ዘወትር በዕለተ ሰንበት መጾም አይገባም፤ እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ አርፎበታልና፡፡ ቅዳሜ ስዑርን ብቻ ሊጾሙ ይገባል እንጂ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ በመቃብር ውስጥ አድሮበታልና፡፡
 • በሊህ በስድስቱ ቀኖች ከቂጣ፣ ከጨው፣ ከውኃ ብቻ በቀር አይብሉባቸው፤ በሊህ ቀኖች ከወይን፣ ከሥጋ ተለዩ የኀዘን ቀኖች ናቸውና የደስታ ቀኖች አይደሉም፡፡ ዐርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ጹሟቸው፡፡ የሚችል እስከ ሌሊቱ ዶሮ ጨኸት ጊዜ ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው፣ ሰውየው ሁለቱን ቀኖች በአንድነት መጾም ባይቻለው ግን የቅዳሜን ጾም ይጹም፡፡
 • ዐቢይ ጾምንና ዐርብን፣ ረቡዕን የማይጾም የታወቀ ደዌ ያለበት ካልሆነ በቀር ካህን ቢሆን ይሻር፣ ሕዝባዊ ቢሆን ይለይ፡፡

 

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

እንዴት እንጹም?

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የደነገገቻቸው ሰባት የአዋጅ አጽዋማት እንደአሏት ይታወቃል፡፡ እነዚህም፡- ጾመ ነቢያት፣ ጾመ ነነዌ፣ ዐቢይ ጾም፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ፍልሰታ፣ ጾመ ድኅነት እና ገሀድ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊም በጾም ወቅት እንዴት መጾም እንዳለበት ቅዱሳት መጻሕፍት በስፋት ይተነትናሉ፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል ከሃይማኖተ አበው፣ እንዲሁም ከፍትሐ ነገሥት ያገኘናቸውን መረጃዎች በጥቂቱ እናካፍላችሁ፡፡  በቅድሚያ ግን በሃይማኖተ አበው ሠለስቱ ምእት ምዕራፍ ፳፤፲፰-፳፱ ላይ የሰፈሩትን እናስቀድም፡-

 • ጌታ ያዘዘውን ጾም አትሻር፣ እነዚህም ረቡዕ፣ ዐርብ ናቸው፡፡ ደዌ ካላገኘህ በቀር በበዓለ ሃምሳ፣ ልደት፣ ጥምቀት፣ በዋሉባቸው ዕለታት (ረቡዕ፣ ዐርብ) በቀር ይኸውም ኤጲፋንያ(ጥምቀት) ነው፡፡
 • ምእመናን የሚጾሙዋት ጾመ አርብዓ (ዐቢይ ጾም) ከፋሲካ የሚቀድሙ ሰባቱን ዕለታት (ሰሙነ ሕማማትን) ጾምነታቸውን በፍጹም ጥንቃቄ ጠብቅ፡፡
 • አንተ ሰውነትህን ለማድከም በምትጾምባቸው ዕለታት ወንድምህ ሊጠይቅህ ቢመጣ እግዚአብሔርን ደስ በምታሰኝ በበጎ ሕሊና በፍቅር ሆነህ ከእርሱ ጋር ተመገብ፣ ይህንንም የምነግርህ የጌታ ጾም በሆኑበት ዕለታት ትበላ ዘንድ አይደለም፡፡ እሊህም ረቡዕና ዐርብ አርባውም (ዐቢይ ጾም) ቀን ናቸው፡፡ አንተ ብቻ በራስህ ፈቃድ በምትጾምበት ቀን ነው እንጂ ይኸውም ሰኞ፣ ማክሰኞ፣ ሐሙስ ነው፡፡
 • በቅዳሜ ቀን ግን መጾም አይገባም፡፡ በቅዳሜ ቀን ፀሐይ እስኪገባ መጾም የሚገባ ሥራ አይደለም፡፡ የሚገባ ጊዜ አለ እንጂ፡፡ እስከ ስድስት ያም ባይሆን እስከ ሰባት፡፡
 • እሑድ ቀን በጠዋት እጅግ ማልደህ ከሌሊቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒድ። ስትሔድም ልቡናህን በማባከን ወዲያና ወዲህ አትይ። በንጹሕ ቅዳሴም ጊዜ ሕማሙን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን እያሰብክ በፍጹም ፍርሃት ቁም፡፡
 • የዐርብና የረቡዕ ጾም ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ይሁን፤ ከዚህ አብልጠህ ብትጾም ግን ለነፍስህ ጥቅም ይሆንሃል፡፡ የማሰናበቻ(ዕትዉ) እስኪፈጸም ድረስ ከቤተ ክርስቲያን አትውጣ፣ ሕማም ቢያገኝህ ነው እንጂ፣ ድንገተኛ መንገድ ቢሆን ነው እንጂ፡፡
 • ሁለት ሁለት ቀን መጾም ቢቻልህ በዚህ ብትጸና ጾምህ በትሕትና ይሁን፣ ልቡናህ አይታበይ፡፡
 • ትዕቢት ሰይጣን ያለማው ጦር ነውና በእርሱም ሰይጣን ከልዑል ማዕረጉ ተዋርዶዋልና በትዕቢቱ አሽከላነትም የሰውን ልጆች ሁሉ ያጠምድበታል፡፡ እንደ እርሱ ወደ ገሀነም ሊያወርዳቸው ይፈቅዳል፡፡
 • በከበረች በእሑድ ቀን መቼም መቼም ትጾም ዘንድ ማንም አያስትህ፡፡ አትስገድባት፣ በዋዜማው(ቅዳሜም) ቢሆን ዳግመኛም በከበረች በፋሲካ ቀኖች (በበዓለ ሃምሳ) አትስገድ፣ ቅዳሴ በሚቀደስበትም ጊዜ ሁሉ ሥጋውን ደሙን ከተቀበልክ በኋላ አትስገድ፣ ይህ ሥርዓት ከቤተ ክርስቲያን የተገኘ አይደለምና፡፡
 • በሰንበት ቀኖችም እንደ ሌሎች ቀኖች አትጹም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስኩብ በመቃብር ከነበረባት፣ ድኅነት በተደረገባትና ከፋሲካ ዋዜማ ካለች ከአንዲት ቅዳሜ ቀን (ቀዳም ስዑር) በቀር፡፡
 • እሑድና ቅዳሜን የሚጾም የመርቅያን ክሕደቱ ልቡናህን አያስትብህ፣ በቅዳሴ ጊዜ ቸል አትበል፣ ሰውነትህን ለከበረ ለሥጋው ለደሙ የበቃ አድርግ። የበቃህ ሳትሆን ከእርሱ እንዳትቀበል ጽኑ ፍዳ እንዳይፈርድብህ፡፡
 • ወንድሞች ወደ አንተ በመጡ ጊዜ እግራቸውን ማጠብን ቸል አትበል፣ ይህችን ሥራ ቸል የሚልዋትን ስለዚህ ትእዛዝ ሥላሴ በፍዳ ይመረምሯቸዋልና ምንም ኤጲስ ቆጶሳትም እንኳ ቢሆኑ እግዚአብሔር አስቀድሞ የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቦ እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ አዝዟቸዋልና፡፡

ይቆየን

አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ ጌታችን ጾመ፡፡ (ቅዱስ ያሬድ)

በመጋቤ ሐዲስ ምሥጢረ ሥላሴ ማናዬ

ጾም በብሉይ ኪዳንም፣ በሐዲስ ኪዳንም በፈጣሪ መኖር ለሚያምኑ የፈጣሪያቸውን ስሙን ጠርተው ለሚማጸኑ የተሰጠ አምላካዊ ትእዛዝ መሆኑ ለሁሉም ግልጽ ነው፡፡ በብሉይ ኪዳን በነቢያት የተጾሙ፣ ለሰዎች ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት ያገለገሉ አጽዋማት እንዳሉ መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ “ሙሴም ወደ ተራራው ወጣ አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ቆየ” (ዘጸ.፳፬፥፲፰) እንዲል፡፡ ሙሴ በተራራው የቆየው እየጾመ ነበር፡፡

ነቢያት በጾም ከፈጣሪያቸው ጋር ተገናኝተውበታል፡፡ ምንም እንኳን ድህነተ ነፍስን ማግኘት ባይችሉም በመጾማቸው አባር ቸነፈርን ከሕዝቡ አርቀዋል፡፡ በብሉይ ኪዳን ያሉ አጽዋማት በሙሉ በፍጡራን የተጾሙ ናቸው፡፡ የሐዲስ ኪዳን ጾም ግን የተጀመረው በጌታ ጸዋሚነት ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን አጽዋማት ረድኤተ እግዚአብሔር የሚገኝባቸው እና የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መነሻና ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ቅዱስ ያሬድ ከላይ በርእሱ የነገረን የጌታችን ጾም የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ጾም የአጽዋማት ሁሉ በኵር ነው፡፡ በኃጠአት ብዛት በመርገም በጠወለገ ሰውነት የተጾሙ አጽዋማትን አድሷል፣ ቀድሷልም፡፡ ውኃ ከላይ ደጋውን፣ ከታች ቆላውን እንዲያለመልም የጌታም ጾም ከላይ ከመጀመሪያ የነበረ የአበውን ጾም ቀድሷል፣ ጉድለቱን ሞልቷል፡፡ ከእርሱ በኋላ የተነሡ የሐዋርያትን፣ የጻድቃን፣ የሰማዕታትን፣ የደናግል፣ የመነኮሳትን፣ የምእመናንን ጾም ቀድሶ የሰጠ ነው፡፡ በአጠቃላይ የጌታችን ጾም እንደ በር ነው፡፡ በር ሲከፈት ከውጭ ያለውን እና ከውስጥ ያለውን ያገኛል፡፡ የጌታችን ጾምም ከፊት የነበሩትን የነቢያትን አጽዋማት ኋላ ከተነሡ ከሐዋርያት አጽዋማት ጋር ያገናኘ ነው፡፡ በመርገም ውስጥ የነበሩትንና ከመርገም የተዋጁትን ያስተባበረ ጾም ነው፡፡

ቅዱስ ያሬድ እንደነገረን “ጌታችን የጾመው ለምን ነው?” የሚለውን ትልቅ ጥያቄ መልሶልናል “አርአያነቱን ይሰጠን ዘንድ” በማለት፡፡ ጌታችን የጾመው እንደ ፍጡራን ክብር ለመቀበል ኃጠአት ኖሮበት ስርየት ለማግኘት አይደለም፡፡ የጌታችን ጾም እርሱን ከመጥቀም በታች ነው፤ ለእኛ ጥቅም ጾመ እንጂ፡፡ አርአያነቱን አይተን፣ ፍለጋውን ተከትለን ልንጠቀምበት ጾምን ቀድሶ ሰጠን፡፡ ጾም ዲያብሎስን ድል የምንነሳበት ጋሻ፣ ከኃጢአት የምንሰወርበት ዋሻ፣ የመንግሥተ ሰማያት መውረሻ መሆኗን አርአያ ሆኖ ሊያሳየን ጾመ፡፡ የጾምንም ጥቅም በግብር በትምህርት በሚገባ አስረዳን፡፡

ይህ ዐቢይ ጾም(ታላቁ ጾም) ሁዳዴ፣ አርባ ጾም፣ የጌታ ጾም እየተባለ ይጠራል፡፡ ዐቢይ ጾም ማለት ከግሱ እንደምንረዳው እጅግ ትልቅ ጾም ማለትን ያሳያል፡፡ በእርግጥ የጾም ትንሽ የለውም፤ አንድም ቀን ይሁን ሳምንት ጾም ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጾም ዐቢይ(ትልቅ) የተባለበት ምክንያት፡-

የታላቆች ታላቅ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ሁሉ ጌታ የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ስለጾመው ነው፡፡

የሐዲስ ኪዳን አጽዋማት ሁሉ በኩር በመሆኑ ነው፡፡

ስምንት ሳምንታትን፤ ኀምሳ አምስት ቀናትን በውስጡ የያዘው በቁጥር እጅግ ከፍ ያለ በመሆኑ በቁጥር ከአጽዋማት ሁሉ ከፍተኛ ነው፡፡

ሁዳድ(የመንግሥት እርሻ)፡- በአንድ መንግሥት የሚተዳደሩ ሕዝቦች በሙሉ በግዳጅ ወጥተው የሚያርሱት፣ የሚያጭዱት የሚሠሩት እንደሆነ ሁሉ ይህም ጾም የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የመንግሥቱን የምስራች በምትነግር ወንጌል ያመኑ ምእመናን በአዋጅ በአንድነት የሚጾሙት በመሆኑ ነው፡፡

አርባ ጾም አያሻማም ግልጽ ነው፡፡ ጌታችን የጾመው አርባ መዓልትና አርባ ሌሊት ነው፡፡ “አርባ መዓልት እና  አርባ ሌሊት ጾመ”(ማቴ.፬፥፪) እንዲል፡፡ ጾሙ ስምንት ሳምንታትን ኀምሳ አምስት ቀናትን ያካተተ ነው ብለናል፡፡ ጌታችን የጾመው አርባ ቀን ነው ለምን ኀምሳ አምስት ቀናትን እንጾማለን? የሚሉ ጥያቄዎች በውስጣችን ሊመላለሱ ይችላሉ፡፡ ጌታችን በጾመው አርባ ቀን ላይ ቅዱሳን ሐዋርያት ከመጀመሪያው አንድ ሳምንት፣ ከመጨረሻው አንድ ሳምንት ጨምረውበታል፡፡ በዚህ ምክንያት ጾሙ ከስድስት ሳምንታት ወደ ስምንት ሳምንታት፣ ከአርባ ወደ ኀምሳ አምስት ቀናት ከፍ ሊል ችሏል፡፡ ለምን ብለን ጥያቄ ማንሳት የለብንም፡፡ ምክንያቱም የጨመሩት ከጌታችን ጋር ፣ በቃልም፣ በተግባርም ከጌታ የተማሩ፣ የምሥጢር ደቀ ማዛሙርት የሕግ ምንጮች እኛ ወደ ክርስቶስ በምናደርገው ጉዞ መሪዎች የሆኑ ቅዱሳን ሐዋርያት ናቸው፡፡ አምነን ከመቀበል ውጭ ምንም ልንል አይቻለንም፡፡ እኛ የክርስትና  ተቀባዮች እንጂ ጀማሪዎች ወይም  መሥራቾች አይደለንም  በቅዱሳን ሐዋርያት  መሠረትነት ላይ የተመሠረትን እንጂ፡፡

“እናንተስ በነቢያትና በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ተመሥርታችኋል”(ኤፌ.፪፥፳) እንዲል የብሎኬት ድርድር መሠረት አያስፈልገኝም ሊል አይችልም፡፡ መሠረቱ ከተናደ ድርድሩ የት ሊቆም ይችላል? እኛም የሐዋርያትን ካልተቀበልን የማንን እንቀበላለን?

ቅዱሳን  ሐዋርያት ከመጀመሪያው የጨመሩት የጌታችን ጾም መግቢያ መቀበያ ንጉሥ ሲመጣ በሠራዊት እንዲታጀብ፣ በብዙ ሕዝብ እንዲከበብ፣ ከፊት ከኋላ ተከብቦና ታጅቦ በክብር እንደሚቀበሉትና እንደሚሸኙት ሁሉ የንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ ጾም ሲመጣ የሚያጅቡ፣ የሚከቡ፣ የሚያከብሩ ዘወረደን ከመጀመሪያው፣ ሕማማትን ከመጨረሻ ጨምረዋል፡፡ ደግሞስ መቀነስ እንጂ መጨመር አያስቀጣ፡፡  በክርስትና ሕይወት የተቀበሉትን መክሊት መቅበር እንጂ አትርፎ ማቅረብ ገብርኄር ያሰኛል፣ ያሾማል፣ ያሸልማል ሐዋርያትም የጨመሩት ገብርኄር ለመሰኘት ነው፡፡

ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ (ከመጋቢት ፩-፲፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የቅድስና ሕይወት

ለሜሳ ጉተታ

ቅድስና የሚለው ቃል ቀደሰ ፤ አከበረ ፤ አነጻ ከሚለው የግእዝ ቃል የተገኘ ነው ፡፡ የቅድስና ባለቤት ምንጭ እና መሠረት እግዚአብሔር ሲኾን ቅድስናውም የባሕርይ ገንዘቡ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች ማለትም ሰዎች፣ ቀናት፣ ንዋያት፣ ቦታዎች፣ ምስጋናና የመሳሰሉት ለእግዚአብሔር ሆነው ሲለዩና ሲቀርቡ ቅዱስ ይሆናሉ፡፡ ይህ የተሰጣቸው ቅድስና የእግዚአብሔር ከመሆናቸው የተነሣ የሚያገኙት በመሆኑ የጸጋ ቅድስና ይባላል፡፡ የእግዚአብሔር ቅድስና ግን የባሕርይ ገንዘቡ ነው ፡፡

ከላይ የሠፈሩትን ሀሳቦች መሠረታዊ መልእክት ስንመለከት የቅድስና ሕይወት ባለቤት እግዚአብሔር መሆኑንና ሰዎችም ይቀደሱ ዘንድ ፈቃዱ መሆኑን እንረዳለን፡፡ ለቈላስይስ ምእመናን የተላከው የቅዱስ ጳውሎስ መልእክትም ከተገለጸው መልእክት በተጨማሪ ሰውን ወደ ቅድስና የሚያደርሱ የተጋድሎ መስመሮችን ያሳያል፡፡ እነዚህ ምሕረትና ርኅራኄ፣ ቸርነትና ትሕትና፣ የዋህነት፣ ትዕግሥት፣ ይቅር መባባልና ፍቅር፣ ማመስገንና ቅዱስ ቃሉን መማር፣ ራስን ማስተማርና መገሠጽ ወደ ቅድስና ሰገነት የሚያወጡ/የሚያደርሱ መሆናቸውን ከጥቅሱ እንገነዘባለን ቈላ. 3፥12-18.

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደኛ ወጣቶች ሁነው ኃጢአትን አሸንፈው የኖሩ ለቅድስና ማዕርግም የበቁ ብዙ ወጣቶችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ በእነዚህ ቅዱሳን ዘመን የእምነት እና የሃይማኖት ነጻነት የለም፡፡ እግዚአብሔርን ማምለክ ማመስገን ለእርሱ መገዛት አይቻልም፡፡ በሕግ የተከለከለ እና የተገደበ እርሱን አምልኮ አመስግኖ ለእርሱ ተንበርክኮ የተገኘ ሁሉ ይቀጣ ነበር፤ ይታሰራል፤ ይገረፋል፤ ለእሳትና ለአንበሶች እራትም ይሆናል፡፡ እነርሱ ግን ለእርሱ ካላቸው ፍቅርና ቅንነት በእምነታቸው ጽናት ለጣዖት አልሰገዱም፣ አላመለኩምም፡፡ ይህንን ሁሉ ግን የፈጸሙት በእምነትና በተጋድሎ ነው ፡፡

ይህንንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ብሎ ገልጾታል፡- “እንግዲህ ምን እላለሁ? ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሶምሶንም ስለ ዮፍታሔም ስለ ዳዊትና ስለ ሳሙኤልም ስለ ነቢያትም እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሡ፤ ጽድቅን አደረጉ፤ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አገኙ፥ የአንበሶችን አፍ ዘጉ፥ የእሳትን ኃይል አጠፉ፥ ከሰይፍ ስለት አመለጡ፥ ከድካማቸው በረቱ፥ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ፥ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ። ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ፤ ሌሎችም መዳንን ሳይቀበሉ የሚበልጠውን ትንሣኤ እንዲያገኙ እስከ ሞት ድረስ ተደበደቡ፤ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጉድጓድ ተቅበዘበዙ። እነዚህም ሁሉ በእምነታቸው ተመስክሮላቸው ሳሉ የተሰጠውን የተስፋ ቃል አላገኙም፥ ያለ እኛ ፍጹማን እንዳይሆኑ እግዚአብሔር ስለ እኛ አንዳች የሚበልጥ ነገርን አስቀድሞ አይቶ ነበርና” (ዕብ.11፡23-40)።

ዛሬ እኛ በአንጻራዊነት ሲታይ የእምነትና የሃይማኖት ነጻነት አለን፡፡ ያለ እኛ ፈቃድ ከእግዚአብሔር ሌላ እንድናመልክ የሚያስገድድ አካል የለም፤ ሰሞኑን በሀገራችን እየታዩ ያሉ የአህዛብ ጥቃቶችና የሰማእታቱ ጥብዐት እንደተጠበቀ ሆኖ፡፡ ከዚህም በላይ ግን በራሳችን ፍላጎት እና ምኞት ተስበን ከእርሱ ልጅነት እንዳንወጣ፣ ከዘላለማዊ ሕይወትም እንዳይለየን ጥንቃቄ ልናደርግ ይገባል፡፡ እንጸና ዘንድም እነ ዳንኤልን እና ሠለስቱ ደቂቅን እንደ መልካም አርዓያ ማንሳት ይቻላል፡፡ እምነት ሥራን ይፈልጋል፡፡ ይህም ሲባል ማመን አንድ ጉዳይ ሲሆን እምነትን ወደ ተግባር መለወጥን፣ የምግባር ሰው መሆንን፣ ተጋድሎና ክርስቲያናዊ ግዴታዎችንም መፈጸምን ይፈልጋል፡፡

ለሰላም በሰላም እንሥራ!

 

ለሜሣ ጉተታ

ዛሬ በሀገራችን ሰላም የሚያደፈርሱ ብዙ ችግሮች ያሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ የተሳሳቱ የታሪክ ትርክቶች፤ ወገንተኛ መሆን፤ አክራሪነት፣ የኢኮኖሚ፣ የሃይማኖት፣ የፖለቲካና፣ የሥልጣን የበላይነትን መፈለግ፤ የሐሳብ ልዩነትን አለማክበር፣ ያለመደማመጥ፣ ያለመግባባት፣ ጽንፈኛ ብሔርተኛ መሆን፣ ዘረኝነትና የሥልጣን ጥማት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ ለዚህ መፍትሔ በዋናነት ታላላቆች  ለትውልዱ አርአያና ምሳሌ ሊሆኑ ይገባል፡፡ ከራሳችን የግልና የቡድን ጥቅም/ፍላጎት በላይ ሕዝብንና ሀገርን ማስቀደም የግድ ይላል፡፡

በተለይም ክርስቲያን ከሁሉም ሰው ጋር በሰላም፣ በአንድት፣ በፍቅር፣ በመግባባት፣ በመደማመጥ፣ በመቻቻል፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት ለሌሎችም አርአያና ምሳሌ በመሆን ልዩነትን በማጥፋት የተጣሉትን በማስታረቅ ሊኖር ይገባል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹የሚያስታርቁ ብዑዓን ናቸው›› ይላልና፡፡ በሌላም በኩል “ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ” (ሮሜ.12፤18) መባላችን ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት መሆኑን ያሳያል፡፡ ክርስቲያኖች ሁላችን ባለንበት ቦታ ሁሉ ሰላምን ሊያጠፉ ከሚችሉ ክፉ ተግባራት ሁሉ መራቅ አለብን፡፡ ነገሮችን በትዕግሥት፣ በጥበብና በማስተዋል ልናልፍ ይገባል፡፡ ካላስፈላጊ ክርክርና ሙግትም ልንርቅ ይገባል፡፡ ሰላምን መፈለግ፣ ነገርን መተው፣ ለይቅርታ መሸነፍ ይገባል፡፡ ይቅር ባይነትና ይቅርታን መጠየቅ አስተዋይነት እንጂ ተሸናፊነት አይደለምና፡፡ ይህ ደግሞ የክርስቲያን ቁልፍ መለያው ነው፡፡

እኛ ክርስቲያኖች በትንሹም በትልቁም፣ በሥራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት፣ በማኅበራዊ ሕይወታችን ላይ የሰላም፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የእርቅ ምክንያት እና ተምሳሌቶች መሆን አለብን እንጂ የግጭት፣ የልዩነት፣ የክርክር፣ የጠብ እና የጥል መንስኤ መሆን የለብንም፡፡ ፍቅር የነበራቸው፣ ታሪክ የነበራቸውና ድሆዎችን ሲረዱ የነበሩ ነገር ግን ዛሬ ስማቸውና ታሪካቸው እንዳልነበረ የሆኑ በርካቶች ናቸው፡፡ በማሳያነት ሶርያን፣ ሊቢያንና ሱዳንን ልናስታውስ ይገባል፡፡ ከምድረ ገጽም ለመጥፋት የተቃረቡም አሉ፡፡ ዜጎቻቸው ሰላምን  በማጣት በየሀገራቱ የተበተኑባቸው አሉ፡፡ የየመንና የሶሪያ ዜጎች በሰላም እጦት ምክንያት ከተደላደለ ሕይወታቸው ወጥተው ብዙዎቹ ሕይወታቸው አልፏል፤ በየሀገራቱ በስደት ተቅበዝባዥ ሁነዋል፣ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ እንኳን ሳይቀር በልመና መሰማራታቸውን ጭምር እያስተዋልን ነው፡፡ ይህ ሁሉ ከሰላም እጦት የመጣ ችግር ነው፡፡  ከዚህ ውጪ የብዙ  ሀገራት ዜጎች ሰላምን በማጣት ሀገራችንን መጠለያ አድርገዋታል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ ትልቅ ትምህርት ሊሆነን ይገባ ነበር፡፡

ሰላምን ለማግኘት በጎ ሥራን መሥራት ከክፋት ከተንኮል መራቅ እንዳለብን ብሎም ሰላምን መሻትና መፈለግን ተግባራችን መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡ ሰላምን የሚሰጠው እግዚአብሔር ነው፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ እኛ ሰላማዊ ስንሆን ነው፡፡ ሰላምን የማይፈልጉት ክፉዎች ብቻ ናቸው፡፡ እነርሱ ደግሞ ተንኮለኞች፣ በወንድማማች መካከልም ጥልንና ክርክርን የሚዘሩ፣ በእግዚአብሔር ዘንድም የማይወደዱ፣ የተጠሉም ጭምር ናቸው፡፡ የልዩነትና የጦርነት እንክርዳድን፣ ጥርጣሬንና ሐሜትን የሚዘሩ ናቸው፡፡ የፍቅር፣ የአንድነት እና የሰላም እንቅፋቶች ናቸው፡፡ ከዜጎች መካከል ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መቻቻልን፣ መደጋገፍን መደማመጥን የሚያጠፉ ናቸው፡፡ ይህ እኩይ ተግባር ደግሞ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፤ በሥጋ መጎዳት ብቻ ሳይሆን በነፍስ ላይም ጭምር ሞትን ያስፈርዳል፡፡

የሀገር ፍቅር ያለው ሰው መገለጫው የሰላም ሰው መሆን ብቻ ነው፡፡ የሀገር ፍቅር ያለው እርቅን የሚፈልግ የይቅርታ ልብ ያለው ሰው ነው፡፡ እግዚአብሔር ጥልን የሚዘሩትን ይጸየፋል፡፡ ፍቅር የሌላቸው ክፉዎች ከእግዚአብሔር መንግሥት የተለዩ፣ ከእርሱም ጋር አንድነት ኅብረት የሌላቸው የጨለማው ልጆች ናቸው፡፡ ለጊዜው ሰላማዊ፣ ደስተኞች ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ውስጣቸው ክፋታቸውን ስለሚነግራቸው በሰላም መኖር ወጥቶ መግባት፣ ተኝቶ መነሳት፣ ደስተኛ የሆነ ሕይወትን መኖር አይችሉም፡፡ ‹‹ለክፉዎች ሰላም የላቸውም›› ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ በአንጻሩ  ደግሞ ‹‹በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር ሰላምም ይሆንላቸዋል›› ተብሏል (ሮሜ.2፡10)፡፡ እናም ሁላችን ለሰላም በሰላም እንሥራ፤ እንጸልይ፤ ለሀገራችን ሰላምን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ መግባባትንና መቻቻልን እንዲያድለን የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን አሜን !

 

‹‹ሰላምን የሚሹ ሰላምን ያደርጋሉ››

ለሜሣ ጉተታ

ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋዋሩ ሥራውን በጥበብ  የዋህነት ያሳይ፡፡ ነገር ግን መራራ ቅንዓትና አድመኛነት  በልባችሁ ቢኖርባችሁ አትመኩ፤ በእውነትም ላይ አትዋሹ፡፡ ይህ ጥበብ  ከላይ የሚወርድ አይደለም ፤ ነገር ግን የምድር ነው ፤ የሥጋም ነው፤   የአጋንንነትም ነው ፤ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ሥራ ሁሉ አሉና፡፡ ላይኛይቱ ጥበብ ግን በመጀመሪያ ንጽሕት ናት ፤ በኋላም  ታራቂ ገር እሺ ባይ ምሕረትና በጎ ፍሬ የሞላባት ጥርጥርና ግብዝነት የሌለባት ናት፡፡ የጽድቅም ፍሬ ስላምን ለሚያደርጉት ሰዎች በሰላም ይዘራል፡፡  ያዕ 3፡ 13-18

ሰላም የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ ነው፡፡ ሰላምን ለማግኘት እግዚአብሔርን መፍራት በሕጉና በትእዛዙ መሠረት መሔድ፣ ከክፋት ከተንኮል መራቅ በጎነትን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ሰላም በስብሰባ ፣ በሥልጠና፣ በውይይትና በሰላማዊ ሰልፍ የሚመጣ አይደለም፤ ሰላማዊ በመሆንና በጎነትን በመሥራት ክፋትን በመጠየፍ እንጂ፡፡ በእውነት ከልብ ሰላማዊ ሰው በመሆን የሚገኝ ነው ሰላም፡፡ መጽሐፍም “ሰላምን አጥብቀህ ተከተል፤ “ሰላምን እሻ ተከተላትም” (2ኛ ጢሞ 2፡22፣ መዝ 34፤14) ይለናል፡፡

ክርስቲያን የሰላም ሰው መሆን አለበት፡፡ ሰላምን አንድነትንና ፍቅርን ከሚያደፈርሱ ነገሮች ተግባርና ሐሳብም ጭምር መራቅ አለበት፡፡ ሁል ጊዜም ስለ ሰላም፣ ስለ ፍቅር፣ ስለአንድነት መለመን አለበት፡፡ ሰላምን ከሚያደፈርሱ ነገሮች ከመራቅ በተጨማሪም ሰዎችን መምከር፣ ማስተማር መገሰጽ አለበት፡፡ ክርስትና የሰላምና የፍቅር ሕይወት ነውና ፡፡ ይህን ለማድረግ ግን የግል ፍላጎትን መተው አለብን ፡፡ ዕብ 12፡14 ላይም “ከሰው ሁሉ ጋር ሰላምን ተከታተሉ፤ ትቀደሱም ዘንድ ፈልጉ፤ ያለ እርሱ ጌታን ሊያይ የሚችል የለምና“ መባሉም ለዚህ ነው ፡፡ ስለ ፍቅር፣ ስለ ሕዝብ፣ ስለ ወገን ሰላም የሚመኝ ሰው በቃሉ ሰላማዊ በልቡና በተግባሩ ግን ተቃራኒ ሆኖ መገኘት የለበትም፡፡ የአብዘኞች የዘመናችን ግለሰቦች ችግር ግን ይህ ነው ፡፡ በቃል እና በአፋቸው ሰላምን ይሰብኩሉ፤ ከመጋረጃ ጀርባ ያለው ተግባራቸው ግን እጅግ በጣም አሰከፊ እና አጸያፊም ነው፡፡ አብዘኞቻቸው ሰላምን በሚያደፈርስ ተግባር ውስጥ ናቸውና፡፡

ሰላም ለሰው ልጅ ሕይወት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ያለ ሰላም እንኳን ልማትን ማልማት፣ መማርና ሠርቶ መለወጥ ይቅርና  ተኝቶ መነሳት፣ ወጥቶ መግባት እንኳን አይቻልም፡፡ ፈጣሪን ለማምለክ፣ ለመማር፣ ለማደግ ለመለወጥ፣ ቤተሰብን ለመመሥረት ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ከግል ሕይወትና ከቤተሰብ የሚጀምር የሕይወት መሠረት ነው፡፡ የሰው እድሜው በምድር እጅግ አጭር ነው፡፡ በዚህ አጭር የሕይወት ዘመን የተረጋጋ ሕይወትን በመኖር መልካም ሥራን ሠርቶ ማለፍ አለበት፤ ለዚህ ደግሞ ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ሰላም ከሌለ  የማይጎዳ የሕብረተሰብ ክፍል የለም ፡፡ ከጦርነት፤ ከጥል፤ ከሁከት የሚገኝ አንድም ነገር የለም ፡፡ ሰላም ስታጣ ሕይወት ይጠፋል፤ መረጋጋትም አይኖርም፡፡ መተማመን ይጠፋል፡፡ በመካከለችንም ጥርጣሬ ይሰፋል፡፡ በዚህ መሐል እርሰ በእርስ መተላለቅም ይመጣል፡፡

‹‹ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› ሮሜ. ፲፪፥፲፰

በለሜሳ ጉተታ

ማኅበራዊ ሕይወት የአንድነት፣ የመቻቻል እና የመደጋገፍ ኑሮ ነው፤ የቤተ ክርስቲያን አስተምሮ በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ መተሳሰብ፣ መረዳዳትና መተጋገዝ እንዳለብን ያስረዳል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ እንዳሉት ‹‹ማኅበራዊ ሕይወታችን የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የመተሳሰብ፣ የመከባበር፣ የመተጋገዝ፣ ምንጭ ስለሆነ የእርስ በርስ ግጭትን በማራቅ ሰላማዊ፣ የለመለመ አካባቢ፣ የለማ ሀገር እንዲኖረን ትልቅ እና መሠረታዊ አስተዋጽኦ አለው››፡፡ ይህም ኃላፊነትና አደራን መወጣት ነው፡፡ ቅዱሳን አባቶቻችን ሀገርን፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ታሪክን፣ ትውፊትን፣ ሥርዓትን ለእኛ ያስረከቡን የክርስትና ፍቅር፣ ውለታና አደራ ስላለባቸው ባለ ራእይና ሩቅ አሳቢ በመሆናቸውም ጭምር ነው፡፡ ክርስቲያኖች ይህን አደራ ተቀብለው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን በመጠበቅ በኅብረት ለመኖር ክርስቲያናዊ ምግባሮችን የመፈጸም ኃላፊነት አለባቸው፡፡

ዘረኝነትና ለዝሙት መገዛት፤ ዕርቅ፣ ሰላምና ፍቅርን አለመፈለግ፤ ትዳርና ቤተሰብን መበተን፤ ክርስቲያናዊ ግዴታን አለመፈጸም እና ከክርስትና ሕይወት መራቅ የመንፈሳዊ ሰው ምግባር አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በሮሜ. ፲፪፥፲፰ ላይ ‹‹ቢቻላችሁስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ›› በማለት መክሯል፤ ክርስትና ፍቅር ነውና፡፡ ያለምንም አድልዎ ሰውን ሁሉ ሳንንቅ በማክበር፣ በሰው ላይም ችግርን ሳንፈጥርና ተንኮልን ሳንሠራ መኖር አለብን፤ ይህ ደግሞ ክርስቲያናዊ መሠረት ነው፡፡

ማኅበራዊ ጉዞ በእምነትና በእውነት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ለበረከት ይሆናል፡፡ ሥራችንን በትጋት፣ በቅንነት፣ በታማኝነት እንዲሁም በታዛዥነት ልንፈጽም ይገባል፡፡ ትዳራችን በእግዚአብሔር ፈቃድ ሲጸና፣ መልካም ቤተሰብ ስንመሠርት፣ የታመሙትንና የተቸገሩትን ስንጠይቅና ስናስተዛዝን፣ የተራቡትን ስናበላና ስናጠጣ፣ ለሞቱት ወገኖቻችን ተዝካር ስናወጣ፣ ችግሮቻችንን ለመቅረፍ በአንድነት ውይይት ስናደርግ፣ ቅዱሳንን፣ ጻድቃንና ሰማዕታትን ስንዘክር እንዲሁም መንፈሳውያት በዓላትን በአንድነት ስናከብር፤ ማኀበራዊ ሕይወታችን ጠንካራ ይሆናል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም የማኀበራዊ ሕይወት ጠቀሜታን ሲገልጽ ‹‹ደስ ከሚለው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሰው ጋርም አልቅሱ፡፡›› ብሏል (ሮሜ. ፲፪፥፲፭)

በሐዲስ ኪዳን በሐዋርያት ስብከት ያመኑ ምእመናን በአንድ ልቡናና በአንድ ሐሳብ ተስማምተው ይኖሩ ነበር፡፡ ያላቸውንም ሀብት የሚያስቀምጡት በጋራ እንጂ በግል አልነበረም፡፡ ንብረታቸውን በሙሉ እየሸጡ ገንዘባቸውን ሰብስበው በሐዋርያት እግር ስር ያስቀምጡ ነበር፡፡ ‹‹ያመኑትም ሁሉ አንድ ልብና አንዲት ነፍስ ሆነው ይኖሩ ነበር፤ በውስጣቸውም የሁሉ ገንዘብ በአንድነት ነበር እንጂ ‹ይህ የእኔ ገንዘብ ነው› የሚል አልነበረም››፡፡ (ሐዋ.፬፥፴፪)

ማኅበራዊ ሕይወት የጽድቅ፣ የቅድስና፣ የበረከት ሥራን የምንሠራበት እና ለዘለዓለም ሕይወትና ክብር የሚያበቃንን ሥራ የምንፈጽምበት ነው፡፡ ለስንፍናችን ሰበብ ማቅረብ የእግዚአብሔርን ጸጋና በረከትን ያሳጣል፤ ሰላም የሰፈነበት ሕይወት እንድንኖር አያደርግም፡፡ ሁሉ ጊዜ ሕይወትን በሀሳብ፣ በጭንቀት፤ በጉድለት ለመምራት ይዳርጋልና ወደ ልቦናችን መመለስ አለብን፡፡ ፩ኛ ጢሞቴዎስ ፮፥፳ ላይም ‹‹የተሰጠህን አደራ ጠብቅ›› ማለቱ ማንነትን ያለመርሳት ኃላፊነት እና አደራን መወጣት እና ለሌሎች ሰዎች መድረስ እንዳለብን ስለሚያሳይ ልንማርበትና በሕይወትም ልንኖርበት ይገባል፡፡

ተምረው ማገልገል ያቃታቸው፣ የጠፉ፣ በዓለም ጉያ ሥር የተሸሸጉ፣ ከቤተ ክርስቲያን እና ከንስሓ ሕይወት የሸሹ ሰዎች የክርስትና ክብር ስላልገባቸው ነው፡፡ የክርስትና ክብር የገባው ለሥጋ ምቾት ቦታ አይሰጥም፡፡ ነፍሱን ያስበልጣል፤ ከሁሉም ነገር ይልቅ ለክርስትና ሕይወቱ ቅድሚያ ይሰጣል፤ ራሱን አሳልፎም ለአምላኩ ይሰጣል፡፡ ሆኖም ዛሬ ብዙዎች በዓለም ጠፍዋል፤ ማንነታቸውን ረስተዋል፤ በዚህም ለዲያብሎስ ለሥጋ ፈቃድና አምሮት ተገዝተዋል፡፡ እንኳን በእኛ ቀርቶ በአሕዛብ ዘንድ የማይሠሩ በዐይን ለማየትና በጆሮ ለመስማት አሰቃቂ የሆኑ ሰይጣናዊ ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛሉ፤ ስለዚህም ወደ ልቡናችን መመለስ ይኖርብናል፡፡

ዛሬ ሰዎች በኅብረትም ሆነ በግል የረከሰ ሥራ እየሰሩ ይገኛሉ፤ ጫት የሚቅሙ፣ ሲጋራ የሚያጤሱ፣ አብዛኛው በዝሙት የተጠቁ እና የሚተዳደሩ፣ ትዳራቸውን በየፍርድ ቤቱ የሚፈቱ፣ በተለያዩ ሱሶች የተጠመዱ፣ ለተለያዩ ሱሶች የተገዙና በመጠጥ ብዛት የሚሰክሩ፣ በስመ ክርስቲያን የሆኑ ነገር ግን በሕይወት የሌሉ ብዙ ናቸውና፡፡ ችግሩንም ለመፍታት ሁላችንም በጋራ ልንሠራ ይገባል፡፡ በተለያዩ መንገዶች ቃለ እግዚአብሔርን የሰማን፣ የተማርን፣ ለሌላውም መትረፍ የነበረብን ክርስቲያኖች ነበርን፡፡ ነገር ግን ለሥጋ በማድላት የተለያዩ ሥጋዊና ቁሳዊ ምክንያቶችን በመደርደር ኃላፊነትን በመርሳት የእግዚአብሔርንና የቤተ ክርስቲያንን ውለታ በመርሳት አደራችንን መወጣት ያቃተን እና ኃላፊነታችንን የረሳን አለን፡፡ ይህ ከማኅበራዊ ሕይወት ውጪ ነውና ያለብንን አደራ እና ኃላፊነት በማሰብ ልንወጣ ይገባል፡፡

ጾመ ሐዋርያት

አባ ዐሥራት ደስታ

    ጾም ከክርስቲያናዊ ምግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ጾም አንድን ክርስቲያን ክርስቲያን ከሚያሰኙት ሥራዎች እና በእግዚአብሔር ዘንድም እንዲወደድ ከሚያደርጉን ተግባራት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ክርሰቲያን ማለት የክርሰቶስ ወገን፤ አካል፤ ቤተሰብ፤ ደቀ መዝሙር ማለት ነው፡፡ ክርስቲያን ክርሰቶስን መስሎ የሚኖር ሰው ነው፡፡ ይህ ደግሞ ሕይወትን በጾም በጸሎት በመምራት ራስንም ከክፋት በመጠበቅ መልካም ሥራንም በመሥራት ራስን በቅድስና በመጠበቅ የሚገልጥ ተግባር ነው፡፡ እኔ ክርስቲያን ነኝ እያለ ግን  ‹‹ይህ ጾም የቄሶች ነው፤ የሰኔ ጾም ነው›› እያለ ምክንያትን የሚያቀርብ ‹‹ክርስቲያን›› እርሱ ራሱን መፈተሸ መመርመር ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ተግባሩ ሐዋርያትን የሚመስል መንፈሳዊ ሰው ነውና ፡፡

 ጾም ራስን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት ከኃጢአትም ለመራቅ ራስን ፍላጎትን ሃሳብን ችግር እና ምኞትንም ለእግዚአብሔር ለመግለጽ እርሱ ከክፋት እዲጠብቀን ለማድረግ ራስን ቤተሰብን አሳልፎ ለእርሱ መስጠት ነው ፡፡ በሃሳብ በተግባር እና በምኞትም ቅዱሳንን የመምሰል የመሆን ተግባር ነው ፡፡ ጾም መታቀብ መለየት ፈቃደ ሥጋን ለፈቃደ ነፍስ ማስገዛት ስለ ሠራነው ክፉ ሥራ ኃጢአት እና በደል ማዘን ማልቀስ ማንባት ለምሕረት ለቸርነት እና ለይቅርታ የእግዚአብሔርን ደጅ መጥናት ነው ፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓተ እምነት መሠረት ጾም የአዋጅ እና የግል ጾም ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ የአዋጅ ጾም የሚባለው ሁሉም ክርሰቲያን በታወቀ እና በተረዳ መንገድ የሚፈጽሙት ጾም በአንድ ሐሳብ እና በአንድ ልብ የሚጾሙት ሲሆን እነርሱም ፡-

 1. ጾመ ነቢያት፤
 2. ጾመ ነነዌ፤
 3. ዐቢይ ጾም፤
 4. ጾመ ሐዋርያት፤
 5. ጾመ ድኅነት (የረቡዕ እና የአርብ ጾም)፤
 6. ጾመ ፍልሰታ፤ እና
 7. ጾመ ገሀድ ናቸው፡፡

ሌላው የጾም  አይነት ደግሞ የግል ጾም ነው፡፡ የግል ጾምን የፈቃድ ወይንም የንሰሐ ጾም ማለት እንችላለን፡፡ ይህ ስለደበላችን ስለ ጥፋታችን እና ስለ ሠራነው ክፉ ኃጢአት እግዚአብሔር ምሕረት ቸርነት እና ይቅርታውን እንዲሰጠን ብለን ከንሰሐ አባታችን ጋርም በመነጋገር የምንፈጽመው ጾም ነው ፡፡

 ጾመ ሐዋርያት የሚባለው ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ የሆነውና ከጰራቅሊጦስ (ርደተ መንፈስ ቅዱስ) ቀጥሎ እስከ ሐምሌ አምስት ቀን ድረስ የሚጾም ጾም ነው፡፡ ይህ ጾም በአላዋቂዎች ወይም የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓትና ትውፊት ባልተማሩ ዘንድ ‹‹የቄስ ጾም›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ይህ አባባል ራስን በሰዎችና በእግዚብሔር ዘንድ ያሳንሳል እንጂ አያስከብርም፡፡ ይህን ጾም ማንኛውም ክርስቲያን የሆነ ሰው ሁሉ መጾም ያለበት ክርስቲያናዊ ተግባር እና ግዴታም ጭምር ነው፡፡

  ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ለስብከተ ወንጌል ወደ መላው  ዓለም ከመሠማራታቸው በፊት  በአንድነት፣ በሰላምና  በፍቅር  የጾሙት ጾም ነው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ ጾመ ሐዋርያት በድሜጥሮስ የበዓላት አቆጣጠር ስሌት (መባጀ ሐመር) ከፍና ዝቅ ስለሚል  የተወሰነ ቀን የለውም ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከአርባ ቀን ይበልጣል አንዳንድ ጊዜም ከሠላሳም ያንሳል፡፡ ለምሳሌም፡- በ2010 ዓ.ም ግንቦት 20 ተጀምሮ 43 ቀን ተጹሟል፡፡ በ2011 ዓ.ም ደግሞ ሰኔ 10 ይጀመርና ለ25 ቀን ይጾማል ማለት ነው፡፡

   ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ከተቀበሉ በኋላ ፍርሃት፣ ጭንቀት፣ ሥጋት ቀርቶላቸው በመላ ሰውነታቸው የተረጋጋ ሕይወትና ሰላም ነግሦባቸዋል ፡፡ ምንም እንኳን ክርስቶስን በመስበካቸው ከአረማውያንና ከአላውያን መከራ ቢበዛባቸውም የልብ ደስታ ይሰማቸው ነበር፡፡  በምግባር ፣በሃይማኖት  ጸንተው በነገሥታት ፊት ያለዕረፍት  በድፍረት ቃለ እግዚአብሔርን እያስተማሩና ግፈኞችን እየገሰጹ በጥብአት ለሰማዕትነትለ ደርሰዋል ጌታችንም በዚሁ ሥራቸው አክብረዋል፡፡

   ሐዋርያት ከብልየት የተለዩት በአእምሮ የጎለመሱት ከፍጹምነት የደረሱት መንፈሰ ቅዱስን በመቀበላቸው ነው፡፡ በዘመነ ብሉይ እንደ ቤት አድሮባቸው አካላቸውን እንደ ልብስ  ልቦናቸውን እንደ መቅደስ አድርጎ ነቢያትን ትንቢት ያናገረ የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ከሐዋርትም ሕጸጽ (ጥርጥርን) አጥፍቶላቸው ለቅድስናም አብቅቶአቸዋል፡፡

    ወላጆች ለልጆቻቸው መልካምና ደስ የሚያሰኝ ስጦታን መስጠት እንዲፈቅዱ ሁሉ እግዚአበሔርም ለቅዱሳን ሐዋርት ከቅዱስ መንፈሱ በመሰጠቱ እነርሱም የዲያብሎስን ውጊያ የማቸነፍ ችሎታንና በርኩሳን መናፍስት ላይ ኃይልን የመገሰጽ ሥልጣን በጾምና በጸሎት ተላብሰዋል፡፡

   ስለዚህ እኛም በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉደ እግዚአብሔር የተባልን የእግዚአብሔር የጸጋ ልጆች የእግዚአብሔርን ሕልውና ከመንፈስ ቅዱስ ከተረዳንና ካወቅን በኋላ በሥጋ ሥራ ተገፋፍተን  ሃይማኖታችን ብንክድ አምላክን ሥራ ብንነቅፍ የመመለስና በሕይወት የመኖርም ተስፋ የለንምና በትሁት ስብእና በንቁ ኅሊና ራሳችንን ለሕገ እግዚአብሔር በማስገዛት የጾምና ጸሎት ወዳዶች እንሁን እንደ ሐዋርያት በክርስቶስ ዘንድ አሸናፊዎች እንሆናለንና፡፡ ጾሙን ጹመን የነፍስ ዋጋን እንድናገኝበት የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁንልን አሜን ፡፡

‹‹የምንጾመው ለምንድን ነው?›› የጾም ጥቅም፣ ዓላማና አስፈላጊነት

ለሜሳ ጉተታ

ጾም፣ ጸሎትና የንስሐ ሕይወት የማይነጣጠሉ የክርስትና ሕይወት መሠረቶች ናቸው፡፡ ጾም በሃይማኖትና በምግባር ለመጽናት ከክፉ አሳብና ምኞት እንዲሁም ተግባር ለመጠበቅ የምግባር ፍሬንም ለማፍራት ይረዳል፡፡ ጾም ፍትወተ ሥጋን፣ የዓለምን ሀሳብ፣ ምኞትና ተግባሩን ለመጥላት የመንፈስ ፍሬን ለማፍራት ከሥጋ ፍሬ ራስን ለመጠበቅ መንግሥቱን ለመውረስ የእርሱ ጥበቃን ለማግኘት ይረዳል፡፡ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን፣ ጸጋንና በረከትን ለማግኘት ይረዳል፤ ምሥጢር እንዲገለጥልንም ያደርጋል፡፡ ጾም የመንፈሳዊ ተግባራትና የበጎ ሥራዎች ሁሉ መነሻ መሠረት/መገኛና መጀመሪያ ነው፡፡

ጾም ሥጋን ለመንፈስ ለማስገዛት፣ በመንፈሳዊ ሕይወትና በአገልግሎት ለመበርታት ለመጽናት፣ ለእግዚአብሔርም ለመገዛት ይረዳል፡፡  ያለ ጾም በመደዳ መብላትና መጠጣት፣ ያለ ልክና አግባብ ሥጋን ያበረታል፤ በአንጻሩ መንፈስን ደግሞ ያዳክማል፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ኃጢአትና በደልን ክፋትን ያሠራል፤ ለዓለምና ለሥጋ ሀሳብ ፍላጎትና አምሮትም ያስገዛል ፍላጎታችን ፤ ሥጋችን እና አሳባችን በነፍሳችን ላይ እንዲሠለጥን ያደርጋል፡፡ ጾም ከዚህ ሁሉ ይጠብቃል፡፡ ጾም ለትሩፋት ያተጋል፡፡ አብዝቶ መብላትና መጠጣት ለፍትወት ያነሣሣል፡፡ ይህ ደግሞ የሰው መልአካዊና ሰማያዊ ብሎም መንፈሳዊ ማንነቱን ንጽሕናና የቅድስና ሕይወቱን ለማቆሸሽ ይዳርጋል፡፡ ክርስቲያን ሕይወቱን በጾም በጸሎትና በንስሐ የሚመራ መንፈሳዊ ሰው መሆን አለበት፡፡ ሮሜ.7፡1፡፡          

ይህ እየታወቀ ግን አሁንም ትውልዱ ‹‹ለምን እንጾማለን?›› በሚል ጥያቄ ተወጥሯል፡፡ ያለንበት ወቅት እና የምንኖርባት ዓለም በልዩ ልዩ ጥያቄዎች የተሞላች ምድር ናት፡፡ ደግነትም ክፋትም የሚንጸበረቅባት ዓለም ናት፡፡ ክርስቲያን  ሁሉን የማወቅ የመመርመር መልካሙን እና ክፉዉንም የመለየት መልካሙንም የመምራጥ ግዴታ እና ኃላፊነት ያለበት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በእርግጥም መጠየቅ ከክፋት ራስን ለመጠበቅ ብሎም በጎዉን ለመሥራት ይረዳል፡፡ ለዚህ ነዉ መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም መርምሩ መልካሙንም ያዙ’’ የሚለን (1ተሰ.5፥20-21)፡፡

አይታይ፣ አይጨበጥ፣ አይዳሰስ፣ አይነገር፣ አይተረክ የነበረው ይህ ዓለም ለምን እንዲታይ እንዲዳሰስ እንዲተረክ ሆነ ብሎ መጠየቅ  አላዋቂ አያሰኝም፡፡ ምክንያቱም ጥያቄው የፍጥረተ ዓለምን ዓላማ  ለመረዳት፣ ተረድቶም ድርሻን ለመወጣት እስከሆነ ድረስ ተገቢ ነውና፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ለምን እንደሚጾም ለሚጠይቅ ሰውም ግልጽ ማብራርያ መስጠት ተገቢ ይሆናል፡- ጾም ለክርስቲያኖች  መንፈሳዊ ተግባር እና ግዴታ መሆኑን፣ መንፈሰዊ ሰው እንደሚያደርግ፣ ከፈተና እንደሚጠብቅ፣ በሃይማኖት እና በምግባርም እንደሚያጸና፣ ለአገልግሎት እንደሚያተጋ፣ ሰውነትን ለእግዚአብሔር ለማስገዛት ራስንም ከኃጢአት ከክፋት ከደበል ለመጠበቅም እንደሚረዳ፣ ከፈቃደ ሥጋ፣ ከተግባረ ዓለም፣ ከከንቱ ምኞት እና ሃሳብም እንደሚጠብቅ፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችንም እንድናፈራ እንደሚያግዘን ማስገንዘብ ተገቢ ነው፡፡

ጾም የእግዚአብሔር ትእዛዝ ነው፡፡ ጾም ለክርስቲያኖች መንፈሳዊ ተግባርና ሕግ እንዲሁም ግዴታቸውም ጭምር ነው፡፡ ያለጾም ክርስቲያንና መንፈሳዊ ሰው መሆን አይቻልም፡፡ ሃይማኖት ባለበት ሁሉ ጾም አለ፡፡ ጾም የሃይማኖት መገለጫ እና መሠረት ነው፡፡ ጾም ለግል ሕይወት ለሀገር ለቤተ ክርስቲያን ለቤተሰብ ብሎም ለዓለም ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

እናም በአጭሩ፡-

 1. ጾም ሥጋን ለነፍስ ለማስገዛት ይረዳል፡፡

ሥጋችን ሁሉ ጊዜ ምቾትና ድሎትን ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ ሥጋ ከመንፈስና ከነፍስ በላይ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ሥጋ ሲሠለጥንብን የመንፈስ ተግባርን መሥራት ክርስቲያናዊ ግዴታዎችን መወጣት መተግበር ንስሐ መግባት፤ ምሥጢራት ላይ መሳተፍ በጎና መልካም ሥራን መሥራት ቃለ እግዚአብሔርን መማር፤ መተግበር ያዳግተዋል፡፡ ይህ በተራው ነፍስንና መንፈስን ያቀጭጫል፤ ሕይወትንም ያሳጣል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ሁሉ ጥፋት ለመዳን ጾም ትልቅ ልጓም በመሆን ያገለግላል፡፡ ጾም ሥጋን ለነፍስ ያስገዛል፡፡ ሁልጊዜ ስለነገረ እግዚአብሔር፣ ስለ መንፈሳዊነት እንድናስብ፣ ስለ ሕይወትና ሞት፣ ስለመልካም ሥራ፣ ስለ ቅድስና እና ስለ በረከት እንድናስብ ያደርጋል፡፡ ንስሐ እንድንገባ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያን ሁሉ ሕይወቱን በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሕይወት መምራት አለበት፡፡ ገላ.5፡16-17፣ ሮሜ.8፡5-6፡፡

የሥጋ ፈቃድ እና ተግባርን የሚፈጽሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ አይችሉም፡፡ ከዚህ ለመውጣት መንግሥቱን ለመውረስ ደግሞ ሕይወትን በጾም መምራት ያስፈልጋል፡፡ ሕይታቸውን ያለ ጾም ጸሎት እና ንስሐ የሚመሩ ሰዎች  የእነሱ ሕይወት መጨረሻው የዘለዓለም ሞት ነው፡፡ እናም ራስን ለመጠበቅ እናም መንግሥቱን ለመውስ መጾም ይኖርብናል፡፡

 1. ጾም ከእግዚአብሔር የምንፈልገውን ነገር እንድናገኝ ይረዳል፡፡

ክርስቲያን ያለ ጾም  ሕይወቱ ባዶ ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር የምንፈልጋቸው ነገሮችን ለማግኘት እርሱን በጾም እንማጸናለን፡፡ ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ቸርነትን፣ ይቅርታን፤ ጤናን፤ በረከትን፤ የእርሱን ጠብቆቱን እንለምንበታለን፡፡ ከኃጢአት እንዲጠብቀን፣ በሃይማኖት እንዲያጸናን፣ በምግባር፤ በመንፈሳዊ ሕይወትና በአገልግሎት፤ በምግባር እንዲያበረታን እርሱን እንማጸናለን፡፡ የሳሙኤል እናት ሐና እግዚአብሔርን የሚፈራ፣ ሰውን የሚያክብር፣ ታማኝ ታዛዥ ቅን ትሁት የሆነ ልጅን ያገኘችው በጾምና በጸሎት ሕይወት ነው፡፡ በቤቱ በመመላለስ ደጅ በመጥናት ሳትሰለች፣ ተስፋም ሳትቆርጥ በጽናት በእምነት በመለመን ነው፡፡ እኛም ከእርሱ የምንፈልገውን ነገር ማግኘት የምንችለው ያለ ትዕቢት በትዕግሥት በመለመን፣ በጽናትና በተስፋ በቤቱ በመጽናት ስንለምን ብቻ ነው 1ኛ.ሳሙ.2፡1፡፡

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን የሆነውን ታቦትን የተቀበለው ከዐርባ ቀናት የጾምና የጸሎት ሕይወት በኋላ ነው፡፡ ዘጸ.34፡1-31፡፡ እኛም ዛሬ ለብዙ ችግሮቻችን ከእርሱ መልስን ለማግኘት ሕይወታችንን በጾም፣ በጸሎትና በንስሐ ሕይወት መምራት ይኖርብናል፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ እና ዳንኤል ሃይማኖትን በምግባር ገልጸው ከሞት ባሕር የተሻገሩት ሕይወታቸውን በጾምና በጸሎት፣ እግዚአብሔርንም በመፍራት ይመሩ ስለነበር ነው፡፡ ዛሬም እኛ ከማናውቃቸው ክፉ ነገሮች እግዚአብሔር ይጠብቀን ዘንድ ሕይወትን በጾምና በጸሎት መምራት ያስፈልጋል፡፡

ጾም የልባችንን መሻት ለእግዚአብሔር ለመግለጽ ይረዳል፡፡ ስናውቅም ሆነ ሳናውቅ የምንሠራው ኃጢአት ከእግዚአብሔር ያርቃል፡፡ ከረድኤተ እግዚአብሔር፣ ከጸጋ መንፈስ ቅዱስ ያራቁታል፡፡ ስለዚህም ለምሕረት፣ ለቸርነት እና ለይቅርታ ማልቀስ ይኖርብናል፡፡ ጾም ከበደልና ከኃጢአት እንመለስ ዘንድ ንስሐን በመግባት ከእግዚአብሔር ምሕረት፤ ቸርነትና ይቅርታን ለማግኘት የምንፈጽመው ክርስቲያናዊ ተግባር ነው፡፡ ጾም በሃይማኖት ያበረታል፤ ከመከራ ሥጋና ነፍስም ያሻግራል፤ በጎ ምግባርንም ለመሥራት ያተጋል፡፡

ማጠቃለያ ፡-

የጾም መሠረታዊ ዓላማ ከምግብ ዓይነት መቆጠብ ከመመገብ እና ካለመመገብ ጋር የሚያያዝ ብቻ ሣይሆን ከምግብ በመራቅ በሚገኘው ውጤት ላይ ነው፡፡ ውጤቱም ፈቃደ ሥጋን በማሸነፍ መንፈሳውያን መላእክትን  መስሎ መኖር ወይንም መሆን ነው፡፡ እንዲሁም ራስን፣ ዓለምን፣ ክፉ ሃሳብ፣ ተግባር እና ምኞትን በማሸነፍ መንፈሳዊ መሆን፣ ራስንም ለእግዚአብሔር ማስገዛት ነው፡፡

ከጾም ዋጋን ለማግኘት በዋናነት እምነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ጾማችንንም በፍቅር፣ በምግባር፣ በሃይማኖት እና በእምነት ልንፈጽመው ይገባል፡፡ ለተራቡት ማሰብ፣ ለተጨነቁት መድረስ፣ ተሰፋ ላጡትም ተሰፋ መሆን ይኖርብናል፡፡ ጾማችንንም በንሰሐ ሕይወትና በጸሎት ልንፈጽመው ይገባል፡፡ በተጨማሪም ፈቃደ ሥጋን በማሸነፍ፣ ይልቁንም ከትዕቢት በመራቅ፣ ትሕትናንም ገንዘብ በማድረግ ሊሆን ይገባል፡፡ ጾሙን ጹመን ለመንግሥቱ እንዲያበቃን ከክፉ ነገርም እንዲጠብቀን  የአምላካችን መልካም ፈቃድ ይሁንልን አሜን፡፡