ዳግም ትንሣኤ

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከትንሣኤ በኋላ የሚውለውን እሑድ ዳግም ትንሣኤ ብላ ሰይማ ታከብረዋለች፡፡ ይህም በአከባበር፥ በሥርዓት የመጀመሪያውን ትንሣኤ ስለሚመስል ነው፡፡ ከትንሣኤ ዋዜማ ጀምሮ የሚጸለየው ጸሎት፣ የሚነገረው ቃለ እግዚአብሔር ሳይለወጥ፤ በሙሉ በዚህ ቀንም ይደገማል፡፡

ዕለቱንም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ለሁለተኛ ጊዜ መታየቱን(መገለጡን) በማሰብ ቤተ ክርስቲያን ታስተምራለች፡፡ የሐዋርያው ቅዱስ ቶማስም ምስክርነት የሚታሰብበት ነው፡፡ ታሪኩ እንዲህ ነው፡-

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዐርብ ተሰቅሎ፣ በሦስተኛውም ቀን መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል በዝግ መቃብር ሞትን ድል አድርጎ ከተነሣና በትንሣኤው ትንሣኤአችንን ካወጀልን በኋላ ሐዋርያት በአንድነት ተሰብስበው ሳለ ተገልጦላቸዋል፡፡ ይህንንም ወንጌላውያኑ በመተባበር ገልጸውታል፡፡ በተለይ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊ “ያም ከሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን በመሸ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ አይሁድን ስለ ፈሩ ተሰብስበው የነበሩበት ቤት ደጁ ተቆልፎ ሳለ ጌታችን ኢየሱስ መጥቶ በመካከላቸው ቆመና ‘ሰላም ለእናንተ ይሁን’ አላቸው፡፡ ይህንም ብሎ እጆቹንና ጎኑን አሳያቸው፤ ደቀ መዛሙርቱም ጌታችንን ባዩት ጊዜ ደስ አላቸው”(ዮሐ.፳፥፲፱-፳፤ማቴ.፳፰፥፲፮-፳፤ሉቃ.፳፬፥፴፮-፵፱) በማለት ገልጾታል፡፡

ይህ ሁሉ ሲሆን ግን ዲዲሞስ የተባለው ቶማስ አብሯቸው አልነበረምና የሆነውን ቢነግሩት አላምንም አለ፡፡ ይህንንም ወንጌላውያኑ ሲገልጹት “… ጌታችንን አየነው” አሉት፡፡ እርሱ ግን “የችንካሩን ምልክት በእጁ ካላየሁ፤ ጣቱንም ወደተቸነከረበት ካልጨመርሁ፤ እጄንም ወደ ጎኑ ካላስገባሁ አላምንም” አላቸው፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፬-፳፭)፡፡

ከስምንት ቀን በኋላም ሐዋርያት፣ ካላየሁ አላምን ያለው ቶማስን ጨምሮ በአንድነት ተሰብስበው ባሉበት በሩ እንደተዘጋ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጥቶ በመካከላቸውም ቆመ፡፡ እንዲህም አላቸው፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን”፡፡ ከዚህም በኋላ ቶማስን “ጣትህን ወዲህ አምጣና እጆቼን እይ፤ እጅህንም አምጣና ወደ ጎኔ አግባ፤ እመን እንጂ ተጠራጣሪ አትሁን” አለው፡፡ ቶማስም ”ጌታዬ አምላኬም” ብሎ መለሰ፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ስለአየኸኝ አመንህን? ብፁዓንስ ሳያዩ የሚያምኑ ናቸው” አለው፡፡ (ዮሐ.፳፥፳፮-፳፱)፡፡

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን ዕለት ዳግም ትንሣኤ ብላ ሰይማ ሥርዓቱንም እንደ ትንሣኤው ትፈጽማለች፣ በድምቀት ታከብራለች፡፡

በዕለቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚነበቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፡-

  • በገባሬ ሰናይ ዲያቆን፡- (፩ቆሮ.፲፭፥፩-፳)
  • በንፍቅ ዲያቆን፡- (፩ዮሐ.፩፥፩- ፍጻሜው)
  • በንፍቅ ቄስ፡- (ሐዋ.፳፫፥፩-፲)
  • ወንጌል፡- (ዮሐ.፳፲፱-ፍጻሜው)
  • ቅዳሴ፡- የዲዮስቆሮስ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *