ጽዮን ማርያም
“እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታልና፥ ማደሪያውም ትሆነው ዘንድ ወድዶአታልና፥ ይህች ለዘለዓለም ማረፊያዬ ናት መርጫታለሁና በዚህች አድራለሁ።” (መዝ. ፻፴፩፥፲፫-፲፬) እንዲል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በመዝሙሩ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማናዊት የእግዚአብሔር ማደሪያ የሆነችውን የእናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዓመታዊ በዓል ኅዳር ፳፩ ቀን በድምቀት ታከብራለች፡፡
“ጽዮን” ማለት “አምባ፣ መጠጊያ” ማለት ነው፡፡ “ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፤ በውስጥዋም ሰው ተወለደ” (መዝ. ፹፮፥፭) በማለት መዝሙረኛው ዳዊት እንደተናገረ አዳምና ልጆቹ በበደል ምክንያት ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ከተፈረደባቸው የሲዖል እሥራት ነጻ ይወጡ ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ ከዳዊት ዘር በተገኘችው ቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፡፡ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ማኅፀኗን ዙፋን አድርጎ ተወለደ፡፡ እኛም ኦርቶዶክሳውያን የእግዚአብሔር ማደሪያ፣ አምባ መጠጊያ የሆነችውን ድንግል ማርያምን የድኅነታችን መሠረት ናትና እናከብራታለን፣ እናመሰግናታለን፣ ከፍ ከፍም እናደርጋታለን፣ በዓሏንም እናከብራለን፡፡
ታቦተ ጽዮን በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትመሰላለች፡፡ ኅዳር ፳፩ ቀን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ በዓል በተለየ መልኩ የምናከብርበት ምክንያት በርካታ ቢሆኑም በዋነኛነት ታቦተ ጽዮን በፍልስጤማውያን ተማርካ በነበረበት ወቅት ዳጎን የተባለውን ጣኦት የሰባበረችበትና ልዩ ልዩ ተአምራት የፈጸመችበትን መሠረት አድርገን ነው፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ ከእግዚአብሔር በታዘዘው መሠረት ሁለት ጽላት ቀርጾ፣ የእንጨት ታቦትንም ሠርቶ ወደ ተራራ ወጣ፤ “ከማይነቅዝ እንጨትም ታቦትን ሠራሁ፤ እንደ ፊተኞቹም ሁለት የድንጋይ ጽላት ቀረጽሁ፤ ወደ ተራራም ወጣሁ፤ ሁለቱም ጽላት በእጄ ነበሩ፤ እግዚአብሔርም በተራራው ላይ በእሳት መካከል የተናገራችሁን ዐሥርቱን ቃላት ቀድሞ ተጽፈው እንደነበረ በጽላቱ ላይ ጻፈ፤ እግዚአብሔርም እነርሱን ለእኔ ሰጠኝ፡፡” (ዘዳ. ፲፥፩-፬) በማለት እንደተናገረው የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው ወደ ምድረ ርስት ተጉዘዋል፡፡
ወደ ትርጓሜው ስንመጣ ታቦተ ጽዮን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም ምሳሌ ስትሆን፣ በውስጡዋ የያዘችው የሕጉ ጽላት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ታቦቷ ከማይነቅዝ እንጨት መሠራቷ የጌታን እናት ንጽሕናን የሚያመለክት ሲሆን በውጪም በውስጧም በጥሩ ወርቅ መለበጡዋ የቅድስናዋና ድንግል በሕሊና ወድንግል በሥጋ መሆኗን የሚያስረዳን ነው፡፡ እስራኤላውያንም በፊታቸው ታቦተ ጽዮንን ይዘው የሚገዳደሯቸውን ሁሉ ድል ይነሡ ነበር፡፡
ፍልስጤማውያን ለጦርነት በእስራኤላውያን ተነሡ፤ በአንድነትም ተሰብስበው እስራኤላውያንን ወጉአቸው፣ እስራኤላውያን ያለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ተሰልፈዋልና በፍልስጤማውን ድል ተነሡ፡፡ የእስራኤል ሽማግሌዎችም “ዛሬ እግዚአብሔር በፍልስጤማውያን ፊት ስለ ምን ጣለን? በፊታችን እንድትሄድ ከጠላቶቻችንም እንድታድነን የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ከሴሎ እናምጣ” አሉ፡፡ ነገር ግን ቀድሞ እስራኤላውያን በድለዋልና ለፍልስጤማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ ታቦተ ጽዮንም ተማረከች፡፡ (፩ኛ ሳሙ. ፬፥ ፩-፲፩) ፍልስጤማውያን እግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑ ታቦት ወስደው ወደ ዳጎን ቤት አስገብተው ከዳጎን አጠገብ አኖሩ፡፡ በነጋም ጊዜ ዳጎን በእግዚአብሔር ፊት በግንባሩ ወድቆ አግኝተውታል፡፡
በሆነው ነገር ግር ቢሰኙም መልሰው ዳጎኑን አንስተው በስፍራው አቁመው በሩንም ዘግተው ሄዱ፡፡ በነጋም ጊዜ ግን ሲገቡ ዳጎን በግንባሩ ወድቆ ራሱ እና ሁለቱ እጆቹ ተቆርጠው ወድቀው አገኙአቸው፡፡ የእግዚአብሔርም እጅ በአዛጦን ሰዎች ላይ ከበደ፤ የአውራጃዎቿ ሰዎችም በእባጭ በሽታ ተመቱ አይጦችም በከተሞቻቸው ፈሰሱ፤ በከተማውም ላይ ታላቅ መቅሰፍት ሆነ፡፡ የቃል ኪዳኑ ታቦትም ጠንክራብናለች በማለት ከከተማቸው አውጥተው ወደ አስቀሎና ላኳት፤ የአስቀሎናም ሰዎች እጅግ ታወኩ፡፡ “እኛንና ሕዝባችንን ልታስገድሉን የእስራኤልን አምላክ ታቦት ለምን አመጣችሁብን?” ብለው ሰደዱአት፡፡ የእግዚአብሔርም ታቦት በፍልስጤማውያን ዘንድ ለሰባት ወር ቆየች፡፡ ምድራቸውም አይጦችን አወጣች፡፡ ከሕዝቡም ብዙዎች ተቀሰፉ፡፡ በመጨረሻም ከከተማቸው አውጥተው በኮረብታው ላይ ወደ አሚናዳብ ቤት ወሰዷት፤ በዚያም ለሃያ ዓመታት ቆየች፡፡
ከሃያ ዓመት በኋላም እግዚአብሔር ለዳዊት ፍልስጤማውያንን በእጁ አሳልፎ ሰጠው ድልም አደረጋቸው፡፡ “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦት” እንዲል ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የእግዚአብሔር ታቦትን ይዘው በእልልታና በዝማሬ በክብር ወደ እስራኤል ተመለሰች፡፡ ዳዊትም በተከላት ድንኳን ውስጥ አኖራት፡፡
ከዚህ ታሪክ በተጨማሪ የኅዳር ጽዮን በዓል የሚከበርበት ምክንያት፡-
፩. ነቢዩ ዘካርያስ ጽዮንን በተቅዋመ ማኅቶት አምሳል ያየበት፣
፪. ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ይዞ አክሱም የገባበት፣
፫. በዮዲት ጉዲት ዘመን በዝዋይ ደሴት ቆይታ ሰላም ሲሆን ተመልሳ አክሱም የገባችበት፣
፬. አብርሀ እና አጽብሐ በአክሱም ከተማ ከ፫፻፴፫-፫፻፴፱ ዓ.ም ቤተ መቅደሱን ሠርተው ቅዳሴ ቤቱን ያከበሩበት ዕለት ስለሆነ ኅዳር ፳፩ ቀን ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በዓሉን በድምቀት ታከብራለች፡፡ (መድብለ ታሪክ፤ ገጽ ፻፶፪)፡፡
በታቦተ ጽዮን ከተመሰለችው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡