ኒቆዲሞስ

ቤተ ክርስቲያናችን ልጆቿ በምድራዊው ሐሳብ እና ውጣ ውረድ ተጠልፈን እንዳንወድቅ የዲያብሎስን ወጥመድ ሰባብረን  ሰማያዊውን እያሰብን እንኖር ዘንድ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማትን ሠርታለች፡፡ ከእነዚህ አጽዋማት አንዱና ዋነኛው ደግሞ የዐቢይ ጾም ነው፡፡ ዐቢይ ጾም የኀምሳ አምስት ቀን ጾም ሲሆን፣ በውስጡም ስምንት ሳምንታት አሉት፡፡ እነዚህ ስምንት ሳምንታት ሁሉም የየራሳቸው መጠሪያ ስም ሲኖራቸው ሰባተኛው ሳምንት ኒቆዲሞስ በመባል ይታወቃል፡፡ (ዮሐ. ፫፤፩)

ኒቆዲሞስ ከፈሪሳውያን ወገን ሲሆን የእስራኤል መምህርና የአይሁድ ሸንጎ አባል ነበር፡፡ የስሙ ትርጓሜም “የሕዝብ ገዢ” እንደ ማለት ሲሆን፣ በትውፊት እንደሚታወቀው ኒቆዲሞስ በአይሁድ ላይ አለቃ ከመሆኑ በተጨማሪ እጅግ ባለጸጋም ነበር፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፋሲካ በዓል በኢየሩሳሌም ሳለ ያደረገውን ተአምራት አይተው ብዙዎች አምነውበት ነበር፡፡ ኒቆዲሞስም ከእነዚህ ምልክትን አይተው ካመኑ አማኞች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ (ዮሐ. ፪፥፳፫)፡፡ ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ኢየሱስ ሄዶ “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” እንዳለውም ተጽፏል፡፡ (ዮሐ.፫፡፪)፡፡

ኒቆዲሞስ በሌሊት ወደ ጌታ መምጣቱ (ዮሐ. ፩-)

ኒቆዲሞስ በመጀመሪያ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የመጣው በቀን ሳይሆን በሌሊት ነበር፡፡ ለዚህም የቤተ ክርሰቲያን አባቶች በዋናነት ሁለት ምክንያቶችን ያስቀምጣሉ፡፡ የመጀመሪያው የአይሁድ መምህር ሆኖ ሳለ በቀን በሕዝብ ፊት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መማር ስላፈረ ነው የሚል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አይሁድ “ከእኛ ወገን በክርስቶስ ያመነ ቢኖር ከምኩራብ ይሰደድ” የሚል አዋጅ አውጀው ነበርና ያንን ፈርቶ ነው ይላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ ፍራቻዎች ኒቆዲሞስን ወደ ክርስቶስ ከመምጣት አላገዱትም፡፡

ኒቆዲሞስ በርቀት በአደባባይ ድንቅ ተአምራትን ሲያደርግ ያየውን ኢየሱስ ክርስቶስን ቀርቦ መጠየቅ መማር ፈልጓል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረጋቸው ተአምራት የተረዳው ነገር ቢኖርም ቀርቦ ደግሞ ከእርሱ ከራሱ ስለማንነቱ መስማት ፈልጓል፡፡ ወደ ክርስቶስም ቀርቦ “መምህር ሆይ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከሆነ በቀር አንተ የምታደርጋቸውን እነዚህን ምልክቶች ሊያደርግ የሚችል የለምና መምህር ሆነህ ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደመጣህ እናውቃለን” አለው፡፡ (ዮሐ.፫፥፪)

ኒቆዲሞስ መጀመሪያ ወደ ክርስቶስ ሲመጣ ልክ እንደ ናትናኤል “መምህር ሆይ አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ” (ዮሐ.፩፥፶) ብሎ አምላክነቱን አምኖና መስክሮ አልነበረም፡፡ በኒቆዲሞስ ዕይታ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ተልኮ የመጣ መምህር መሰለው እንጂ አምላክነቱን አልተረዳም ነበር፡፡ የክርስቶስ አምላክነት እና የዓለም መድኃኒትነት ገና አልተገለጠለትም፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ስላወቀ ለኒቆዲሞስ የሚድንበትን እና ስለ እርሱ ማንነት የሚያውቅበትን ትምህርት አስተምሮታል(ዮሐ.፫፥፲፫)፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለኒቆዲሞስ ያስተማረውን ሲያብራራ “ሰው ከውኃና ከመንፈስ ድጋሚ ካልተወለደ በስተቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ማየት አይችልም፡፡ አንተ ገና ከእግዚአብሔር አልተወለድክምና ስለ እኔ ያለህ ዕውቀት መንፈሳዊ ሳይሆን ሥጋዊና ሰዋዊ ነው፤ ግን እልሃለሁ ማንም ሰው ከእግዚአብሔር ድጋሚ ካልተወለደ በስተቀር ክብሬን ማየት አይችልም ከመንግሥቴም ውጪ ነው” እንዳለ፡፡

ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ ነው፡፡ ፈሪሳውያን ደግሞ የአብርሃም ልጆች በመሆናቸው እጅግ የሚመኩና ዳግም ስለመወለድ ቢነገራቸው ፈጽመው የማይቀበሉ ነበሩ (ዮሐ. ፰፥፴፫)፡፡ ኒቆዲሞስ ግን ምንም እንኳን ከፈሪሳውያን ወገን ቢሆንም ክርስቶስ ዳግም መወለድ እንዳለበት ሲነግረውና የአይሁድ መምህር ሆኖ ሳለ ክርስቶስ እየነገረው ያለውን ነገር ባለመረዳቱ ምክንያት “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፣ ነገር ግን ይህን እንዴት አታውቅም?” ብሎ ሲገሥጸው በእምነት ተቀብሎ ተጨማሪ ጥያቄ ወደ መጠየቅ አለፈ እንጂ “የአብርሃም ዘር ሆኜ ሳለ እንዴት ድጋሚ መወለድ አለብህ ትለኛለህ?” አላለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአይሁድ መምህር ሆኖ በቀን በሰዎች ፊት ሊያደርገው ባይደፍርም የራሱን ኩራት (ትዕቢት) አሸንፎት ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጠይቆ ከመማር ወደ ኋላ አላለም፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህን ፍላጎቱ በማየቱ ታላቁን ምሥጢር አስተምሮታል፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑ የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ ሥልጣንን ሰጣቸው” (ዮሐ. ፩፥፲፪) ተብሎ እንደተጻፈ፡፡ ይህ ልጅነት እንዴት እንደሚሰጥ በግልጥ የተነገረውም ለኒቆዲሞስ ነው (ዮሐ፫፥፭)፡፡ ይህን ታላቅ ምሥጢር የገለጸለትም ስለ ትሕትናውና ራሱን ዝቅ ስለ ማድረጉ ነው፡፡

ሰው በማንነቱና ባለው ነገር ለራሱ ከፍተኛ ግምት ሲኖረው በትዕቢት ኃጢአት ይወድቃል፡፡ ሰው በሀብቱ፣ በሥልጣኑ፣ በዘሩ፣ በዘመዶቹ፣ በዕውቀቱ፣ በመልኩ …ወዘተ ምክንያት የትዕቢት ስሜት ሊያድርበት ይችላል፡፡ ክርስቲያን የሆነ ሰው ግን እነዚህ ሁሉ አላፊና ጠፊ መሆናቸውን ዐውቆ ትምክህቱን ሊያድኑት ከማይችሉ ምድራዊ ነገሮች ላይ አንሥቶ በእግዚአብሔር ላይ ማድረግ አለበት፡፡ (መዝ. ፻፵፭፥፫፤ መዝ ፫፥፰)፡፡ ከእነዚህም በተጨማሪ ትዕቢት በትሩፋት ሕይወት ላይ ያሉትን ሳይቀር ሊያጠምድ ይችላል፡፡ የሚጾመው ከማይጾመው፣ የሚጸልየው ከማይጸልየው፣ የሚያስቀድሰው ከማያስቀድሰው፣ የሚመጸውተው ከማይመጸውተው፣ ትሑቱ ከትዕቢተኛው፣ መነኩሴው ከሕጋዊው፣ ገዳማዊው ከዓለማዊው፣ ክርስቲያኑ ከአሕዛቡ … ወዘተ እሻላለሁ በሚል የትዕቢት ስሜት እንዳይወድቅ መጠንቀቅ አለበት፡፡

ጌታችን መድኃታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሳቸውን ለሚያመጻድቁና ባልንጀራቸውን ለሚንቁ እንዲህ ብሎ መለሰላቸው “ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ ነበር፡፡ ፈሪሳዊውም ቆመና እንዲህ ብሎ ጸለየ “አቤቱ እንደ ሌሎች ሰዎች እንደ ቀማኞችና እንደ ዐመፀኞች እንደ አመንዝሮችም ወይም እንደዚህ ቀራጭ ያላደረግከኝ አመሰግንሃለሁ፡፡ እኔ በየሳምንቱ ሁለት ቀን እጾማለሁ፣ ከማገኘውም ሁሉ ከዐሥር አንድ እሰጣለሁ፡፡” ቀራጩ ግን ራቅ ብሎ ቆመ፤ ዓይኖቹንም ወደ ላይ ወደ ሰማይ ሊያነሣ አልወደደም፤ ደረቱን እየመታ “አቤቱ እኔን ኃጢአተኛውን ይቅር በለኝ” አለ፡፡ እላችኋለሁ ከዚያኛው ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፡፡ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፤ ራሱንም የሚያዋርድ ይከብራልና፡፡” (ሉቃ.፲፰፥፲-፲፬)፡፡ ስለዚህ ትዕቢት ወደ ኃጢአት የማይቀይረው ምንም ትሩፋት እንደሌለ ማስተዋልና እርምጃችንን ሁሉ በጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ኒቆዲሞስ ባለ ሀብት፣ የአይሁድ መምህር እና አለቃ ሆኖ ሳለ በትዕቢት ሳይያዝ ራሱን በመንፈስ ድኃ አድርጎ ስለቀረበ “በመንፈስ ድኆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” በሚለው ቃል መሠረት መንግሥተ ሰማያትን ገንዘብ ማድረግ የሚችልበትን ትምህርት እንዲማር ሆኗል፤ ምሥጢሩንም ገልጾለታል፡፡ (ማቴ ፭፥፫)፡፡

ዳግም መወለድ ማለት ሥጋዊ፣ ምድራዊና ጊዜያዊ የሆነውን የድሮ ማንነታችንን ትተን መንፈሳዊ፣ ሰማያዊና ዘለዓለማዊ የሆነውን አዲስ ማንነት ገንዘብ ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህ አዲስ ማንነትም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ከመወለድ የሚገኝ ነው፡፡ ያጣነውንና የተወሰደብንን ጸጋ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅነት የምናገኘው በጥምቀት ነው፡፡ “ጌታችን ከመንፈስ ቅዱስ እንድንወለድ ያዘዘን ሥጋዊው ልደት በሥጋ የወለዱንን የእናት የአባታችንን ርስት ያወርሰናል እንጂ ሰማያዊውን ርስት ሊያወርሰን አይችልምና ነው፡፡ ሰማያዊውን ርስት ልንወርስ የምንችለው መንፈሳዊውን ልደት ስንወለድ ነው፡፡ “እንኪያስ እናንተ ልጆች ናችሁ እንጂ ባሮች አይደላችሁም፤ ልጆች ከሆናችሁም በኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ወራሾች ናችሁ፡፡” (ገላ. ፬፥፯) እንዲል፡፡ መንፈሳዊውን ልደት የምንወለድ ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ስለሆነ ዳግመኛ ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም በማለት አስተማረው፡፡

ጥምቀት ዳግመኛ ተወልደን ክርስቶስን የምንመስልበት ነው፡፡ “እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ” (፩ኛቆሮ. ፲፩፥፩) እንዳለ ሐዋርያው፡፡ ጌታችን መድኃነኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን ለኒቆዲሞስ ሲያብራራ “ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡” ብሎታል፡፡ (ዮሐ. ፫፥፮)

ኒቆዲሞስ በሌሊት ገስግሶ ወደ ጌታችን የመጣው በፊቱ ቀርቦም “መምህር ሆይ” ብሎ የእርሱን አላዋቂነት፣ የክርስቶስን ሁሉን አዋቂነት መሰከረ፡፡ ጌታችንም አመጣጡ ከልብ መሆኑን ዐውቆ ምሥጢረ ጥምቀትን (ዳግም ልደትን) ገለጸለት፡፡ ምሥጢሩም የኦሪት ምሁር ለነበረው ኒቆዲሞስ ለጆሮ የከበደ፣ ለመቀበል የሚቸግር ሆነበት፡፡ የከበደውን የሚያቀል፣ የጠበበውን የሚያሰፋ አምላክ ምሥጢሩ ለኒቆዲሞስ እንደ ከበደው ስላወቀ ቀለል አደረገለት፡፡ ዳግም ልደት ከእናት ማኅፀን ሳይሆን ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ እንደ ሆነ አብራራለት፡፡

ኒቆዲሞስም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረውን ትምህርት ተቀብሎ በሃይማኖት ጸንቶ፣ በምግባር ታንጾ ተከትሎታልና  ጌታችን በመስቀል ላይ ነፍሱን በገዛ ፈቃዱ አሳልፎ ከሰጠ በኋላ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥጋ በአዲስ መቃብር ከቀበሩት ሁለት ሰዎች ውስጥ አንዱ ኒቆዲሞስ ነው፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስም ይህንን ሲመሰክር “ቀድሞ ሌሊት ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሄዶ የነበረው ኒቆዲሞስም መጣ፤ ቀብተውም የሚቀብሩበትን መቶ ወቄት የከርቤና የሬት ቅልቅል ሽቶ አመጣ፡፡ እንደ አይሁድ አገናነዝ ሥርዓትም የጌታችን የኢየሱስምን ሥጋ ወስደው ከሽቱ ጋር በበፍታ ገነዙት፡፡” (ዮሐ. ፲፱፥፴፱-፵) እንዲል፡፡

ዮሴፍና ኒቆዲሞስ በዚህ ብቻ አላበቁም ጌታን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአዲስ መቃብር ቀበሩት፡፡ “በዚያም በተሰቀለበት ቦታ የአትክልት ስፍራ ነበር፤ በዚያ የአትክልት ስፍራ ውስጥም በውስጡ ሰው ያልተቀበረበት አዲስ መቃብር ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስንም በዚያ ቀበሩት” እንዲል፡፡

ከኒቆዲሞስ ምን እንማር?

ራስን ዝቅ ማድረግ

ብዙዎቻችን ባለን የኑሮ፣ የዕውቀት እና የሥልጣን ደረጃ ራሳችንን ከፍ ከፍ አድርገን የመማር ዐቅም ያጣን፤ ቁጭ ብሎ መማር ለደረጃችን የማይመጥን የሚመስለን ስንቶቻችን እንሆን? ኒቆዲሞስ ፈሪሳዊ፣ የአይሁድ አለቃ፣ መምህረ እስራኤል፣ ምሁረ ኦሪት ቢሆንም ሕዝብን ከመምራትና ከማስተማር ይልቅ ራሱን ዝቅ አድርጎ ከጌታ እግር ሥር ቁጭ ብሎ መማርን መረጠ፡፡

የጎደለንን ማወቅ

ቤተ ክርስቲያናችንና አገልግሎታችንን እየተፈታተነ ያለው ጎደሎዎቻችንን አለማወቃችን ነው፡፡ ኒቆዲሞስ ያለውን ሳይሆን ያጣውን፤ የሞላለትን ሳይሆን የጎደለውን ፍለጋ ወደ ክርስቶስ መጣ፡፡ ዕውቀት ብቻውን ምሉዕ አያደርግም፤ አለቅነትም ቢሆን ገደብ አለው፡፡ ኒቆዲሞስ ምሁረ ኦሪት እንጂ የሐዲስ ኪዳን መምህር አይደለም፤ መምህረ እስራኤል ዘሥጋ እንጂ መምህረ እስራኤል ዘነፍስ አይደለም፡፡ የሕይወቱን ክፍተት ሊሞላ የሚችል አንድ ክርስቶስ ብቻ ነውና ኒቆዲሞስ ጉድለቱን አምኖ ጎደሎውን ሊያስሞላ ወደ ክርስቶስ መጣ፡፡ “የሚጎድለኝ ምንድን ነው?” ብሎ ጠየቀ፡፡

ልቡናን ከፍ ማድረግ

ኒቆዲሞስ ይዞ የመጣው ሥጋዊ ሕዋሳቱን ነበር፡፡ ጌታችንም የኒቆዲሞስ አመጣጥ ለመልካም እንደ ሆነ ዐውቆ ለሥጋዊ ዕውቀት እጅግ የሚከብደውን ምሥጢረ ጥምቀትን ገለጸለት፡፡ “እውነት እውነት እልሃለሁ ዳግመኛ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም“ አለው፡፡ ነገር ግን ኒቆዲሞስ አልገባውም፡፡ እንዲህም ብሎ ጠየቀው፡- “ሰው ከሸመገለ በኋላ ዳግመኛ መወለድ እንደምን ይችላል? ዳግመኛ ይወለድ ዘንድ ወደ እናቱ ማኅፀን ተመልሶ መግባት ይችላልን?” አለ፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም መልሶ እንዲህ አለው፡- “እውነት እውነት እልሃለሁ፤ ዳግመኛ ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው ወደ እግዚአብሔር መንገሥት ሊገባ አይችልም፡፡ ከሥጋ የተወለደ ሥጋ ነውና፤ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና፡፡ ስለዚህ ዳግመኛ ልትወለዱ ይገባችኋል” በማለት አስረዳው፡፡

ኒቆዲሞስ መጀመሪያ ምሥጢሩን መረዳት አልተቻለውም ነበር፡፡ ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሥጢሩን ፍንትው አድርጎ ሲያብራራለት ልቡናው ምሥጢሩን ለመቀበል ተዘጋጀ፡፡ ምሥጢራትን ለመቀበል ልቡናውንም ከፍ ከፍ አደረገ፡፡ እኛም ሰማያዊው ምስጢር ይገለጥልን ዘንድ ከኒቆዲሞስ መማር ይገባናል፡፡

በሌሊት ለአገልግሎት መትጋት

እንደ ሌሊት ለመንፈሳዊ ሕሊና፣ ለተመስጦ የሚመች ጊዜ የለም፡፡ ቀን ለሥጋ ሲራወጥ የነበረ አካልና መንፈስ ሌሊቱን ለነፍስ በመገዛት ሥጋውን ማድከም አለበት፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኑን በቅዳሴ፤ ሌሊቱን ደግሞ በማኅሌት፣ በሰዓታት፣ በኪዳን እግዚአብሔርን ስታምሰግን የምታድረው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ሐዋርያቱን “ወደ ፈተና

እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ” ማለቱን ማስተዋል ይገባል፡፡ (ማቴ. ፳፮፥፵፩)፡፡ አሁንም ቤተ ክርስቲያን

እንደ ኒቆዲሞስ ለኪዳን፣ ለማኅሌት፣ ለጸሎት በሌሊት የሚገሰግስ ምእመንን ትፈልጋለች፡፡

 እስከ መጨረሻ መጽናት

ክርስትና ለጀመሩት ሳይሆን ለጨረሱት፤ ለወጠኑት ሳይሆን ለፈጸሙት የድል አክሊል የምታቀዳጅ ናት፡፡ የመሮጫው መም ጠበበን፤ ሩጫው ረዘመብን ብለው ከመስመሯ ለሚወጡ ዴማሶች ቦታ የላትም (፪ኛጢሞ. ፬፥፲)፡፡ ጌታችንን በመዋዕለ ስብከቱ ብዙ ሺሕ ሕዝብ ቢከተለውም እስከ መስቀሉ አብረውት የነበሩ ጥቂቶች ናቸው፡፡ ኒቆዲሞስ አንድ ጊዜ ከአምላኩ የረቀቀው ተገልጾለት፣ የራቀው ቀርቦለት በሚገባ ተምሯልና ክርስቶስ በፈቃዱ ነፍሱን ከሥጋው በለየበት ሰዓት ከአርማትያሱ ዮሴፍ ጋር ሆኖ የክርስቶስን ክቡር ሥጋ ከመስቀል አውርዶ፣ ገንዞ በሐዲስ መቃብር ለመቅበር ታድሏል፡፡

በዚህ የመከራ ሰዓት ከዮሐንስና ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ውጭ ማንም በሥፍራው አልነበረም፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ከመስቀሉ ሥር የተገኙት የቁርጥ ቀን ልጆች ዮሴፍና ኒቆዲሞስ ናቸው፡፡ ይህም ኒቆዲሞስ ፈተናውን ሁሉ ተቋቁሞ እስከ መጨረሻው ለመጽናቱ ምስክር ነው፡፡ በክርስትና ሕይወታችን በምቹ ጊዜ የምናገለግል፣ ፈተና ሲመጣ ግን አገልግሎታችንን ጥለን የምንሸሽ፣ ሰበብ አስባብ ፈልገን የምናፈገፍግ መሆን አይገባም፡፡ “እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል፡፡” እንደተባለ እስከ መጨረሻው መጽናት ይገባል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፬፫)

በወንጌልና በትውፊት ከሚታወቀው የኒቆዲሞስ ታሪክ የመንፈሳዊ ሕይወት ዕድገቱን በማስተዋል እኛም የክርስትና ጉዞአችን ምን እንደሚመስል መመልከት ይገባናል፡፡ ክርስትና ጉዞ ነው፤ ዕለት ዕለት በእምነት እየጠነከርን በትሩፋት እየበረታን እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ በጽናት መቆየት ያስፈልጋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *