በእንተ ዕርገት

መምህር በትረማርያም አበባው

ዕርገት ዐርገ ዐረገ፣ ወጣ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ወደ ላይ መውጣት ማለት ነው፡፡ “ነበልባሉም ከመሠዊያው ላይ ወደ ሰማይ በወጣ ጊዜ የእግዚአብሔርም መልአክ በመሠዊያው ነበልባል ውስጥ ዐረገ” (መሳ.፲፫፥፳) ከዚህ እንደምናየው ዐረገ ማለት ወደ ላይ ወጣ ማለት ነው፡፡ ይህ ቃላዊ ትርጓሜው ሲሆን ምሥጢራዊው ትርጓሜ ግን ዕርገት ማለት የሰው አምላክ መሆን ተብሎ ይተረጎማል፡፡ በዚህ አንጻር ርደት ማለት ደግሞ የአምላክ ሰው መሆን ተብሎ ይተረጎማል፡፡ “ጌታ ኢየሱስም ከእነርሱ ጋር ከተናገረ በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ” ይላል (ማር.፲፮፥፲፱)፡፡ በዚህ አነጋገር ደግሞ የቤዛነት ሥራውን ማጠናቀቁን ያሳየናል፡፡

የዕርገት ዓይነቶች

ስለ እግዚአብሔር በምንነጋገርበት ጊዜ ግን ዐረገ ማለት ወደ ላይ መውጣትን አያመለክትም፡፡ በተመሳሳይ ወረደ ማለትም ወደ ታች መውረዱን አያመለክትም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በሁሉ ቦታ ያለ ስለሆነ ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት ወረደ ብለን ስለ እግዚአብሔር ስንናገር ሰው ሆነ ወይም ተዋሐደ ብለን እንተረጉመዋለን፡፡ “አምላክ በእልልታ፣ እግዚአብሔር በመለከት ዐረገ” (መዝ.፵፯፥፭) እንዲል፡፡

ዕርገተ ክርስቶስ በሁለት ይከፈላል፡፡ እነዚህም የርኅቀት ዕርገት እና የርቀት ዕርገት ናቸው፡፡

የርኅቀት ዕርገት

በሉቃስ ወንጌል ትርጓሜ ላይ “ወእምዝ አውፅኦሙ አፍኣ እስከ ቢታንያ ወአንሥአ እደዊሁ ወአንበረ ላዕሌሆሙ ወባረኮሙ ወእንዘ ይባርኮሙ ተረኀቆሙ ወዐርገ ሰማየ፤ እስከ ቢታንያ አወጣቸው ከአጻዌ ኆኅት እስከ ፓትርያርክነት ያለውን ማዕረግ በአንብሮተ ዕድ ሾማቸው ባርኳቸው እየራቃቸው ወደ ሰማይ ዐረገ የርቀት ያይደለ የርኅቀት” ይላል (ሉቃ.፳፬፥፶)፡፡ ርኅቀት ማለት መራቅ ማለት ነው፡፡ ክርስቶስ ከትንሣኤ በኋላ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ ዐርጓል፡፡  “ይህንም ከተናገረ በኋላ እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው፤ እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኩር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ እነሆ…” (ሐዋ. ፩፥፱-፲) እያለ ከእነርሱ እየራቀ እየራቀ ሄዶ ተሰወራቸው፤ ለዚያም ነው ይህንን ዕርገት ኢትየጵያውያን ሊቃውንት የርኅቀት ዕርገት ብለው የሚጠሩት፡፡

የርቀት ዕርገት

ይህንን ዕርገት በተመለከተ በሃይማኖተ አበው ትርጓሜ (ሃይ. አበ.፲፯፥፱) ላይ “ወተንሥአ እሙታን አመ ሣልስት ዕለት፤ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ፤ በከመ ጽሑፍ በከበሩ መጻሕፍት እንደተጻፈ እንደ ተነገረ ዐርገ በስብሐት ውስተ ሰማያት፤ በቅዳሴ መላእክት በክብር በብርሃን በሥልጣን ዐረገ” ካለ በኋላ የሥጋ ዕርገት በማሕፀን የቃል ዕርገት በአርባ ቀን ይላል፡፡ የቃል ዕርገት በ፵ ቀን ያለው ከላይ ያየነው የርኅቀት ዕርገትን ሲሆን ከትንሣኤ በኋላ በአርባ ቀን ማረጉን የሚያሳውቅ ነው፡፡ የሥጋ ዕርገት በማሕፀን ያለው ቃል ሥጋ ሲሆን የቃል ገንዘብ ማለትም ረቂቅነት፣ ምሉእነት፣ ሁሉን ቻይነት እና የመሳሰሉት የሥጋ ገንዘብ መሆናቸውን እና የሥጋ ገንዘብ የሆኑት ደግሞ የቃል ገንዘብ መሆናቸውን የሚያመለክት ቃል ነው፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የቃል ርደት የሥጋ ዕርገት ምክንያት ናት የምንለውም ይህንን በማኅፀን የተደረገውን ረቂቅ ዕርገት ለማመልከት ነው፡፡ ሥጋ ቃልን በመዋሐዱ ግዘፉን ሳይለቅ የቃልን ረቂቅነት ገንዘቡ አድርጓልና ይህንን ምሥጢር ሊቃውንቱ የርቀት ዕርገት ይሉታል፡፡ ይኸውም ሥጋ በማሕፀን እያለ ከቃል ጋር በመዋሐዱ በኪሩቤል ጀርባ ተቀመጠ ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በአንቀጸ ብርሃን “ወሶበ ርእዩ እግዚኦሙ ዘአስተጋብአ ኵሎ ፍጥረታተ እንዘ ይነብር ውስተ ሕፅንኪ ወዘይሴሲ ለኵሉ ፍጥረት ይጠቡ ሐሊበኪ ከመ ሕፃን ኀሠሥዎ ውስተ አርያም ወበህየ ረከብዎ ምስለ አቡሁ ወመንፈስ ቅዱስ ከመ ትካት” የሚለው ይህንን ነው፡፡ ቃልም በኪሩቤል ጀርባ ሳለ ምልአቱን ሳይለቅ በድንግል ማሕፀን ተወሰነ፡፡ መጋቢት ፳፱ ቀን ጌታ ሲፀነስ የቃል  ገንዘብ ለሥጋ፤ የሥጋ ገንዘብ የቃል የሆነበትን ቀን ቀድሞ ፍጡር የነበረ ሥጋ ፈጣሪ ሆኗልና ዐረገ ይባላል፡፡ የሥጋ ዕርገት በማሕፀን የተባለውም ሥጋ አምላክ መሆኑን ለማመልከት ነው፡፡ የቃል ዕርገት በ፵ ቀን መባሉም ቃል ሥጋን ገንዘብ በማድረጉ ከሐዋርያት ሳይለይ በሥጋ ወደ ሰማይ በማረጉ ነው፡፡

ለምን በ፵ ቀን ዐረገ?

በ፵ ቀን ማረጉ በአራተኛው ክፍለ ዘመን ሰው እንደሆነ ለማጠየቅ ነው፡፡ አራተኛው ክፍል ዘመን የተባለውም ዘመነ ካህናት ነው፡፡ የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ዘመነ አበው፣ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን ዘመነ መሳፍንት፣ ሦስተኛው ክፍለ ዘመን ዘመነ ነገሥት ሲሆን አራተኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ ክርስቶስ ሰው የሆነበት ዘመነ ካህናት ነው፡፡ ሌላው አዳም በተፈጠረ በ፵ ቀን ገነት ገብቷልና የዚያ ምሳሌ፡፡ ማረጉም ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ነው፡፡ ትንቢቱም “ዐርገ እግዚአብሔር በይባቤ ወእግዚእነ በቃለ ቀርን” የሚለው ነው፡፡ (መዝ.፵፯፣፭) ምሳሌውም በመቅድመ ወንጌል እንደተገለጠው “ወዐርገ ውስተ ሰማያት ከመ ያለቡ ዕርገተ ጻድቃን ንጹሓን እምድኅረ ትንሣኤ ኀበ መንግሥት ዘድልው ሎሙ፤ ከትንሣኤ በኋላ በጣዕም በሥን በመዓዛ በብርሃን በክብር ተዘጋጅቶላቸው ወደ አለ ወደ መንግሥተ ሰማያት ጻድቃን መግባታቸውን ያስረዳ ዘንድ ወደ ሰማይ ዐረገ” ይላል፡፡ ጻድቃን ሁሉ በመንግሥተ ሰማያት ጸጋ እየተጨመረላቸው ለዘለዓለም የሚኖሩ መሆኑን ያስረዳል፡፡ መጽሐፈ መነኮሳት ወይትዌሰክ ሥን በዲበ ሥን እንዲል በክብር ላይ ክብር እየተጨመራቸው በማያቋርጥ ጸጋ እንደሚኖሩ የሚያስረግጥ ነው፡፡ ክርስቶስ ከትንሣኤ በኋላ በአርባኛው ቀን ወደ ሰማይ እንዳረገ ሁሉ ጻድቃንም በዳግም ምጽአት ጊዜ ከሞት ተነሥተው ወደ መንግሥተ ሰማያት ገብተው ለዘለዓለም እንደሚኖሩ ያስረዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

 

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *