ደብረ ዘይት

በእንዳለ ደምስስ

በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት ደብረ ዘይት ተብሎ ይጠራል፡፡ ደብረ ዘይት በኢየሩሳሌም የሚገኝና የወይራ ዛፍ በብዛት ያለበት ተራራ ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን እያስተማረ፣ ድውያንን እየፈወሰ፣ የተራቡትን እየመገበ፣ ለሚሹት እየተገለጠ ውሎ ማታ ማታ ግን ወደ ደብረ ዘይት ተራራ እየወጣ ይጸልይ ነበር፡፡ “ከዚያም በኋላ ሕዝቡን አሰናብቶ ሊጸልይ ብቻውን ወደ ተራራ ወጣ” እንዲል፡፡ (ማቴ. ፲፬፥፳፫)፤ በሆሣዕና ዕለት ከደብረ ዘይት ተነሥቶ ወደ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ገብቷል፤ ከደብረ ዘይት ግርጌ በጌቴ ሴማኒ ጸሎት አድርጓል፤ የአይሁድ ጭፍሮችም መጥተው የያዙት ከዚሁ ደብረ ዘይት ተራራ ነው፡፡ (ማቴ.  ፳፮፥፴፮) በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ሆኖ ስለ ዓለም ፍጻሜና ምልክቱ አስተምሯል፤ (ማር. ፲፫፥፫) በደብረ ዘይት ተራራ ወደ ሰማይ ዐርጓል፤ (ሉቃ. ፳፬፥፶፩-፶፪) በትንቢት እንደተነገረለትም በመጨረሻው ሰዓት በዓለም ፍጻሜ ለፍርድ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ይገለጣል።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፤ አምላካችን ዝም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነዳል፣ በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ” (መዝ. ፵፱፥፫) እንዲል በዚህ የደብረ ዘይት ሳምንት ስለ ዳግም ምጽአት ምልክቶች፣ ስለ ምጽአት እና ተስፋው ይታሰባል። በተለይም በወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ በምዕራፍ ፳፬ በስፋት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ለመሆኑ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ዓለም ከመኖር ወደ አለመኖር ለማሳለፍ ከመምጣቱ በፊት የሚታዩ ምልክቶች ምን ምን ናቸው?

የምጽአት ምልክቶች

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቤተ መቅደስ ወጥቶ በሄደ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንፃ አሠራር ካሳዩት በኋላ “ይህን ሁሉ ታያላችሁን? ድንጋይ በድንፈጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህን የነገራቸውን ነገር ሰምተው ብቻ ዝም ብለው አላለፉትም፡፡ “ንገረን ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውታል፡፡ (ማቴ ፬፥፩-፪)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱ አብረውት እየዋሉ፣ አብረውት እያደሩ የቃሉን ትምህርት፣ የእጁን ተአምራት እየሰሙ እና እያዩ ምሥጢር ሳይከፈልባቸው ቆይተዋልና በቅድሚያ ከሚመጣው ሁሉ ይጠነቀቁ ዘንድ እንዲህ አላቸው፡፡ “የሚያስታችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉና ብዙዎችንም ያስታሉ፡፡” ሲል በተማሩት ጸንተው ይኖሩ ዘንድ አሳስቧቸዋል፡፡ ይህ ማስጠንቀቂያ ብዙዎች ክርስቶስን ተቃውመው እንደሚነሡና በጠላትነት እንደሚነሡባቸው፤ ነገረ ግን የሚመጣባቸውን ሁሉ ተቋቁመው በሃይማኖታቸው ጸንተው እንዲኖሩ ያጸናቸው ዘንድ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የነገረ ምጽአቱን ምልክቶች ሲናገር ከላይ የገለጸውን ብቻ ብሎ አላበቃም፡- “ጦርነትን፣ የጦርነትንም ወሬ ትሰሙ ዘንድ አላችሁ፤ ይህ ሊሆን ግድ ነውና ተጠንቀቁ፤ አትደንግጡ፣ ነገር ግን ፍጻሜው ገና ነው፡፡” ሲል ከሚያስቡት በላይ ከባድ ጊዜ እንደሚመጣ ነግሯቸዋል፡፡ ምልክቶቹንም ሲዘረዝር “ሕዝብ በሕዝብ ላይ፣ መንግሥትም በመንገሥት ላይ ይነሣሉ፤ በየሀገሩም ረኃብ፣ ቸነፈርም የምድር መናወጥም ይሆናል፡፡ እነዚህም የምጥ ጣር መጀመሪያ ናቸው፡፡” ብሏቸዋል፡፡

በደቀ መዛሙርቱም ላይ ስለሚደርሰው መከራ ሲገልጽ፡-”ያን ጊዜም ለመከራ አሳልፈው ይሰጡአችኋልም፣ ይገድሏችኋልም፤ ስለ ስሜም በሰው ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፡፡” በማለት የመከራውን አስከፊነት አስረድቷቸዋል፡፡ በወቅቱ ስለሚሆነውና በሰዎች ዘንድ ፍቅር ጠፍቶ አንዱ አንዱን አሳልፎ እንደሚሰጥ ሲገልጽም “ያን ጊዜም ብዙዎች ሃይማኖታቸውን ይለውጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ እርስ በርሳቸውም ይጣላሉ፡፡” ብሏል፡፡ (ማቴ.፳፬፥፱-፲)

ዛሬ በዘመናችን እንደምናየውና እንደምንሰማው ብዙዎች ራሳቸውን “ነቢይ” እያሉ በመጥራት እንክርዳድ የሆነውን የሐሰት ትምህርታቸውን በዓለም ላይ ይዘራሉ፡፡ ይህንንም በተመለከተ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አድሮ “ብዙዎች ሐሰተኞች ነቢያትም ይመጣሉ፤ ብዙዎችንም ያስታሉ፤ ከዐመፅም የተነሣ ፍቅር ከብዙዎች ዘንድ ትጠፋለች፡፡ እስከ መጨረሻው የሚታገሥ ግን እርሱ ይድናል፡፡ በአሕዛብ ምስክር ሊሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፤ ያን ጊዜም ፍጻሜ ይደርሳል፡፡” ሲል በዘመኑ ስለሚሆነው ነገር በስፋት ገልጾላቸዋል፡፡ ይህም እኛ በዚህ ዘመን ያለን ክርስቲያኖችም ልናስተውለው፣ ዘወትር ከሚመጣው ክፉ ነገር ሁሉ እንጠበቅ ዘንድ በሃይማኖት በመጽናት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በመልካም ምግባራት ዘመኑን ልንዋጅ ይገባል፡፡

ይህ መቼ እንደሚሆን ሲገልጽም “እንግዲህ በነቢዩ በዳንኤል የተባለውን የመፍረሱን የርኵሰት ምልክት በተቀደሰ ቦታ ቆሞ ባያችሁት ጊዜ አንባቢው ያስተውል” ሲል ጊዜውን ይነግረናል፡፡ ይህም በነቢዩ ዳንኤል የተነገረው ትንቢት በቤተ መቅደስ የጥጦስ ጣዖት የታየ እንደሆነ ፍጻሜው እንደ ደረሰ ይጠቁመናል፡፡ (ማቴዎስ አንድምታ)፡፡ የጊዜውን አስከፊነት ሲያመለክትም ያን ጊዜም በይሁዳ ያሉ ወደ ተራሮች እንዲሸሹ፣ በሰገነትም ያሉ በቤት የሚገኘውን እንዳያነሡ፣ በእርሻም ያሉ ያስቀመጡትን ልብስ ለመውሰድ ወደ ኋላ እንዳይመለሱ ይነግረናል፡፡ በዚያ ወራት ለፀነሱና ለሚያጠቡ ወዮላቸው ማለቱ፡- የፀነሡት ከመንገድ ይወልዳሉ፤ የወለዱትም ወተት፣ ፍትፍት አምጡ ብለው ያስቸግሯቸዋልና ይጨነቃሉ፤ እንዲሁም ብዙዎች በዚያ ወራት ኃጢአትን በሐልዮ ፀንሰው ፣ በነቢብ ወልደው፣ በገቢር ለሚያሳድጉ ሰዎች ወዮላቸው መከራ ነፍስ አለባቸው ሲል ነው፡፡ ሽሽታችንም በክረምት ወይም በሰንበት እንዳይሆን ልንጸልይ እንደሚገባ ያስጠነቅቀናል፡፡ በክረምት ላዩ ዝናብ፣ ታቹ ውኃ ነውና መሻገር እንደማይቻል ያሳየናል፡፡ ስለ ተመረጡት ብሎ እግዚአብሔር ቀኖቹን ባያሳጥራቸው ኖሮ እጅግ አስከፊ እንደሆነም ያመለክተናል፡፡

ሐሰተኞች ነቢያት፤ ክርስቶስ በዚህ አለ እያሉ የሚያስቱ እንደሚነሡ፣ የተመረጡትን እስኪያስቱ ድረስ ታላላቅ ተአምራትን እስከማድረስ እንደሚደርሱ ይነግረናል፡፡ ከእነዚህም ምልክቶች በኋላ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መላእክቱን አስከትሎ በምድርና በምድር ያለውን ሁሉ ከመኖር ወደ አለመኖር ያሳልፍ ዘንድ ይመጣል፡፡ ይህንንም ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ሲገልጽ “ከእነዚያም ቀኖች መከራ በኋላ ወዲያውኑ ፀሐይ ይጨልማል፣ ጨረቃም ብርሃኑን አይሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማያት ኃይል ይናወጣል፡፡ በዚያም ወራት የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል፡፡ ያን ጊዜም የምድር አሕዛብ ሁሉ ያለቅሳሉ፤ የሰው ልጅንም በኃይልና በብዙ ክብር በሰማይ ደመና ሲመጣ ያዩታል፡፡ መላእክቱንም ከታላቅ የመለከት ድምፅ ጋር ይልካቸዋል፡፡” (ማቴ. ፳፬፥፳፱-፴፩) ይህ ሁሉ የምጥ ጣር መጀመሪያ ነውና ነገረ ምጽአቱ እንደቀረበና በደጃፍ እንዳለ ልናስተውል ይገባል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በዐቢይ ጾም አምስተኛ ሳምንት “ደብረ ዘይት” ብላ ነገረ ምጽአቱን ታስባለች፡፡ ምእመናንም ነገረ ምጽአትን አስበው ከክፋት ተጠብቀውና መልካም ምግባራትን እየፈጸሙ ንስሓ ገብተው የጌታችን የመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ተቀብለው ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ ታስተምራለች፡፡

የዕለተ ሰንበት መዝሙር (ከጾመ ድጓ)

“እንዘ ይነብር እግዚእነ ውስተ ደብረ ዘይት ወይቤሎሙ ለአርዳኢሁ ዑቁኬ ኢያስሕቱክሙ ወንበሩ ድልዋኒክሙ፤ ብዙኃን ይመጽኡ በስምየ እንዘ ይብሉ አነ ውእቱ ክርስቶስ ወዘአዝለፈ ትዕግሥቶ ውእቱ ይድኅን፤ ወአመ ምጽአቱሰ ለወልደ እጓለ እመሕያው ይትከወስ ኲሉ ኃይለ ሰማያት ወምድር፤ አሜሃ ይበክዩ ኲሎሙ ኃጥአነ ምድር፡ ወይወርድ እግዚእነ እምሰማይ ዲበ ምድር በትእዛዙ ወበቃሉ ወበ አዕላፍ መላእክቲሁ በንፍሐተ ቀርን ዘእም ኀበ እግዚአብሔር ይምሐረነ አብ በይእቲ ሰዓት እሞተ ኃጢአት እስመ ገባሬ ሕይወት ውእቱ እግዚኣ ለሰንበት፡፡”

ትርጉም:- ጌታችን በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጦ ሳለ ለደቀ መዛሙርቱ ማንም እንዳያስታችሁ ተጠንቀቁ፤ተዘጋጅታችሁም ኑሩ ብዙዎች እኔ ክርስቶስ ነኝ እያሉ በስሜ ይመጣሉ፤ እስከ መጨረሻው የጸና እርሱ ይድናል፡፡ የሰው ልጅ በሚመጣበት ጊዜ የሰማያትና የምድርኃይላት ሁሉ ይናወጣሉ።ያን ጊዜ በምድር ኃጢአት ያደረጉ ሁሉ ያለቅሳሉ አላቸው፤ ጌታችንም ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ በመለከት ድምፅ ከአእላፍ መላእክት ጋር በክበበ ትስብዕት በግርማ መለኮቱ ከሰማይ ወደ ምድር ይወርደል፡፡ በዚች ዕለትም ከሞተ ኃጢአት አብ  ይማረን የሕይወት ባለቤት የሰንበትም ጌታ ነውና፡፡

ምንባባት መልእክታት

(፩ኛተሰ. ÷፲፫ፍጻ.)

“ወንድሞቻችን ሆይ÷ ስለ ሞቱ ሰዎች÷ ተስፋ እንደሌላቸው ሰዎች እንዳታዝኑ ልታውቁ እንወዳለን፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ እንደ ተነሣ ካመንን እንዲሁ እግዚአብሔር ሙታንን በኢየሱስ ያስነሣቸዋል፤ ከእርሱም ጋር ያመጣቸዋል፡፡ …”

  ጴጥ. ÷፯-፲፬

“አሁንም ሰማይና ምድር በዚያ ቃል ለእሳት ተዘጋጅተዋል፤ ኃጥኣን ሰዎች እስከሚጠፉበት  እስከ ፍርድ ቀንም ተጠብቀዋል ነገር ግን ወንድሞቻችን ሆይ÷ ይህን አትርሱ፤ በእግዚአብሔር ዘንድ አንዲት ቀን እንደ አንድ ሺህ ዓመት÷ ሺህ ዓመትም እንደ አንድ ቀን ነውና፡፡ …”

ግብረ ሐዋርያት

(የሐዋ. ፳፬÷፩-፩)

“በአምስተኛውም ቀን ሊቀ ካህናቱ ሐናንያ ከመምህራኑና ጠርጠሉስ ከሚባል አንድ ጠበቃ ጋር ወረደ፤ ጳውሎስንም በአገረ ገዢው ዘንድ ከሰሱት፤ ጳውሎስም በቀረበ ጊዜ ጠርጠሉስ እንዲህ እያለ ይከስሰው ጀመረ፤ “ክቡር ፊልክስ ሆይ÷ በዘመንህ ብዙ ሰላምን አግኝተናል፤ በጥበብህም በየጊዜው በየሀገሩ የሕዝቡ ኑሮ የተሻሻለ ሆኖአል፤ ሥርዓትህንም በሁሉ ዘንድ ስትመሰገን  አግኝተናታል፡፡ …”

ምስባክ

(መዝ. ፵÷)

“እግዚአብሔርሰ ገሃደ ይመጽእ፤ ወአምላክነሂ ኢያረምም፤ እሳት ይነድድ ቅድሜሁ፡፡”

ትርጉም፦ እግዚአብሔር በግልጥ ይመጣል፡ አምላካችንም ዝም አይልም፤ እሳት በፊቱ ይነዳል በዙሪያውም ብዙ ዐውሎ አለ፡፡”

ወንጌል

(ማቴ. ፳፬÷፩-፭) 

“ጌታችን ኢየሱስም ከቤተ መቅደስ ወጥቶ ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ወደ እርሱ ቀርበው የቤተ መቅደሱን የሕንፃ አሠራር አሳዩት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ ይህን ሁሉ ታያላችሁን? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ በዚህ አይቀርም፡፡” (ተጨማሪውን ያንብቡ)

ቅዳሴ: – ቅዳሴ ዘአትናቴዎስ

 

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *