“ልትድ ትወዳለህን?”

በኢየሩሳሌም በበጎች በር አጠገብ አንዲት መጠመቂያ ነበረች፡፡ ይህች መጠመቂያም በእብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ስትባል አምስት አርከኖች ነበሯት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች፣ ሰውነታቸው የሰለለ በርካታ ድውያን ተጠምቀው ይድኑ ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ወንዙ ወርዶ ውኃውን እስኪያነዋውጠው ድረስ ይጠባበቁ ነበር፡፡ ውኃው በሚነዋወጥበት ጊዜም በመጀመሪያ ወርዶ የተጠመቀባት ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር፡፡ (ዮ.፭፥፩-፬)

በዚህ ሥፍራ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ያህል ድኅነትን ሽቶ ከዛሬ ነገ እድናለሁ እያለ ይጠባበቅ የነበረ በሽተኛ (መጻጉዕ) ነበር፡፡ ሕሙማኑ በቤተ ሳይዳ መጠመቂያ የተሰበሰቡት ድኅነትን ፍለጋ ነው፡፡ ዛሬ ደዌ የጸናበት ከደዌ (ከበሽታ) ለመፈወስ ወደ ጠበል እንደሚሄድ በዘመነ ብሉይ የእግዚአብሔር መልአክ (ቅዱስ ሩፋኤል) በሳምንት አንድ ቀን ወደዚያች መጠመቂያ ገብቶ ውኃውን ሲያናውጥ ቀድሞ ወደ መጠመቂያይቱ የገባ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበር፡፡ ዕለቷም ቀዳሚት ሰንበት (ሰንበተ አይሁድ) ነበረች፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት በበሽታ ሲማቅቅ የነበረውን ሰው በዚያ በቤተ ሳዳ መጠመቂያው አጠገብ ተኝቶ አገኘው፡፡ የጠየቁትን የማይረሣ፣ የለመኑትን የማይነሣ አምላክ ነውና የመጻጉዕን ስቃይ ተመለከተ፡፡ ዝም ብሎም ያልፈው ዘንድ አልወደደም፡፡ ፈቃዱንም ይፈጽምለት ዘንድ “ልትድን ትወዳለህን?” ሲል ጠየቀው፡፡ በሽተኛውም “አዎን ጌታዬ ሆይ፤ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፤ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል” አለው፡፡ (ዮሐ. ፭፥፮-፯) መጻጉዕ አጠገቡ ያለው ቆሞም በሐዘኔታ እየተመለከተ የሚጠይቀው ማን እንደሆነ አላወቀምና ለሠላሳ ስምንት ዘመናት ከአልጋው ጋር ተጣብቆ በሕመም ሲሰቃይ መኖሩን፣ እንደ ሌሎቹም በሽተኞች በፍጥነት ወደ መጠመቂያው መውረድ እንዳልቻለ ለማስረዳት ሞከረ፡፡

ጌታችን መድኃኒታቻን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃሉ ብቻ መፈወስ ይችላልና በቅፍርናሆም የመቶ አለቃው ልጅ በታመመ ጊዜ መቶ አለቃው በእምነት ሆኖ “አቤቱ አንተ ከቤቴ ጣራ በታች ልትገባ አይገባኝም፤ ነገር ግን በቃልህ እዘዝ፣ ልጄም ይድናል“ብሎ እንደጠየቀው “እንግዲህ ሂድ እንደ እምነትህ ይሁንልህ” ብሎ በዚያች ስዓት ልጁን እንዳዳነው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ (ማቴ.፰፥፰) ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ለመጻጉዕ በቅድሚያ ፈቃዱን ነው የጠየቀው፡፡ መጻጉዕም ከዚያ ሲያሰቃየው ከነበረው ደዌ መፈወስ ሽቷልና ምላሹ “አዎን ጌታዬ ሆይ” ነበር፡፡

መጻጉዕ በመጠመቂያው ዳር አልጋው ላይ ተጣብቆ ሳለ ከእርሱ በኋላ መጥተው ከእርሱ በፊት ድነው የሚሄዱ ሰዎች ሲመለከት ሠላሳ ስምንት ዓመታት አሳልፏል፡፡ ዓመቱ በረዘመ ቁጥር ተስፋ ቆርጦ ቤተ ሳይዳን ቤቴ ብሎ ከመኖር በስተቀር ምንም አማራጭ አልበረውም፡፡ በቤተ ሳይዳ መጠመቂያ ስፍራ አምስት መመላለሻዎች ማለትም፡- በሽተኞች፣ አንካሶች፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ድኅትን ሽተው የአምላካቸው ማዳን ይጠባበቁ ነበር፡፡ በየሳምንቱም መልአኩ ከሰማይ ወርዶ ውኃውን ባናውጠው ጊዜ ቀድሞ የገባው አንድ ሰው ብቻ ይድናል፡፡ ይህንን ዕድል ለማግኘት ደግሞ መጻጉዕ አልታደለም፤ ለምን ቢሉ ሌሎች ቅድመውት ወደ መጠመቂያው ይወርዳሉ፡፡ እርሱም ብቻ አይደለም አንካሶች፣ ዕውሮችና እግራቸው የሰለለ ሰዎችም አቅሙ ስለማይኖራቸው ወደ መጠመቂያው ቢወርዱም በሌላው ስለሚቀደሙ ከውኃው የሚያወጣቸው አያገኙም፡፡ ስለዚህ ከውኃው መልሶ የሚያወጣቸው ሰው ያስፈልጋቸዋል፡፡

መጻጉዕ በዚህ ስፍራ የአንድ ጎልማሳ ዕድሜን ያህል ጊዜ እግዚአብሔርን ደጅ በመጥናት አሳልፏል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህን ሰው ችግር ያወቀው ማንም ሳይነግረው ነው፡፡ ይፈውሰውም ዘንድ ወደ እርሱ ቀርቦ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ጌታችን የሚፈልገው ይህንን ሰው መፈወስ እንጂ የራሱን ማንነት ማሳየት ስላልነበረ “ላድንህ ትወዳለህን?” አላለውም፡፡ ይህ ሰው የጌታችንን ማንነት አያውቅም፡፡ ነገር ግን ድኅነትን ናፍቋልና “ልትድን ትወዳለህን?” ባለው ጊዜ አላመነታም፡፡ “አዎን ጌታዬ ሆይ” ሲል መለሰ፡፡

ጌታችንምመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በሽተኛውን ይፈውሰው ዘንድ ፈቃዱ ስለሆነ ወደ መጠመቂያው ውረድ አላለውም፡፡ በተቃራኒው ጌታችን በቃል ብቻ መፈወስ ይችላላና “ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ” አለው፡፡ ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ባላሰበው ባልጠበቀው መንገድ ፈወሰው፡፡ ይህ ሰው ሠላሳ ስምንት ዓመት ሙሉ ሲጠባበቃት የነበረችውን የቤተ ሳይዳ ጠበል ሳያገኝ ፣ በመልአኩ መውረድ ሳይሆን በመላእክት ፈጣሪ ቃል ተፈወሰ፡፡

ከላይ የመቶ አለቃውን ልጅ በቃል ብቻ እንደፈወሰው አይተናል፤ በተጨማሪም በጠበል ተጠምቆ መዳንን በተመለከተ ዕውር ሆኖ የተወለደውን ሰው ታሪክ ማንሣት እንችላለን፡፡ ዕውር ሆኖ በተወለደው ሰው ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ “ይህ ሰው ዕውር ሆኖ የተወለደው በማን ኃጢአት ነው? በራሱ ነውን? ወይስ በወላጆቹ?” ብለው በጠየቁት ጊዜ “የእግዚአብሔር ሥራ ሊገለጥበት ነው እንጂ እርሱ አልበደለም፤ ወላጆቹም አልበደሉም፤ …” አላቸው፡፡ በዚህ ብቻ አላበቃም በምድር ላይ ምራቁን እንትፍ አለ፤ ምራቁንም ጭቃ አድርጎ የዕውሩን ዐይኖች ቀባው፡፡ እንዲህም አለው” ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ” አለው፤ ከቶ ለእግዚአብሔር የሚሣነው ነገር የለምና ዕውሩ በታዘዘው መሠረት ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ፡፡ (ዮሐ. ፱፥፩-፯) መጻጉዕንም ጠበል ሳያስፈልገው “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” ብሎታልና ተፈውሶ እርሱን ለሠላሳ ስምንት ዓመት ተሸክማው የነበረችውን አልጋ ተሸክሞ ለመሄድ በቃ፡፡

 በእነዚህ ታሪኮች እንደተመለከትነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ በወደደው መንገድ ማለትም፡- በጠበል፣ ያለ ጠበልም፤ በቃሉ፣ በዝምታ፣ በሌሎችም መንገዶች ማዳን እንደሚችል እንረዳለን፡፡ መጻጉዕንም ሳይውል ሳያድር፣ ላገግም ሳይል በቅጽበት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ ለመሄድ ችሏል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህንን መሠረት አድርጋ የዐቢይ ጾም አራተኛ ሳምንትን “መጻጉዕ” ብላ ሰይማዋለች፡፡

ጌታችን መጻጉዕን ብቻ ፈውሶት ሔደ? ቢባል የፈወሰው እርሱን ብቻ አይደለም፡፡ እርሱን በሥጋ ቢፈውሰውም ተአምራቱን አይተው በማመናቸው በነፍሳቸው የተፈወሱ ይበዛሉ፡፡ “ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት፣ ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ” እንዲሉ አበው በዚያ ሥፍራ በሥጋ ታመው በነፍሳቸው አምነው የዳኑ ብዙዎች ናቸው፡፡

ይህ ሰው ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሲሔድ ሰንበት ለሰው ድኅነት እንደተፈጠረች ያልተረዱ አይሁድ ከአልጋው ተነሥቶ የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ በአደባባይ ሲያዩት በተሠራው የድኅነት ሥራ አልተደሰቱም፡፡ በዚህም ምክንያት “ዛሬ ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አይገባህም” አሉት፡፡ “እንኳን ለዚህ አበቃህ!” ያለው ግን አንድም ሰው አልነበረም፡፡

መጻጉዕም መልሶ “ያዳነኝ እርሱ አልጋህን ተሸክመህ ሂድ አለኝ” አላቸው፡፡ አይሁድም አንድ ጊዜ ጠይቀው ብቻ አላለፉትም ያዳነውን “ሰንበትን ሽሯል” ብለው ለመክሰስ ፈልገዋልና   “አልጋህን ተሸክመህ ሂድ ያለህ ሰውዬው ማነው?” በማለት ጠየቁት፡፡ በወቅቱ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመካከላቸው ተሰውራቸዋልና በቦታው ሊያገኘው አልቻለም፡፡ ነገር ግን መጻጉዕ ያዳነውን ጌታችንን በቤተ መቅደስ አገኘውና ሄዶ ያዳነው ኢየሱስ እንደሆነ ለአይሁድ ነገራቸው፡፡

መጻጉዕ ከዚህ በኋላ ወደ አይሁድ ሄዶ ጌታን መክሰሱና ለጌታ ሞት የመማከራቸው ምክንያት መሆኑ ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እነሆ ድነሃል፤ ግን ከዚህ የባሰ እንዳያገኝህ ዳግመኛ እንዳትበድል ተጠንቀቅ” ብሎት ነበርና (ዮሐ. ፲፰፥፳፫) ነገር ግን ሊሰማው አልፈቀደም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘበት በምሴተ ሐሙስ ለሊቀ ካህናቱ አግዞ ጌታችንን በጥፊ መታው፡፡ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር” እንዲሉ አበው የሠላሳ ስምንት ዓመት ስቃዩን ረስቶ፣ ከዚያ በላይ መከራ እንደሚያገኘው እየተነገረው ያዳነውን አምላኩን ካደ፡፡

ምንባባትና መልእክታት

የቅዱስ ጳውሎስ መልእክት (ገላ. ፭÷፩-ፍጻሜ)

“እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትኑሩ፡፡ እነሆ÷እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ፤ “ብትገዘሩም በክርስቶስ ዘንድ ምንም አይጠቅማችሁም፡፡” ደግሞም ለተገዘረ ሰው ሁሉ የኦሪትን ሕግ መፈጸም እንደሚገባው እመሰክራለሁ፡፡  …” (ገላ. ፭÷፩-ፍጻሜ)

የቅዱስ ያዕቆብ መልእክት (ያዕ.፭÷፲፬- ፍጻሜ)

“ከእናንተ የታመመ ሰው ቢኖር በቤተ ክርስቲያን ያሉ ቀሳውስትን ይጥራና ይጸልዩለት፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተጸለየበትንም ዘይት ይቅቡት፡፡ የሃይማኖት ጸሎትም ድውዩን ይፈውሰዋል፤ እግዚአብሔርም ያስነሣዋል፤ ኃጢአትንም ሠርቶ እንደሆነ ይሰረይለታል፡፡ …”  (ያዕ. ፭÷፲፬- ፍጻሜ)

ግብረ ሐዋርያት (የሐዋ. ÷፩-፩)

“ጴጥሮስና ዮሐንስም በዘጠኝ ሰዓት ለጸሎት በአንድነት ወደ ቤተ መቅደስ ወጡ፡፡ ከእናቱ ማኅፀንም ጀምሮ እግሩ ሽባ ሆኖ የተወለደ አንድ ሰው ነበር፤ ወደ መቅደስም ከሚገቡት ምጽዋት ይለምን ዘንድ ሁል ጊዜ እየተሸከሙ መልካም በሚሏት በመቅደስ ደጃፍ ያስቀምጡት ነበር፡፡ ጴጥሮስንና ዮሐንስንም ወደ መቅደስ ሲገቡ አይቶ ምጽዋት ይሰጡት ዘንድ ለመናቸው፡፡ ጴጥሮስም ከዮሐንስ ጋር ትኩር ብሎ ተመለከተውና “ወደ እኛ ተመልከት” አለው፡፡ ወደ እነርሱም ተመለከተ፤ ምጽዋት እንደሚሰጡትም ተስፋ አድርጎ ነበር፡፡ ጴጥሮስም “ወርቅና ብር የለኝም ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ እነሆ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሥተህ ሂድ” አለው፡፡ በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ ያን ጊዜም እግሩና ቁርጭምጭሚቱ ጸና፡፡ …” (የሐዋ. ÷፩-፩)

የዕለቱ ምስባክ (መዝ.÷)

“እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ ዓራተ ሕማሙ፤

ወይመይጥ ሎቱ ኩሉ ምስካቤሁ እምደዌሁ

አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሃለኒ፤ እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል፤ እኔስ አቤቱ ማረኝ።” (መዝ. ፵÷፫)

ወንጌል (ዮሐ.፩-፳፬)

“ከዚህ በኋላ የአይሁድ በዓል እንዲህ ሆነ፤ ጌታችን ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ። በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ መጠመቂያ ነበረች፤ ስምዋንም በዕብራይስጥ ቤተ ሳይዳ ይሉአታል፣ አምስት እርከኖችም ነበሩአት፡፡ በዚያም ዕውሮችና አንካሶች፣ ሰውነታቸውም የሰለለ ብዙ ድውያን ተኝተው የውኃውን መናወጥ ይጠባበቁ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ መጠመቂያው ወርዶ ውኃውን በሚያናውጠው ጊዜ ከውኃው መናወጥ በኋላ በመጀመሪያ ወርዶ የሚጠመቅ ካለበት ደዌ ሁሉ ይፈወስ ነበርና፡፡ በዚያም ከታመመ ሠላሳ ስምንት ዓመት የሆነው አንድ ሰው ነበር፡፡ ጌታችን ኢየሱስም በአልጋው ተኝቶ ባየ ጊዜ በደዌ ብዙ ዘመን እንደቆየ ዐውቆ “ልትድን ትወዳለህን?” አለው፡፡ ድውዩም መልሶ “አዎን ጌታዬ ሆይ ነገር ግን ውኃው በተናወጠ ጊዜ ወደ መጠመቂያው የሚያወርደኝ ሰው የለኝም፡፡ እኔ በምመጣበት ጊዜ ሌላው ቀድሞኝ ይወርዳል፡ አለው፡፡ ጌታችን ኢየሱስም “ተነሥና አልጋህን ተሸክመህ ሂድ” አለው፡፡ ወዲያውኑም ያ ሰው ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሄደ፤ ያች ቀንም ሰንበት ነበረች፡፡ …” (ዮሐ. ፭ ፩-፳፬)

ቅዳሴ ቅዳሴ ዘእግዚእነ

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *