ደወል ቤት

                                                ደወል ቤት                                            
አንድ ሰው ነበረ…
በልጅነቱ ዕድሜው በቤቱ የኖረ፣
ከደጁ ላይጠፋ ኪዳኑን ያሰረ፤
ሲለፋ ሲደክም ሲሮጥ ሲንደረደር
ከጾም ከጸሎት ጋር ሲተጋ ሲታትር፣
በሥጋ በመንፈስ እንደቃሉ ሚኖር፡፡
    ያቀደው ባይሞላ ድካም ቢሆን ትርፉ
ታናናሽ ያላቸው እየተውት ሲያልፉ፣
ልቡ ተቀይሞ ከአምላኩ ተኳርፎ
ለቅዳሴ ቆሞ ግንብ ተደግፎ
በኑሮው በዕድሉ በዕድሜው ሲቆዝም
ዘርዝሮ ሲያላምጥ ያልጨበጠውን ህልም፣
አንደበቱ ታስሮ በኩርፊያ መቀየም
ተንሥኡ ሲባል…. ዝምምም ፡፡
ሰላም ለናንተ …ዝምምም፡፡
በፍርሀት ስገዱ ወደ ምሥራቅ እዩ
ተሰጥኦ መልሱ እጅ ንሱ ጸልዩ፣
ዝምምም…
የውዳሴው ዜማ ሲፈስ ሲቀዳ
ልሳን እንደሌለው እንደማያውቅ ድዳ፣
በዓለም ዙረት ድካም ልቡ ከስላ ነድዳ፡፡
“ምን ፈልገህ ነው?” ሲል ፈጣሪን ሲሞግት
ከአንደበቱ ጸሎት ከመዝሙረ ዳዊት፣
“ለምን” ብቻ ቀርታው ከእልፍ አእላፍ ቃላት፤
ዝ ውእቱ ሲባል… ዝምምምም
ስብሐት ሲባል…ዝምምምም…
ስላልተነገረች የሀሳቡ ቀለም፣
ስላልተጠየቀች የህልውናው ትልም፡፤
በታጠፈ አንጀቱ በበረዳት ነፍሱ
የጥያቄ ዓይኖቹ በዕንባ ሳይርሱ፣
ላፍታ ሳይላወስ ያ ትንታግ ምላሱ…
መጽናናት ሳያሻው የአዋቂ ጥገና
የኤልያስ እሳት ወይ የሙሴ መና፡፡
ሁሉ በእርሱ እንዲሆን ሀሳቡ እያወቀ
አካሉ እያለቀ ልቡ እየተፋቀ፣
ወይ መቅደስ አልገባ ወይ ከፊቱ አልራቀ፡፡
በዓለም ሥርቆት ኃጢአት አልተጨማለቀ፣
በአመንዝራ ስሜት እቅፍ አልወደቀ!
ደጀ ሰላም ቆሞ ሁሌ እንደጠየቀ፡፡
ተሰጥኦ አይሻ ይትበሀል አያምረው
“ለምን” ሲል ፈጣሪን ሠርክ እንደጠየቀው፣
በቤትህ አድጌ ቃልህ ቃሌ ሆኖ
ዕጣፈንታ ዕድሌ በእጅህ ተወስኖ፣
የአካሌ ግንባታ ከአፈርህ ተዘግኖ…
ልጅነቴ አንተ ጋር የዕድሜዬ እኩሌታ
ኪዳን ሠርክህ ሆኖ የኑሮዬ ዋልታ፣
እንቅልፍ የማይወስደኝ ደወልኽን ሳልመታ፡፡
ለነፍሰ ገዳዮች ለሌባ ቀማኛ
ያልከለከልካትን ሲሳይና አዱኛ፣
ለኔ እንዴት ነሳኸኝ ምን ባስቀይምህ ነው
ለማትረባ እንጀራ አቅሜን ምትፈትነው?!
ለምን? ለምን? ለምን? ፊቴ ደስታን አጣ
ጽድቅን መለመኛ ጸሎት ሳይታጣ?!
እንጀራ ልመና ከመቅደስህ ልምጣ፡፡
ባሻገርከኝ ገደል ባለፍኩት ፈተና
በመከራዬ ውስጥ አውቅሀለሁና፣
አታይም አልልም ባጉል ምንፍቅና፡፡
ለሰው የሚሻውን እንድትሰጥ ባውቅም
ነገር ግን በቃሌ ስጠኝ አልልህም፡፡
ከጸሎት ቆጥሬ የሲሳይን ድካም
ለምን ራበኝ ብዬ ዕንባ አላባክንም
ነገር ግን…
ኪዳን ላይ ብታጣኝ ከደጀ ሰላምህ፣
የቅዳሴ ድምጼን ባይሰሙ ጆሮችህ፣
ወዴት ጠፋ ብለህ መጠየቅ አያሻም
ከእንግዲህ መጥቼ ምንም አልጠይቅም፣
ቆፍሬ ለማደር ወጥቻለሁ እኔም፡፡
አለና ዞር ሲል ለመሄድ ሲነሣ
ከመቅደሱ ቅጥር ወድቆ የተረሳ፣
አጥንቱ ተሰብራ ሥጋው ተቆራርሳ
መለመን ያቃተው ´ሚሄድ በዳበሳ
አረጋዊ አየና ልቡ ደነገጠ!
ከጎን በመኪና በውድ ነገሮች በተንቆጠቆጠ
ጤና ያጣ ወጣት መሬት ያልረገጠ፣
በልዩ መሳሪያ ብረት ተደግፎ
ወደ ቤተ መቅደስ በጎን ሲሄድ አልፎ፣
የልቡ ደወል ቤት አንድ ጊዜ ደወለ
ምን ጎደለኝ ብሎ ቃጭሉ አቃጨለ፡፡
ያኔ ሽፋሽፍቱ ሳያውቅ ዕንባ አዘለ
ድምጹ ከአንደበቱ ወጣ ፈነቀለ፡፡
ንሴብሕ ንዌድስ ንግባእኬ እያለ፡፡
እናም…
በጆሮህ ያልገባ ካይን የተከለለ
በድህነትህ ውስጥ በማጣትህ መሀል ጸጋና ሀብት አለ፡፡

                                                                                                             በቃለጽድቅ በላይነህ

1 reply

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *