“የሰላም መንገድ” (መዝ.፲፬፥፮)

በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ሰላም ማለት ጸጥታ፣ ዕረፍት፣ እርጋታ፣ እርካታ ማለት ሲሆን የእርስ በእርስ ስምምነት፣ በአንድነት አብሮ መኖር፣ መቻልና የዕረፍት ስሜት እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ያስረዳል፡፡

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ክፉዎች የሰላምን መንገድ የማያውቁ መሆናቸውን “ደምን ለማፍሰስ እግራቸው ፈጣን ነው፣ ጥፋትና ጉስቁልና በመንገዳቸው አለ፣ የሰላምን መንገድ አላወቁአትምና እግዚአብሔርን መፍራት በዓይናቸው ፊት የለም” (መዝ.፲፬፥፮) ሲል ይገልጻል፡፡

በሌላም ክፍል በጎ ዘመንን ሊያይ የሚወድ ቢኖር ሰላምን መፈለግና የሰላምን መንገድ መከተል እንደሚገባው ሲያስረዳን፡- “ልጆቼ ኑ ስሙኝ እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችሁ ዘንድ፤ ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው? አንደበትህን ከክፉ ከልክል፣ ከንፈሮችህም ሸንገላን እንዳይናገሩ ከክፉ ሽሽ፣ መልካንም አድርግ፣ ሰላምን ሻት ተከተላትም” በማለት ሰላምን መከተል እንደሚገባ ያስረዳናል፡፡ (መዝ.፴፫፥፲፫-፲፬)

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ልጆቹ ለምንሆን ለእኛ ሲያስተምረን እግዚአብሔር የፈቀደለትንና እርሱ በሕይወቱ ገንዘብ አድርጎት በእግዚአብሔር እንደ ልቤ ተብሎ የተመረጠበትን ጥበብ ሲነግረን “እግዚአብሔርን መፍራት አስተምራችኋለሁ” አለ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔርን መፍራት ከሁሉ ይልቅ ቀዳሚ ነውና፡፡ ለዚህም ነው አባትና ልጅ ተባብረው(ተቀባብለው) የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት እንደሆነ የነገሩን (መዝ.፻፲፥፲፤ ምሳ.፩፥፯፤9፥፲)፡፡

ከሁሉ አስቀድሞ በሕይወታችን እግዚአብሔርን መፍራት አስፈላጊ ነው፡፡ ሰላምን የምንሻበት መንገድ እርሱ ነውና፡፡ ቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔርን መፍራት ሕይወትን የሚያስገኝና በጎ ዘመንን ለማየት የምንችልበት የጥበብ (የዕውቀት) ሁሉ መሠረት እንደሆነ ከገለጸ በኋላ “ሕይወትን የሚፈቅድ ሰው ማን ነው? በጎ ዘመንንም ለማየት የሚወድድ ማን ነው?” ብሏል፡፡ ከላይ እንዳየነው ሕይወትን ለማግኘት የሚሻ በጎ ዘመንንም ለማየት የሚፈልግ ጥበብን (ማስተዋልን) ገንዘብ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን የሰላምን መንገድ መከተል፣ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የሚሻ ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት ስንመለከትም፡-

ኛ. አንደበትን  ከክፉ መከልከል፡-

የሰው ልጅ በልቡ ያሰበውን በአንደበቱ ይናገራል፡፡ በልብ የታሰበውን መልካምም ይሁን ክፉ የሚያውቀው እግዚአብሔር ብቻ ሲሆን፣ ነገር ግን የታሰበው ነገር በውጫዊ ሰውነት ላይ በሚታዩ ምልክቶች(ገጽን በማየት) መታወቅ የሚችልበት አጋጣሚ ከተፈጠረ ወይም በአንደበት ቢነገርና በሥራ ቢተገበር ሰዎች ይረዱት ይሆናል፡፡

አንደበትን ከክፉ ካልከለከሉት ሰዎችን የሚጎዳና የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የማለፍ፣ በዚያም ሰበብ ተናጋሪውን ሳይቀር ለሞት የማብቃት ዕድል አለው፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ “ምላስም እሳት ናት እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ  ዐመፅ የተመላበት ዓለም ናት ሥጋችንን ትበላዋለች፣ ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች፣ ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች” በማለት የገለጸው፡፡(ያዕ.፫፥፮) ስለዚህ ሕይወትን የሚፈቅድና በጎ ዘመንን ለማየት የሚፈልግ ሰው አንደበቱን ከክፉ ነገር መከልከልና መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ተናግሮ ሰውን ላለማስቀየምና ላለማስከፋት መጠንቀቅ፣ ሌላውንም ሰው ወደ ጥፋት ላለመምራት ማስተዋል ተገቢ ነው፡፡ አንደበት ኃያል ነው ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው ይበልጣል ይባላልና፡፡

አንደበትን ከክፉ ካልከለከልነው ስድብንና ሐሜትን እናበዛለን፡፡ ይህ ደግሞ ከሕይወት ጎዳና የሚያወጣ ክፉ ተግባር ነው፡፡ በጓደኛ፣ በባልና ሚስት፣ በአንድ ሀገርና በሌላው ሀገር፣ በጎሳና በጎሳ፣ በጎረቤትና በጎረቤት መካከል ሐሜትና መነቃቀፍ፣ ስድብና ጥላቻ ካለ በጎ ዘመንን ማየት አይቻልም፡፡ ነገር ግን ሕይወትንም ሆነ በጎ ዘመንን ለማየት አንደበትን ከክፉ መከልከልና በጎ ነገርን መናገር አስፈላጊ ነው፡፡

ኛ. ከክፉ መሸሽ፡-

ከክፉ  መሸሽ  ማለት  ክፉን  ከማድረግ  መቆጠብና  ክፉ  ከሚያደርጉት  ጋር  በክፋታቸው አለመተባበር ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሰው ሁል ጊዜም ቢሆን ከክፉዎች ጋር ኅብረት የለውም፡፡ አባታችን ያዕቆብ ልጆቹን በሚመርቅበት ጊዜ ክፉ ሥራ ከሠሩ ከልጆቹ የክፋት ሥራ ጋር እንደማይተባበርና ከክፋት ጋር ኅብረት እንደሌለው ገልጧል፡፡ “ስምዖንና ሌዊ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በጭቅጭቃቸውና በጦራቸው ዐመፅን ፈጸሟት፣ በምክራቸው ሰውነቴ አትገናኛቸው፣ ሐሳቤም በዐመፃቸው አትተባበርም፣ በቊጣቸው ሰውን ገድለዋልና በገዛ ፈቃዳቸውም የሀገርን ሥር ቆርጠዋልና ቁጣቸው ርጉም ይሁን፣ ጽኑ ነገርና ኩርፍታቸውም ብርቱ ነበርና በያዕቆብ እከፋፍላቸዋለሁ በእስራኤልም እበታትናቸዋለሁ” (ዘፍ.፵፱፥፭)፡፡ ያዕቆብ ምንም እንኳ በሥጋ የወለዳቸው ልጆቹ ቢሆኑም በፈጸሙት ክፉ ሥራ ግን እንደማይተባበር ከክፉ ሥራቸው የራቀና ከክፋት የተለየ መልካም ሐሳብ እንዳለው ገልጧል፡፡

ዛሬም ቢሆን የሰው ልጆች ክፋትና በደል እየበዛ ባለበት ሰዓት የእግዚአብሔር ልጆች ከክፋት፣ ከተንኮል፣ ከውሸት፣ ከሌብነት፣ ከቅሚያ፣ ከዝርፊያ፣ ከጭካኔ፣ ከሴሰኝነት፣ ከዘማዊነት፣ ከዘረኝነት በአጠቃላይ ለራስም ሆነ ለሀገር ከማይበጁ እኩይ ምግባራትና ከሚፈጽሟቸው ሰዎች ጋር መተባበር የለብንም፡፡ ቅዱስ ዳዊት እንደነገረን ሕይወትን ለማግኘት የምንሻና በጎ ዘመን ለማየት የምንፈልግ ሁሉ ከክፉዎች ጉባኤ መለየትና አለመተባበር ያስፈልጋል፡፡

ኛ. መልካም ማድረግ

ሕይወትን ለማግኘትና በጎውንም ዘመን ለማየት የሚሻ ሰው ሁሉ መልካምን ሊያደርግ ያስፈልገዋል፡፡ ከክፉ መሸሻችንና ከክፉዎች ጋር አለመተባበራችን መልካም ሥራ ለመሥራት መሆን አለበት እንጂ ከሥራ ርቀን እንዲሁ እንድንኖር አይደለም፡፡ ያለ በጎ ሥራ መኖር ስንፍና ነውና፡፡

እግዚአብሔር የሰውን ውድቀቱንና መጥፋቱን የማይሻ አምላክ ስለሆነ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በክፉ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ሁሉ ሊመለስና በሕይወት ሊኖር ይገባዋል፡፡ በቀደመው ስሕተቱ ወንድሙን ያሳዘነ፣ ሰው የገደለ፣ አካል ያጎደለ፣ ግፍን የፈጸመ፣ የድሃውን ገንዘብ በተለያየ ሰበብ የዘረፈ፣ ጉቦ የተቀበለ፣ በእነዚህና መሰል እኩይ ሥራዎች ሀገሩን የጎዳ፣ እግዚአብሔርን የበደለ ሁሉ ከልብ በመጸጸት በልቅሶና በዋይታ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ያስፈልገዋል፡፡ ለዚህም አምላካችን ልዑል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅኤል ላይ አድሮ ኃጢአተኛው ከኃጢአቱ ተመልሶ በሕይወት መኖር እንዳለበት አስገንዝቦናል፡፡

“እኔ ሕያው ነኝና ኃጢአተኛው ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንጂ ኃጢአተኛው (በደለኛው) ይሞት ዘንድ አልፈቅድም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፡፡ የእስራኤል ቤት ሆይ ተመለሱ ከከፉ መንገዳችሁ ተመለሱ ስለምንስ ትሞታላችሁ?” (ሕዝ. ፴፫፥፲፩) እንዲል፡፡

እግዚአብሔር በነቢዩ ላይ አድሮ እንደ ነገረን በደለኛ ሰው በበደሉ ቀጥሎ መጥፋት የለበትም፡፡ መመለስና በሕይወት መኖት ያስፈልገዋል እንጂ፡፡ እሱም እንደ በደሉ ዓይነት ይቅርታ ጠይቆ፣ ንስሓ ገብቶ፣ የበደለውን ክሶ፣ የሰረቀውን መልሶ፣ የሰበረውን ጠግኖ፣ ያጎደለውን መልቶ በፍጹም መጸጸት ሊመለስና መልካም በመሥራት ሌት ተቀን ከሚተጉት ጋራ በመልካም ሥራ ሊተባበር ያስፈልገዋል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን “ስለዚህ ሐሰትን ተውአት ሁላችሁም ከወንድሞቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ እኛ አንድ አካል ነንና አትቆጡ፣ አትበድሉም፣ ፀሐይ ሳይጠልቅም ቊጣችሁን አብርዱ፣ ለሰይጣንም መንገድን አትስጡት፣ የሚሰርቅም እንግዲህ አይስረቅ ነገር ግን ድሃውን ይረዳ ዘንድ በእጆቹ መልካም እየሠራ ይድከም” (ኤፌ.፬፥፳፭) ይላል፡፡

ኛ.ሰላምን መሻት

ሰላም ለሁሉ ነገር አስፈላጊና ሁሉን ለማድረግ የምንችልበት የመልካም ነገር ሁሉ በር ነው፡፡ ሰላምን መፈለግ ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንንም ለማየት ያስችላል፡፡ ሰላምን በሁለት መልኩ እናያለን፡፡ እሱም የውስጥ ሰላምና የውጭ ሰላም ወይም ውስጣዊ ሰላምና ውጫዊ ሰላም ተብሎ ይመደባል፡፡

የሰው ልጅ ለመኖር ውስጣዊ ሰላምም ሆነ ውጫዊ ሰላም ያስፈልጉታል፡፡ ውስጣዊ ሰላም የምንለው አንድ ሰው ከፍርሃት፣ ከጭንቀት፣ ከመረበሽ፣ ከሥጋት… ወዘተ ነጻ ሆኖ መኖር ሲችል ውስጣዊ ሰላም አለው ይባላል፡፡ ይህም የውስጥን ሰላም ከሚያደፈርሱ፣ አእምሮን ከሚረብሹ፣ ልብን ከሚያቆስሉ፣ የጸጸት እሮሮን ከሚያስከትሉ ነገሮች ስንርቅና ለአእምሮ የሚመች ሥራ ስንሠራ ውስጣችን ሰላም ይሆናል፡፡

ውጫዊ ሰላም የምንለው ደግሞ፡- ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከጎረቤት፣ ሀገራት ጋር ተስማምተንና ተግባብተን ተቻችለንና ተረዳድተን በፍቅር ተሳስረን በመኖር ከጥል ከመለያየት፣ ከመጠላላት፣ ከመገፋፋት፣ ከመነቃቀፍ ተቆጥበን የጠብንና የጦርነትን ወሬ ባለመስማትና በስምምነት ተግባብቶ በመኖር የሚገለጥ ነው፡፡ ስለዚህ ሰላም ለሁሉ እንደሚያስፈልገው ካወቅን የሰላም መገኛ ማን እንደሆነና ሰላም ከየት እንደሚገኝ ማወቅ ደግሞ አስፈላጊ ነው፡፡

ሰላም የሚገኘው የሰላም ባለቤት ከሆነው ከልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ እንደገለጠው እውነተኛ ሰላም ከእግዚአብሔር ይገኛል፡፡ እርሱ የሰላም አምላክ ነውና (ሮሜ.፲፭፥፴፫)፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰላም አለቃ ተብሏል፡፡ “ሕፃን ተወዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፣ ኃያል አምላክ፣ የዘለዓለም አባት፣ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል” (ኢሳ. 9፥፮) እንዲል፡፡

ዓለም ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመን ያህል ሰላሙን አጥቶ በመቅበዝበዝ ይኖር የነበረ ሲሆን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው መሆን፣ እውነተኛውን ሰላም አግኝቷል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ሞት ምክንያት ፍርሃት ጸንቶባቸው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜንም እሰጣችኋለሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፣ ልባችሁ አይደንግጥ አትፍሩም” (ዮሐ.፲፬፥፳፯) በማለት ፍርሃትን፣ ስጋትን፣ ጭንቀትን፣ ሁከትን፣ መረበሽን የሚያርቀውን (የሚያስወግደውን) እውነተኛውን ሰላም አደለን፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት እንዳለው ሕይወትን ለማግኘትና በጎ ዘመንን ለማየት የምንሻ ሁሉ ሰላምን መሻት ያስፈልጋል፡፡ ደግሞም ሰላምን መሻት ብቻ ሳይሆን መከተል ተገቢ ነው፡፡ ምክንያቱም መሻት ብቻውን ዋጋ ሊኖረው ስለማይችል፡፡ መሻታችን ወደ ማግኘት የሚደርሰው የምንሻውን ነገር ለማግኘት ወደ መገኛው መጓዝና መቅረብ ሲቻል ነው፡፡ ለዚህም ነው ሰላምን ሻት ካለ በኋላ ተከታላትም በማለት በሰላም መንገድ መጓዝ፣ የሰላም ወሬ ማውራት፣ ለሰላም የሚስማማ ሥራ መሥራት፣ የራሳችንን ሰላም መጠበቅና የሌላውንም ሰላም አለማደፍረስ ማለት እንደሆነ የነገረን፡፡ የእግዚአብሔር ሰላም ለሁላችን ይሁንልን፡፡ ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *