ታላቁን የሕዳሴ ግድብ አስመልከቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

በአገራችን ኢትዮጵያ የሕዝባችን የዘመናት ድህነትና የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ ለአገራችንም ብልፅግና ሆነ ለሕዝባችን ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ የዕድገት ደረጃ ላይ መድረሱ ከዚያም በላይ ከሦስት ወራት በፊት በግድቡ የመጀመሪያ ሙሌት ተደርጎ ለሕዝባችን የብስራት ድምጽ መሰማቱ ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ደስታቸውን መግለጻቸው ይታወቃል፡፡

በቀጣይም የግድቡ የዕለት ከዕለት ሥራ እየተከናወነ ሕዝባችንም የተለመደ ድጋፉን እያደረገ ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ ተስፋ የተጣለበት መሆኑ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ ሕዝባችን በዚህ ተስፋ ውስጥ በገንዘቡንም በጉልበቱም በሙያውም የበኩሉን ድጋፍ እየተረባረበ ባለበት ወቅት ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በአገራችን ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ግድባችንን አስመለክቶ አገራትን ወደ ግጭትና አለመግባበት ውስጥ የሚከት የጥፋት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመታዊው ጉባኤው ላይ እንዳለ በሐዘን ተመልክቶታል፡፡

የተወደዳችሁ በአገር ውስጥ ሆነ በውጭው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን እና ሌላውም የዓለምም ሕዝብ

ታሪክ እንደሚያስታውሰን አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ውስጥ ታፍራና ተከብራ የኖረችውና ለመላው የጥቁር ሕዝብ ምሳሌ የሆነችው አገሪቱ አገረ እግዚአብሔር ሕዝቡ ሕዝበ እግዚአብሔር በመሆኑና በዚህም የሰውና የእግዚአብሔር አንድነት አገራችን በእግዚአብሔር ተጠብቃ የኖረች አገር መሆኗ ነው፡፡

ከዚህም ጋር በዘመናት አገሪቱን እንዲመሩ የተጠሩ መሪዎችና ሕዝቧ በአገራችን ላይ ይነሳሱ የነበሩ ወራሪዎች ያሰቡት ሳይሳካለቸው አገሪቱ ድንበሯ ከነክብሯ ተጠብቆ የኖረችና የሕዝባችን አገራዊ አንድነት ተጠብቆ የኖረ በመሆኑ ነው፣

ዛሬም ቢሆን ከአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሆነ ከሌሎች ተመሳሳይ አካላት በአገራችን ላይ እየተላለፈ ያለው የጥፋት ጥሪ መተዛዘቢያ ከሚሆን በስተቀር አገራችን ጠባቂዋ በሆነው እግዚአብሔርና በሕዝባችን አንድነት ተከብራና ተጠብቃ እንደምትኖር ሙሉ እምነታችን ነው፡፡

የተወደዳችሁ በአገር ውስጥ ሆነ በውጭው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን እና ሌላው የዓለምም ሕዝብ

አገራችን ኢትዮጵያ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ያላነሱ ልጆቿ እንደየአካባቢያቸውና እንደ አደጉበት አካባቢ የተለያዩ ቋንቋ እየተናገሩ ባሕላቸውንና ሥርዓታቸውን ጠብቀው በመከባበርና በአንድነት መንፈስ እየተረዳዱ የሚኖሩበት እንግዳ በመቀበልና ቤት ያፈራውን ተካፍሎ በመኖር የሕዝባችን ልዩ መታወቂያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡

  • ፍትሐዊ
  • የዓለምም ሕብረተሰብ

አሁንም ከኃያላኑ መሪዎችም ሆነ ሌሎች አገራችንን በሩቅ ሁነው ከሚጎመጇት አካላት እየተጎሰመ ያለው የትፋት ጥሪ ኢትዮጵያን እንደ ትናንት አባቶቻችን በአንድነት በመከባበር በመደማመጥም ጭምር መቆም ከቻልን ከአቅማችን በላይ የሚሆን ነገር እንደሌለ ከእኛ ይልቅ የአገራችንን ዕድገት የማይፈልጉ ከእኛ የበለጠ ይገነዘቡታል፣ ያውቁታልም፡፡

ዓለማችን በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ ያጣችው ነገር ቢሆን ሰላም ነው፡፡ ሰላም እንደሚታወቀው ከአንድ አቅጣጫ ብቻ የሚገኝ ሳይሆን በጋራ ለዓለም ሰላም መቆም ሲቻል ብቻ ነው፡፡

ስለዚህ ይህንን የአገራችን ሰላምም ሆነ ጥቅም ሊያሳጣ በሚችል መልኩ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአገራችን ላይ ያስተላለፉት የጦርነት ጥሪ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይቃወማል፡፡ መላውም የዓለም መንግሥታትና ሕብረተሰብ ችግሩን በጥልቀት እንዲገነዘቡት ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

በአገር ውስጥ ሆነ ከአገር ውጭ የምትገኙ ኢትዮጰያውያን ልጆቻችን እንዲሁም አገር የመምራት ኃላፊነት የተጣለባችሁ የፌደራልና የክልል መሪዎች ከዚህም ጋር በአገሪቱ ውስጥ የምትገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በአሁኑ ጊዜ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን የትኛውንም የየግልና ቡድን አመለካከታችንን ወደ ጎን በመተው አንድነታችንን ልናጠናክርበት የሚገባ ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ኢትዮጵያዊ አንድነታችሁን ከምንጊዜውም የበለጠ ጠብቃችሁ ለአገራችን ሕልውና እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፣ ይቀድስ፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

አሜን!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵሱም

ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

ጥቅምት 16 ቀን 2013 ዓ.ም

አዲስ አበባ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *