በስመ አብ ወወልድ ወንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ከኢትዮጰያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን

ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

     የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቁጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልዓተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ጥቅምት 23 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ በዚሁ መሠረት፡-

  1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በቀረበው የጉባኤ መክፈቻ ንግግር የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ ሆኖ እንዲያገለግል ምልዓተ ጉባኤው ተቀብሎታል፡፡
  2. ለምልዓተ ጉባኤው ቀርቦ ውይይት የተካሄደበት የ39ኛው አጠቃላይ የሰበካ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ጉባኤው ተቀብሎ ያፀደቀው በመሆኑ ለሚመለከታቸው ሁሉ ተላልፎ በሥራ እንዲተረጎም ተወስኗል፡፡
  3. የቤተ ክርስቲያን ወቅታዊ ችግሮች አስመልክቶ በጉባኤው ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ባለፈው አንድ ዓመት በአገራችን በኢትዮጰያ በቤተ ክርስቲያናችንና በቤተ ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ የደረሰው ግፍና መከራ እንዲቆም በየምክንያት በክርስቲያንነታቸው ምክንያት የታሠሩ ካህናትና ምእመናን ጉዳያቸው እየታየ ከታሠሩበት እንዲፈቱ፣ የመንግሥት የበታች ባለሥልጣናትም ለጥፋተኞች ከሚያደርጉት ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ጉባኤው አጥብቆ አሳስቧል፡፡ ከዚሁ ጋር በቤተ ክርስቲያንና በቤተ ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ ላለፈው ለደረሰው ጥፋትና ለወደፊትም የሕግ ክትትል በማድረግ ችግሩን የሚከላከሉ የሕግ ባላሙያዎች ኮሚቴ ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት ድረስ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
  4. ወቅታዊ አገራዊ ሰላምን በተመለከተ ጉባኤው በሰፊው ተነጋግሯል፡፡ በአገራችን ያለው ወቅታዊ የሰላም እጦት፣ እየታየ ያለው አለመግባባት ለዜጎች ተረጋግቶ አለመኖርና ከሁከት አልፎ ተርፎ ለሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት እየሆነ በመሆኑ በቀጣይም አላስፈላጊ ሁከት ውስጥ እንዳይገባ ከወዲሁ እርቅና ሰላም ማምጣት አስፈላጊ መሆኑን ጉባኤው አምኖበታል፡፡ በመሆኑም የእርቅና የሰላም ሂደቱን የሚያስፈጽሙ ብፀዓን አባቶችን በአስታራቂነት ሰይሟል፡፡
  5. በአገራችን ኢትዮጰያ የሕዝባችን የዘመናት የድህነት የኑሮ ጉስቁልና አስወግዶ ለአገራችንም ብልፅግና ሆነ ለሕዝባችን ዕድገት ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ አስመልክቶ ጥቅምት 13 ቀን 2013 ዓ.ም የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አካባቢያዊ ጦርነት እንዲነሣ ያስተላለፉት መልእክት አገራችን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ወይም በሞግዚትነት ለማስተዳደር የተደረገ ሙከራ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ተቃውሞታል፡፡ የዓለምም መንግሥታትና ሕዝቦች እንዲህ ዓይነቱን ትንኮሳና የቅኝ ግዛት ፍላጎት እንዲቃወሙ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
  6. በሕግ ቤተ ክርስቲያኑ አንቀጽ 50 የሚገኘው በአሁኑ ጊዜ ባለው የሀገረ ስብከቱ አሠራር ላይ አመቺ ሆኖ ስላልተገኘ ከሕገ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲወጣና የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት እንደማንኛውም ሀገረ ስብከት ራሱን ችሎ ሊቀ ጳጳስ ተመድቦለት እንዲመራ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡ ከዚህም ጋር አሁን እየተሠራበት ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ከወቅቱ ጋር ተገናዝቦ መሻሻል እንዳለበት ስለታመነ ይኸው እየተሠራበት ያለው ሕግ ቤተ ክርስቲያን መርምረውና አጥንተው መሻሻል የሚገባቸውን ነጥቦች አሻሽለው ወደፊት በቋሚ ሲኖዶስ ከሚመረጡ የሕግ ባለሙያዎች ጋር ሕጉን አሻሽለው ለግንቦቱ ርክበ ካህናት እንዲያቀርቡ ሦስት ብፀዓን አባቶችን ጉባኤው መድቧል፡፡
  7. የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አፈጽረም አስመልክቶ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እየተወሰኑ የተፈጸሙና ያልተፈጸሙትን በመለየት ሊፈጸሙ ያልቻሉበትን ምክንያት ተገልጾ ለፊታችን ግንቦት ርክበ ካህናት ውጤቱ እንዲቀርብ መመሪያ ሰጥቷል፡፡
  8. የብፀዓን አባቶች የሥራ ምደባና ዝውውር በማስፈለጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያለውን ሀኔታ ከመረመረ በኋላ በአገር ውስጥና በአገር ውጭ ዝውውርና የሥራ ምደባም ተካሂዷል፡፡
  9. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በቆጋ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ተከስቶ የነበረውን የዶግማና የቀኖና ጥሰት አስመልክቶ ችግሩ በአጣሪ ልዑካን እንዲጣራ ተደርጎ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በመንፈስ ቅዱስ ጵጵስና ተሹመናል ያሉት መነኮሳት የፈጸሙት ድርጊት አግባብነት የሌለው ከሕገ ቤተ ክርስቲያን ውጭ ሆኖ ስለተገኘ መነኮሳቱ በራሳቸው የለበሱት ልብሰ ጵጵስናና የጵጵስና ቆብ አውልቀው ንስሓ ተሰጥቷቸው በምነኩስናቸው ብቻ ተወስነው በገዳሙ በቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንዲኖሩ ተወስኗል፡፡ ከዚሁ ጋር ተፈጸመ የተባለው ዳግም ጥምቀትና ክህነት ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ውጭ የሆነና ቤተ ክርስቲያናችን የማትቀበለው በመሆኑ ይህንን ድርጊት የፈጸሙ ሁሉ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
  10. የኦሮሚያ ቤተ ክህነት አደራጅ ኮሚቴ ነን ከሚሉ አባላት ጋር በተደረገ ውይይት መግባባት ደረጃ ላይ በመደረሱ ክህነታቸው የተያዘ ካህናት ክህነታቸው ተለቆ በቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ውስጥ የሥራ መደብ ተሰጥቷቸው እንዲያገለግሉ ተወስኗል፡፡
  11. የቤተ ክርስቲያኒቱ የ2013 ዓ.ም አጠቃላይ በጀት ላይ የተነጋገረው ምልዓተ ጉባኤ ከበጀትና ሂሳብ መምሪያ በቀረበው የበጀት ድልድል ላይ ተነጋግሮ ማስተካካያዎችን በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል አጽድቋል፡፡

    የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከላይ በተጠቀሱ ነጥቦች እና እንዲሁም በወቅታዊ አገራዊ ጉዳይ ላይ በስፋት ተነጋግሯል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች የደረሰው ጎርፍ መጥለቅለቅና የአንበጣ መንጋ በበርካታ ወገኖቻችን ላይ ያደረሰው ችግር ከፍተኛ መሆኑን ጉባኤው ተገንዝቧል፡፡ በመሆኑም ሕብረተሰቡ ለተቸገሩ ወገኖቻችን የተለመደ ድጋፉን ከማድረግ ወደ ኋላ እንዳይል ምልዓተ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡

     በአገራችን በኢትዮጵያ በዓለማችንም ጭምር እየታየ ያለው አለመግባባት፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የበሽታ ወረርሽኝ የመሳሰሉት ሁሉ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ ተመልክቶ ሰላሙንና አንድነቱን ለዓለማችንና ለሕዝባችን ይሰጥልን ዘንድ ከኅዳር 1-7 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ በመላ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡

በመጨረሻም፡-

    አገራዊ ሰላምና አንድነት አስመልክቶ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በወሰነው መሠረት የእርቅ ሂደቱ የሚቀጥልበት ሆኖ ከዚሁ ጋር የፌደራል መንግሥቱ፣ የየክልል መሪዎች እንዲሁም መላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለአገራችን አንድነትና ሰላም ለልማቱና ለሕዝባዊ አንድነቱ በጋራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን እያቀረበ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ከጥቅምት 11 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለ13 ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ በጸሎት አጠናቋል፡፡

ሰላመ እግዚአብሔር ከሁላችን ጋር ይሁን

እግዚአብሔር አገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይጠብቅ፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *