ሕይወትን በማስተዋልና በዓላማ ስለመምራት

ዲያቆን መዝገቡ ዘወርቅ

“ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፤ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፡፡” (1ኛ ቆሮ. 9፥26)

በማስተዋልና በዓላማ የሚመራ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ የተሰበሰበ ኑሮ (Focused Life) የሰውን ልጅ በሥጋም በነፍስም ስኬታማ የሚያደርግ እና በተፈጥሮአችን የተሰጠንን አቅም ተግባራዊ ለማድረግ የሚረዳን የኑሮ መሥመር ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ ሕይወታችንን እግዚአብሔር ወደሚደሰትበት መልካም አቅጣጫ ለመምራት የሚጠቅሙንን መንገዶች ለመዘርዘር እንሞክራለን፡፡

  1. ራስን ዘወትር መመርመር

“ነገር ግን እያንዳንዱ የገዛ ራሱን ሥራ ይፈትን፡፡” (ገላ. 6፥4)

ጥሩ ለውጥ የሚጀምረው በቅን ልቡና እና በሰከነ መንፈስ ነገሮች ሁሉ እየሄዱበት ያለውን አቅጣጫና ሥርዓት ለመታዘብ፣ ለመመርመር እና ለመረዳት ከመፈለግ፣ ከመነሣሣት እና ከመምከር ነው፡፡ ብናስብበት ይህ ለሁላችንም ከባድ ነገር አይደለም፡፡ ብዙ ጥረትም አይጠይቅም፡፡ ልክ ሳሎን ውስጥ ተመቻችተን ተቀምጠን ቴሌቪዥኑ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን እንደምናጤነው እና እንደምንከታተለው ሁሉ ሕይወታችንንም እንደዛው ገለል ብለን፣ በመሐል በመሐል የተወሰነ ጊዜ እየወሰድን በሕሊናችን፣ በልባችን እና በነፍሳችን ዙሪያ ሕይወት ያጠላችውን ብዥታ የበዛበት ጉምና ጭጋግ በድፍረት እንደ መጋረጃ ገለጥ አድርገን የኑሮአችንን፣ የማንነታችንን፣ የፍልስፍናችንን እና የእምነታችንን የምስል ቅንብር እንደ ሌላ ሰው ሆኖ መመልከት፣ ማስተዋልና መታዘብ ነው፡፡

ሕይወታችንን በቅንነት እና በየዋህነት ስንታዘበው ብዙዎቻችን ደስ አንሰኝበትም፡፡ እንዴት እንደሚሆን በትክክል ባይገባንም ብዙ ነገሮች መለወጥ እና መስተካከል እንዳለባቸው ውስጣችን ይነግረናል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ራሱን ቢፈትሽ እና ቢታዘብ በተደጋጋሚ የሚከተሉትን ደስ የማይሉትን ነገሮች በሕይወቱ ውስጥ ሊያስተውል ይችላል፡፡

ክርስቲያን እንደሆንኩ ሰዎች ቢያውቁም፣ ለራሴም የምነግረው ነገር ቢሆንም እምነቴ ግን ሥር ያልሰደደ እና የተለመደ ነው፡፡ በክርስትና ሕይወት በተለይ ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት የሚገኘው ደስታ አልታይህ ይለኛል፡፡ ስላልታየኝ እና ስላልቀመስኩትም ለማመን እና ለመቀበል ከባድ ይሆንብኛል፡፡ በአንጻሩ ግን እንደፈለግኩት በመሆን፣ በጓደኞቼ ዘንድ በመወደድና በመከበር፣ በምኞትና በመዝናናት በማገኘው የነጻነት እና የደስታ ስሜት ስለማየው፣ ስለምቀምሰው፣ ጓደኞቼ እንዲሁም ሳይንሳዊ አእምሮዬ ጭምር ሰለሚመሰክርለት በቀላሉ ያሳምነኛል፣ እኔም በቀላሉ እጄን እሰጥለታለሁ፡፡ መደሰት ቢሆንም የምንጊዜም ፍላጎቴ እየተንሰፈሰፍኩ የምቃርማቸው ጊዜያዊ ደስታዎች ግን ነገና ከነገ ወዲያ ላጣጥማቸው ያቀድኳቸውን ከፍ ያሉ ደስታዎች ሲነጥቁኝ ይታወቀኛል፡፡ በዚህ የተነሳም ውስጤ ይከፋፈላል፡፡ የደስታ ምንጭ ናቸው ብዬ የማምንባቸው ነገሮች እርስ በእርሳቸው ሲጋጩና ሲጣረሱ ሳይ የነበረኝ ብሩህ ተስፋ ሁሉ ይጨልማል፣ የሆነ ደስ የማይል ፍርሃት እና እምነት የማጣት ስሜት በውስጤ ይጠነሰሳል፡፡ ይህን ፍርሃቴን እና መከፋፈሌን ለመሸሽ ስል የበለጠ ጊዜያዊ የደስታ እና ራስን የማደንዘዣ መንገዶችን ማዘውተር እጀምራለሁ፡፡ እውነተኛ ፍርሃቴን የሚያስታውሱኝን ሰዎችን፣ መጻሕፍትን፣ ቦታዎችን እና የገዛ ራሴን አሳቦች ሳይቀር እሸሻቸዋለሁ፤ አልፎ አልፎም እጠላቸዋለሁ፡፡ በዚህ የተነሳም ውስጤ እውነተኛ ሰላሙን ያጣል፡፡ ምክንያቱም ልብ፣ ነፍስና አእምሮ ካልታረቁ፣ የእውነት ተነጋግረው ካልተግባቡ እውነተኛ ሰላም የሚባል ነገር አይታሰብምና፡፡ ሰላምና እረፍት ማጣት፣ እንዲሁም በውስጤ ተሸክሜ የምዞረው ያልተጋፈጥኩት እና እልባት ያጣሁለት መከፋፈል ደግሞ በሙሉ ትኩረት፣ ኃይልና የራስ መተማመን የዕለት ከዕለት ሥራዬን እንዳልሠራ እንቅፋት ሆኖ ሲጋረጥብኝ አስተውላለሁ፣ እታዘባለሁ ብሎ ሊያስብ ይችላል ፡፡

ቆም ብሎ ራስን መታዘበ እና መመርመር ሲባል ሌላ ተአምር ሳይሆን ዕለት ዕለት ቤተ ክርስቲያን የምታስታውሰን የምታዘክረን ጉዳይ ነው፡፡ እርሱም የንስሓ የመጀመሪያው ደረጃ ነው፡፡ ከራስ ጋር እውነተኛ እና ልባዊ ንስሓ መግባት ከተቻለ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ ያለው የምስጢረ ንስሓ ፍራቻ ድካም የፈጠረው አስፈሪ ቅዠት ስለሆነ እንደ ጉም ተኖ መጥፋቱ የማይቀር ነው፡፡ ከራስ ጋር የሚደረግ ንስሓ የሚጀመረው ድካምን እና ጉድለትን፣ እውቀትንና ብስለት ማጣትን አምኖ ከመቀበል ነው፡፡ ይህ ደግሞ የሰው ልጅ በራሱ ጥረት ብቻ ወደ እውነተኛ ድኅነት እና ደስታ መድረስ እንደማይችል፣ ይልቁንስ ከኃጢአት፣ ከስንፍና እና ከድካም ባርነት ነፃ ወጥቶ ከደስታዎች ሁሉ በላይ ለሆነው የእግዚአብሔር የክብሩ ወራሽነት፣ የባህርይው ተካፋይነት መድረስ እና መብቃት የሚቻለው በራሱ በእግዚአብሔር ጸጋ አጋዥነት እንደሆነ ከልብ ማመን እና መቀበልን ያጠቃልላል፡፡ በእርግጥ እንደዚህ ያለው ለክርስትና ሕይወት ምሰሶና መሠረት የሆነው እምነት በተለይ የ21ኛ ክ/አመን ልጆች ለሆንነው ለእኛ በቀላሉ የምናገኘውና የምንረዳው አይሆንም፡፡ ይሄ ደግሞ በአንድ በኩል ሲያዩት አይገርምም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ጥሩ ለውጥ እውን ለመሆን ጊዜ እና ጥረት ይወስዳልና፡፡

  1. እውነተኛ ዓላማ፣ ግብ እና ስኬትን በሚገባ ማወቅና እነርሱን ጸንቶ መከተል

“በበጎ ሥራ በመጽናት ምስጋናን እና ክብርን የማይጠፋንም ሕይወት ለሚፈልጉ የዘላለም ሕይወት ይሰጣቸዋል፡፡” (ሮሜ. 2፥7)

ትኩረት ለማጣት መሠረታዊ ከሆኑት ችግሮች ዋነኛው በሚሠሩት ሥራ እና በሚኖሩት ኑሮ ከራስ ወዳድነት እና ከጥቅም አሳዳጅነት ወይም ለመኖር ካለ ጉጉት እና ፍርሃት የዘለለ ወይም ከተራ የውድድርና ከማን አንሳለሁ ባይ እልህ ያለፈ ላቅ ያለ የበሰለና የሰላ ትርጉም ወይም ዓላማ ማጣት ነው፡፡ ሕይወቱ ትርጉም የማይሰጠውና ይህ ነው የሚለው ትልቅ ዓላማና ራዕይ የሌለው ሰው ደግሞ ለነገሮች ሁሉ ያለውን እምነት እና ተስፋ ይነጠቃል፡፡ ምክንያቱም ዓላማ ላለመኖሩ እና በሕይወቱ ትርጉም ለማጣቱ መሠረቱ ከልብ የሚያምንበትና የሚታመንለት፣ ነፍሱ የተማረከችለት ከራሱ ፍላጎት በላይ የሆነ አንዳች ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ሰው ኑሮው አሳዛኝ ጦርነት ነው ማለት ይቀላል፡፡ በዚህ ጦርነት ደግሞ እርሱና ፍላጎቱ በአንድ ወገን ዓለም በሞላና በዙሪያው ያሉት ሰዎች ደግሞ ሊውጠው እንደሚያገሳ አንበሳ በሌላ ወገን ይሰለፋሉ፡፡ ይህ ሰው ሙሉ እምነቱን እና ተስፋውን በራሱ ጥበብና ኃይል ላይ ስለጣለ ሁሌም በሚከበው የጭንቀት እና የፍርሃት፣ እንዲሁም የብቸኝነት ባሕር ውስጥ ይዋኛል፡፡ እንዲህ በመጨነቅና ነገ ምን ይገጥመኝ ይሆን በሚል ፍርሃት እና ስጋት ተይዞ ብዙ መጓዝ ይከብደዋል፡፡ በመጨረሻም ጭንቀቱ፣ ፍርሃቱ፣ በውስጡ የሚብላላው ትርጉም ማጣቱና መከፋፈሉ እየከበደው ሄዶ የራስ መተማመን እና ተነሳሽነቱን በአጠቃላይ ትኩረቱን እና የመሥራት ፍላጎቱን አሽመድምዶ እጅ አልሰጥም በሚል ብቻ የሚንገዳገድ፣ ሕይወት ያደከመችው ጎስቋላና ምስኪን ሰው እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ እንደገና ኃይሉን እና ትኩረቱን ለመመለስ ይህ ሰው ከላይ መጀመሪያ ላይ እንደተነሳነው ድካሙን አምኖ ከመቀበልና ለለውጥ ከመዘጋጀት ቀጥሎ የሚኖርለት፣ የሚያምንበት እና ካስፈለገም መሥዋዕትነት የሚከፍልለት ከተራ ፍላጎቱ እና ራስ ወዳድ ምኞቱ ውጭ የሆነ ዓላማ ወይም የእምነት መሠረት ለማግኘት መንቀሳቀስ፣ ጉዞ መጀመር ይኖርበታል ማለት ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ደግሞ እምነታችንን እና ተስፋችንን የምንጥለው በእግዚአብሔር ሲሆን የኑሮ ዓላማችንም እግዚአብሔርን መምሰል እና የክብሩ ተካፋይ መሆን ነው፡፡ እሱን ለመምሰል እና የክብሩ ተካፋይ ለመሆን ደግሞ እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም አሳብህ፣ በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህና በፍጹም ኃይልህ ውደደው፤ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ በሚሉት ሁለት ዓበይት ትእዛዛት ሕይወታችንን መቃኘት ያስፈልጋል፡፡

የክርስትና ሕይወት የመገለጥ ሕይወት ነው፡፡ ለዚህም ነው ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን እና የምትሰብካቸውን ትእዛዛት፣ ቀኖናዎች፣ ምስጢራትና አስተምህሮዎች እያንዳንዳችን የምንጠቀመባቸው እንደተረዳናቸው እና እንደተገለጠልን መጠን ብቻ የሚሆነው፡፡ እግዚአብሔር ለማንም ከልቡ ለሚጠይቀው፣ በቅንነት በሩን ለሚያንኳኳ፣ በትዕግስትና በትጋት ለሚፈልገው ሁሉ ለእያንዳንዱ በሚጠቅመውና በአቅሙ መጠን ምስጢራትን ይገልጥለታል፤ መረዳትን እና መንፈሳዊ እውቀትን ደስታንም ይጨምርለታል፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገለጥበት፣ የሚነጋገርበት፣ በአጠቃላይ የልቡናን እና የአእምሮን በር የሚያንኳኳበት መንገድ እጅግ ብዙ፣ ለእያንዳንዳችንም የተለያየ ነውና ከእኛ የሚጠበቀው በየዕለቱ እገዛና ምክር፣ የነፍስ ስንቅ ፍለጋ መጻሕፍትን ማንበብ፣ ሰዎችን ማማከር፣ ቃለ እግዚአብሔርን መስማት፣ መንፈሳዊ ቦታዎችን መሳለም፣ ተፈጥሮን ማስተዋልና መመርመር ነው፡፡ በምርመራችን እና በአስተውሎታችን በአጠቃላይ በዕለት ከዕለት ገጠመኞቻችን ውስጥም ረቂቅ በሆነ መንገድ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኛ ሲመጣ እና ውስጣችንን ሲያነሳሳው ተገቢውን ምላሽ መስጠት፣ አጋጣሚውን በልባችን መዝገብ ውስጥ ማስፈር፣ ጸጋውንም ተገንዝቦና ተረድቶ ለመልካም ተግባር የሚገፋፋ ከሆነም ወዲያውኑ ወደ ተግባር መለወጥ ይገባል፡፡ እንዲህ ከእግዚአብሔር ጋር እየተነጋገሩ፣ ጸጋውን አጋዥ እና ድጋፍ እያደረጉ እግዚአብሔርን በማወቅ ማደግ ያስፈልጋል፤ እርሱም የዘላለም ሕይወት ነው፡፡ በወንጌል “እውነተኛ አምላክ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት፡፡” (ዮሐ.17፡3) እንደተባለ፡፡ በየጊዜው ልባችንን ለእግዚአብሔር የበለጠ በሰጠን፣ ቅናታችን እና ፍላጎታችን የበለጠ እየተቀጣጠለ እና እያደገ በመጣ ቊጥር ጣዕሙን እና ደስታውን የበለጠ እየቀመስነው እየተረዳነውና እያጣጣምነው በዚህም መልኩ እስከዘላለም ድረስ እያደግን የበለጠ እየተገለጠልን የምንኖርበት የማያቋርጥ የለውጥና የእድገት ሕይወት ይኖረናል ማለት ነው፡፡

  1. የእግዚአብሔርን አጋዥነት በማመን አቅማችን ከፈቀደው፣ ከጥቂቱ እና በአቅራቢያችን ካለው ሥራ መጀመር

“ሁለት መክሊትም የተቀበለው ደግሞ ቀርቦ፥ ጌታ ሆይ፥ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ አነሆ፥ ሌላ ሁለት መክሊት አተረፍሁበት አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም፥ አንተ በጎ፥ ታማኝም ባሪያ፤ በጥቂቱ ታምነሃል፥ በብዙ እሾምሃለሁ፥ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡”                                                      (ማቴ. 25፥22-23)

ብዙዎቻችን በተሳሳተ አረዳድ ተመርተን አንድን ሥራ ለመሥራት አስቀድሞ ለሥራው ፍቅር እና መነሣሣት እንደሚያስፈልግ እናምናለን፡፡ በዚህ አስተሳሰባችን የተነሳም መነሣሣታችን እና የሥራ ፍላጎታችን የሚቀጣጠልባት ያችን የሕልም ቀን ስንጠባበቅ የረባ አንጀት የሚያርስ ሥራ ሳንሠራ ዕድሜያችን ይገባደዳል፡፡ በእግዚአብሔር እምነቱን የጣለ ሰው ግን እግዚአብሔር በጀመርነው ሥራ ውስጥ ቀርቶ ከዓለት ላይም ውኃ ማፍለቅ እንደሚቻለው በማመን አጠገቡ ያለውን በጊዜው የታዘዘውን እና የሥራ ድርሻውን ማንኛውንም ተግባር ይጀምራል፡፡ በኋላ እግዚአብሔር በሥራው ውስጥ ለእርሱ ብቻ የሚገለጥ እርሱ ብቻ ጣዕሙን የሚያውቀው ጸጋና ምስጢር እንደሚገልጥለት በማመን፣ ስለሥራውና ስለሕይወቱ፣ ስለፍላጎቱና ስለስሜቱ ከሚገባው በላይ አብዝቶ በማሰብ እና በመፈላሰፍ ሳይጨነቅ በቀጥታ ያለችውን ትንሽ ኃይልና ተስፋ ይዞ ወደ ሥራው ይገባል፡፡ በእርግጥም እግዚአብሔር ለዛ ሰው በእምነት በሚጀምረው ሥራ ውስጥ ያነጋግረዋል፣ ምስጢራትን ይገልጥለታል፣ መነሳሳቱን እና ለሥራው ያለውን ፍቅር ቀስ በቀስ ያቀጣጥልለታል፡፡ የመንፈስ ደስታ፣ የልብ ሙቀት እና የነፍስ ሐሴት፣ የአእምሮ እርካታ ያቀምሰዋል፡፡ ያንን በትንሹ የታመነ ሰው እግዚአብሔር ለትልቅ ነገር ያጨዋል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሌላ ነገር ሳይሆን ያ ሰው የጥሩ ሥራ ሽልማቱ ብዙ ሥራ ተጨማሪ ሥራ ነው እንደሚባለው በእምነት በጀመራት ትንሽ ሥራ እምነቱ ስለጠነከረለት እና አዲስ ደስታንና ምስጢርንም ስላየና ስለቀመሰ የበለጠ እምነቱን ለማጠንከር እና የላቀውንም ደስታ ገንዘብ ለማድረግ በያዘው ሥራ ይቀጥላል፤ ሌላ ከበድ ያለ ሥራንም ለመጀመር ይደፋፈራል፡፡ በእምነት በተጀመረ ሥራ እግዚአብሔር የሚገልጠውን ድንቅ ምስጢር ያውቃልና፡፡

  1. በሥራችን ውስጥ አብሮ የሚሠራውን የእግዚአብሔርን እጅ ማስተዋል፣ ጸጋውንም በምስጋና መቀበል

“ትምክህታችን ይህ ነውና፤ በእግዚአብሔር ጸጋ እንጂ በሥጋዊ ጥበብ ሳይሆን በእግዚአብሔር ቅድስናና ቅንነት በዚህ ዓለም ይልቁንም በእናንተ ዘንድ እንደኖርን የኅሊናችን ምስክርነት ነው፡፡” (2ኛ ቆሮ.1፥12)

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ሥራ ከጀመርን በኋላ ቀስ በቀስ በውስጣችን አንዳች ደስ የሚል መንፈስና ኃይል ሲንቀሳቀስ፣ ሲገፋፋን እና ሲያበረታታን ካልታወቀን ያንን ሥራ በተገቢው መንፈስ እና መንገድ እየሠራነው አይደለም ማለት ነው፡፡ በሂደት ፍላጎታችን ሁሉ ጠፍቶ ትኩረታችንም ተበታትኖ ሥራው የደስታ ምንጭ መሆኑ ቀርቶ የስቃይ ምልክት መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ በእምነት በትክክለኛ መንፈስ የተቃኘ ሥራ ግን ቀስ በቀስ መንፈሳዊ ደስታን እና መነሣሣትን በውስጣችን እያቀጣጠለ ሥራውን በሙሉ ልብ እና በተመስጦ እንድንሠራው ከማድረጉም በላይ ሥራውን ከጨረስን በኋላ በእምነት እና በኃይል የበለጠ ጠንክረን ሌላ ሥራ በደስታ ለመቀበል የተዘጋጀን እንድንሆን ያደርገናል፡፡ በእምነትና በትክክለኛ መንፈስ የሆነ ሥራ ሲሠራ በሚሠራው ሥራ እግዚአብሔር ስለሚደሰት ሠሪውም ዓላማው የሆነውን እግዚአብሔርን መምሰል፣ ለእግዚአብሔር መታመን እና የእግዚአብሔር የክብሩ ወራሽ መሆንን በትንሽ በትንሹ ስለሚያሳካበት ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ሥራ በመጀመሪያ እግዚአብሔር አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ ነፍስህ፣ አሳብህና ኃይልህ ውደደው የሚለው ዐቢይ ትእዛዝ ይፈጸምበታል፡፡ ምክንያቱም አንድ ክርስቲያን ሥራውን ሲሠራ አሳቡን እና ጭንቀቱን ሙሉ በሙሉ በወላጆቹ ላይ ጥሎ በሕይወቴ ምን ይመጣብኝ ይሆን ብሎ ጭንቀት እንደማይገባው ሕፃን ልጅ ወይንም ለነገ ምን እንመገባለን ብለው እንደማይጨነቁ የሰማይ ወፎች በመሆን ሥራው ባይሳካልኝስ፣ ቢያቅተኝስ፣ ባልጨርሰውስ ብሎ ሳይጨነቅ፣ ፍርሃት ሳይገባው በሙሉ ልቡ ሥራውን በእርጋታ ይሠራል፡፡ እናም በፍጹም ልቡ ሥራውን እየሠራ በእግዚአብሔር ጸጋ በመታመን እግዚአብሔርን ያሥደስታል፡፡ ይህ ሰው በሚሠራው ንጹሕና ከኃጢአት የራቀ መልካም ሥራ ነፍሱም በፍጹም ደስታ የሥራውን መንፈሳዊ አንድምታ በመረዳት አብራ ትሳተፋለች፡፡ በዚህም ይህ ሰው በፍጹም ነፍሱ እግዚአብሔርን ያሥደስታል፡፡እርሱም በሥጋውና በነብሱ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አሳቡም እንዲሁ ከተንኮል እርቆ ይልቁንም ሥራው የሚጠይቀውን እውቀትና ጥበብ በመረዳትና በማሰላሰል አልፎም ለሰዎች የሚጠቅሙ ችግር የሚፈቱ፣ ጊዜ የሚቆጥቡ ዘዴዎችን በመፍጠር የጥበብና የፈጠራ ተቋዳሽ በመሆን በዚህም እግዚአብሔርን መምሰልን የክብሩ ወራሽነትን በምድር ላይ በትንሹም ቢሆን በመቅመስ በፍጹም አሳቡ እግዚአብሔርን ይወዳል ያከብራልም፡፡ እንዲሁም የሰውነቱን አቅም አሟጥጦ የሚበላበትን እና የሚጠጣበትን የሚተኛበትን ሰዓት ሳይቀር ዘንግቶ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በመሥራት በዚህም በውስጡ የሚንቀሳቀሰው እና የሚያነሳሳው የእግዚአብሔር መንፈስ ምግብ ሆኖት “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም::” (ማቴ. 4፥4) ተብሎ የተጻፈው ቃል በሕይወቱ ሲተረጎም እያየ በፍጹም ኃይሉ ሥራውን ይሠራል፡፡ የሚሠራው ሥራ ለራሱ ክብርና ዝና፣ ጥቅምና ምቾት ሳይሆን በዋናነት ለሌሎች የሚጠቅምና አገለግሎት የሚሰጥ የሥጋና የነፍስ ምግብ የሚሆን ቢሆንም እርሱ ግን ለራሱ ጥቅም እንደሚውል የራሱ ጉዳይ እንደሆነ አድርጎ በመሥራት “ባልንጀራህንም እንደ ራስህ ውደድ” (ሉቃ.10፥27) የተባለችውን ሁለተኛዋን ዐቢይ ትእዛዝ በተግባር ይገልጥበታል፡፡ በዚህም እግዚአብሔርን የበለጠ ያሥደስታል፡፡ እርሱም እግዚአብሔርን በማክበር እና አርአያውን ፈለጉን በመከተል የሚገኙትን ላቅ ያሉ ምስጢራት እና የመንፈስ ደስታዎች ይቀምሳል፡፡ በዚህም ተስፋው ይታደሳል እምነቱም በዓለት መሠረት ላይ እንደተሠራ ቤት የጠነከረ ወጀብና አውሎ የማያናውጠው ይሆናል፡፡ ሕይወቱም የተረጋጋ ከባካናነት የራቀ እና ስኬታማ ይሆናል፡፡

አንድ ክርስቲያን በቅንነት፣ በየዋህነት፣ በመንፈሳዊ ጥበብና ዕውቀት በመመራት እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ሲንቀሳቀስ፣ አካባቢውን በአርምሞ እና በተደሞ ሲያስተውል፣ በሥራ ሲጠመድ እና በዚህ ሁሉ መሀል እዝነ ልቡናውን አንቅቶ የእግዚአብሔርን ድምፅ ሲጠባበቅ ከሚሰማቸው፣ ከሚቀምሳቸውና ከሚገለጡለት ድንቅ ምስጢራት፣ ተአምራት፣ ጥበባትና ጸጋዎች የሚያገኘው የመንፈስ ደስታ፣ የአእምሮ እርካታ እና የነፍስ ሐሴት በውጭ ሆኖ ለሚያይ ሰው የማይቻሉ የሚመስሉ ውጫዊና ውስጣዊ ፈተናዎችን እንዲቋቋም ያስችለዋል፡፡ የዚህ ክርስቲያን ሕይወት ውጫዊ ሁኔታውን እና አካባቢውን አይተው ሲመዝኑት በስቃይና በመሥዋዕትነት ብቻ የተሞላ ደስታና ነጻነት የተለየው ይመስላል፡፡ እርሱ ግን በውስጡ በሚሰማው የተለየ ደስታና ኃይል ሕይወቱ በጸጋ እና በሐሴት እንደተሞላች ያያል እግዚአብሔርንም ያመሰግናል፡፡ ክርስትናም የስቃይ ሕይወት ሳይሆን የላቀውን ደስታ የመምረጥ ሕይወት እንደሆነ በተግባር ይረዳል፡፡

ይህ ሰው አንዳንዴ ጤነኛ የሚባል ዓይነት ሰው የማይደፍራቸውን እና የማይሞክራቸውን እብድ ሊያሰኙ የሚችሉ ነገሮችን ሲናገር ወይም ሲያደርግ ሊታይ ይችላል፡፡ እርሱ የሚመራበት እና የሚከተለው በውስጡ የሚንቀሳቀሰውን የእግዚአብሔር ጸጋ እና መነሣሣት እንጂ ሰዎች ምን ይሉኛል የሚል የይሉኝታ ስሜትን ወይንም ይህን በማድረጌ ሰዎች ቢሳለቁብኝስ፣ ቢያገሉኝስ የሚል የፍራቻ ስሜትን አይደለም፡፡ ለእኛም ለእያንዳንዳችን የእግዚአብሔን ጸጋውን እና መነሣሣቱን የምንቀበልባቸው መንገዶች እና ጥሪዎች የተለያዩ በመሆናቸው አንዳንዴም ከጓደኞቻችን እና በዙሪያችን ካሉ ሰዎች መለየትን፣ ወጣ ማለትን፣ እምቢ ማለትን፣ ጠንካራ አቋምንና መመሰጥን የሚጠይቁ ሊሆኑ ስለሚችሉ በይሉኝታ እና በምን ይሉኛል አጉል ፍራቻ ተተብትበን ከፍ ወዳለ መንፈሳዊ እድገት ሊያቀርበን የሚችለውን የእግዚአብሔርን ጸጋ ሳንቀበል፣ ሳንጠቀምበት መቅረት የለብንም፡፡ አለበለዚያ ግን እንደዚህ ባሳለፍናቸው ገጠመኞችና ችላ ባልናቸው የእግዚአብሔር ስጦታዎች የተነሣ ሥራችን እና ኑሮአችን በውስጣችን መነሣሣትን የማይጨምር መንፈሳዊ እድገት እና ደስታ የተለየው አሰልቺ ሆኖብን በሙሉ ልብ እና በትኩረት መሥራት ሊያዳግተን ይችላል፡፡

  1. ከምናብ ዓለም እና በግብታዊነት ከሳልናቸው ሕልሞች ወጥተን የምንችለውን እና የተፈቀደልንን ሥራ በትሕትና መሥራት

“እርስ በርሳችሁ በአንድ አሳብ ተስማሙ፤ የትዕቢትን ነገር አታስቡ፤ ነገር ግን የትሕትናን ነገር ለመሥራት ትጉ፡፡ ልባሞች የሆናችሁ አይምሰላችሁ፡፡” (ሮሜ. 12፥16) 

ሌላው ብዙ ጊዜ ትኩረት ለማጣታችን ምክንያት የሚሆነው የምንገኝበት ቦታ እና ሁኔታ፣ የምንሠራው ሥራ፣ የምናገኘው ገቢ እንዲሁም የስኬት ደረጃ እኛ በምናባችን እና በሕልማችን ከልጅነታችን ጀምሮ በምኞት ብቻ እየኮተኮትን እና ውኃ እያጠጣን ሰማይ ካደረስነው ልንሆነው እና ልንደርስበት ከምንመኘው የስኬት ጫፍ፣  ክብርና ዝና ጋር የሰማይና የምድር ያክል የተራራቀ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የተነሣ የምንሠራው ሥራ ክብሩ ዝቅ ስለሚልብን የምንወደውና ያለምንለት ስላልሆነ ያስቸግረናል፡፡ በሙሉ ልባችን ልንሠራው ይከብደናል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ የልጅነት ምኞታችን በመሆኑ ማማረራችን ሳያንስ እኛነታችን ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማነፃፀር አንደኛ ወይም መሪ ሆነን ካልተገኘን፣ የምንፈልገውን ያክል ካልተከበርን በቅናት እና በጥላቻ ስሜት ይያዛል፤ መበለጣችን ያመናል፡፡ የበለጡንን፣ የቀደሙንን ሰዎች ምንም ሳይበድሉ ያለ ምንም ምክንያት እንጠላቸዋለን፡፡ ይህም ሥራችንን እንድንጠላ ከማድረጉ ባሻገር የሥራ ቦታችንን የቁም እስር ቤት፣ ከሥራ ባልደረቦቻችንን ጋር ተናቦ እና ተጋግዞ መሥራትን ደግሞ ከጠላት ጋር ማዕድ የመካፈል ያክል ያከብድብናል፡፡

ክርስቲያን ግን እንዲህ አያስብም፡፡ ልቡ ትሕትናን ገንዘብ ስለምታደረግ እና በየጊዜው ራሷን ስለምትፈትሽ እግዚአብሔር በፈቀደለት፣ በባረከለት፣ በእጁ ላይ ባለው ትንሽ ነገር ይታመናል እንጂ ያለ ቅጥ የተለጠጠ እና አቅምን ያላገናዘበ ምኞት አይኖረውም፡፡ በማይችለውና በማይወደው ሥራ ገብቶ አያማርርም፡፡ ምክንያቱም ክርስቲያን ማለት የአንድ አካል ብልት እንደሆነ እና በዚህም ምክንያት እግር እኔ መራመድ አይመጥነኝም ማየት ነው የምፈልገው ብሎ እንደማይለው ሁሉ የሚችለውን ስጦታው የሆነውን ሥራ ይፈልጋል እንጂ የማይችለውን እና ተሰጥኦው ያልሆነውን ሥራ ክብሩን ከፍ ለማድረግ፣ ሆዱን ለመሙላት ወይም ከሰዎች ላለማነስ በሚል እችላለሁ እሠራለሁ ብሎ አይገባም፡፡  በተሰማራበት ሥራ የሚበልጠው ሰው ቢያጋጥመውም በዚያ ተናዶ ልክ አንድ መክሊት ተሰጥቶት ጌታውን እንዳሳዘነው ክፉ አገልጋይ መክሊቱን ሳይቀብር ይልቁንስ ለእኔ ለምን አምስት መክሊት አልተሰጠኝም ብሎ ሳይቀና እና ሳያማርር በተሰጠው ሁለት መክሊት ነግዶ እንዳተረፈው ትጉህ አገልጋይ በአቅሙ በተሰጠው ስጦታ የቻለውን ለማትረፍ ይሠራል፤ ከተሻለው ከሚበልጠው ወንድሙም እገዛና ምክርን በየጊዜው በመጠየቅ እንዲያም ሲል ተጋግዞ እና ተባብሮ የተሻለ ላቅ ያለ ሥራ በመሥራት በፍቅር ይኖራል፡፡ እንደዚህ በማሰቡም የራሱን የሥራ ድርሻ ለይቶና ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ ሁሉንም ልሥራ ሁሉንም ልጨብጥ አይልም፡፡ እርሱ በራሱ ሥራ እንደሚታመነው ሁሉ ሌሎች ሰዎችም ስጦታቸው እና ድርሻቸው የሆነውን ሥራ በአግባቡ እንደሚወጡ ያምናቸዋል፡፡ በሌሎች ከመቅናት ጥላቻና ቂምን ከመጠንሰስ ይልቅ የአንድ አካል ብልቶች አንዱ ሲታመም ሌሎቹ ህመሙ እንደሚሰማቸው አንዱ ሲደሰት ሌሎቹም አብረው የደስታው ተካፋይ እንደሚሆኑት እርሱም ከሚያዝኑት ጋር ያዝናል ከሚጨነቁት ጋር ይጨነቃል ኀዘናቸውን እና ጭንቀታቸውን ለማቅለልም የቻለውን ያደርጋል፡፡ ከሚደሰቱት ጋርም በሙሉ ልቡ ደስታቸውን ደስተው አድርጎ ይደሰታል፡፡ በዚህም ውስጡ ሰላም እና ጸጋ የተሞላ፣ ሕይወቱም ርጋታን የተላበሰ እና ሥራውንም በሙሉ ልብና ትኩረት የሚሠራ ይሆናል፡፡

  1. ራስን መግዛት

“ወዳጆች ሆይ ነፍስን ከሚወጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደመሆናችሁ እለምናችኋለሁ፡፡” (1ኛ. ጴጥ. 2፥11)

በመጨረሻም ሊረሳ የማይገባውና ለብዙዎቻችን የትኩረት ማጣት መነሻ የሆነው ራስን መግዛት ካለመቻል የሚመጣው የስሜት ሕዋሳት ወይም የሥጋ ፍላጎት ልቅነት ነው፡፡ የስሜት ሕዋሶቻችን የሆነ ደስ የሚላቸውን እና የሚጣፍጣቸውን ነገር አንዴ ከጀመሩ እጅ እጅ እስኪላቸው እና ድጋሚ የማያምራቸው እስኪመስል ድረስ ካልተመገቡት በመመገብና በመጠጣት ብዛትም ካልደነዘዙና ካልሰከሩ በቀር እረፍት አይሰጡም፡፡ በተጨማሪም የስሜት ሕዋሳት ያሰኛቸውን ምግብ ሲሰጧቸው ከዚያ ከሚመገቡት ጊዜያዊ የደስታ ምንጭ እና ምግብ ውጭ ሌላ ደስታ የሚሰጥ ነገር እንደሌለ እንደውም ከዛ ድርጊት ውጭ የሆኑ ነገሮች ሁሉ ደስታችንን በአጭሩ ለመቅጨት የሚንሰፈሰፉ ጠላቶች እንደሆኑ አድርገው አዕምሮን ማሳመን ይችላሉ፡፡ አይስክሬም እንደመላስ ወይም ኳስ እያዩ ወይም እየተጫወቱ በስሜት እንደመሰቀል ዓይነት ሰውነትን የሚያግል ደስታ መስጠት የማይቻለው የዕለት ከዕለት ኃላፊነታችን የሆነው ሥራችን ገና ስናስበው እንደ ተራራ ገዝፎና ከብዶ ይታየናል፡፡ በዚህም የተነሳ በሙሉ ኃይልና ትኩረት ልንወጣው ቀርቶ ገና ሳንጀምረው ይደክመናል፤ ልንቀርበውና ልንደፍረው ያስፈራል፡፡

አንድ ክርስቲያን ግን የተመኙትን ሁሉ ያለገደብ መፈጸም ፍጻሜው ሞት እንደሆነ ስለሚያውቅ ሥጋውን በየጊዜው እየጎሰመ ለነፍሱ ፈቃድ ያስገዛዋል፡፡ ሐዋርያው “ሁሉ ተሰጥቶናል ሁሉ ግን አይጠቅመንም” ብሎ የተናገረውን አብነት በማድረግ ነገሮችን ሁሉ በመጠን ያከናውናል፡፡ ጠቢቡ “ለሁሉም ጊዜ አለው” ያለውን በመከተልም አንድ ነገር ላይ ብቻ ከልክ ባለፈ ስሜት ጥብቅ ሳይል የሥራ ድርሻውን፣ የቤተሰብ ኃላፊነቱን እና ማኅበራዊ ግዴታውን በሰዓቱና በአግባቡ ይወጣል፡፡ መሥራት ባለበት ሰዓት በትጋት ይሠራል፡፡ እረፍት መውሰድ ባለበት ሰዓት ደግሞ እረፍት ይወስዳል፡፡ ሥጋውን ማድከም ባለበት ሰዓት ሥጋውን ያደክማል፡፡ ሥጋውን ማጠንከር ማንቀሳቀስና ማነቃቃት ባለበት ሰዓት እንዲሁ በአግባቡና በመጠን ያደርጋል፡፡ እንግዲህ እዚህም ላይ ሊሠመርበት የሚገባው ሥጋን መጎሰም እና በመጠን መኖር ሲባል ነጻነት የሌለው የእስር ቤት ዓይነት ሕይወት እንዳልሆነ ነው፡፡ ልክ እንደ እምነት ሁሉ ራስን የመግዛት እና ለነገሮች ተገቢውን ጊዜና ቦታ የመለየትና የማወቅ ጥበብም በራስ ጥረት ብቻ የሚመጣ የሚገኝ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ አጋዥነት ዕለት ዕለት በመትጋት እና ጣዕሙን በመቅመስ እያደጉ እየተማሩ የሚሄዱበት ሕይወት መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የድካማችንን ብዛት ዐይተን ተስፋ ሳንቆርጥ የእግዚአብሔር ጸጋ እንደሚያበረታን እና እኛ በትንሹ በታመንን ቁጥር የተለየ ከአሁን በፊት የማናውቀው የላቀ አዲስ ደስታ እንደሚገለጥልን በማመን እና በመደፋፈር ልቅ የሆኑ የሥጋ ፍላጎቶቻችንን እና የስሜት ሕዋሶቻችን የሚወልዷቸውን ምኞቶች በትንሽ በትንሹ ዕለት ዕለት መመጠን እና መቈጣጠር ባጠቃላይም እራሳችንን መግዛትን መለማመድ፣ ተደፋፍረን መጀመር ይኖርብናል፡፡ አለበለዚያ ውስጣዊ ሰላምን እና መነሣሣትን ተላብሶ በሙሉ ልብና ትኩረት በማይናወጥ እምነትና ዓላማ ሥራችንን መሥራት ኃላፊነታችንንም መወጣት የማይታሰብ የህልም ቅዥት ይሆንብናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር