የግእዝ ሥርዓተ ንባብ (pronounciation)

ነሐሴ 19 ቀን 2006 ዓ.ም.

በመ/ር ደሴ ቀለብ
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፊሎሎጂ መምህር

የግእዝ ሥርዓተ ንባብ ስምንት ናቸው፡፡ እነርሱም፡- 

  1. ማንሳት                       5. ማናበብ

  2. መጣል                       6. አለማናበብ

  3. ማጥበቅ                      7. መዋጥ

  4. ማላላት                      8. መቁጠር ናቸው፡፡

1. ማንሳት፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ሳድስ ከመሆን የተለየ ሆኖ ቃሉ በከፈተኛ ድምፅ የሚነገር ወይም የሚነበብ ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የግስ ዓይነቶች በከፍተኛ ድምፅ የተነበቡ ተነሽ ናቸው የሚባሉት፡፡

ምሳሌ፡- ነበረ = ተቀመጠ

ሐበነ = ስጠን

ተዘከረኒ = አስታውሰኝ

ውእቱ = ነው፣ ነበር፣ እሱ፣ ናቸው ወዘተርፈ፡፡

አንስት ሖራ = ሴቶች ሔዱ

ይግበሮ = ይሥራው

ያጥምቆ = ያጥምቀው

2. መጣል (ተጣይ)፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ መጨረሻው ሳድስ ሆኖ የማይነሳ ማለት ነው፡፡

ምሳሌ፡- ማርያም፣ ሚካኤል፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቤተ መንግሥት፣ ቅድስት፣ መቅደስ ወዘተርፈ፡፡

3. ማጥበቅ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ከቃሉ ውስጥ የሚጠብቅ ፊደል ኖሮ ቃሉ ጠብቆ እንዲነበብ የሚያደርግ ነው፡፡

ምሳሌ፡- ቀደሰ = አመሰገነ

ሰብሐ = አመሠገነ

ተዘከሮ = አስታውሰው

ነጸረ = ተመለከተ

4. ማላላት፡- ይህ ሥርዐተ ንባብ በቃሉ ውስጥ የሚጠብቅ ፊደል ሳይኖርና ንባቡም ላልቶ ሲነበብ ነው፡፡

ምሳሌ፡- ቀተለ = ገደለ

ነበረ = ተቀመጠ (ኖረ)

አምለከ = አመለከ

ገብረ = ፈጠረ (ሠራ)

ፈጠረ = ፈጠረ (በአማርኛው ይጠብቃል)

5. ማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት እንደ አንድ ሆነው ሲናበቡና ን፣ በን ወይም የን ሲያመጡ ነው፡፡

ምሳሌ፡- ቤተ ክርስቲያን = የክርስቲያን ቤት

ቤተ መቅደስ = የማመስገኛ ቤት

ትምህርተ ሃይማኖት = የሃይማኖት ትምህርት

ድንግለ ሙሴ

ብሥራተ ገብርኤል

ዜና ሥላሴ

ውዳሴ ማርያም

ጥዑመ ልሳን

ወልደ ኢየሱስ

ተዋሕዶ ቃል

ዜና ቤተ ክርስቲያን

6. አለማናበብ፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ ቃላት ራሳቸውን ችለው ሲነበቡ ወይም አንዱ ላንዱ አጎላማሽ ሲሆን ነው፡፡

ምሳሌ፡- ቅዱስ አምላክ ይባላል እንጂ ቅዱስ አምላክ አይባልም፡፡

ድንግል ማርያም

መጽአ ወልድ – ወልድ መጣ

ጳውሎስ ሐዋርያ

7. መዋጥ፡- መዋጥ ማለት ከቃሉ ውስጥ ያለ ፊደል እንዲሁ ሳይጎላ በውስጠ ታዋቂነት የሚነበብ ነው፡፡ ከዚህ ላይ ማስተዋል ያለብን ፊደሉ በጽሑፍ ጊዜ ግን ሥርዓቱን ጠብቆ ይጻፋል፡፡

ምሳሌ፡- ወይን (wan) ተብሎ እንጂ ወይን (wayyin) ተብሎ አይነበብም፡፡

ድንግል – ከዚህ ላይ ን ተውጣለች

ገብር – ከዚህ ላይ ደግሞ ብ ተውጣለች፡፡ ስለዚህ ገብር ባለሁለት ቀለም ነው፡፡

ኤልሳዕ ከዚህ ላይ ደግሞ ዕ ትዋጣለች፡፡

ርኩስ ኩ ተውጣለች፡፡

ከዚህ ላይ ብዙውን ጊዜ የሚዋጡት ቀለሞች ሲሆኑ መዋጥና አለመዋጣቸው ግን እንደ ንባቡና እንደትርጓመው ይለያያል፡፡

8. መቁጠር፡- ይህ ሥርዓተ ንባብ በአንድ ቃል ውስጥ የሚገኙ ፊደላትን ያለምንም መዋጥ ማንበብ ማለት ነው፡፡

ምሳሌ፡– ውእቱ ከሚለው ቃል ሁሉም ፊደላት ይነበባሉ እንጂ ሳድስ ስለሆነች ብቻ የምትዋጥ አይደለችሙ፡፡

ይእቲ፣ መላእክት፣ ማርያም፣ ማእከል፣ እኅት፣ ትማልም፣ ዮሐንስ፣ አጽፋር (ጥፍሮች) ስእርት (ፀጉር)፣ ኤልያስ፣ ብሔር (ሀገር) እሙንቱ፣ ስብሐት፣ ሐዋርያት፣ መጻሕፍት (ህ ትቆጠራለች)

ከእነዚህ ሥርዓተ ንባቦች በተጨማሪ ሌሎችም አሉ፡፡

 

ለምሳሌ፡- ወዳቂና ሰያፍ

ሀ. ወዳቂ፡- የምንለው ሥርዓተ ንባብ የቃሉ መጨረሻ ፊደል ካዕብ፣ ሳልስ፣ ራብዕ ኀምስና ሳብዕ ሆኖ የማይነሳ እና ቃሉ ሲነበብ የመጨረሻውን ፊደል በመያዝ እንዲወድቅ የሚያደርግ የሥርዓተ ንባብ ዓይነት ነው፡፡

ምሳሌ፡- ኀቤሁ ወደሱ የዚህ ቃል የመጨረሻ ፊደል ሁ ካዕብ ሲሆን ወዳቂ ነው፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ልዩነቶች እንዳሉ ማወቅ ያስፈልገናል፡፡ ለምሳሌ ውእቱ የሚለው ነባር አንቀጽ ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ እንዲሁም ግሶች በትዕዛዝም ሆነ በሓላፊ ሲመጡ ወዳቂ ናቸው ማለት አንችልም፡፡

 

ለምሳሌ፡- ሖሩ = ሔዱ ወይም ሑሩ = ሒዱ ብንልም ተነሽ እንጂ ወዳቂ አይደለም፡፡ ለሣልስ ምሳሌ ከይሲ ብእሲ መዋቲ መሃሪ ወዘተርፈ ሲሆኑ ግስ ከሆነ ግን አይወድቅም፡፡

 

ምሳሌ፡- ሰአሊ ለነ ቅድስት ከዚህ ላይ ሰአሊ የሚለው ቃል ወዳቂ አይደለም ለራብዕ ምሳሌ አንበሳ፣ ዜና፣ ወዘተረፈ ከዚህ ላይም በግስ የሚነገር ከሆነ አይወድቅም፡፡

 

ለምሳሌ፡- እላ አንስት ሖራ /እነዚያ ሴቶች ሔዱ/ ከዚህ ላይ « ሖራ » የሚለው ይነሳል እንጂ አይወድቅም፡፡

ለኀምስ ምሳሌ ውዳሴ፣ ቅዳሴ፣ ይባቤ፣ ወዘተረፈ

ለሳብዕ ምሳሌ ዶርሆ/ዶሮ/፣ መንበሮ፣ ቀቲሎት/

ንዑስ አንቀጽ የሆኑት ሁሉ ወዳቂ ናቸው፡፡ በተጨማሪ ቦዝ አንቀጽ የሆኑ ወዳቂዎች እንዳሉም ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን በግስ ትአዛዝ ወይም ዘንድ አንቀጽ የሆኑት ሊነሱ እንደሚችሉ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡