መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
አውጣኪ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እና የኬልቄዶን ጉባኤ – ካለፈው የቀጠለ
በጉባኤው ፓትርያርክ ዲዮስቆሮስ እምነቱን እንዲገልጽ ተጠይቆ ሁለቱ ባሕርያት (የመለኮትና የሥጋ) ያለ መቀላቀልና ያለ ትድምርት፣ ያለ መለወጥና ያለ መለያየት በአንድ አካል እንደተዋሐዱ በሚገባ አስረዳ፡፡ እንዲሁም በቅዱስ ቄርሎስ ትምህርት መሠረት ‹‹አአምን በአሐዱ ባሕርይ (ህላዌ) ዘቃለ እግዚአብሔር ሥግው፤›› ብሎ አስረዳ፡፡ ጉባኤውም በዚህ በዲዮስቆሮስ እምነት ላይ ምንም እንከን፣ ምንም ስሕተት አላገኘም፡፡ ጉባኤው በሌላ መንገድ ‹‹አውጣኪ በጽሑፍ ካቀረበው የተለየ በቃል ቢናገር ምን ትፈርድ ነበር?›› ብለው በጠየቁት ጊዜ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ ‹‹አውጣኪ የጻፈውን ትቶ ሌላ የክህደት ነገር ቢናገር፣ እሱን ማውገዝ ብቻ ሳይሆን በእሳትም እንዲቃጠል እፈርድበት ነበር፤›› ብሎ መለሰ፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ በእንደዚህ ያለ ነጐድጓዳዊ አነጋገር ሁሉን ግልጥልጥ አድርጎ በተናገረ ጊዜ፣ ኬልቄዶናውያን ጸጥ አሉ፡፡ ዲዮስቆሮስን በመቃወም የተናገሩ የምሥራቅ አህጉር ጳጳሳት ግን ንግግሩ ልባቸውን ነክቶት ‹‹በድለናል፤ ይቅርታ እንጠይቃለን!›› በማለት ጮኹ፡፡
አውጣኪ፣ ቅዱስ ዲዮስቆሮስ እና የኬልቄዶን ጉባኤ – የመጀመሪያ ክፍል
በአውጣኪ አባባል ‹‹ሁለቱ ባሕርያት ማለት የሥጋና የመለኮት ባሕርያት በተዋሐዱ ጊዜ የመለኮት ባሕርይ የሥጋን ባሕርይ ውጦታል፤ አጥፍቶታል፡፡ ሥጋና መለኮት ከተዋሐዱ በኋላ በክርስቶስ ላይ የሚታየው የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው፡፡ በክርስቶስ የሥጋ ባሕርይ ተውጦ የመለኮት ባሕርይ ብቻ ነው የሚታየው፤›› ይል ነበር፡፡ ይህ አባባል በእኛም ቤተ ክርስቲያን ማለት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የተወገዘ ነው፡፡ አውጣኪ በተጨማሪ ከሥጋዌ በኋላ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው ለማለት ‹‹ክርስቶስ ዘዕሩይ ምስሌነ በትስብእቱ›› ማለት ‹‹ክርስቶስ በትስብእቱ (በሥጋው) ከእኛ ጋር አንድ ነው›› የሚለውን ኦርቶዶክሳዊ አነጋገር አይቀበልም ነበር፡፡ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት መሠረት ‹‹ክርስቶስ ፍጹም አምላክ ፍጹም ሰው ነው፡፡›› ነገር ግን ፍጹም ሰው ካልሆነና እኛን ወክሎ በመስቀል ላይ በሥጋው መከራን ካልተቀበለ፣ የእኛ የሰዎች ድኅነት አስተማማኝ አይሆንም፡፡ በክርስቶስ የሥጋና የመለኮት ባሕርያት ተዋሕደው በመስቀል ላይ በአንድነት ባሕርዩ በተቀበለው መከራ ድኅነትን አግኝተናል፡፡
የጌታችን ልደት እና የመላእክት አገልግሎት
ሊቃውንት እንዳስተማሩን እግዚአብሔር አምላክ ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደበት እና ዓለምን ያዳነበት ምሥጢር ከምሥጢራት ዅሉ በላይ ነው፡፡ ይህን ምሥጢር ከማድነቅ ሌላ ሊናገሩት አይቻልም፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም በመገረም ይህን ጥበብ እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፤ ‹‹ምን እላለሁ? ምንስ እናገራለሁ? ከዘመን አስቀድሞ የነበረው እርሱ ሕፃን ኾኗልና፡፡ እኔ ፈጽሜ አደንቃለሁ፡፡ ከሰማየ ሰማያት በላይ የሚኾን፣ በዘለዓለማዊ ዙፋን የሚኖር እርሱ በበረት ተጣለ፡፡ ከሥጋዌ አስቀድሞ አይዳሰስ የነበረ አንዱ እርሱ በምድራውያን እጅ ተዳሰሰ፡፡ ኀጢአትን የሚያስተሰርይ እርሱን በጨርቅ ጠቀለሉት፡፡ ይህን ወዷልና፤›› (ሃይማኖተ አበው ዘዮሐንስ አፈወርቅ፣ ፷፮፥፲፯)፡፡ ቅዱስ ዲዮስቆሮስም በቅዳሴው የእግዚአብሔርን ሰው የመኾን ምሥጢር እንዲህ በማለት ገልጾታል፤ ‹‹በጐለ እንስሳ ተወድየ አሞኀ ንግሡ ተወፈየ ወከመ ሕፃናት በከየ እንዘ ይስእል እምአጥባተ እሙ ሲሳየ፤ በእንስሳት በረት ተጨመረ፡፡ የንጉሡንም እጅ መንሻ ተቀበለ፡፡ ከእናቱ ጡቶች ምግብን እየለመነ እንደ ሕፃናት አለቀሰ፤›› (ቅዳሴ ዲዮስቆሮስ ቍ. ፲፯)፡፡
ለብርሃነ ልደቱ መዘጋጀት
ዛሬም እኛ በኀጢአት ስንዋከብ ዘወትር ልናየውና ልንመላለስበት የሚገባን ብርሃነ ልደቱ ተሰውሮብናል፣ ከቸር እረኛችን የራቅን የተቅበዘበዝን በጎች ኾነናል፡፡ አንዳንዶቻችን በምናስበው ዐሳብ፣ በምንሠራው ሥራ ውስጥም የአምላክን ሰው የመኾን ምሥጢር ረስተነዋል፡፡ የምንኖረው ልክ ክርስቶስ እንዳልተወለደ ነው፡፡ ስለዚህ ያጣነውን ይህን ጸጋ ለማግኘትና ብርሃነ ልደቱን ለማየት፣ በዚያ ውስጥም ለመመላለስ የክርስትናችንን እና የመንፈሳዊነታችንን ጥልቀት ለመጨመር መሻት አለብን፡፡ ስለዚህ እስኪ እኛም በእነዚህ ሳምንታት የብሉይ ኪዳን ሰዎች የነበሩበትን ኹኔታ እየዘከርን፣ ያለንበትን አኗኗር እየመረመርን፣ ስላጣነው ብርሃን ለማሰብ፣ ያጣነውን መልሰን ለማየትና ለማግኘት እንትጋ፡፡ መጻሕፍትን ለማንበብ፣ በጉዳዩ ላይ በተመስጦ ለማሰብ እና ለመወያየት ጊዜ እንስጥ፡፡ ብርሃነ ልደቱን ለማየት እንዲያበቃንም ‹‹አቤቱ ብርሃንህንና ጽድቅህን ላክ፤ ቸሩ እረኛችን ሆይ፥ ተቅበዝብዘናልና እባክህ ሰብስበን›› እያልን እግዚአብሔርንእንማጸነው፡፡
ኖላዊ ኄር
ክብር ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳስተማረን ወደ በጎች ስፍራ በበሩ የማይገባ፥ በሌላም በኩል የሚገባ ሌባ፥ ወንበዴም ነው፡፡ በበሩ የሚገባ ግን የበጎች ጠባቂ ነው፡፡ ለእርሱ በረኛው ይከፍትለታል፤ በጎቹም ቃሉን ይሰሙታል፤ እርሱም በጎቹን በየስማቸው ይጠራቸዋል፤ አውጥቶም ያሰማራቸዋል፡፡ ምንደኛ (ቅጥረኛ) እረኛ ግን ለበጎቹ አይጨነቅም፤ በጎቹም አያውቁትም (ዘካ. ፲፩፥፬-፭፤ ዮሐ. ፲፥፩-፲፪)፡፡ ዛሬም በእናት ቤተ ክርስቲያናችን የተሾሙ አባቶች እንደነሙሴ፣ እንደነዳዊት፣ እንደነብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያንም ለአገርም የሚጨነቁ ሊኾኑ ይገባል፡፡ እኛ ምእመናንም እግዚአብሔር አምላካችን መልካም እረኞችን እንዳያሳጣን መለመን ይኖርብናል፡፡ እንደዚሁም ራሳችንን ለሃይማኖታችን ማስገዛት፣ መልካም እረኞችንም አብነት ማድረግና መከተል ይጠበቅብናል፡፡
ክርስቲያናዊ ኑሮ በዘመነ አስተምሕሮ
በባሕሩ ዓለም ውስጥ የምትገኘው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሰዎች በፈቃደ ሥጋቸው ተሸንፈው ባመጡት ጥላቻ፣ ኑፋቄ፣ ክህደት፣ ፍቅረ ንዋይ፣ በአጠቃላይ በልዩ ልዩ የኀጢአት ማዕበልና ሞገድ እየተናወጠች ናት፡፡ ይህን ማዕበልና ሞገድ ጸጥ በማድረግ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ሰላምንና ጽድቅን ማስፈን የሚቻለውን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ቅዱሳን ሐዋርያት በአንድነት ኾነን ‹‹ጌታ ሆይ እንዳንጠፋ አድነን?›› እያልን እንማጸነው፡፡ የሰላሙ ዳኛ፣ የሰላሙ መሪ፣ የሰላሙ ጌታ፣ የሰላሙ ንጉሥ፣ የሰላሙ ባለቤት እርሱ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን፣ መረጋጋትን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን ካወጀ በቤተ ክርስቲያናችን ፍቅር፣ አንድነት ሰላም ይሰፍናልና፡፡
ብፁዕ አቡነ ኤልያስ፣ ቤተ ክርስቲያንን ከነጣቂ ተኩላዎች መጠበቅ እንደሚገባ አሳሰቡ
ብፁዕነታቸው ይህን መልእክት ያስተላለፉት በጋሞ ጎፋ ሀገረ ስብከት በዐርባ ምንጭ ከተማ በደብረ ኃይል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን በተካሔደው የፀረ ተሐድሶ ጉባኤ ላይ ተገኝተው ‹‹እናንተ ግን ክፉውን ከመካከላችሁ አውጡ፡፡ በውጭ ባሉት ግን እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል›› (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፲፫) በሚል ኃይለ ቃል ትምህርተ ወንጌል በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፣ መናፍቃንን አወገዙ
ተወግዘው የተለዩት ግለሰቦች ‹ምስሉ ፈረደ›፣ ‹ፍጥረቱ አሸናፊ›፣ ‹ያሬድ ተፈራ›፣ ‹በኃይሉ ሰፊው› እና ‹እኩለ ሌሊት አሸብር› እንደሚባሉ፤ ከእነርሱ መካከልም ምስሉ ፈረደ እና ፍጥረቱ አሸናፊ መዓርገ ቅስና፤ ያሬድ ተፈራ እና እና በኃይሉ ሰፊው መዓርገ ዲቁና እንደ ነበራቸውና ሥልጣነ ክህነታቸው እንደ ተያዘ፤ የሰንበት ት/ቤት አገልጋይ የነበረውን እኩለ ሌሊት አሸብርን ጨምሮ ከዚህ በኋላ ዅሉም ግለሰቦች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት እንደ ተለዩና ‹አቶ› ተብለው እንደሚጠሩ ብፁዕነታቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በቍጥር 148/11/2010፣ በቀን 01/03/2010 ዓ.ም በጻፈው ደብዳቤ በተሐድሶ ኑፋቄ ውስጥ ኾነው ሕዝበ ክርስቲያኑን እያደናገሩ የሚገኙ ቀሳውስትን፣ ዲያቆናትንና ምእመናንን በአጠቃላይ የዐሥራ ሦስት ግለሰቦችን ስም በመጥቀስ ቀሳውስቱና ዲያቆናቱ ከክህነት አገልግሎት፤ ምእመናኑ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አባልነት መታገዳቸውን ያሳወቀ ሲኾን፣ በደብዳቤው ከተጠቀሱ ግለሰቦች መካከልም ምስሉ ፈረደ እና ፍጥረቱ አሸናፊ ይገኙበታል፡፡
ጾመ ነቢያት
ይህን ምሥጢር በማሰብ በየዓመቱ ከኅዳር ፲፭ ቀን ጀምሮ እስከ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት ዋይዜማ ድረስ እንድንጾም አባቶቻችን መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ሠርተውልናል፡፡ ይህ ጾም፣ ከሰባቱ አጽዋማት አንዱ ሲኾን፣ በስያሜም ‹‹ጾመ ነቢያት (የነቢያት ጾም)›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወቅቱ ለአዳም የተነገረው የድኅት ተስፋ የተፈጸመበት ስለ ኾነም ‹‹ጾመ አዳም (የአዳም ጾም)›› ይባላል፡፡ ስለ እግዚአብሔር ሰው መኾን በስፋት ትምህርተ ወንጌል የሚሰጥበት ወቅት በመኾኑም ‹‹ጾመ ስብከት (የስብከት ጾም)›› የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የጾሙ መጨረሻ (መፍቻ) በዓለ ልደት በመኾኑ ደግሞ ‹‹ጾመ ልደት (የልደት ጾም)›› በመባል ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ‹‹ጾመ ሐዋርያት›› እየተባለ ይጠራል፡፡ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ‹‹በዓለ ትንሣኤን ዐቢይ ጾምን ጾመን እናከብረዋለን፤ በዓለ ልደትንስ ምን አድርገን እናከብረዋለን?›› በማለት ነቢያት በጾሙበት ማለት ከልደተ ክርስቶስ በፊት ባለው ወቅት ጾመዋልና፡፡
በአውሮፓ የሕፃናት እና ታዳጊዎች ሥርዓተ ትምህርት ተመረቀ
እንደ ዶ/ር በላቸው ጨከነ ገለጻ ወጥ የኾነ ሥርዓተ ትምህርት አለመኖር በአውሮፓ የሚኖሩ ታዳጊ ሕፃናትን ለማስተማር ከባድ ከሚያደርጉት ኹኔታዎች ተቀዳሚው ምክንያት ሲኾን፣ ይህን በመገንዘብ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ባወጣው የሥራ መመሪያ መሠረት በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፓ ማእከል የተተኪ ትውልድ ሥልጠና ክፍል ባለሙያዎችን በመመደብ ሥራውን እንዲጀምር ተደርጓል፡፡
ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናትና ታዳጊዎች ታስቦ የተዘጋጀው ሥርዓተ ትምህርቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፣ የአማርኛ ቋንቋ እና የመዝሙር ጥናት የተሰኙ አምስት የትምህርት ዘርፎችን ያካተተ ሲኾን፣ የትምህርቶቹ አርእስትና ይዘቶችም በቤተ ክርስቲያን የሚከበሩ በዓላትንና ወቅቶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጁ ናቸው፡፡