• እንኳን በደኅና መጡ !

ዜናዎች፣ ወቅታዊ ክንውኖች እና ልዩ ልዩ ይዘቶች

‹‹በላይ ያለውን ሹ›› (ቈላ. ፫፥፩)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቈላስይስ ሰዎች በላከው መልእክቱ እንደተናገረው ‹‹ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ በአለበት በላይ ያለውን ሹ፡፡ የላይኛውን አስቡ፤ በምድር ያለውን አይደለም፡፡ እናንተ ፈጽማችሁ ሞታችኋልና፤ ሕይወታችሁም ከክርስቶስ ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ የተሠወረች ናትና፡፡ ሕይወታችሁ ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ፥ ያን ጊዜም ከእርሱ ጋር በፍጹም ክብር ትገለጣላችሁ፡፡›› (ቈላ. ፫፥፩-፬)

ኢትዮጵያዊው ማኅሌታይ ቅዱስ ያሬድ

…ከዚያም ጉዞውን ወደ ደቡብ አቅጣጫ ወደ ሰሜን ተራሮች አደረገ፡፡ በዚያም አሁን በስሙ የታነጸው ቤተ ክርስቲያን ባለበት ቦታ ላይ በምናኔ ተወስኖ ፈጣሪውን በብሕትዉና እያገለገለ ኖረ፡፡ ደብረ ሐዊ ከተባለው ተራራ ላይ  በምናኔ ብዙ ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በጸለምት ዋሻ በአንዱ ግንቦት ፲፩ ቀን በ፭፻፸፩ ዓ.ም ተሠውሯል፡፡

‹‹እኔ እግዚአብሔር ነኝ›› (ዘፀ. ፮፥፪)

እግዚአብሔር አምላካችን ሰማይና ምድርን፣ መላእክትን፣ ሰውን እንዲሁም ፍጥረታትን በሙሉ የፈጠረ አምላክ ነው፡፡ ለፍጥረታቱም ህልውናውን እንደብቃታቸው ይገልጻል፤ በጥንተ ተፈጥሮ እግዚአብሔር አምላክ መላእክትን ለባውያን (አዋቂዎች) አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ በሰጣቸው ዕውቀት ተመራምረው ፈጣሪያቸውን ያመልኩት ዘንድ እንዲሁም ከባሕርዩ ፍጹም ርቀት የተነሣ በመካከላቸው ሳለ ተሰወረባቸው፡፡ መላእክትም ተፈጥሮአቸውንና ፈጣሪያቸውን መመርመር ጀመሩ፤ አንዱም ለአንዱ ‹‹አንተ ምንድን ነህ? ከየትስ መጣህ?›› ይባባሉ፣ እርስ በርሳቸውም እየተያዩ በተፈጥሮአቸው ይደነቁ ነበር፡፡ በኋላም ‹‹ማን ፈጠረን? ከየትስ መጣን?›› የሚለው የማኅበረ መላእክት ጥያቄ መበርታቱን የተረዳው ሳጥናኤል ሹመቱ ከሁሉ በላይ ነበርና አሻቅቦ ቢያይ ‹እኔ ነኝ ባይ› ድምጽ አጣ፤ ዝቅ ብሎም ቢያዳምጥ ከእርሱ በክብር ያነሱ መላእክት ይመራመራሉ፤ ‹ለምን እኔ ፈጠርኳችሁ ብዬ ፈጣሪነትን በእጄ አላስገባም› ብሎ አሰበ፤ ከዚያም ‹እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ› በማለት ተናገረ፡፡…

የቀለሙ ልጅ

ከጸሐፊው ማስታወሻ…

አባቴ ሲጠራ ሲነሣ ሰማሁኝ
የአብራኩ ክፋይ የቀለሙ ልጅ ነኝ
አባቴን አታንሳው እኔ እበቃለሁኝ
አባትህ ተረት ነው ብለህ ለጠየከኝ…

‹‹ከእነዚህ ታናናሾች አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም›› (ማቴ. ፲፰፥፲፬)

የማቴዎስ ወንጌልን ከቁጥር ዐሥራ አንድ ጀምረን ስናበብ እንዲህ የሚል ቃል እናገኛለን፤ ‹‹የሰው ልጅ የጠፋውን ሊፈልግ፣ የተጎዳውን ሊያድን መጥቷልና፤ ምን ትላላችሁ? መቶ በጎች ያለው ሰው ቢኖር ከመካከላቸውም አንዱ ቢጠፋው፥ ዘጠና ዘጠኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋውን ሊፈልግ ይሄድ የለምን? እውነት እላችኋለሁ፤ ባገኘው ጊዜ ካልጠፉት ከዘጠና ዘጠኙ ይልቅ ጠፍቶ ስለ ተገኘው ፈጽሞ ደስ ይለዋል፡፡ እንዲሁም ከእነዚህ ታናናሾቹ አንዱ እንኳ ይጠፋ ዘንድ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት አይፈቀድም፡፡›› (ማቴ. ፲፰፥፲፩-፲፬)

ሰሙነ ፋሲካ

በሰሙነ ፋሲካ ከትንሣኤ እሑድ ጀምሮ እስከ ሳምንቱ እሑድ ድረስ የሚገኙት ዕለታት የተለያየ ስያሜ አላቸው፤ እነርሱም፡-

‹‹እርሱ እንደተናገረው ተነሥቶአል›› (ማቴ. ፳፰፥፮)

በዕለተ ቅዳሜ ለእሑድ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ክፈቱልኝ መግነዝ ፍቱልኝ ሳይል ከመቃብር ተነሣ፤ ነቢዩ ዳዊትም ‹‹እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ›› ብሎ እንደተናገረው አምላካችን ከሙታን ተለይቶ ተነሥቶአል፡፡ ትንሣኤ ሙታንን እናከብርም ዘንድ ይገባልና ክርስቲያኖች በሙሉ ደስ ይበለን! (መዝ. ፸፯፥፷፭)

የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞት (ሰሙነ ሕማማት)

ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ዘጠኝ ሰዓት ሲሆን ‹‹ሁሉ ተፈጸመ›› አለ፡፡ ያን ጊዜም   ቅድስት ነፍሱን ከቅዱስ ሥጋው በፈቃዱ ለየ፡፡ አይሁድም ቀጣዩ ቀን ሰንበት ነውና እኒህ ሰዎች እንደተሰቀሉ አይደሩ ብለው ጭን ጭናቸውን ሰብረው ያወርዷቸው ዘንድ ጲላጦስን ጠየቁት፤ እርሱም ፈቀደላቸው፡፡ ጭፍሮቹም የሁለቱን ወንበዴዎች ጭናቸውን ሰብረው አወረዷቸው፡፡ ወደ ጌታችንም ሲቀርቡ ፈጽሞ ሞቶ አገኙት፤ በዚህም ‹‹ከሥጋውም አንዳች ከቤት ወደ ሜዳ አታውጡ፤ አጥንቱንም አትስበሩ›› ተብሎ የተነገረው ምሳሌያዊ ትንቢት ፍጻሜ ያገኝ ዘንድ ጭኑን ሳይሰብሩት ቀሩ፡፡ (ዘፀ.፲፪፥፵፮)

በእንተ ዕለተ ስቅለት

ጨረቃ ደም ሆነች፤ ፀሐይም ጨለመ
ከዋክብት ረገፉ፤ ሐኪሙ ታመመ
ልዑል ተዋረደ፤ ጌታ ሎሌ ሆነ
ፈጣሪ ሠራው ፍጡሩ በየነ…

ቀራንዮ

ቀራንዮ … ቀራንዮ …ቀራንዮ ጎልጎታ

የተለየሽው ከሁሉ ቦታ

የመከራ ቤት የደም ማማ

የመስቀል ዙፋን የግፍ አውድማ…

በፌስቡክ የትስስር ገጽ ያግኙን

ስለ ማኅበረ ቅዱሳን መሰረታዊ መረጃዎች

ስያሜ

ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡

የማኅበሩ ርእይ

ቤተ ክርስቲያን ሁለንተናዊ የመሪነት ሚናዋን ስትወጣ ማየት

ተልእኮ

ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ መሳካት እና ለሕልውናዋ የሚተጋ፣ የተደራጀ ፣ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ፤ ርቱዕ ዘመናዊ፤ ሁለገብ መሪ ትውልድ ማፍራት እና ማሰማራት

እሴቶች

  • መንፈሳዊነት

    ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
  • አገልጋይነት

    የማኅበሩ አባላት አገልግሎትን የክርስቲያናዊ ሕይወታቸው መገለጫ አድርገው በመቀበል በበጎ ፈቃድ ሰማያዊውን ክብርና ጸጋ በመሻት፣ ምድራዊ ክብርና ውዳሴ ከንቱን ሳይፈልጉ፣ በትሕትና እና በክርስቲያናዊ ፍቅር በታማኝነት ያገለግላሉ::
  • የሐሳብ መሪነት

    ማኅበሩ ለቤተ ክርስቲያን ዘላቂ አገልግሎት የሚያስፈልጉ፣ ኦርቶዶክሳዊ እሳቤን የተከተሉና ዘመኑን የዋጁ የመሪነት ሐሳቦችን በማፍለቅ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር በመመካከር ይሠራል::
  • ተባባሪነት

    ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሁሉም የቤተ ክርስትያን አካላት የወል ተግባር ነው ብሎ ያምናል:: በመሆኑም እንደየጉዳዩ አግባብነት ካላቸው ባለ ድርሻ እና አጋር አካላት ጋር በመግባባት፣ በመመካከር እና በቅንነት ለተልእኮ አንድነት ብዝኃ ጸጋን በማክበር አብሮ ይሠራል::
  • ሙያ አክባሪነት

    የማኅበሩ አባላት ባላቸው ልዩ ልዩ ሙያ /ዕውቀት/ ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የተሰባሰቡ በመሆናቸው፣ በማኅበሩ አሠራሮች ሁሉ ከኦርቶዶክሳዊው ትምህርተ ሃይማኖት ጋር በማይጋጩ በእውነተኛ መረጃ ለሚደገፉ ሙያዊ ምክረ ሐሳቦች ተገቢውን ክብርና ቅድሚያ ይሰጣል:: በቤተ ክርስቲያንም ለመንፈሳዊ እና ለዘመናዊው (አስኳላ) ሙያ ተገቢው ክብር እንዲሰጥ ይሠራል::
  • ምክንያታዊ ሞጋችነት

    ማኅበሩ በእውነተኛ መረጃ ላይ ተመሥርቶ ቤተ ክርስቲያንን ከውስጥም ሆነ ከውጭ የሚፈትኑ አስተሳሰቦችን፣ አሠራሮችን፣ ልማዶችን እና ትርክቶችን በግልጽና በመንፈሳዊ ጥብዓት እና በእውነት እንዲሞገቱና መፍትሔ ላይ እንዲደረስ ይሠራል::
  • ተጠያቂነት

    የማኅበሩ አገልግሎት ግብ ሰማያዊ ዋጋ ማግኘት ስለሆነ ኀላፊነትን በአግባቡ አለመወጣት በእግዚአብሔር እና በሰዎች ዘንድ የሚያስጠይቅ በመሆኑ በየትኛውም እርከን ላይ ያለ አባል እና አመራር በማኅበሩ አሠራር መሠረት በተሰጠው ኀላፊነት ተጠያቂ ይሆናል፡፡

ዓላማዎች

  • የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አስተዳደር፣ የአሠራር ሥርዐትና አስተሳሰብ፣ በቴክኖሎጂ እና በልዩ ልዩ መንገዶች በመደገፍ ዘመኑን ለዋጀ ጠንካራ አገልግሎት ማብቃት፤
  • የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን ሙሉ ሰብእናን የሚገነባ ሥርዐተ ትምህርት በማስተማር ዘመኑን የዋጁ ምሉዕ ኦርቶዶክሳዊ የሆኑ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያገለግሉ እንዲሁም በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ በፖለቲካዊ እና በሀገር አስተዳደር ጉዳዮች መሪ/ንቁ ተሳታፊ አገልጋዮችን ማፍራት እና ማሠማራት፤
  • የተተኪውን ትውልድ ምንጭ ለማጎልበት የሰ/ት/ቤቶችን አቅም በማጠናከር የሕጻናት እና የወጣቶችን የተተኪነት ሚና ማሳደግ፤
  • ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነትን በተግባር የሚገልጽ ቤተሰብ እና አንድነቱን የጠበቀ ኦርቶዶክሳዊ ማኅበረሰብ በመገንባት የተደራጀ እና የተናበበ አገልግሎት መስጠት፤
  • በተደራጀ እና ተደራሹን ማእከል ባደረገ መንገድ ስብከተ ወንጌልንና ሐዋርያዊ ተልእኮን ዘርፈ ብዙ በሆኑ መንገዶች በመላው ዓለም ማስፋፋት፤
  • በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነዙትን የርእዮተ ዓለም፣ የሐሰት ትርክቶች እና የአጽራረ ቤተ ክርስቲያንን እንቅስቃሴ ጥናት እና ምርምር ላይ ተመርኩዞ መሞገት እና የተሳሳቱትን በማረም፣ በጠንካራ የዕቅበተ እምነት አገልግሎት የቤተ ክርስቲያንን ሕልውና ማስጠበቅ፤
  • በተመረጡ ገዳማት እና አብነት ትምህርት ቤቶች የልኅቀት ማእከል እና የተለየ ክርስቲያናዊ ተልእኮ የሚፈጽሙ እንዲሆኑ የሚያስችል ሁለገብ የአእምሮ ልማት ድጋፍ ማድረግ፤
  • ማኅበሩ ዘመኑን የዋጀ ተቋማዊ የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት ተልእኮውን ማሳካት የሚችልበት አቅም መፍጥር ( በአመራር፣ በሰው ኃይል፣ በመንፈሳዊነት፣ በግንኙነት፣ በዕውቀት፣በልማት፣ በፋይናንስ፣ በቴክኖሎጂ)፤
  • ዓለም አቀፍ ግንኙነትና የትብብር አገልግሎትን መርሕ ያደረገ የኦርቶዶክሳውያን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ማሳደግ፣

አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ
የሸዋ ሊቀ ጳጳስ ፲፱፻፴፪-፲፱፻፹፪ዓ.ም.

የማኅበሩ ህንጻ