መንፈሳዊነት
ኦርቶዶክሳዊነት ርትዕት ሃይማኖት፣ ጽኑ እምነት፣ መልካም ምግባርና መንፈሳዊ እውቀት በአንድነት የተዋሐዱበት፤ አርአያ እግዚአብሔርን አጽንቶ በሐዋርያዊ የሕይወት ተጋድሎ እግዚአብሔርን በግብር ወደ መምሰል የሚታደግበት ፍጹም ሰማያዊ ሕይወት በመሆኑ፤ አባላት በየትኛውም ቦታ፣ ጊዜና ሁኔታ በማሰብ፣ በመናገር እና በመሥራት/በተግባር በሚገለጽ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር ታንጸው፣ ፍኖተ አበውን ተከትለው፣ በታማኝነት እና በፈሪሐ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት ያገለግላሉ::
ዲያቆን ረዳ ውቤ አረፉ
ኅዳር 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ዮሴፍ ይኲኖ አምላክ
በሲዳሞ ክፍለ ሀገር፣ ቡሌ ወረዳ በሚገኘው ጎንፈራ ቀበሌ፥ ከወላጅ አባታቸው አቶ ውቤ አብዲና ከእናታቸው ከወ/ሮ መሰለች ተመስገን፥ መጋቢት 5 ቀን 1955 ዓ.ም የተወለዱት ዲ/ን ረዳ ውቤ፤ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በልዩ ልዩ የሕክምና መስጫ ተቋማት ሲረዱ ቆይተው በ50 ዓመታቸው ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞተ ሥጋ ተለይተው፥ ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም በቡራዩ ፄዴንያ ስመኝ ማርያም ገዳም ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
በእኛ ዘመን ምንጮቻችን እንዳይነጥፉ
ኅዳር 17 ቀን 2005 ዓ.ም.
የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊ አገልግሎት መሠረት የሆኑት፤ የአባቶች ካህናት፣ ሊቃውንት መምህራን፣ ጳጳሳት የአገልጋዮቿ መፍለቂያ፤ ለዘመናት የማይነጥፉ ምንጮች ሆነው የኖሩት አብነት ትምህርት ቤቶቻችን፤ በዚህ ዘመንና ትውልድ ህልውናቸውን ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ፈተና እንደተጋረጠባቸው የዐደባባይ ምስጢር ከሆነ ቆይቷል፡፡
ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ የሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት እንዲሁም ቅን አሳቢ እውነተኛ ልጆቿ ሁሉ ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የተግባራዊ መፍትሔው አካል በመሆን ሲንቀሳቀሱም ይታያል፡፡
የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ለጊዜው ከቦታው ይነሣል
ኅዳር 15 ቀን 2005 ዓ.ም.
የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ችግርን ለመቅረፍ እንዲያስችል በሚዘረጋው የቀላል ባቡር መሥመር ዝርጋታ ምክንያት የብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት እንደሚነሣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡
አቶ አበበ ምሕረቱ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የኮምኒኬሽን አገልግሎት ክፍል ሓላፊ የሐውልቱ መነሣት ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያት ምን እንደሆነ ሲገልጹ “በቀላል ባቡር መስመር ዝርጋታ ምክንያት መንገዱ ከዳግማዊ አፄ ምኒልክ አደባባይ ጀምሮ ወደ አውቶቡስ ተራ የሚወስደው መንገድ አትክልት ተራ ድረስ ባቡሩ በዋሻ ውስጥ ነው የሚያልፈው፡፡ በተጨማሪም የባቡሩ መስመር ከምኒልክ አደባባይ ወደ ሽሮ ሜዳ ይዘረጋል፡፡ እንደሁም ከአውቶቡስ ተራ ወደ ቅድስት ልደታ ለማርያም የሚታጠፈው መስመር መነሻም ነው፡፡ ስለዚህ በአሁኑ ወቅት ከማዘጋጃ ቤት አጥር ጀምሮ ወደ ትግበራ የተገባበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን፡፡ ሥራው ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሲደርስ ስዊድን አገር የሚገኘውና ከፍተኛ ልምድ ያለው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ሥራውን በበላይነት የሚቆጣጠረው ሲሆን በሚያስመጣቸው ባለሙያዎች አማካይነት በክብርና በጥንቃቄ ሐውልቱን አንሥቶ የዋሻው ግንባታ እንደተጠናቀቀ አንዲትም ሣ/ሜትር ሳይዛነፍ እንደነበረ በቦታው ላይ በክብር እንዲያስቀምጥ ይደረጋል፡፡ ሐውልቱ የሀገር ቅርስና ሀብት ነው፤ ለዚህም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ሥራ ይሠራል፡፡” ብለዋል፡፡
የማኅበሩ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ተራዘመ
ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም. በእንዳለ ደምስስ የማኅበረ ቅዱሳን የኅትመትና ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዋና ክፍል በኢቢኤስ የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ለመጀመር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን በእኛ በኩል ዝግጅታችንን ለመጀመር ዝግጁ ሆነን እየተጠባበቅን የምንገኝ ሲሆን ከኢቢ ኤስ ቴሌቪዥን በኢትዮጵያና በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የጀመረው ስርጭት ከኅዳር 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ካልታወቀ አቅጣጫ በተደረገ ከፍተኛ የሳተላይት […]
“በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤” ዘፀ.33፥1-3
ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
በመ/ር ኢዮብ ይመኑ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ
በረሃብ ስደት ምክንያት ከከነዓን ወደ ግብፅ የመጡት ሰዎች ከዮሴፍ ጋር ሰባ ነበሩ፡፡ /ሐዋ.7/ በግብፅም በአባታቸው በያዕቆብ ምርቃት ቁጥራቸውም እጅግ በዛ፡፡ ይህም የቁጥራቸው መብዛት ከ1280-1445 ቅድመ ልደተ ክርስቶስ የተነሣውንና ዮሴፍን የማያውቀውን ንጉሥ አስፈራው፡፡ /ዘፀ.1፥8/ ንጉሡም ጠላት ይሆኑብናል ያም ባይሆን ጠላት ቢነሳብን አብረው ይወጉናል በሚል ፍርሃት አገዛዝ በማጥናት በቀን በሌሊት በከባድ ሥራ እየጠመደ በጭካኔ ጡብ እያስገነባ ፊቶም፣ ራምሴ፣ ዖንን የተባሉ ታላላቅ ከተሞችን እያሠራ ኖራ እያስወቀጠ ጭቃ እያስረገጠ በሥራ ደክመው ልጅ እንዳይወልዱና ጉልበታቸውን እየደከመ በጅራፍ አየገረፈ መከራ አጸናባቸው፡፡ ይህን ቢያደርግም ጉልበታቸው እየበረታ ከእርሱ መከራ የአባቶቻቸው ምርቃትና ቃል ኪዳን እየረታ አሁንም ሲበዙ ወንድ ሲወለድ በመግደል እስራኤልን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ ግን የመከራው ብዛት የሕዝቡም ጩኸት የራሔልም እንባ እግዚአብሔርን፡- “የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ” አስብሎ በእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱስ ሚካኤል ተራዳኢነት በሙሴ ጸሎት በግብፅ ምድር በ9 መቅሰፍቶች 10ኛ ሞተ በኩር 11ኛ ስጥመተ ባሕር የወጡት እስራኤል ከነዓን ገብተዋል፡፡ ይህም የኅዳር 12 መታሰቢያ በዓል መጽሐፍ ቅዱስ “በመንገድ ላይ እንዳላጠፋህ… በፊትህ መልአክ እሰዳለሁ፤” ዘፀ.33፥1-3 እንዳለ ከመከራ የወጡትን እስራኤል በጉዞአቸው ካለው መሰናከል እየጠበቀ “በመንገድ ላይ” እንዳይጠፉ እያማለደና በምሕረት እየታደገ ከጠላት ሲዋጉ አብሮ እየቀደመ ከዲያብሎስ ተንኮል እየሰወረ እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላቸው ሥፍራ ያስገባው “መልአክ” የቅዱስ ሚካኤል መታሰቢያ በዓል ነው፡፡
ማእከላቱ ጠቅላላ ጉባኤያቸውን አካሄዱ
ኅዳር 11 ቀን 2005 ዓ.ም.
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ማኅበረ ቅዱሳን የአሰላ፣ የአምቦ፣ የፍቼ፣ የደብረ ብርሃን፣ የወሊሶ እንዲሁም የወልቂጤ ማእከላት ከጥቅምት 25 እስከ ኅዳር 2 ቀን 2005 ዓ.ም ባሉት ጊዜያት ጠቅላላ ጉባኤያቸውን ከወረዳ ማእከላት፣ ከግንኙነት ጣቢያዎች፣ ከግቢ ጉባኤያት የተወከሉ አባላት፣ የየሀገረ ስብከቱ ተወካዮች፣ የወረዳ ሊቃነ ካህናት፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተወካዮች እና የማኅበረ ቅዱሳን የዋናው ማእከልና የመሐል ማእከላት ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ልዑካን በተገኙበት አካሂደዋል፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር
ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.
ሊቀ ልሣናት ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን
ሥነ ምግባር፡- ማለት ደግነት፣ በጎነት፣ መልካም ጠባይ ማለት ሲሆን ክርስቲያን የሚለው ቃል ሲጨመርበት ደግሞ የተሟላና የተለየ ያደርገዋል፡፡ መልካም ጠባይ ማንም ሰው ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የተሟላ ዘላቂና የሁል ጊዜ ሆኖም ለሰማያዊ መንግሥት የሚያበቃው በክርስትና እምነት ሲኖሩ ነው፡፡
ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፡- በምድር እያለን ሰማያዊ ኑሮ ኖረን ለሰማያዊ መንግሥት የምንበቃበት ሕይወት ነው፡፡ ሰውን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነውና፡፡ በመሆኑም ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር በሚከተሉት ሕግጋት ሊለካ ይችላል፡፡
ደብረሊባኖስ ገዳምን የሚታደጉ ሰፋፊ ፕሮጀክቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ
ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ማለደ ዋስይሁን
የደብረ ሊባኖስ ገዳምን በሁለንተናዊ መልኩ ለማሳደግ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የገዳሙ ጸባቴ አባ ኃይለ መስቀል ውቤ አስታወቁ፡፡ ኅዳር 9 2005 ዓ.ም በማኅበረ ቅዱሳን ጽሕፈት ቤት ከገዳሙ ወዳጆች ጋር በተደረገው የምክክር መርሐ ግብር ላይ ይፋ እንደተደረገው ገዳሙ ያሉበትን ችግሮች ቀርፎ በቀጣይም አርአያ ምሳሌ ወደሚሆንበት ደረጃ የሚያደርሱትን እንቅስቃሴዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ባለሙያዎች ጋር በመተባበር ለማከናወን መታቀዱን ጸባቴው ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ትሴብሕ ወትዜምር ግብፅ……
ኅዳር 10 ቀን 2005 ዓ.ም.
በዲ/ን ማለደ ዋስይሁን
የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ሂደት ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ እንደ ምሳሌ
የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊን ዕረፍት ተከትሎ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ላለፉት ስድስት ወራት ያህል ትኩረት የሰጠችው ተተኪ ፓትርያርኳን ለመምረጥ አስፈላጊውን ሁሉ መፈጸም ላይ ነበር፡፡ የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወዲያ ውኑ ባደረገው ጉባኤ ለቤተ ክርስቲ ያኒቱ ዐቃቤ መንበር መሾም ሲሆን ብፁዕ አቡነ ጳኩሚስ ዘቤሔይራ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው ተሰይ መዋል፡፡ ከዚያ ተከትሎ ግብፅ እግዚአብሔር ያዘዘውን ፓትርያርኳን ለማግኘት ተገቢ የምትለውን ቀኖናዊ እርምጃዎች ሁሉ መውሰዷን ቀጠለች፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ የፓትርያርክ ምርጫ ሂደቱን ያከናወነችው እ.ኤ.አ በ1957 በወጣው ድንጋጌ መሠረት ነው፡፡
የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ /ለሕፃናት/
ኅዳር 7 ቀን 2005 ዓ.ም.
በኪዳነማርያም
አባታችን አብርሃም እግዚአብሔርን በማያውቁ፣ ጣዖት በሚያመልኩ መንደር ውስጥ ይኖር ነበር፡፡ አባቱ ጣዖት እየቀረጸ የሚሸጥ ነበር፡፡ አንድ ቀን አባቱ ሸጠህ ና! ያለውን ጣዖት ከረሀቡ ያስታግሰው ዘንድ አብላኝ ብሎ ቢጠይቀው አልሰማህ አለው፡፡ የጠየቀውን አልመልስልህ ሲለው ሰባብሮ ጣለው፡፡ ወደ ሰማይ አንጋጦ ጨረቃን ጠየቃት አልመለሰችም፣ ፀሐይን ጠየቀ አልመለሰችም፡፡ ተስፋው ሲሟጠጥ አምላከ ፀሐይ ተናበበኒ (የፀሐይ አምላክ አናገረኝ) አለ፡፡ እግዚአብሔርም ሰማው ከዘመዶችህ ተለይተህ እኔ ወደ ማሳይህ ስፍራ ውጣ አለው፡፡ አባታችን አብርሃምም እንደታዘዘው በመፈጸሙ እግዚአብሔር ቃልኪዳን ገባለት፡፡ ዘርህን እንደ ምድር አሸዋ አበዛዋለሁ የምድርም አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ አለው፡፡ አብርሃምም ከሣራ ይስሐቅን ወለደ፣ ይስሐቅም ታዛዥ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን አንድያ ልጅህን ሠዋልኝ ባለው ጊዜ አብርሃም ታዘዘ፡፡ ልጁ ይስሐቅም አባቱን ታዘዘ፡፡ አምላክህን ከምታሳዝነው እኔንም ዓይን ዓይኔን እያየህ ከምትራራ በጀርባዬ ሠዋኝ ብሎ አባቱን አበረታው፡፡ እግዚአብሔርም የአብርሃምን እምነት የልጁን ታዛዥነት ዓይቶ በይስሐቅ ፋንታ ነጭ በግ በዕፀ ሳቤቅ አዘጋጅቶ እንዲሠዋ አደረገ፡፡ የበጉም ምሳሌ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡